የበቁ ሴቶች ሽልማት ሲያበቃ፤ የተደበላለቀ ስሜት!

መቼስ እንደ ሰርግ፣ ምርቃት እና ሌሎችም ግብዣዎች ሲኖሩ ከድግሱ እስከ ድምቀቱ ሴቶች ወሳኝ መሆናቸው አያጠያይቅም፡፡ አስባችሁታል ትልቅ ድግስ በሆቴል ተደግሶ ወንዶች ብቻ ታዳሚ ቢሆኑ ምን እንደሚመስል? ያው የኃላፊዎች ስብሰባ ነዋ የሚመስለው፤ እሱ ቦታ የእነሱ ስለሆነ፡፡ እና ስለ ድምቀት ካወራን አይደምቅም በቃ፡፡ ሴቶች የተለያዩ ከለር ያላቸው አልባሳት እና ጌጣጌጥ ለብሰው ተውበው ሲቀላቀሉ ይደምቃል፡፡ በቃ እኛ እኮ ድምቀት ነን፡፡  

እናላችሁ ሰሞኑን አንድ ትልቅ የግብዣ ቦታ ላይ ከባለቤቴ ጋር ታድመን ነበር፡፡ ወንዶችም ሴቶችም እንደልባቸው እንዲጨዋወቱ ጠረጴዛ ተለያየና በየፊናችን ተቀመጥን፡፡ አንዳንዶቹ በቅርበትም በርቀትም ይተዋወቃሉ፡፡ እኔ ጥቂቶቹን ካልሆነ ቀረቤታ ያለው እውቀት ከብዙዎቹ ጋር አልነበረኝም፡፡ ብቻ ድባቡ ድግስ ስለነበረ ሞቅ ያለ ትውውቅ እና ሳቅ ይነግሱ ዘንድ ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ እኔ የተግባቢነቴን ያህል ሁልጊዜ ቶሎ የማልቀላቀልባቸው ቦታዎችም አሉኝ፤ አንዳንድ ቦታ ላይ ቆጠብ የሚያደርገኝ ነገር አለ፡፡ በዚህኛውም አዲስ ቤተሰብ ተቆጥቤ ሁኔታዎችን እንደሚታዘብ ሰው ስቁለጨለጭ ነበር ያመሸሁት፡፡  የድግስ ላይ የሴቶች መግባብያ ሰነድ “አቤት እንዴት አምሮብሻል፣ ደግሞ ይሄኛው ሀገር ልብስ የመቼ ነው፣ አቤት ጌጣጌጦችሽ እኮ፣ ሽንቅጥ ብለሻል፣ ልጃገረድ መስለሻል…” ወዘተ የሚሉት ከልብ የመነጨ ይሁን ያልመነጨ የማይታወቅ መሞጋገሻ ቃላት ናቸው፡፡

የአንዷ በዘናጭነቷ እነሱ የሚያውቋት እኔም በጥቂት ድግሶች ላይ ያስተዋልኳት ሴት ሀገር ልብስ በውዳሴያቸው መረብ ውስጥ ገባ እና መነጋገርያ ርእስ ሆኖ ዘለቅ ያለ መወያያ ሆነ፡፡ “መቼስ ስታውቂበት፣ ልብሶችሽ እኮ ልዩ ናቸው፣ ማች የምታደርጊባቸው ጌጣጌጦችሽ፣ ጫማዎችሽ…ወዘተ” የሚሉ አስተያየቶች በተለይ በተደጋጋሚ ድግሶች ላይ አይተው ያደነቋት ሁለት ሴቶች እያከታተሉ ካሞገሷት በኋላ አንደኛዋ “ለመሆኑ ለአንድ ሀገር ልብስ ስንት ታወጫለሽ? ልብሶችሽን፣ ጫማዎችሽን እና ጌጣጌጦችሽ በቁጥር ታውቂያቸዋለሽ?” በማለት ጠየቀቻት፡፡ ዘናጯ ሴት እንደመኩራራት ብላ በቁጥር እንደማታውቃቸው፣ የለበሰችውን ሀገር ልብስ ይሁን ጫማዎች ከአንዴ በላይ መድገም እንደማትወድ እና ሀገር ልብሶቿ እያንዳንዳቸው ከ50 ሺህ ብር በላይ እንደምታወጣባቸው፣ 100 ሺህ የፈጀም እንዳላት አብራራች፡፡ ከጠያቂዎቿ አንዷ “ቤትሽ መጥቼ እዘርፍሻለሁ” ስትል ሌሎችም እየተሳሳቁ ተጋሯት፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ “ታድላ!” በሚል ስሜት በፈገግታ እያጀቧቸው ነበር፡፡

ይሄ ሁሉ ሲሆን እኔ ፈገግታም ሆነ ጨለምታ ከፊቴ ጠፍተው በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ነበርኩ፡፡ እንደዚህ ያሉ ለአንድ ቀን ፍጆታ ብቻ በብዙ ሺዎች የሚከፈልባቸው አልበሳት የሚለብሱ እህቶች ባሉባት አዲስ አበባ ማህበራችን ኤውብ ለማህበረሰብ ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጡ የብዙዎችን ሕይወት እየታደጉ ያሉ ጥቂት ሴቶችን ለመሸለም በዓመት አንድ ጊዜ የምታዘጋጀውን የብቁ ሴቶች ሽልማት መርሀ ግብር ለማዘጋጀት አቅም በማጣቷ ዘንድሮ ለመጨረሻ ጊዜ ለመደገስ ተገዳለች፡፡ በአለፉት አስር ዓመታት ማንም ያላያቸውን ወደ 60 የሚሆኑ ሴቶች እንዲታዩ፣ እንዲሸለሙ እና ለስራቸው የሚያግዛቸውን ሁኔታዎች እንዲመቻችላቸው አድርጋለች፡፡ በዚህም ብዙ ሺዎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ምን ዋጋ አለው! አያቴ “ጥሩ ሰው አይበረክትም!” ትለኝ ነበር፡፡ ጥሩ ስራም አይበረክትምና! ይህ የበቁ ሴቶች ሽልማት የዘንድሮው በገንዘብ እጥረት ማዘጋጀት ስላልተቻለ የመጨረሻው እንደሆነ ተነግሮናል፡፡

ወደ ወጋችን ልመልሳችሁ እና በዚያ ድግስ ላይ ታድያ በአንድ ሀገር እየኖርን ይሄ ሁሉ የአኗኗር እና የአስተሳሰብ ልዩነት ምንጩ ምን ይሆን የሚለው የበለጠ በስሜቴ ገዝፎ ይሰረስረኝ ነበር፡፡ ስለአፈጣጠራችን፣ ስለአኗኗራችን፣ ስለተግባራችን እና ስለ ልዩነታችን እያሰላሰልኩ በሀሳብ እየነጎድኩ፡፡ “እውነት እኛ ሁሉ የዚች የእምዬ ኢትዮጵያ፣ የደሀይቱ፣ ያላደገቺቱ፣ የለማኚቱ ልጆች ነን ወይንስ ማን ነን?” እያልኩ ስወዛገብ ቀደም ሲል የምታውቀኝ  እና ያልተለመደው ዝምታዬ የጨነቃት አንደኛዋ ሴት “ተጫወቺ እንጂ ፍጼ ምነው ዝም አልሽ?” አለቺኝ፡፡ ቀደም ሲል መኖሬንም ያላስተዋሉ ሴቶች የአይናቸው አቅጣጫ ወደ እኔ ተወረወረ፡፡ “እሺ እጫወታለሁ፤ የእናንተ ጨዋታ እና የእሷ የእህታችን ሀገር ልብሶች በምናቤ እየታዩኝ ቀልቤን ስበውት እየተደመምኩ ነው” ከማለቴ አነጋገሬ ይሁን የድምፀቴ አጣጣል “ምነው ጋዜጠኛ ነሽ እንዴ!” አስባለኝ፡፡ ልክ ያለቦታዬ እንደተገኘሁ ዓይነት ስሜት ተሰማኝ፤ ግን የበታችንት ያልሆነ ስሜት፡፡

መቼስ ማውራት ከጀመርኩ ቀልብ እንደምስብ ስለማውቅ ገባሁበት፡፡ “እኔም እኮ ሀገር ልብሶችሽን ሲያደንቁ እና ለዘረፋ ሲመቻቹ ብቀላቀላቸው ብዬ እያሰብኩ ነው፡፡ ምነው ቀደም ብዬ ባውቅሽ እና በዘረፍኩሽ ሁሉ ብዬ ተመኘሁ፡፡ በተለይ ጥሩ የሀገር ልብስ ሲገጥመኝ ከሰርግ እና ከተለያዩ ዝግጅቶች በላይ በጉጉት የምጠብቀው እና በዓመት አንዴ በሸራተን አዲስ የሚደረግ ትልቅ ግብዛ ፊቴ ድቅን ይላል፡፡  እዚያ ላይ ለመታደም ደግሞ እንደዚህ ያለ አንድ ቆንጆ የሀገር ልብስ ያስፈልገኛል እና የዓመት ሌባሽ ለመሆን” ከማለቴ ሁሉም በሳቅ ፈረሱ፡፡ እኔ ደግሞ አላማዬ ይህንኑ ቀልባቸውን ማግኘት ነበር እና የምርም የቀልድም አስመስዬ ወሬዬን ቀጠልኩ፡፡ የሁሉም ዓይኖች እኔ ላይ ናቸው፡፡ እኔም እድሉን ተጠቅሜ ቀጠልኩ አንዳቸውም ስለምን እንደማወራ ስላልገባቸው፡፡ “ከምሬ መስሎሽ አትደንግጪ፤ አልዘርፍሽም፡፡ ልብስሽ እና ጌጣጌጥሽ በተለየ ለዚያ ዝግጅት ስለሚመጥን ነው፡፡ ለነገሩ ሁላችሁም ዘናጮች ናችሁ!” አልኳቸው፡፡ እነሱ ግን ያውም በሸራተን የሚካሄድ እነሱ የማያውቁት እኔ ብቻ የማውቀው ድግስ ስለመኖሩ በጥርጣሬ እና በጠያቂነት አተያይ እንዳብራራላቸው ጠየቁኝ፡፡

የሸራተኑ ዝግጅት በጣም ትልቅ ጋላ ዲነር ነው፤ የበቁ ድንቅ ሴቶች፤ የደሀ እናቶች፣ የኢትዮጵያ ልዩ ሴቶች በሕዝብ ጥቆማ ተመርጠው በሴቶች በሚዘጋጅ ትልቅ የሽልማት ዝግጅት የሚሸለሙበት፣ የሚወደሱበት ምሽት ነው” በማለት ተነፈስኩ፡፡ አንዳንዶቹ “የደሀ እናቶች” በሚለው ላይ ቀልባቸው ሲያርፍ ሌሎቹ ደግሞ “ጋላ ዲነር”  ግራ ገብቷቸው ነበር እና ለሁሉም ጥያቄ ትንታኔ ሰጠሁ፡፡ ቢያንስ እዚያ ቦታ ላይ በልብሷ እና በጌጣጌጧ ብቻ ስትደነቅ ከነበረችው ሴት በላይ መደነቅ የሚገባቸው ሴቶች እንዳሉ በማሳወቄ ብቻ ሳይሆን ገንዘብ በተሻለ ቦታ እና በምክንያታዊነት እየወጣ መሆኑን በመናገሬ ደስታ ተሰማኝ፡፡ በዚህም ቀደም ሲል ያልተሰጠኝን ቦታ አገኘሁ፣ ስለኤውብ አወራሁ፣ ተደመጥኩ፣ የተዘበራረቀውን ስሜቴን ለጊዜውም ቢሆን አረጋጋሁት፤ ያው ለጊዜው፡፡ ለነገሩ አልኩ እንጂ እሷም ሆነች እነሱ ገንዘባቸውን በፈለጉት ነገር ላይ ቢያውሉት መብታቸውስ አይደል!

ይሁንና ግን ይህ አስረኛው የኤውብ የበቁ ሴቶች ሽልማት በአቅም ማጣት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እሁድ ኦክቶበር 29 ቀን 2023 ብቻ መከበሩ እና የመጨረሻ መሆኑ ለተዘበራረቀው ስሜቴ መልስ አይሰጠውም፡፡ እናም ነገ ይዞልን የሚመጣውን በረከት በተስፋ የምጠብቅ ነኝ!

Written by: Fitsum Atenafework Kidanemariam

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *