
የላቁ ሴቶች (Women of Excellence) ይብዙልን!
\”ወግና ባህል ማን ይጠላል!\” ያውም የሀገራችን የኖርንበት፣ ያደግንበት እንከን ቢኖረውም እንከን አልባነቱ ጎልቶ እንዲታይ አእምሮአችን አምኖ የተቀበለው ወግና ባህላችን፡፡ ይሄ ወግና ባህል ብዙ እና ሰፊ ቢሆንም እኔ ዛሬ ላወጋችሁ የፈለግኩት ከእኛ ከሴቶች ጋር ቁርኝት ያለውን ወግና ባህላችን ነው፡፡ ወግና ባህልን የማክበር ኃላፊነት የሁላችንም ማለቴ የሴቶችም የወንዶችም ሆኖ እያለ እኛ ሴቶች የበለጠ ጠበቅ እንድናደርገው ሆኖ መቀረጹ እና የዚህም ደግሞ ምንጭ ግልጽ ያለመሆኑ በዘመኔ ሁሉ ግርም የሚለኝ ነገር ነው፡፡ ወግና ባህል ምን ማለት እንደሆነ ለብዙዎቻችን አዲስ አይሆንም፡፡ ለምሳሌ ትዳር የሁለቱ ጥምረት ሆኖ ቤቱ የሚሰየመው ግን በአባወራው ነው፤ ጥሪ እንደ ሰርግ ወይንም ተዝካር ያሉ በካርድ የሚደረጉ ጥሪዎች ጠሪው የሚያውቁት ሴቷን እንኳን ቢሆን የሚጻፈው የአባወራው ሥም ነው፤ ለምሳሌ ያህል እንጂ ብዙ ማለት እችላለሁ፡፡
ወግና ባህላችን መሠረት ካደረገባቸው አንዱ እና ዋነኛው ሀይማኖታችን ነው፡፡ በሀገራችን ላይ የተደረጉ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያስረዱን ወደ 67% የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለያዩ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ሲሆኑ 33% ደግሞ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እንደሆኑ ነው፡፡ በሃይማኖታዊ ተምህሮ በተለይ እኔ በምከተለው በክርስትናው እምነት \”ወንድ የቤት እራስ\” እንደሆነ ነው፡፡ በእርግጥ ሴቷ ዘውድ መሆኗንም ተምረናል፡፡ ይሁንና ሰው ሰው ለመሆን የእራስ መኖር የግድ አስፈላጊ ሲሆን ዘውዱ ግን ከክብር ጋር ተያይዞ የሚጫን ውጫዊ ቁስ ነው፡፡ ተምህሮው ወንድ ልጅ ይከበር ዘንድ ዘውድ መጫን እንዳለበት ማሳያ ቢሆንም ሴቷ ግን ያለ ወንድ ወይንም ያለእራስ መኖር እንደማትችል ማሳያ ነው፡፡ በእስልምናውም ወንዱ የበላይ መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ አመላካቾች አሉ፤ አንድ ወንድ ከአንድ በላይ ሚስት ማግባት መፈቀዱ ብቻ እንኳን ብዙ ማሳያ ነው፡፡ እንግዲህ ይሄ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ሃይማኖታዊ የሆነው የወግና ባህላችን አካል አንዱ ነው፡፡
እኔ ይህንን ሀሳብ ይዤ የመጣሁት ለዘመናት የኖርንባቸውን እና እየኖርንባቸው ያሉትን እነዚህን ወግና ባህላት ወይንም ልማዶች ለመቃወም አይደለም፡፡ ብቃወምስ ደግሞ \”አፈንጋጭ፣ አክራሪ፣ አክቲቪስት…ወዘተ\” ከመባል ውጪ ምን አተርፋለሁ? ምንም! ግን ደግሞ ይሄ ዓለም የወንዶች ዓለም መሆኑን ከሚያምኑ መሀከል ነኝ፤ ያው ማመን እና መቃወም ይለያይ የለ! ለወንዶች መዳላቱን ደግሞ ገና ከትውልዳችን ይለያልኮ! ወንድ ሲወለድ እልልታው ሰባቴ ሲደምቅ ሴት ስትወለድ ግን ሶስቴ ብቻ ሆኖ እንደሚለው ማለት ነው፡፡
ዋናው ሀሳቤ ግን ዛሬ ላይ ቆሜ ሳስተውለው የወግ፣ የልማድና የባህል ተጽእኖ ሳይበግራቸው ከድቅድቁ ጨለማ ውስጥ ፍንጥቅጥቅ ብለው የሚወጡ ከዋክብትን የሚመስሉ ሴቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዙ መምጣታቸውን እንደ እኔ ልብ ብላችሁልኛል! እነዚህ የዘመናችን ቆፍጣና ሴቶች በየዘርፉ ማለትም በቢዝነሱ፣ በበጎ አድራጎት ሥራው እና አመራሩ፣ በመንግስታዊ የስልጣን ማማ እና በተለያዩ ኢኮኖሚውን የሚያግዙ ተግባራት ላይ ተሰማርተው ማየት እየተለመደ ነው፡፡ በሀገራችን ላይ ያለውን የወግና ባህል ጫና አሸንፎ በተሰማሩበት የሥራ መስክ ስኬታማ መሆን ለሴቷ ድርብ ድርብርብ ድል ነው፡፡ ግን ደግሞ ብዙም ሲወደስላት አይስተዋልም፡፡ ለምሳሌ አንድ የራሷን ቢዝነስ የምታስተዳድርን ሴት ብንወስድ ቢዝነሷን ከጥንስሱ እስከ ስኬቱ ለማድረስ የምትጓዘው ጉዞ የትዬለሌ ነው፡፡ \”አትችይውም፣ ይቅርብሽ፣ ለሴት አይሆንም፣ ደፋር (ዓይን አውጣ)፣…ወዘተ\” ከሚሉ ክንፍ ሰባሪ አባባሎች በተጨማሪ መገለልና መፈራቷም እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡ በጉዞዋ መሀከል አለበለዝያም ከጅምሩ ደግሞ እማወራ ከሆነች የቤቱም የደጁም ሥራዎች ይቁለጨለጩባታል፤ ቤት ማለት እኮ ለእሷ እንደ አባወራው ማረፍያዋ አይደለም፡፡ በተለይ አውደ ዓመት እና ሌሎች ድግሳ ድግሶች ሲኖሩ የቤት ሙያዋን (ግዴታዋን) ማስመስከሪያዎቿ ስለሆኑ ድካሙ ብዙ ነው፡፡ ማህበራዊ ግንኙነቶች እንደ የሴት እድር፣ የታመመ መጠየቅ፣ ልጆች ካሉም ልጆችን ከማሳደግና መንከባከብ በአብዛኛው የእሷ ኃላፊነትና ግዴታ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ እናም የቤቱንም የደጁንም ሞልታ እራሷን ከሰው መሀከል ለማዋል ብዙ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባታል፤ ደግሞም ትችለዋለች፡፡ ሴት ናታ!
እናም ሀገራችን ቀደም ካሉት ዘመናት በተሻለ እንደ እነዚህን የመሳሰሉ ድርብ ጀግና ሴቶች እየበዙላት ነው፡፡ ተመስገን! ይሄን ሁሉ መሰናክል አልፎ የስኬት ማማ ላይ መገኘት ድንቅ ነገር ነው፡፡ በተለይ ደግሞ እንደ ኤውብ ያሉ በሴት የተመሰረቱ ማህበራት እንደእነዚህ ያሉ ሴቶችን አጉልተው የሚያሳዩ መነጽሮች እየሆኑልን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለሚቀጥሉት ወጣት ሴቶች ጥሩ ተስፋ ነው፡፡ ምንም እንኳን በማህበረሰቡ አሁንም አጋዥ የሆኑ አመለካከቶች እና ሲስተሞች ባይኖሩም ወጣት ሴቶች አርአያ የሚያደርጓቸው ሴቶች፣ ያልተሰበሩ ቆፍጣና ሴቶች፣ መቻልን በተግባር እያሳዩ ያሉ ድንቅ ሴቶች ወደ አደባባይ ሲወጡና ሲወደሱ እያዩ ነው፡፡ የሰው ልጅ ደግሞ ከመስማት ይልቅ በማየት ያምናል፡፡ እስከመቼስ የምዕራባውያን ሴቶችን ተምሳሌት እያደረግን እንኖራለን! ድንቅ ሥራዎችን እየሰሩ በይፋ ያልተነገረላቸው/ያልተዘመረላቸው፣ የቀደሙትን እና አሁንም በመስራት ላይ ያሉትን እድሜ ለኤውብ እና ለጥቂት ማህበራት ይሁንልን እና ለሕዝብ እያወጧቸውና እያስተዋወቋቸው እንዲሁም እየሸለሟቸው ነውና በጣም ደስ ያሰኛል፣ ያኮራል፣ ያበረታታልም፡፡
ኤውብ አባል ከሆንኩ ሰነባብቻለሁ፤ አንጋፋ ኤውበር ነኝ፡፡ በመሆኑም እየተካሄደ በሚገኘው የላቁ ሴቶች (Women of Excellence) ሽልማት በሂልተን ሆቴል የእራት ሥነስርዓት(Gala Dinner) ከመጀመርያው ጀምሮ ተሳትፊያለሁ፡፡ በጥቅምት ወር መጨረሻ የሚደረግ እንደ ጥቅምት አበባ በናፍቆት የምጠብቀው ዝግጅት ነው፡፡ ለእኔ የኢትዮጵያ ሴቶች በሙሉ ይልቁብኛል፡፡ ምክንያቱም በጣም ጥቂቶች ካልሆኑ በስተቀር ከላይ የጠቀስኩት ወግ፣ ልማድና ባህል ሰለባ ሆነው/ሆነን ሳለን በአሸናፊነት ለእራስ እና ለሌሎችም መትረፍ ከቃላት በላይ ነውና! በኤውብ ከእያሉበት ተፈልገው የሚወጡት የላቁ ሴቶች ደግሞ ከቃላት ብቻ ሳይሆን ከአእምሮም በላይ ናቸው፡፡ የእነሱን ጉዞ ማዳመጥ፣ እነሱን በአካል ማግኘት እንዴት ደስ የሚያሰኝ ስሜት እንዳለው ያየነው እናውቀዋለን፡፡ ለዚያን ምሽት ያድርሰን!
ፍፁም አጥናፍወርቅ ኪ/ማርያም