እንኳንም አገባሁ!

ፍፁም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

መቼስ የእኛ ማህበረሰብ አዛኝ ነው፤ ማለቴ ያው ሴት ልጅ ስትዳር ማየት ያስደስተዋል፡፡ ከተዳረች በኋላ ደግሞ ስትወልድ፤ ከዚያም ጾታ እያሰባጠረች ደጋግማ ስትወልድ፡፡ እናም ለአቅመ ትዳር ደርሳለች ብለው የሚያስቧትን ሴት የቅርበታቸው ልኬት (boundary) እንኳን ሳይገድባቸው “መቼ ነው የምታገቢው? ሠርግ አብይን እንጂ? ምን እየጠበቅሽ ነው…ወዘተ” ማለት ነውር አይደለም፡፡ እንዲያውም አሳቢነታቸውን ማሳያ እንጂ፡፡ በዚህ አያቆምም ካገባች በኋላ ደግሞ “ቶሎ ቶሎ ውለጂ እንጂ! ምነው ወንድ/ሴት ብቻ እህት/ወንድም ድገሚ እንጂ? ልጆችሽ አንቺን ስለማይመስሉ አንቺን የመሰለችማ መውለድ አለብሽ! (አስመስሎ ለመውለድ ሳይንሱ እንዴት ነው? በዚያውም ጾታ አሰራሩንም የሚያውቅ ይጠቁመን)”፡፡ ለነገሩ ይህ ድንበር ዘለል ጥያቄ ያንገሸግሻቸው የነበሩ ሴቶችም ልክ ሲያገቡ ወድያው ስሜቱን ይረሱት እና እነሱም ያንኑ ዜማ ሌላኛዋ ተረኛ ላይ ይደግሙታል፡፡ በእርግጥ አልፎ አልፎ ወንዶችም ለአቅመ ጋብቻ ሲደርሱ “ምን እየጠበቅህ ነው!” ይባላሉ፡፡ ልዩነቱ የእኛ አቅመ ትዳር በእድሜ የሚመዘን የእነሱ ደግሞ በቁስ (በሥራ፣ በቤት፣ በመኪና፣ በከብት ብዛት፣ በመሬት…ወዘተ) የሚመዘን መሆኑ ነው፡፡ ይህም የማህበረሰቡ እይታ ነው፡፡ እኔ አሁን “ማህበረሰባችን በማያገባው ገብቶ ለምን ይጠይቃል?” የሚለውን ለመሞገት ወይንም “ተዉን?” ብዬ ለመማጸን አይደለም የጻፍኩት፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ምንም ማምጣት እንደማልችል እያወቅሁ ምን አደከመኝ! ማህበረሰብን መለወጥ የዘመን ሥራ ነውና!

የእኔ ጽሑፍ መነሻ ሀሳብ የትዳር ዓለም የሕይወት ሌላኛው ምዕራፍ መሆኑን የምናውቀውን እኛን ሴቶችን የትዳሩ ዋነኛ ተጠቃሚ የሆንን ያህል ማር ማሩን ብቻ እየነገሩን የበለጠ እንድንጓጓለት የሚያደርጉት ነገር ቅኔው ስላልገባኝ ነው፡፡ ያም አለ ይህ እኔስ እንኳንም አገባሁ! “መቼ ነው የምታገቢው?” የሚለው ውትወታ ስለቀረልኝ እንዳይመስላችሁ! ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ ትዳር ድንቅ ተቋም ነው!  ትዳር የአንድ ሴት እና የአንድ ወንድ ጥምረት ነው (ይህ ሌሎች በኃይማኖት ይሁን በባህል የተፈቀዱ ጋብቻዎችን አያካትትም)፡፡ የጥምረቱ መሠረት (ትክክለኛው ጥምረት) የሁለቱ ሰዎች መፈቃቀር፣ መፈላለግ፣ እና መግባባት ነው፡፡ የትዳሩ ማብሰርያ ሠርግ አልያም “እወቁልን” ሲሆን ሁለቱ ተጋቢዎች ለመጣመራቸው ደስታቸውን የሚያበስሩበት እና ምስክር የሚጠሩበት ድግስ ነው፡፡  ታድያ “ዓለምሽ ዛሬ ነው ዛሬ እቴ ሸንኮሬ” ከሚለው ጀምሮ በአብዛኛው የሰርጉ እለት ዜማዎች የሴቷን እድለኝነት፣ ደስታ፣ ክብር፣ ዓለም…ወዘተ የሚተርኩ ናቸው፡፡ አዎ ትዳር ሌላ ዓለም ነው፡፡ ይህ ምንም አይካድም፡፡ ሁለታቸውም ተጋቢዎች ለዓመታት ከተገነባው፣ ከሞቀውና ከደመቀው የወላጆቻቸው ቤት ወጥተው ወደ አዲሱ እና እራሳቸው “ሀ” ብለው ለኩሰው፣ ቆስቁሰው፣ ተጫጭሰው እና ተጨነባብሰው የሚያሞቁት አዲስ ጎጆ እና አዲስ ዓለም ነው፡፡ ጥሮ ተጣጥሮ የራስን ዓለም፣ የራስን ጎጆ እንደመቀለስ እና የራስን ቤተሰብ እንደመመስረት ምን ደስ የሚል ዓለም አለ! ችግሩ ግን አጨነባበሱ፣ አጣጣሩ መለያየቱ ነው፡፡ እንኳንም አገባሁ ያልኩትም በምክንያት ነው፡፡ ምክንያቱን ለማወቅ ከጓጓችሁ ጽሑፌን እስከመጨረሻው ዝለቁት፡፡  

እኛ ሴቶች ለትዳር እንደምናስፈልግ በደንብ ስለገባኝ ነው እንኳንም አገባሁ ያልኩት፡፡ እኔ በማግባቴ ካገኘሁት ዋነኛ ጥቅም አንዱ በጣም ጠቃሚ ሰው መሆኔን ማወቄ ነው፡፡ በዚህ ምድር ላይ ጠቃሚ ሆኖ ኖሮ እንደማለፍ ምን አስደሳች ነገር አለ! “ልጅ በመውለድ እና ትውልድ በማስቀጠል ይሆን?” ልጅማ የጋራ ሥራ ውጤት እና የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ ሴቶች እያልኩ ሳወራ ጠበብ ላድርገው እና ትኩረቴን እንደ እኛ ያለችውን በከተማ ያለች ባለትዳር ሠራተኛ ሴት ላድርገው፤ ልክ እንደባሏ ለቤቱ ዳቦ አምጪ (Bread winner) የሆነችውን ሴት፡፡ ልክ እንደባሏ ከተሰጣት 24 ሰዓት ውስጥ 8 ሰዓቱን በቅጥር ወይንም በቢዝነስ ሥራ የተሰማራች ባለትዳር ሴት፡፡ ይህቺ ሚስት እና ባሏ በሥራ ደክሟቸው ወደቤት ሲገቡ ያላቸውን የሥራ ክፍፍል ያው ያገባችሁት ታውቁታላችሁ፡፡ ሴቷ የፈለገ የቤት ረዳት ቢኖራት ተጨማሪ ሰዓታት በቤቷ ውስጥ ትሠራለች፡፡ ሥራው በጓዳ ከመንጎዳጎድ አንስቶ ልጆችን እንደየአመላቸው መንከባከብን ይጨምራል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ እሱም አልበቃ ብሎ በቢሮ ሰዓት ኃይለኛ ስብሰባ ወይንም አስቸኳይ ሥራ መሀከል የጥሪ ሙከራ (missed call) ይደረግላታል ከቤት ውስጥ ረዳረቷ፤ “ጤፍ አልቋል የተቦካው ብቻ ነው ያለው፣ ዘይት አልቋል፣ ሽንኩርት…ወዘተ”፡፡  አልፎ አልፎ ከት/ቤት የሚመጡ ጥሪዎችም አይጠፉ፡፡ ከ8ቱ የመደበኛ የሥራ ሰዓታት ላይ ቀልብን የሚሰርቁ የማጀት መልእክቶች በሽበሽ ናቸው፡፡ ለካስ ደግሞ የሰፈር ለቅሶ አለ፤ እድርተኛ መሆን የባህላችን አንዱ ወግ ነው፤ ሴቷ  የእድሩ ተረኛ ከሆነች ሌላ ማጀት ይጠብቃታል፡፡ ባልየውም ድንኳን መትከልና ማፍረስ እንዳለ ሆኖ ካርታ እና ሌሎች ጨዋታዎች እየተጨዋወተ ማጽናናት እንደሚጠበቅበት አልዘነጋሁም፡፡ እሱም ትልቅ ሚና ነውና፡፡ ወላጆች በሕይወት ካሉ እድሜአቸው እየጨመረ ሲመጣ የሆስፒታል ቀጠሯቸውም ከወትሮው ቶሎ ቶሎ ስለሚሆን ሴት ልጅ ለዚህ የተመረጠች ናት፡፡ ወንዱም ያደርጋል፤ ግን በአብዛኛው በሚለው ይያዝልኝ፡፡  ብቻ ሁሉን ቢያወሩት ሆድ ባዶ ይቀራል እንዲሉ እስቲ ልገድበው! ለነገሩ ባልየውም ቢሆን ከቤተሰቦቹ ቤት ሲወጣ በአዲሱ ቤቱ በኢኮኖሚው (በቀጥታ)፣ በልጆች ጉዳይ (በመጠኑ) እና በአስቤዛ ሸመታ (አልፎ አልፎ)  ስለሚሳተፍ ከነበረበት ምቹ ቀጠና (comfort zone) በተወሰነ መልኩ መውጣቱ አይቀርም፡፡ የሴቷ ግን ድርብርብ ነው ለማለት ነው፡፡ አስባችሁታል ሁለቱም ከውጪ ሥራ ሲገቡ ጋቢያቸውን ለብሰው ሶፋቸው ላይ ቁጭ ብለው የቲቪ ሪሞት ይዘው ጣብያ እየቀያየሩ ሰበር ዜናውን፣ ኳሱን፣ ናሽናል ጆግራፊውን ቢኮመኩሙ ማጀቱ ምን እንደሚውጠው!?

በነገራችን ላይ ትዳር ጥሩ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸውን ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ባለትዳር ሴት በመሆናችን የምንማራቸውና የምንወጣቸው ናቸው፡፡ በተለይ በወላጆቻችን ቤት ሥራው ላይ እምብዛም ያልነበርን ሴቶች በትዳሩ ውስጥ ብዙ ሥራዎችን እንማራለን፡፡ ከሥራውም በላይ የዓለምን ሚዛን እናውቃለን፡፡ የቤት እመቤትነቱ ድርሻ የእኛ መሆኑን አሜን ብለን እንቀበላለን፡፡ በወላጆቻችን ቤት ለእያንዳንዷ ሥራ ተመርቀን እንዳልሰራን በትዳራችን ቤት ምርቃት እና ሙገሳ አንጠብቅም፡፡ ለምሳሌ አስቤዛ ለመግዛት ካልተመቸን ባሎቻችን እንደ ልጅ ከተላኩልን ምስጋናችን ወደር የለውም፡፡ ባሎቻችን በቤት ውስጥ ያለውን ጫና ያለመጋራታቸው ብዙም አያሳስበንም፤ ይልቁንም የተበላሸ ነገር ሲጠግኑ እናወድሳቸዋለን፡፡ ወላጆቻችንን ስላከበሩልን እና ስለወደዱልን እንፈነጥዛለን፡፡ እንደ ሰው ስላከበሩን፣  እንደ ሚስት ስለወደዱን፣ ስላልሰደቡን፣ ስላልመቱን እጅግ አመስጋኞች ነን፡፡  እንደዚህ ያሉ ባሎች ምድሪቷን ይሙሉልን እንላለን፡፡ ታድያ ከዚህ በላይ ምን እውቀት አለ! በዚህ አጋጣሚ ያገባችሁ ሠራተኛ ሴቶች አክባሪያችሁ እና አድናቂያችሁም ነኝ! የውጭ ሥራ ባይኖራችሁም ሙሉ በሙሉ በቤት ሥራ ላይ የተሰማራችሁትንም ሴቶች ጭምር! ምክንያቱም ባሎች የወላጆቻቸው እንክብካቤ ሳይጎድልባቸው (አቅም በፈቀደ) ሁለተኛ ወላጆች በመሆን አደራችሁን እየተወጣችሁ ነውና! በዚህ አጋጣሚ ይህ ጽሑፍ የገጠሯን ሴት የትዳር ገጽታ አልዳሰሰም፡ የእሷ ደግሞ እጅግ ይለያልና፡፡

ማጠቃለያዬ ላይ ግን አንድ ጥያቄ አለኝ! የሰርግ ዘፈኖች ይቀየሩልን?! “ዓለምህ ዛሬ ነው ዛሬ ወንድም ሸንኮሬ” መባል አለበት፡፡ ቢያንስ የወላጆቻቸው እንክብካቤ ተጠብቆላቸው አንድ ሥራ ብቻ እንዲሠሩ ተፈቅዶላቸው ቤታቸው ማረፍያቸው ለሆነላቸው አባወራዎቻችን ክብር ሲባል፡፡ እስከመቼ ይዋሻል! ሐቅ ያንቃልኮ! ለዛሬ ጨረስኩ፡፡

– ፍፁም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *