ማረጥ ፀጋ ነው!

ማረጥ ፀጋ ነው! Fitsum Atenafework Kidanemariam AWiB Blog

ከምርቃቶች አንጋፋዎቹ እድሜ እና ጤና ይስጥሽ/ይስጥህ ናቸው፤ እድሜ ፀጋ ነዋ፣ እድሜ መስታወት ነዋ፣ መኖር ካለመኖር የተሻለ ነዋ! ከዚያ እኛም ስንመረቅ አሜን ብለን እንቀበልና ከኋላ ተከትለው የሚመጡት ነገሮች ያሉ የነበሩና ወደፊትም የሚኖሩ ሐቆች መሆናቸውን ልባችን እያወቀው ደርሰው ስናያቸው ሰበር ዜና ይሆኑብናል፡፡ ሰሞኑን በተደጋጋሚ በአካባቢዬ ያሉ ሴቶች ስለማረጥ (menopause) አንስተው አውግተናል እና ዛሬ ሰፋ ባለው በዚህ መድረክ ከእናንተ ጋር ማውጋት ፈለግሁ፡፡ በተለይ የሕክምና መጽሔቶች ላይ ካልሆነ ብዙ ያልተጻፈበት እና ያልተባለለት ማረጥ የእኛ የሴቶች አንዱ አጀንዳ ነው፡፡ ለምን ይሆን ይሄ ፀጋ ያልተነገረለት!

ከዚያ በፊት ግን እንደ መግቢያ ፈገግ ካስባለን አንድ ገጠመኜን ላውጋችሁ፡፡ የሥራ ባልደረባዬ የነበረች ሴት ዲቪ ይደርሳትና ቤተሰቦቿን (ባለቤቷን እና ሁለት ልጆቿን) ይዛ ለመሄድ ተፍ ተፍ ስትል የወር አበባዋ ይቀራል፡፡ ከዚያ የቢሮ የእረፍት ሻይ ቡና ሰዓት ላይ ሞቅ ደመቅ አድርጋ “እናንተ ፔሬዴ እኮ ቀረ፤ እኔ በበኩሌ ከጉዞዬ እሚያደናቅፈኝ እርግዝና አልፈልግም!” ትላለች፡፡ አንዳንድ ሰዎች (ወንዶችም ሴቶችም) መቼስ በቀልድ እያስመሰሉ መሸንቆር ዋና ሥራቸው የሆኑ እስኪመስል እንደዚያ ያለ ጨዋታ አሰፍስፈው የሚጠብቁ አሉ፤ እናም ከአንድ ሁለቱ ያስተናገደቻቸው ምጸታዊ አስተያየቶች አይረሱኝም፡፡ አንደኛዋ “እንዴ አሁንም ከባልሽ ጋር ያንን ነገር ታደርጋላችሁ?” ማለት! አሁንም የሚለው ይሰመርበት፡፡ ሌላው በሽሙጥ የሚታወቀው የሥራ ባልደረባችን ደግሞ “ለሰርጋችሁ እለት የአብርሀም የሣራ ጋብቻ ይሁንላችሁ! ተብላችሁ ስትመረቁ አሜን ከማለት አትከራከሩም ነበር? ሣራ በስተእርጅናዋ መውለዷ ሴቶች ተስፋ እንዳትቆርጡ ለማለት እኮ ነው!” ከማለቱ በዚያን ጊዜ እድሜዋ ወደ 40ዎቹ መጨረሻ የነበረችው ባልደረባችን በሁለቱም አስተያየት ተበሳጭታ ቀይ ፊቷ ቲማቲም መምሰሉ ትዝ ይለኛል፡፡ በወቅቱ ክፉም ደግም ባለመናገሬ በግል ስታማክረኝ  “ሐኪም ቤት ሄደሽ ተመርመሪ!” ነበር  ያልኳት፤ አደረገችውም፤ እናም እያረጥሽ ነው ተባለች፡፡ ተበሳጭታ አሁንም እንዳጽናናት በሚመስል ምስጢሯን ነገረችኝ፡፡ ቀጣይ ምክሬ ከጅምሩ ልጅ መውለድ እቅዷ ውስጥ ያልነበረ መሆኑን አስታውሻት በፀጋ እንድትቀበል ከመምከር ባለፈ እውቀት አልነበረኝም፡፡ ያልተዋጠላት ባልደረባዬ እኔንም ከሌሎቹ ጋር ደምራ ተቀየመችኝ፡፡ ስህተቴ ምን እንደሆነ እስካሁን አልገባኝም፡፡

እንግዲህ የዚህች የሥራ ባልደረባዬን ምሳሌ ያመጣሁላችሁ በምክንያት ነው፡፡ ብዙዎቻችን ሴቶች የእድሜን ፀጋነት ስንቀበል ከእድሜ ጋር ተከትሎ የሚመጣውን ማረጥ በፀጋ መቀበል ይቸግረናል፡፡ እናም መካድ (denial) ሲያወዛግበን እንኖራለን፤ በራሳችን ላይ የምንጨምረው አላስፈላጊ ጫና እለዋለሁ፡፡ ሰውን እንኳን ሲወዱት ከነምኑ ምናምኑ ነው ይባል የለም እንዴ! እድሜንም እንደዚያው መሆኑን እንደምን ተዘነጋን! ማረጥ ደግሞ ያንን ነገር ከማድረግ ጀምሮ ምንም አይከለክልም፤ ከመውለድ በስተቀር፡፡ መውለድን ደግሞ  ማረጥ ብቸኛው ከልካይ አይደለም፡፡ መሀንነት የሚባል ከማረጫ እድሜ በፊት የተሰጠ ተፈጥሯዊ ያለመውለድ እድል እንዳለ እያስታወስን! በዚያ ላይ ልባችን የፈቀደው ሰው ካልመጣም ሌላው ያለመውለድ ምክንያት ነው፡፡ ይህንን ጽሑፍ የምታነቡ ማረጥ መቼ እንደሚከሰትባችሁ/እንደሚከሰትላችሁ እያሰባችሁ ያላችሁ እንዲያው ቁርጥ ያለ ቀን ወይም እድሜ እንደሌለው ብታውቁትም ላስታውሳችሁ እወዳለሁ፡፡ የአሜሪካ ጥናት እራሱ እርግጠኛ ስላይደለ ያስቀመጠው በአርባዎቹ እና በሃምሳዎቹ በሚል ሲሆን አማካዩን 51 ዓመት አድርጎታል፡፡ ይህ አማካይ ሆኖ ሲቀመጥ እድሜአቸው ከ51 በላይ ሆኖ ያላረጡ ሴቶች መኖራቸውን ያመለክታል፡፡ ቀደም ያሉ ጥናቶች ደግሞ መነሻውን አልፎ አልፎ ከሠላሳ አምስት ዓመት ጀምሮ ሊከሰት እንደሚችልም አስቀምጠውታል፡፡ ስለሆነም የእያንዳንዳችን የማረጫ ማለቴ የፀጋ እድሜ የተለያየ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡  

እንግዲህ እኔን ጸሐፊዋን ጨምሮ በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ያለን ሴቶች እባካችን ማረጥ ፀጋ መሆኑን አምነን እንቀበል! ሰውነታችን ሙቀት እንደሚለቅብን፣ እንደሚያልበን፣ የስሜት መለዋወጦች እንደሚከሰቱብን፣ የቆዳ መድረቅ ሊከሰትብን እንደሚችል፣ እንቅልፍ ማጣት እንደሚከሰት፣ የፀጉር መሳሳት እና ሌሎችም ተያያዥ ምልክቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ተነግሮናል፤ እድሜ ለአጥኚዎች! ታላላቆችማ በተለይ በእኛ ሀገር ማረጥ እንደ ስድብ ስለሚቆጠር እና እየተሸማቀቁ ስለሚያሳልፉት አይነግሩንም፡፡ አቤት ሴት ልጅ ግን በስንቱ ተሸማቃ ኖራ እንደምታልፍ አስባችሁታል! የወር አበባው ገና መጀመርያ ሲመጣ ተሸማቃ፣ ጡቷ ሲያጎጠጉጥ ተሸማቃ፣ ወንዶች ሲለክፏት (ሲያባብሏት ማለቴ ነው) ተሸማቃ፣ ስታረግዝ ተሸማቃ፣ ከመውለድ ጋር በሚፈጠረው የሆርሞን እና የሰውነት ቅርጽ ለውጥ ተሸማቃ፣ ብቻ ከመሸማቀቅ ብዛት ተሸምቅቃ አለማለቋ የምትገርም ልዩ እና ድንቅ ፍጡር ናት፡፡

ይህን የምታነቢ ስለ ማረጥ እና ተያያዥ ጉዳዮች የሚያሳስብሽ እህት ከዛሬ ጀምሮ እርሽው! ሙቀት ሲለቅብሽ ቀዝቃዛ ሻወር አለልሽ፣ ስሜትሽን ለማዳመጥ የጥሞና ጊዜ ይኑርሽ፣ ለሚሳሱት ፀጉሮችሽ እና አጥንቶችሽ እንዲሁም ለሚደርቀው ቆዳሽ ጥሩ የተመጣጠነ ምግብ እና እንቅልፍ አለልሽ፤ ሜክአፕ የሚባል ዘመናዊ መዋብያ የተሰራውም እኮ የጎደለንን በጊዚያዊነት ለመሙላት ነው፤ ብቻ የእኔ ውድ እህት ማረጥ እንደ እድሜ ፀጋ ስለሆነ ባለፀጋ ነሽና ማለቴ ነንና ደስ ሊለን እንጂ ልንሳቀቅ አይገባንም! ምናልባትም አግብተሽ መውለድን በመጠባበቅ ላይ ሳለሽ ድንገት ማረጥ መጥቶ ሕልምሽን ያጨናገፈብሽ ከመሰለሽ የምልሽ አንድ ነገር ነው፤ እምነት መልስ አለው፡፡ እግዚአብሔር ወደዚች ምድር ያመጣንን ሰዎች እንደመልካችን እና ባህርያችን የተለያየ ስጦታ ነው የሰጠን፡፡ የልጅ ስጦታ የተሰጣቸው እንዳሉ ሁሉ ሌላ ስጦታ ለምሳሌ የማሳደግ ስጦታ የተሰጣቸው አሉ፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት በሃያዎቹ ዓመታቸው ትዳር መስርተው የልጅ ስጦታ ባለመሰጣታቸው ያልወለዱ ብዙዎችን እንደምናውቀው ሁሉ፡፡ ዘግይተው ትዳር መስርተው ልጆች የወለዱም ብዙ እናውቃለን፡፡ እና የእኔ እህት ልበልሽ ወይንስ ጓደኛ ብቻ አንቺ ድንቅ ሴት ያንቺ የሆነውን ዛሬን ኑሪ፤ እስከዛሬ መኖርሽ እራሱ ፀጋሽ ነው፡፡

በነገራችን ላይ ይሄ ጽሑፍ የሚመለከተን ሴቶች ምን ያህል እድለኞች እንደሆንን ታውቃላችሁ? ሁለት ምእተ ዓመት ያየን አንጋፋዎች እኮ ነን፤ አስራ ዘጠኝ ሺህ እና ሃያ ሺህ (19… እስከ 2016 የኖርን እድለኞች!) እና እድሜ ይስጠን! ማረጥ ይስጠን! አሜን! ዋናው ነገር ደግሞ ወደዚች ምድር የመጣንበትን የሕይወታችንን ዓላማ (purpose of our life) ማወቅ እና ለዚያ መኖር ነው! ማረጥ ካልፈለግሽ አጭር እድሜ መኖር ነበር ሕልምሽ ማለት ነው!

ከማጠቃለሌ በፊት ቅዳሜ እለት ልደቴ ነበር፤ የተወለድኩት የካቲት 16 19…ዓ.ም. ነው፡፡ የልደቴን ቀን በጣም እወደዋለሁ፤ ብዙ ዓመት ኖሬ ሌላ እድል እንደተሰጠኝ የማስተውልበት እለት ነው፡፡ በቲክቶክ በለቀቅኩት አጭር ቪዲዮም ይህንን ደስታዬን ገልጬ ቀጣዩን እድሜዬን በደስታ እና በመልካምነት ለመኖር ቃል ገብቻለሁ፡፡ አንዳንድ ሴቶች ግን ልደታቸውን እንደማይወዱት ያጫወቱኝ አሉ፡፡ ምናልባትም መኖር እየወደዱ ማረጥ ስለሚፈሩ እንዳይሆን እሰጋለሁ፤ አፍ አውጥታ “ማርጀት አልወድም” ያሉኝ ሴቶችም አሉ፡፡ እህቴ በምድር ላይ የማያረጅ እራሱ አለማርጀት የሚለው ቃል ብቻ ነው! ለዛሬ ጨርሻለሁ!

Written by: Fitsum Atenafework Kidanemariam

Share on your page!

2 thoughts on “ማረጥ ፀጋ ነው!”

  1. ድንቅ መልእክት ፍፁም፡፡ አውነት ነው ለማረጥ የደረስን ታድለናል፡፡ ይህንን ጽሁፍ ሳነብ ምን መጣልኝ መሰልሽ ለምን አንድ ቅዳሜ ግማሽ ቀን በዚህ ዙሪያ በAWiB roundtable disuccsion ጊዜ ውይይት አናዘጋጅም፡፡ ይህ ጉዳይ ለአንዳንድ እህቶቻችን የጭንቅት መንስዔ ስለሚሆን መወያየቱ ጥሩ ነው፡፡ ባለሙያ ጋብዘን ከራሳችንም ልምድ ጨምረን መማማር እንችላለን፡፡
    ምን ይመስልሻል?

  2. Woinshet Sileshi

    Thank very much fise..for sharing insightful idea…be blessed❤️❤️❤️ Am happy and feel blessed for my passed successful years and dreaming the coming years to come to be fruitful and touch others life…Fise i also born in February 14..my birthday is so special to me bc birthday and Valentine’s Day…wow amazing thank you God for all your abundant blessings❤️❤️❤️

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *