የዋኋ የሥራ ባልደረባዬ¡

አንዲት የቀድሞ የሥራ ባልደረባዬ ከረምረም ብላ ከቆየች በኋላ ስልክ ትደውልና ሞቅ ደመቅ ያለ ሰላምታ ትሰጠኛለች፣ ቤተሰቤን በሥማቸው እያስታወሰች ደህንነታቸውን ትጠይቀኛለች፣ ታደንቀኛለች፣ ታሞጋግሰኛለች፤ ከዚያ በደንብ ካሟሟቀችኝ በኋላ “እኔ የምልሽ እስቲ አንድ ነገር ልጠይቅሽ?” በማለት ትጀምርና አከታትላ ከግነት ጋር ደርዘን ጥያቄዎችን እና መረጃዎችን ትጠይቀኛለች፡፡ ምላሼ እስኪገባት ትንታኔ ጠይቃ የፈለገችውን መረጃም ይሁን እውቀት ካገኘች በኋላ “መቼስ እኔ ካልደወልኩ አትደውይም፣ እኔ ደግሞ በአንቺ የሚጨክን አንጀት የለኝም” በማለት ወቀሳዋን አስረግጣ ከነገረችኝ በኋላ ስልኩን ትዘጋዋለች፡፡ ይሄ አንዴ ሳይሆን በደወለችልኝ ቁጥር የሚደጋገም ነው፡፡ አንድ ቢሮ በነበርንበት ጊዜም ሆነ ከዚያ ቢሮ ከወጣሁ በኋላ (ቀድምያት ነበር የወጣሁት) ይህንኑ ታደርጋለች፡፡ ከዚያም በተጨማሪ በተለይ አብረን በነበርንባቸው የሥራ ዘመናት ስለ እሷ መልካም ባህርይ እና ስለሥራዋ ለኃላፊዎችም ሆነ ለሥራ ባልደረቦቻችን እንድናገርላት (Advocate እንዳደርግላት) ትጎተጉተኝ ነበር፡፡ አንዳንዴ ከእኔ ባገኘችው መረጃ፣ ምክር ወይንም እውቀት በመጠቀም ያገኘችውን ለውጥ ወይም ውጤት እንድታሳውቀኝ እጠይቃታለሁ፡፡

እሷ እቴ! አድርጋውም አታውቅም፡፡  ምክንያቱም የምትደውለው የናፍቆት ሰላምታዋን ለመስጠት ነዋ! ይህችን የዋኋን ባልደረባዬን (የዋህ¡) የዛሬ ጽሑፌ መነሻ ያደረግኳት በምክንያት ነው፡፡ መደወሏ፣ የምትፈልገውን መረጃ መጠየቋ እና ስለእሷ በእራሷ አንደበት መናገሩ ያስፈራትን እንድናገርላት መማጸኗ፣ በዚህ መልኩ የተሻለ ነገር ለማግኘት መሻቷ ክፋት አልነበረውም፡፡ እንደባለሙያ የምናውቀውን መናገር፣ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው መደገፍ  ግድ ይለናል፤ እኛም ጎደሏችንን አንብበን አልያም ያውቃሉ ከምንላቸው ጠይቀን እንደምንሞላው፡፡  የእኔ ግራ መጋባት እና ጥያቄ ግን “አንዳንዶች እንደዚህች የዋኋ ባልደረባዬ ያሉ ሰዎች ግልጽነት፣ አመስጋኝነት፣ መልካም ግንኙነት እና ለሚገባው ዋጋ (credit) መስጠት  እንደምን ተሳናቸው ይሆን?” ነው፡፡

ለባልደረባዬ ይህ ዓይነት ባህርይ የግሏ አይደለም፡፡ እንደዚህ ያሉ ሰዎች በዙሪያችን ብዙ አሉ፡፡ የሚፈልጉትን መረጃ ለማግኘት ብቻ የሚደውሉ ነገር ግን የደወሉበትን ምክንያት በግልጽ ማሳወቅ የማይፈልጉ እናም ለተሰጣቸው ድጋፍ ዋጋ መስጠት የተሳናቸው፡፡  ድብቅነት ባህላችንም አይደል!  ይህስ ይሁን ግን ደግሞ “የደወልኩት እኔ ሰው ፈላጊ ስለሆንኩ ነው!” በሚል ሽንገላ ሲታጀብ ያስገርማል፤ ባህላችንም አይደለም፡፡ የዋህነት አልኩት እንዴ¡

አንድ ለሴቶች ብቻ እንደ ተጻፈ ቅዱስ መጽሐፍ የማየው ብዙ የተማርኩበት ሎይስ ፍራንኬል (ፒኤችዲ) የጻፈችው “Nice Girls Don’t Get the Corner Office: Unconscious Mistakes Women Make That Sabotage Their Careers” የተሰኘ መጽሐፍ አለ፡፡ እዚያ ላይ ስለእኛ ስለሴቶች በሙያዋ ያየችውን ስህተቶቻችን እና የምናሻሽልበትን ምክሮቿን ጽፋለች፡፡ በነገራችን ላይ “NICE”  የሚለውን የተጠቀመችበት በሥራቸው (በሙያቸው) ስኬታማ የሆኑ ሴቶች ለማለት ነው፡፡ ከጠቀሰቻቸው አንድ መቶ አንድ ስህተቶች ውስጥ ከላይ የጠቀስኳትን የሥራ ባልደረባዬን እና መሰሎች ባህርይ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም ተቀራራቢ የሆነ ስህተት ጠቁማ ምክር መክራለች፣ እናም እንጋራ!

ሙያተኛ ሴቶች (Career Women) በእውቀት እና በልምድ የሚበልጧቸውን ሴቶች ወይንም ወንዶች የሕይወት አቅጣጫ መሪነት (Mentorship) እና ስለእነሱ የሚናገርላቸውና የሚመሰክርላቸውን (advocacy) ጠቀሜታ ችላ ይላሉ፡፡ በዚህም የተነሳ በሙያቸው በትክክለኛ መንገድ ለማደግ (getting promoted) ይቸገራሉ፤ ካለች በኋላ በመ/ቤቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሕይወት አቅጣጫ መሪ (Mentor) የሚያገኙበትን መንገድ መፈለግ እና ተጠቃሚ መሆን አለባቸው ትላለች፡፡ ድንቅ ምክር ነው፡፡ በነገራችን ላይ የቀድሞዋ የሥራ ባልደረባዬ በዚህ ረገድ ተጠቃሚ መሆኗን ልብ በሉ፡፡ በዚህ ልናደንቃት ይገባል፡፡ ልክ እኔ ጋር ደውላ የምትፈልገውን እንደምታገኝ ሌሎችም ጋር ይህንኑ እንደምታደርግ እንገምት፡፡ እሷ የጎደላት ቅንነት ነው፡፡ እኔ ዘግይቼም ቢሆን ስለነቃሁ ፊት ለፊት ስህተቷን ነግሪያታለሁ፡፡ በዚህ የተነሳ መደወሏን አቁማለች፡፡ ይሄኛው ነው የዋህነቷ፡፡ ይቅርታ ጠይቃ አገባቧን ብታስተካክል ያለኝን ለማጋራት ምን ገዶኝ ነበር! አጉል ብልጣብልጥነት ግን ለተወሰነ ጊዜ ተጠቃሚ ሊያደርገን እንጂ ዘላቂነት አይኖረውም፡

ወደ ፀሐፊዋ ምክር እንመለስና ስንቶቻችን ነን በግልጽነት ምክር እና አቅጣጫ የሚያስይዙን ሰዎችን የምንቀርብ እና የምንጠይቅ? እንደዚያ የምናደርግ ካለን እሰየው ነው፡፡ የዚህ እድል ተጠቃሚዎች ከሆንን በኋላስ ደግሞ ላገኘነው ወይንም ለምናገኘው አገልግሎት ምስጋናችንን የምንሰጥ ስንቶቻችን ነን? ሰዎች የደረሱበትን ደረጃ ለመድረስ ዋጋ ከፍለዋል፤ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ስሜታቸውን እና ሌላም፡፡ እናም ከእነሱ ለምናገኘው ማንኛውም ጥቅማጥቅም በአክብሮት እና በምስጋና አጸፋውን ልንሰጣቸው ይገባናል፡፡

በአጠቃላይ ሜንቶርሽፕ ማግኘት አንድ አማራጭ ነው፡፡ ታድያ ደግሞ የምንፈልገውን መረጃ ይሁን እውቀት ወይንም ማንኛውም ነገር ከሰው ስንጠይቅ ዙርያ ጥምጥም በመሄድ ጠይቀን ያገኘን ሳይሆን በብልጣብልጥነት ያገኘን መስሎን እርካታ የምናገኝ ሰዎች ይህ ባህርያችን መታከም ያለበት ትልቅ የአእምሮ ቀውስ ነውና እንፈወስ! መጠየቅ ብልህነት ነው፣ የዋህ እና ግልጽ ጠያቂዎች እንሁን! ለተሰጠን ነገር (መረጃ፣ ቁሳቁስ ወይንም እውቀት) ደግሞ አመስጋኞች እና ዋጋ ሰጪዎች እንሁን፡፡ ምናልባትም ነገም ሲቸግረን ለመጠየቅ የሚያሳቅቀን ነገር ወይም የማስመሰል ድራማ መተወን አይኖርብንም፡፡ ከዚያም ባለፈ ከልክ ያለፈ እራስ ወዳድነት በመልካም ግንኙነትን የሚገኘውን ጣፋጭ ፍሬ ከማሳጣቱም በላይ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ይህንን ጽሑፌን የምታነቡት ሙያተኛ (Professional) እንደሆናችሁ አምናለሁ፡፡ የሙያተኝነት (professionalism) አንዱ መገለጫ የሰዎችን ሀሳብ ማክበር እናም በምላሹ የራስ ሀሳብ እንዲከበር መሻት መሆኑን ላስታውሳችሁ እወዳለሁ፡፡ መከባበር ደግሞ ከብልጣብልጥነት የጸዳ ነው፡፡ የዋሆች እንሁን! ለዛሬ ጨርሻለሁ!

– Fitsum

Share on your socials!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *