ፖለቲካውን እንጫወተው!

የዛሬ ጽሑፌን መነሻ ሀሳብ የወለደልኝ አብረን ሰርተን ለዓመታት ሳላገኛት ኖረን በቅርብ ቀን ያገኘኋት የሥራ ባልደረባዬ ናት፡፡ ይህቺ ሴት አብረን ስንሠራ በጣም አስገራሚ ባህርይ ነበራት፡፡ በተለይ አለቃ/ኃላፊ ለፀብ ከፈለጋችሁ የመረጃው ምንጭ እሷ እንደምትሆን ከጀርባዋ ይወራ ነበር እና ከሠራተኞች በቡና ወይንም በማንኛውም ሁኔታ ልትቀላቀል ስትመጣ “ጨዋታ ቀይሩ!?” ይባል እንደነበር አልረሳውም፡፡ ሌላው በማንኛውም ውይይት ወይም ስብሰባ ኃላፊያችን ስህተት መሆኑ ቢታወቅ እንኳን የእሱ ደጋፊ ናት፡፡ እሱ በሌለበት “ግን አንቺ ያንን ሀሳብ አምነሽበት ነው?” ተብላ ስትጠየቅ “እሱ ካመነበት ትክክል ቢሆን ነው ብዬ አምናለሁ፤ አለቃ እኮ ነው!” ስትል ፍርጥም ብላ ነበር፡፡ አለቃችንም በፍጥነት ተቀባይነት እንዲያገኝለት የሚፈልገውን ሀሳብ የሚያሳልጠው በእሷ በኩል ነው፡፡ ታድያ አይናችን እያየ ሁለቴ የማይገባትን ሹመት አግኝታለች፡፡ ያን ጊዜ አንዱ ባልደረባችን “አይ ፖለቲካ!” እያለ ይማረር ነበር፡፡ እኔ በወቅቱ ምን ማለቱ እንደሆነ ባይገባኝም በኋላ ፖለቲካውን እየኖርኩት ስሄድ ነበር የገባኝ፡፡ 

ፖለቲካ ማህበራዊ ሳይንስ ነው፡፡ የፖለቲካ አባቱ አርስቶትል ነው ይባላል፡፡ እኔ ስለ ፖለቲካ ካወራሁ የእድሜዬን 60% (አጋነንኩ እንዴ!) የኖርኩበትን የቢሮ ወይንም የድርጅት ፖለቲካ ነው፡፡ ሀገር በፖለቲካና በፖለቲከኞች እንደምትመራ ሁሉ ድርጅቶችም እንደዚያው በፖለቲካ ይቃኛሉ፡፡  የድርጅት ፖለቲካ አባቱ ማን እንደሆነ ግን ምንም የተጻፈ ነገር አላገኘሁም፡፡ ብቻ ግን ማንም ሆነ ማን ፖለቲካው ያስፈለገው የድርጅቱን አላማ እና ግብ ለማሳካት ነው፡፡ ሠራተኞችም የሚቀጠሩት አጀንዳቸውን ለማራመድ ሳይሆን ድርጅቱ የተቋቋመለትን ዓላማ ለማራመድ ነው፡፡ ይሁን እና በዚህ ሂደት ውስጥ አንዳንድ ሠራተኞች የራሳቸውን አጀንዳ ማከላቸው አይቀሬ ነው፡፡ እኛ ሰዎች ደግሞ የራሳችንን አላማና ግብ ለማሳካት ስንጠቀምበት ድርጅቱን አስቀያሚ ገፅታ እናላብሰዋለን፡፡ 

የድርጅት ፖለቲካ አዎንታዊም አሉታዊም ገጽታ አለው ማለት ነው፡፡ በአዎንታዊ ገጽታው ካየነው የድርጅቱን ስትራተጂክ ዓላማዎችን ግብ እንዲመቱ የሚከወኑ እንቅስቃሴቆች ወይም ተግባራት ሲሆኑ ለሠራተኞችም በንቃት እና በትጋት ሠርተው ስኬታማ የሚሆኑበት ነው፡፡ የድርጅት ፖለቲካ የማይቀር ስለሆነ ጥሩ ተጫዋች መሆንን ይጠይቃል፡፡ ብዙ ጊዜ የተመደብንለትን ሥራ፣ የድርጅቱን ግብ፣ ተልእኮና ራእይ እየወደድን ነገር ግን ውስጡ ከሚሠሩ ሠራተኞች ጋር ሳንግባባ ቀርተን ሥራችንን እስከመጥላት ብሎም እስከመልቀቅ የተገደድንበት ጊዜ ይኖራል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ግምቴ ከእኔ ከራሴ ገጠመኞች ተነስቼ ነው፡፡ ይሄ የሚከሰተው ደግሞ የድርጅቱ ፖለቲካ አሉታዊ ገጽታው የገዘፈ ሲሆን ነው፡፡ እናም የድርጅት ፖለቲካ የሚናቅ ነገር ስላይደለ ሁላችንም ምክንያቱን ወይም መነሾውን ብናውቅ ይጠቅመናል እንጂ ጉዳት የለውም በማለት ነው ይህንን የከተብኩላችሁ፡፡

አሉታዊ ገጽታ ያለው የድርጅት ፖለቲካ የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉት ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ ከእነዚህም ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፤

የውስጥ እድገት ወይም ስልጣን ለማግኘት የሚደረግ ሽኩቻ በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ሠራተኞች ማደግ ያለባቸው በሚያስመዘግቡት የሥራ ውጤት እና በሚያሳዩት መልካም ሥነ ምግባር መሆኑን ሕግና ደንቦች ቢያስቀምጡትም እውነታው ግን ለኃላፊዎች ቀኝ እጅ መሆን እና የእነሱን አጀንዳ ማራመድ ሲሆን ፖለቲካ ቀደመ እንላለን፡፡ ኃላፊዎች በተለይ ከድርጅቱ ይልቅ የእራሳቸውን ጥቅማጥቅም ቅድምያ የሚሰጡ ከሆነ ለተልእኳቸው አጋር መሻታቸው አይቀሬ ነው፡፡  ያው ከቦታው ላይ ወይ በቅቷቸው አልያም ድክመታቸው ተነቅቶባቸው እስኪነሱ ሁሉ በእጃቸውም አይደል! በዚህ ፍልምያ ያሉ ሠራተኞች የሥራውን አካባቢ (work environment) መጥፎ ያደርጉታል፡፡

በሁለተኛነት የተቀመጠው በድርጅቱ ከሚከናወኑ ለውጦች ጋር እራስን ያለማዘጋጀት እና ያለመቀበል የሚያመጣው ፍርሀት ነው፡፡ ሰዎች ለውጥን መቀበል የሚቸገሩት ደግሞ ከተደላደሉበት የሥራ እርከን የመነሳት ፍርሀት ሲሆን ለዚህ ደግሞ በእራስ ያለመተማመን ዋናው ምክንያት ነው፡፡ ምናልባትም እራሳቸውን ያላበቁ እና ያልተዘጋጁ ሠራተኞች ከሆኑ ደግሞ በፖለቲካው ውስጥ ያላቸው ሚና የባሰ ይሆናል ማለት ነው፡፡

በሶስተኛ ደረጃ የተቀመጠው ደግሞ በድርጅቱ ውስጥ ስለሚከናወነው ማንኛውም እንቅስቃሴ ወይም ውሳኔ በቂ መረጃ ማጣት ነው፡፡ እንደዚህ ያሉ ሁኔታዎች ለሀሜት፣ ለሽብር፣ ለመከፋፈል እና አፍራሽ ለሆኑ ድርጊቶች በር ይከፍታሉ፡፡ የድርጅቱም ፖለቲካ በዚያው የተቃኘ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ምቀኝነት እራሱን የቻለ የድርጅት ፖለቲካ ፈጣሪ መሆኑን አስባችሁ ታውቃላችሁ? አንዳንድ ሠራተኞች ሠርተው በውጤታቸው መውጣት፣ በድክመታቸው እራሳቸው ላይ መሥራት እና መብቃት ሲችሉ በሌሎች ላይ ከፍተኛ የቅናት እና የምቀኝነት መንፈስ ያድርባቸዋል፡፡ ከዚያማ ዘመቻቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ግምቱን ለእናንተ ትቼዋለሁ፡፡

እምነት ማጣት ደግሞ ሌላው ምክንያት ነው ይባላል፡፡ ሠራተኞች በድርጅቱ ላይ እምነት ሲያጡ፣ በተለይ በአሠሪዎች ወይንም በኃላፊዎች እምነት ሲያጡ ስጋት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ስጋት ደግሞ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ከሥራ ይልቅ ወሬ እና ሐሜት ይነግሳሉ፤ ድርጅቱም  ሠራተኞችም የተዛባ ፖለቲካ ውስጥ ይወድቃሉ ማለት ነው፡፡

አንዳንድ ድርጅቶች የበቁ ሠራተኞችን የሚመርጡበት አካሄድም (Reward System) የራሱ የሆነ ሚና አለው፡፡ ሠራተኞች በሥራቸው፣ በውጤታቸው እና በመልካም ሥነምግባራቸው ሳይሆን ለኃላፊዎች በሚያቀብሉት መረጃ ወይንም ከመስመር የወጣ ግንኙነት በሚሆንበት ድርጅት ውስጥ ምን ልንጠብቅ እንችላለን!?

እንግዲህ እነዚህ ጥቂቶቹ ሲሆኑ ሌሎችም ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡ እስቲ ሁላችንም ወደ መ/ቤታችን በሀሳባችን እንመለስና ምን ዓይነት የድርጅት ፖለቲካ እንዳለ እናስታውስ፡፡ “ፖለቲካ የለም” የምንል ሰዎች ካለን ድርጅቱ የለም አለበለዝያ ድርጅቱ የአንድ ሰው (one man show) ነው ማለት ነው፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት አዎንታዊ የሆነው የድርጅት ፖለቲካ ለድርጅት እድገት እና ለሠራተኞችም ጠቃሚ እና ተጽእኖ ፈጣሪ ነው፡፡ አሉታዊ የሆነው ፖለቲካ ደግሞ እንደዚያው ጠቃሚ ያልሆነ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ እያንዳንዳችን ገለልተኛ ሆነን ሥራችን ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ የድርጅቱን ፖለቲካ በደንብ መረዳት እና ማወቅ ያለብን መሆኑን ለመጠቆም ነው፡፡

እኔ “ሥራዬን እስከሠራሁ እና ውጤታማ እስከሆንኩ ሌላው ትርፍ ነው” የሚል አመለካከት ነበረኝ፡፡ እናም በድርጅት ውስጥ ከእኔ ውጤት ይልቅ ፖለቲካውን አብልጠው የተጫወቱት የተሻለ ድምጽ የነበራቸውን ዘመን ሳስታውስ ጥሩ ስሜት አይሰማኝም፡፡ ዛሬ ትናንት ስላይደለ አልመልሰውም፡፡ ለእናንተ ያለኝ ምክር ጠንካራ ሠራተኛ ከመሆን ጎን ለጎን ጥሩ የድርጅት ፖለቲካ ተጫዋች መሆን ያዋጣል የሚል ነው፡፡ ለዛሬ ጨረስኩ፡፡

ፍፁም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

Share on your socials!

1 thought on “ፖለቲካውን እንጫወተው!”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *