ሚዛን አይዝመም!

በማለዳ ስልክ ሲደወል አልወድም፡፡ እናቴ ነብሷን ይማረውና በጠዋት ሲደወልላት “ደግሞ ማን ሞተ ሊሉኝ ነው?” እያለች ነበር የምታነሳው እና እንዳጋጣሚ ደግሞ ሁሉም የማለዳ ስልኮች የሞት ዜና እንዳልነበሩ አስታውሳለሁ፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን በቃ የድሮ የእናቴ ስሜት ተጋብቶብኝ አልለቀቀኝም፡፡ ታድያ የፈራሁት የሆነው ለጥቅምት 7 አጥብያ ከሳምንታት በፊት ለባለቤቴ በእጅ ስልኩ ላይ ተደውሎ ነው፡፡ ቀደም ሲል በማናውቀው ቁጥር ደዋይ ለባለቤቴ በማለዳ ከ11 ሰዓት በፊት ደወለ እናም ባናቀውም ማንሳት ነበረበት፡፡ ባለቤቴ በወጣትነቱ የወለዳት ልጅ ነበረችው እናም ደዋይ የእሷን ስም ጠርቶ አባቷ መሆኑን ጠየቀው፡፡ ባለቤቴም እንደ ሕጻን እየተኮላተፈ “አዎ ነኝ፤ ምን ሆነች??” ብሎ ጠየቀ፡፡ “ልቤን እያለች ነውና ቶሎ ድረሱላት” ሲለው በቃ የሆነውን እንዴት ልቀጥልላችሁ፡፡ ፒጃማችን ላይ የቀን ልብስ ደርበን ነበር በፍጥነት እያሽከረከርን የደረስነው፤ “ልቤን ወጋኝ” ብላ ለሆስፒታል እንኳን ሳትደርስ ሕይወቷ አልፎ ነበር እኛ የደረስነው፡፡
ይሄንን ታሪክ ለምን የነገርኳችሁ ይመስላችኋል? አዎ ነብስ ይማር ማለታችሁማ አይቀርም ከዚያ በላይ መጨዋወት ያለብን ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡ ለእኛ ቤት እንደዚህ ያለ አስደንጋጭ ሞት አዲስ ቢሆንም ይሄንን የምታነቡ ሰዎች ተመሳሳይ የቅርብ ወይንም የሩቅ ቤተሰብ ታሪክ እንዳላችሁ እገምተለሁ፡፡ ሁልጊዜ እደዚህ ያለ አስደንጋጭ ሞት ስንሰማ “ለካስ ሞትን ተሸክመን ነው የምንኖረው!?” ብለን እንደ ማንቂያ ደወል ይሆነን እና ወድያው ደግሞ ረስተነው ሕይወት ይቀጥላል፤ መርሳትን እግዚአብሔር ይስጠውና! መርሳት ባይኖር እንደምን እንችለው ነበር!
መርሳታችን መፍትሔ ስላይደለ ከዚህ ታሪክ ግን ብዙ ትምህርት እንውሰድ! በመጀመርያ ደረጃ ስንቶቻችን ነን የጤናችንን ሁኔታ የምናውቀው!? እስቲ መቼ ነው ሳንታመም በቅድምያ የጤና ምርመራ ለማድረግ ሄደን የነበረው!? በየአመቱ ወይንም በዓመት ሁለት ጊዜ የጤና ምርመራ የምታደርጉ ሰዎች በእርግጥም የምትደነቁ ናችሁ፡፡ አንዳንዶቻችን እኮ ሲያመን እንኳን መንቀሳቀስ እስከቻልን ድረስ እንደ ሕመም አንቆጥረውም፡፡ ሲጀመር ሕመማችንን ስናዳምጠውስ አይደል! እራሳችንን አናዳምጥም እኮ፡፡
ሁለተኛ ትምህርት ልምምድ ማድረግ ነው፡፡ የምን ልምምድ መሰላችሁ መቼስ ሰዎች ሲያስቀይሙን መቀየም ሰውኛ ነው፡፡ አንዳንዴ ግን በደላቸው ይገዝፍብንና ከነቂማችን ለጥ እንላለን፤ ያውም ለቀናት እና ለዓመታት፡፡ አንዳን ጊዜ ታውቃላችሁ በዳዮች በደል መፈጸማቸውን ሁሉ ላያስተውሉት ይችላሉ፡፡ በቃ ያመኑበትን ከአደረጉ ወይንም ከተናገሩ በኋላ ቤታቸው ገብተው በሰላም ለሽ ይላሉ፡፡ እኛ ደግሞ ባህላችን ይሉኝተኛ እና ግልጽ ንግግር የማያበረታታ ስለሆነ አልያም በግልጽ በደላችንን የመግለጽ ልምምዱም ስለሌለን ዝግት ብለን በቂም እንብሰከሰካለን፡፡ ምናልባትም ፊት ለፊት ተነጋግረንበት ቢሆን ኖሮ ይቅርታ ተጠይቀን ካልሆነም በመናገራችን ሰላማችንን አግኝተን እኛም እንተኛ ነበረ እኮ! አልታደልንማ፤ ቂም ከከፋም በቀልን አርግዘን እንኖራለን፡፡
ሦስተኛው ይቅርታ መጠየቅም ይሁን ይቅር ማለት የሚከብደን ብዙዎች አለን፡፡ በደሉ ትንሽ ወይንም ትልቅ ሊሆን ይችላል፤ እሱ እንደተሸካሚው ይለያያል፡፡ በድለን በዳይ መሆናችንን እያወቅን እንኳን ይቅርታ መጠየቅ የኪሊማንጃሮ ተራራን ያህል የሚገዝፍብን ብዙዎች ነን፡፡ በቃ አለ አይደል የተለማማጭነት እና የበታችነት ስሜት ከየት መጣ ሳንለው ይከመርና ይፈታተነናል፡፡ በድለን ይቅርታ ማለት የሚከብደንን ያህል ተበድለን ይቅርታ ስንጠየቅም ሞቼ ነው ቆሜ ይቅርታ የምቀበለው፤ የልብ ሰርቶ ይቅርታ ማለት አይገባኝም…ወዘተ እንልና ይቅርታውን እንገፋዋለን፡፡ ደግሞ እኮ በተለይ በእምነት ክርስቲያን ከሆንን የዘወትር ፀሎታችን ላይ አባታችን ሆይ ስንል እኛ ይቅር ብለናል እና ይቅር በለን ብለን እራሱ ፈጣሪን እንደ ሰው ሽምጥጥ እናደርገዋለን፡፡ ከባድ ነው አይደል!? ማለቴ ከባድ ነን መሰለኝ!?
እነዚህን ሦስት ነጥቦች ለምን እንዳነሳሁት ይገባችኋል መቼስ፡፡ እንዲህ ተሸክመን የምንዞረው ሞት ለጥቂቶች የተሰጠ አይደለም፤ ለሁላችንም እንጂ፡፡ ታድያ ከቀደሙን ሰዎች ለምን አንማርም!? ሕይወት እንደሆነ በጭንቀት የተለበጠች ናት፤ በጭንቀት ደግሞ ውጤት አምጥተን አናውቅም አይደል!? አለመጨነቅ እንደማይቻል ጠፍቶኝ አይደለም፤ ግን እራሳችንን እስክንረሳ አለመጨነቅን እንለማመድ ማለቴ ነው፡፡
ለጤናችን በአመት አንድ ቀን እንስጠው! በቃ እስክንታመም፣ እስኪፈልጠን እና እስኪቆርጠን አንጠብቅ! ይሄንን ስታነቡ አንድ ቀን ምን አላት እኔ በዓመት ሁለቴ ቼክ አደርጋጋሁ የምትሉኝ እናንተ አርአያዎቻችን ናችሁ፡፡ በተለይ ስንታመም እራሱ የምንክድ ብዙዎች አለንና!
ቂም ይዘን አንተኛ! ሲጀመር የሆነ የማብሰልሰል ስሜት አለው አይደል! ቂም? አያስተኛም እኮ! እንቅልፍ ይሻማል፡፡ ከዚያያ ባለፈ ደግሞ ለምን ብለን እንሞኛለን ያቄምንበት ሰው ከቁብ ላይቆጥረን፤ ስለዚህም ባለማቄም ጤናችንን እንጠብቅ!
ይቅርታ መጠየቅም ሆነ መስጠት የበታችነት ተብሎ የሚታሰብበትe ዘመን አልፏል፤ ከነበረ ማለቴ ነው፡፡ ባይኖርማ ከየት እናመጣው ነበር፤ ግብዝነቱን፡፡ ስለሆነም ለይቅርታ የሚከፈት ልብ ይኑረን፤ ለልባችንም ጤ ነውና፡፡ ይውርታ ከልብ ሲሆን ነው ሲበባል ሰምቼ ነው ለልባችን ጤ ነው ያልኩት፤ ከአእምሯችንም ከሆ ወይንም ከሆችን ብቻ ከየትም ብለን አውጥተን እንለማመደው፤ ክብራችን ቅንጣት አይነካምና!
እናንተ የጤና ምርመራ በወቅቱ የምታደርጉ፤ ከቂም የፀዳችሁ እና ይቅርታን የተለማመዳችሁ ሰዎችe ምንኛ ብፁሀን ማለቴ እድለኞች ናችሁ! ከእናተ ተሞክሮ ቆርጦ ያካፍለን! እንግዲህ ይሄ ሁሉ ያወራሁላችሁ የቤተሰባችን አስደንጋጭና ድንገተኛ ሞት ከውስጤ ሊጠፋ ስላልቻለ ነው፡፡ ይሄኔ የጤና ምርመራ ያደረገችው መቼ ይሆን!? ተጣልተታ አስቀይመዋት ወይንም እሷ አስቀይማ ቂም ይዛ ነበር ይሆን!? ማን ያውቃል! ይቅርታ ልታደርግለት የንትፈልገው ሰው ይኖር ይሆን!? ድንገተኛ እና አስደንጋጭ ሞት እኮ ክፉ ነው፡፡ ደግሞስ ብር የተበደረችው ወይንም ያበደረችው ሰው ይኖር ይሆን!? ብቻ ይሄ ነው ሳንል ድንገት ስንጠራ የማናውቃቸው እና ሰዎች የማያውቁልን ነገሮች ብዙ ናቸውና ለዛሬ በዚሁ ልቋጭ! ፈጣሪ ከአስደንጋጭ ሞት ይሰውረን! ለዛሬ ጨርሻለሁ!
Share with your Circle!
