እርቅ ከእራስ!

መቼስ እኛ ሰዎች ስንባል አንዱ መተዳደርያ ደንባችን በትንሹም በትልቁም ብስጭትጭት ማለት፣ መነጫነጭ፣ ማማረር የመሳሰሉት ጥቃቅን እና አነስተኛ ባህርያት ናቸው፡፡ እርግጥ ነው ስሜትን መግለጽ ሰውኛ ነው፡፡ ግን ደግሞ የእኛ ልምምድ ትንሽ በዘት ይላል፡፡ ለምሳሌ ታክሲ ረዳቶች ሁልጊዜ የሚያበሳጩን ለምን ይመስላችኋል? የካፌ አስተናጋጆችስ? የቤት ሰራተኞች? የቢሮ ጥበቃዎች?  መቼስ መኪና የሚነዳ ሰው እንደምሳሌ ከተጠቀሰማ ትእግስት አዲዮስ ነው ጨዋታው፤ ባለው ይብሳላ! ይሄ ባህርይ የሁላችንም ሲሆን እኔ እንደ ዋና ምክንያት የምወስደው ሁላችንም ከእራሳችን ጋር የተጣላን የመሆናችን ውጤት ነው፡፡ አዎ በደንብ ተጣልተናል፡፡ ከእራሳችን ጋር አልተግባባንም፣ እራሳችንን አናዳምጥም፤ እርስ በእርስ አንደማመጥም፣ ጥሞና የለንም፣ ስክነት የለንም፡፡ ፈራጆች ነን ያውም ጅምላ ፈራጆች፡፡ እና ያንኑ ያልታረቀ ባህርያችንን ይዘን ከቤተሰቦቻችን፣ ከሥራ ባልደረቦቻችን፣ ከቢዝነስ አጋሮቻችን፣ ከማህበረሰቡ፣ ከቁሳቁሱ እና ከእንስሳው ጋር ሳይቀር እንገናኛለን፤ እንላተማለን፡፡ ልክ ነዋ! ከእራሱ ያልታረቀ ሰው እንዴት ሌላውን ሰው ሊያዳምጥ እና ሊያከብር ይቻለዋል! ስሜት አልባ የሆነውን በር እንኳን ጓ አድርጎ በማስደንገጥ (ለካ ስሜት የለውም) የሚረካ ሰው ቤት ይቁጠረው! እንስሳትን ሳይቀር በድንጋይ ማባረር እና መምታት ከምን ጋር ይገናኝ ይሆን!? የእርቅ ከእራስ ድርቅ መትቶናል ወገኖቼ!!!

አንድ ገጠመኝ ላውጋችሁ፡፡ አንዷ በወፍ በረር የማውቃት (የሩቅ ወዳጄ) በአንድ አጋጣሚ አገኘኋት እና አጋጣሚውን ተጠቅማ የምታማክረኝ ነገር እንዳላት እና ጉዳዩም ለጋራ ጥቅም እንደሆነ በማግባባት በቀጠሮ እንዳገኛት ተቃጠረችኝ፡፡ ዛሬ ጊዜው በቅርበት የሚያውቁትን ወዳጅ ለማግኘት እንኳን አልብቃቃ ባለበት “የጋራ ጥቅም” የሚለው ካለሁበት የስልጠና እና የማማከር ሥራ ባህርይ አንጻር ስላማለለኝ መጀመርያ በስልክ ወይንም በኢሜል ብንግባባ የሚል ሀሳብ አቀረብኩ፡፡ በእጄም አላለች፤ “በአካል እንገናኝ፤ በዚያ ላይ ከ15 ደቂቃ በላይ አልወስድብሽም!” በማለት ስላግባባችኝ እሺታዬን ሰጠኋት፡፡ ቀጠሮ ለማስታወስ ደጋግማ በመደወሏ የቀጠሮውን ቀን አሳጥረን በዚያው ሰሞን ተገናኘን፡፡ እሷም እንደ እኔው የጀበና ቡና አድናቂ ኖራለችና ቡናችንን ፉት እያልን ጨዋታ ተጀመረ፡፡ የተፈለግኩበትን በጉጉት እየጠበቅሁ ማዳመጤን ያዝኩ፡፡

ብዙ ነገሮችን ለመስራት ከሕልም ያለፈ እቅድ እንዳላት አጫወተችኝ፡፡ መሬት ያወረደቻቸውንም ሥራዎች ስትዘረዝርልኝ እያደነቅሁ እና “አቦ ይቅናሽ!” እያልኩ ነበር በጥሞና የማዳምጣት፡፡ በቆይታችን ግን ከእኔ ጋር የሚያገናኘውን ውል (ጫፍ) ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ቡናችንንም ጨርሰናል፡፡ አንዳንድ ሰው ስለሥራው፣ ስለእቅዱ፣ ስለ ነገው ሲያወራ ጭልጥ ብሎባችሁ አያውቅም? እንደዚያ ነበር የሆነው እና ከአንድ ሰዓት ያላነሰ የፈጀውን ወጓን እንዴት አድርጌ ሰብሰብ እንድታደርግልኝ እንደምጠይቃት እያውጠነጠንኩ ስልኬ ጠራ እና ገላገለኝ፡፡ “ይቅርታ መሄድ ስላለብኝ ከእኔ ጋር ለመስራት ያሰብሽውን አሳውቂኝ” አልኳት፡፡ መቸኮሌ አበሳጫት፤ እናም ለአስራ አምስት ደቂቃ ተቀጣጥረን ከአንድ ሰዓት ያለፈ የሰጠኋትን ጊዜ ከቁብም ሳትቆጥረው “ዳሩ እናንተ የሚዲያ ሰዎች እኮ እዚህም እዚያም  ስለምትፈለጉ ለቁምነገር አትሆኑም!” ብላኝ እርፍ!

አሁን ይህቺ ሴት ለአቅመ ምሳሌነት (ከእርቅ ከእራስ ጋር በተገናኘ)  እንዴት በቃች በሉኝ፡፡ አንደኛ እኔ የሚዲያ ሰው አይደለሁም፤ ብሆንም እንኳን የጅምላ ፍረጃን ምን አመጣው! ፈራጅነት አንዱ ከእራሳቸው ጋር የተጣሉ ሰዎች መገለጫ ነው፡፡ ሁለተኛ ቃል ከገባችው በላይ ረዥም ሰዓት የእራሷን ብቻ ስታወራ ምን ያህል አሰልቺ እንደነበረች ያለመረዳቷ ሌላ ውስጣዊ ፀብ ነው፡፡ “ይቅርታ ጊዜሽን ወሰድኩ!” ከማለት ይልቅ ወቃሽ መሆኗም እንደዚያው ሌላ ፀብ፡፡ እንደምንም ታግሼ ሀሳቧን ሳስጨርሳት ደግሞ የፈለገችኝ በጭራሽ ከእኔ ጋር በሙያም ሆነ በስነ ምግባር ለማይገናኝ ጉዳይ ነበር፡፡ ይህም እኔ ቃለ ምልልስ ለመስጠት በቀረብኩባቸው ሚዲያዎች ሁሉ እንድትቀርብ እና ስራዋን እንድታስተዋውቅ እንዳመቻችላት፡፡ እኔ እኮ በፀሐፊነቴ፤ ለሴቶች እና ለሕጻናት መብት ተሟጋች በመሆኔ እንጂ በቢዝነሴ ወይም በሙያዬ ማን አቀረበኝ! አልተደማመጥንም፣ አልተግባባንም፣ በቃ ምን አለፋችሁ እራሷ አውርታ፣ መረጃ ሰጥታ፣ ፈርጃ፣ ወቅሳ፣ ተበሳጭታ፣ ተቀይማ ጨረሰችው፡፡ ምክንያቱም ከእራሷ ጋር አልታረቀችማ! ያኔ እኔን አያድርጋችሁ!

ብዙ እንደዚህ ያሉ ገጠመኞች ስላሉኝ ነው “እርቅ ከእራስ!” ትክክለኛ እና ወቅታዊ ነገር መሆኑን ያመንኩት፡፡ ሰዎች ከእራሳቸው ጋር ሲታረቁ መጀመርያ የሚያዩት እራሳቸውን ነው፡፡ ድርጊታቸውን ወይንም አስተሳሰባቸውን ቆም ብለው ያጤናሉ፡፡ በጎ በጎውን እየመረጡ ማሰብ እና ማድረግ፣ እራስን ማዳመጥ፣ ከእራስ ጋር መግባባት፣ በትንሹም በትልቁም ብስጭትጭት ያለማለት፣ ሌሎችን ማዳመጥ እና ሀሳቦችን በበጎ ጎን ማየት፣ ሌሎችን ያለመፈረጅ፣ መመርመር፣ በጎ ያልሆነውን በጥሞና ማየት እና በእርጋታ መገሰጽ፣ ይቅር ባይ መሆን…ወዘተ የሚሉት ከእራስ ጋር የመታረቅ ምልክቶች (symptom) ናቸው፡፡ ለምሳሌ የሚያበሳጭ ነገር ማበሳጨቱን አያቆምም፡፡ ብዙ የምንበሳጭባቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ከእራሳችን የታረቅን ሰዎች ስንሆን ግን ብስጭታችን ምክንያታዊ እና መፍትሔ ፈላጊ ይሆናል እንጂ በትልቁም በትንሹም ነጭናጮች ወይም ብስጩዎች ሆነን አንቀርም፡፡

ከእራሳቸው የታረቁ ሰዎች እራሳቸውን ከማየት ባለፈ ሌሎችንም ያስተውላሉ፡፡ ለሌሎች ሰዎች ስሜትም ይጠነቀቃሉ፡፡ ከአንደበታቸው በሚወጣው እንዲሁም በድርጊታቸው ሁሉ እራሳቸውን ብቻ በማስደሰት ላይ አያተኩሩም፤ ይልቁንም ሌሎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ይመረምራሉ እንጂ፡፡ ሌላው ቢቀር መስማማት በሌለበት ቦታ ማስማማት ቢያቅታቸው እንኳን እነሱ ተጨማሪ አባባሽ አይሆኑም፡፡

ከላይ እንደጠቀስኳት ወገናችን ያሉ ሰዎች የእራሳቸውን ገድል አውርተው ሲጨርሱ መረጃ በሌላቸው ነገር ላይ እርግጠኛ ሆነው ሌሎችን ሲፈርጁ ስመለከት የሆነ ያልተግባባ ማንነት ቢኖራቸው ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እኔም ፈራጅ ሆንኩ እንዴ! ከእራስ መታረቅ ለሁላችንም አንዱ የሕይወት ፍልስፍና መሆን አለበት፡፡ እኔ “የሕይወቴ ቅኝት” ብዬ የጻፍኩት መጽሐፌ ነው ከእራሴ ጋር የተጣላሁባቸውን ዘመኖች እንዳስታውስ እና ከእራሴ መታረቅ አንዱ የሕይወቴ ግብ ሆኖ እንድለማመደው ያደረገኝ፡፡ በልምምዴ ውስጥ በብዙ ነገር እየተጠቀምኩ ነው፤ እስቲ እናንተም ሞክሩት! ደግሞ ከእራሴ መች ተጣላሁ እንዳትሉ! ያለንበት የኑሯችን ሁኔታም ለፀባችን አጋዥ ነው እና ለእራሳችን ታማኞች ሆነን መጣላታችንን እንመን፡፡ እርቅ የሚኖረው መጣላታችንን ስናምን ነውና! ለዛሬ ጨርሻለሁ!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *