ሴትየዋ!

እኛ ሀገር “ከፍትፍቱ ፊቱ” የሚባል አሪፍ አባባል አለ፤ ብዙዎቻችን የምንወደው ይመስለኛል አባባሉን፡፡ እናም በተቻለን መጠን የምንጣጣረው ጥሩ ፊት አላት/አለው እንድንባል ነው፤ እኛም ከሌሎች የምንጠብቀው ይህንኑ ነው፡፡  ፍትፍት ለአባባሉ ድምቀት የተመረጠው እንደሚመስለኝ ያው እኛ ኢትዮጵያውያን ፍትፍት እንወዳለን ምክንያቱም በልተን ያጠግበናል፣ እንደ ሰው በምግብነቱ ቆመን እንሄድ ዘንድ ስለሚጠግነን ነው፡፡ ታድያ የአባባሉ ትርጉም ደግሞ ባይበላ ጥንቅር ብሎ ይቅር መጀመርያ ፊት ይሰጠኝ፤ ጥሩ አቀባበል ይደረግልኝ፤ ከዚያ ብበላም ባልበላም ጠግቤ ቆሜ እሄዳለሁ እንደማለት መሰለኝ፡፡ ነገርየው ውሸት ነው፤ ማለቴ አባባሉ ግነት ነገር አለው ምክንያቱም ያልበላ ሰው ወይም የራበው ሰው ፊት አያይም፤ ምግቡ ተወርውሮም ይሁን ተቀባብሎ ይሰጠው ብቻ መብላት ነው የሚፈልገው፤ ሐቁ ይህ ነው፡፡ ያው እኛ በተረት እና በአባባል ከማደጋችን የተነሳ እውነት እና ማስመሰል ተቀላቅለውብናል፡፡ የምርም ደግሞ  ፊት እናያለን፡፡ ከመነሻዬ አሪፍ ያልኩትም ሁላችንም ፊት ማየታችንን ስላመንኩ እንጂ አባባሉን አጥርተን ካየነው አሪፍ ስለመሆኑ ጥያቄ ያስነሳል፡፡

ስለሴትየዋ መጻፍ ሳስብ ይሄ አባባል/ተረት ቀድሞ የመጣልኝ በምክንያት ስለሆነ ነው መግቢያዬ ያደረግኩት፡፡ ምክንያቱም ሴትየዋ ፊት የላትም ማለቴ ከፍትፍት ጋር የሚወዳደር ፊት አልፈጠረባትም፤ አልያም አስፈላጊነቱን አላመነችበትም፡፡ ይህንን ስል ገጽታ የላትም እያልኩ አይደለም፤ ያውም ደማቅና ቆንጆ ገጽታ ነው የተሰጣት፡፡ ግን ሁላችንም የምናውቃት በተቆጪነቷ ነው፡፡ ስትቆጣ ሰው አለ የለም አትልም፣ ቦታና ጊዜ አትመርጥም፣ መናገሯ ወይንም መቆጣቷ ስለሚያስከትለው የስነልቦና ጫና (ስሜት) አትቀምርም፤ በጥቅሉ ጥፋት ካየች ለአፍታም አታልፍም ወይንም አታሳድርም፡፡ ቁጣዋ ባልከፋ! ያው የእኛ ነገር ሰው አየ ወይ አላየ አይደለ ጉዳያችን? በድጋሚ ሌላ የታዘበ ፊት እንፈልጋለን እናም እንሸማቀቃለን ማለት ነው፡፡  ምን አለፋችሁ ከእሷ ጋር ወግ የፈለገ ሰው ማስኩን ማውለቅ አለበት፤ ክንብንቡን፡፡ አለበለዝያ በገረፍ ገረፍ ወሬ ከእሷ ጋር መግባባት ስለማይቻል አንድ ፊቱን ያለማውራት ይመረጣል፡፡ አንድ ጊዜ ብስጭትጭት ያደረገችኝን ገጠመኝ መቼም አልረሳውም፡፡ በአንዱ ወርሀዊ ስብሰባ ላይ እጄን ለጥያቄ አውጥቼ እድል የምትሰጠው እሷ ነበረችና ሳትሰጠኝ ቀረች እና ስለተናደድኩ ከምብከነከን ብዬ አሳቻ ቦታ ጠብቄ ለምን እድል እንዳልሰጠችኝ ስጠይቃት “አንቺ እኮ ወሬ ታረዝሚያለሽ!” በማለት ጮክ ብላ በመናገር ጢሜን አበረረችኝ፡፡ በወቅቱ ሀሳቤን በምችለው ልክ መግለጽ ሲገባኝ እንዴት ወሽመጤን ትቆርጠዋለች ብዬ የምር ተቀየምኳት፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ከእሷ ጋር የሚኖረኝን ቆይታ አስቀድሜ በሀሳቤ ተለማምጄ (rehearse) አድርጌ ነበር የማዋራት፤ በቁጠባ፡፡ የማታ ማታ ነገር እየገባኝ ሲሄድ ቅያሜዬን (እሷ የማታውቀውና ዛሬ ይህን ስታነብ የምትሰማውን) አነሳሁት፡፡ ለምን ያላችሁ እንደሆነ ቃላት ቁጠባ ስላስተማረችኝ፡፡ ከዚህም በተለየ ሰዎችን በፊታቸው ወይንም በቃላቶቻቸው ከመፈረጅ ይልቅ በጥሞና እንዳያቸው እና እንድረዳቸው ምክንያት ሆናኛለች፡፡ እኔ እንግዲህ እንደዚህ የተማርኩባት እና ልረዳት የቻልኩት ከብዙ ጊዜ በኋላ ነው፡፡ ግን ብዙ ሰዎች በዚህ መልኩ አይረዷትም፡፡ እናም በደረቅ እውነቷ  እና ግልጽነቷ ፈርተዋት እና ሽሽተዋት ቀርተዋል፡፡

ለነገሩ ሰው ፊት ጮክ ብላ የምትቆጣውን እና ስሜቷን እንደወረደ የምትገልፀውን ነገር ማንም እንደማይወድላት ለእሷም ባእድ አይደለም፤ ጠንቅቃ ታውቀዋለች፡፡ ችግሩ እሷ መልእክቷን ስለማስተላለፏ እንጂ ስለይሉኝታ ቁብም የላት፡፡ ለመለወጥም አትፈልግም፤ በምርጫዬ ፈልጌ የሆንኩት መሆን ነው ትላለች፡፡ አንዳንዴ ለብዙ ዓመታት ውጭ ሀገር ከመኖሯ የተነሳ እና ከባህሉ የራቀች በመሆኗ ይመስላል፤ ግን እሱም ብቻ አይደለም፡፡ ብዙ ዳያስፖራ ቤተሰቦቻችን እና ጓደኞቻችን ባህሉን እና ወጉን በሻንጣ ሸክፈው ይዘው የሄዱ እስኪመስል በቅርስነት በአደራ አኑረውታል፤ አንዳች ሳይለወጡ፡፡ ግን ወግ ባህላችን በተለይ ይሄ ሴትየዋ እየሄደችበት ያለው ለሰዎች ትክክለኛ እና እውነተኛ እፀፅ መንገር ምን ያህል አቅም አለው ይሆን? በግልጽነት ያለመነጋገር ፣ያለመተቻቸት እና ያለመተራረም መከባበር ነው ያለውስ ማነው? ግልጽነትን የምንፈልገው ከሆነ ማነው የሚያመጣው ወይንም የሚያለማምደን? ሴትየዋ እንደሆነ ወደ እኛ አትመጣም!!

በጊዜ ሂደት ይህቺን ሴት እየቀረኳት እና እያወቅኳት ስሄድ እንኳን ልፈራት እና ልጠላት ይቅርና ጭራሽ ሳለያት ወይንም ድምጽዋን ሳልሰማ የከረምኩ እንደሆነ ናፍቆት ያንገላጅጀኛል፡፡ በእሷ ልክ ለሰው የሚያስብ፣ ሰውን የሚረዳ፣ ጓደኛ የሚሆን፣ ችግር የሚፈታ፣ የታመመ የሚጠይቅ፣ የሚያስተባብር፣ የሰው ጉዳይ የእኔ ጉዳይ ብሎ የሚከታተል፣ የሚያዳምጥ፣ የሚያማክር፣ የሚያስተሳስር፣ የሚያስተሳስብ፣ አስመሳይነት ያልጎበኘው ደረቅ እውነተኛ ሰው ምናልባትም በዘመናችን እና በምድራችን ካለ አንድ እሷ ብቻ ናት፡፡ ይህ እውነተኛ ምስክርነት እህቶቼን እና የልብ ጓደኞቼን ቅር እንደማያሰኝብኝ አምናለሁ ምክንያቱም ማናችንም እሷን አይደለንምና! በቃ ልንገራችሁ አይደል!? ሴትየዋ ሰው ናት! ሙሉ ሰው፤ እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው ሁን ያለው ዓይነት ሰው እሷ ትመስለኛለች፡፡ የእኔ ነገር አጋነንኩ መሰለኝ! ለካ ሰውን ቁጡ ሁን አላለውም!  እሱም (የቁጠኝነቷ ነገር) እኮ በዘመን ብዛት እየቀነሰ መጥቷል! ትንሽ ቅር የሚያሰኘኝ ነገር ቢኖር እኔ እና ጥቂቶች የተረዳናት ስንቀር  ብዙዎች ያልተረዷት እና ያላወቋት መጎዳታቸው ነው፡፡

እንደዚህ ያናዘዘችኝ ሴትዮዋ ግና ማን ትሆን!? ይህቺ ሴትዮ እኛ የማንተዋወቅ የነበርን እና በተለያየ ሙያ ዘርፍ ተሰማርተን የምንገኝ ሴቶች በአንድ ማህበር ጥላ ሥር በእህትማማችነት ያስተሳሰረች፣ መካሪያችን፣ አስተማሪያችን፣ ተቆጪያችን፣ አብቂያችን፣ አዳማጫችን፣ ምክር ጠያቂያችን፣ ዋጋ ሰጪያችን፣ ዛሬ የምጽፍበትን ዌብሳይት ለመከፈት ምክንያት የሆነች፣ የብዙዎቻችን የክት የምንላት ታላቅ እህታችን ናሁሰናይ ግርማ ትባላለች! ናሁዬ አባቷ ስሟን ሲሰይሙ “ጥሩ ነገር ሆነ  ወይንም ሊሆን ነው!” ብለው ነው ይህን በተለምዶ ለወንዶች የሚሰጥ ስም ነጥቀው የሰጧት፤ ነፍሳቸውን በገነት ያኑረውና ትንቢታቸው እውን ሆኗል! እኔ እንደ ጠዋት ፀሐይ እመስላታለሁ፤ ሁላችንም በዘዴ የምንሞቃት! በዚህ ድንቅ የሴቶች ወር ለእኛ ለሴቶች ባደረገችው ውለታ አክብሮቴን እና ፍቅሬን በመግለጽ የጻፍኩት ነው! ለዛሬ ጨረስኩ!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *