ከእራሳችን ጋር አንጠፋፋ!

አንድ የሙያ ስልጠና የመውሰድ እድል ገጥሞኝ ከዚህ ቀደም በየትኛውም የሕይወት መስመር አግኝቻቸው ከማላውቅ ሴቶች እና ወንዶች ጋር ለሁለት ቀናት አሳልፌ ነበር፡፡ አዳዲስ ሰዎችን መተዋወቅ እና ትስስር ማድረግ ከሚያስደስቱኝ ነገሮች አንዱ ነው፡፡ እናም ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ከፈትፈት ወይንም ቀለል ብዬ መግባባት ቋሚ ተግባሬ ነው፡፡ ይህንን በማድረጌም እጅግ ተጠቅሜአለሁ፡፡ በዚህኛው የሁለት ቀናት  ግን አንዴም ከፈትፈት እያልኩ አንዴም ፈራ ተባ በማለት ቆጠብጠብ እያልኩ ቆይታዬን ብዙም ተናፋቂ እንዳይሆን አድርጌ ለመጨረስ ተገደድኩ፤ ወድጄ አልነበረም፤ ሰዎቹ ይሁኑ እኔ ተግባቦታችን የጎደለው ነገር ነበር፡፡

የሆነውን ለምን በአጭሩ አላጫውታችሁም! ሴቶቹ በተለያዩ ሙያዎች አብዛኛዎቹ በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩ ሲሆኑ በኢኮኖሚም እራሳቸውን የቻሉ ከሚባሉ ጎራ ናቸው፡፡ በኢኮኖሚ እራስን መቻል በተለይ ለሴቶች አኩሪ ተግባር ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ኢኮኖሚ ደግሞ በእውቀት ሲታገዝ እንዴት ድንቅ እንደሆነ ሁላችንም እናምናለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ታድያ እነዚህ ያገኘኋቸው ሴቶች ከእውቀታቸው በተሻለ ኢኮኖሚያቸው ገዝፎ የሆነ ሚዛን ያዛባ ይመስላል፡፡ አማርኛ እያወሩ እነሱ እየተግባቡ እኔ ግን ልረዳቸው አልቻልኩም ነበር፡፡ የቃላት አጣጣላቸው፣ እርስ በእርስ የሚወራወሯቸው ግብረ መልሶች ሁሉ ለእኔ አዳዲሶች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ አንዷ ምን አለች መሰላችሁ፤ ” እኔ የዚህ ሀገር ቡና አይጣፍጠኝም፣ ኔስ ካፌ የላችሁም?” ብላ የሆቴሎቹን አስተናጋጆች ጠየቀች፡፡ ምን እንደጠየቀቻቸው እንኳን የገባቸው አይመስሉም ነበርና መልሳቸው አላረካትም፡፡ ከዚያ “ከየት ነው የሚያመጧቸው!?” ከማለቷ ሁሉም በሚባል ደረጃ በሳቅ አጀቧት፡፡ እኔ ግን ያልተለመደው የእሷ ጥያቄ እንጂ የእነሱ ያለመረዳት ሊያስቀኝ አልቻለም፡፡ ይሄ አንዱ ገጠመኝ ነው፡፡

ሌላው ትዝብቴ ደግሞ የአነጋገር ዘይቤ ነበር፡፡ በስልጠናው ላይ ተሳትፎ በሽበሽ የነበረ ቢሆንም ቃላቶቹ ከአንዳንዶቹ አንደበት ሲወጡ ወይ ይቆራረጣሉ አልያም ይጎተታሉ፤ ለምሳሌ አንዲት ያልገባትን ለመጠየቅ የፈለገች ሴት ” እእእእ እኔ የምለው እእእእ ለምን…” ብቻ ምን አለፋችሁ “ቋንቋችን የት አለ!” ነበር ያስባለኝ፡፡ ሌላ ያስተዋልኩት በቡድን ውይይት ወቅት ሴቶች ብቻችንን ስንሆን በሀሳብ ልዩነት ቢኖርም ቢያንስ የሚቋጭ ውይይት ስናደርግ እንቆይ እና ወንዶቹ ሲቀላቀሉ ግን ዝምታ ማብዛት፣ መሽኮርመም፣ እንደ ሕጻናት መኮለታተፍ ብቻ ለእኔ አዲስ ግርታ የፈጠረ የቋንቋ መዛባት አስተውል ነበር፡፡ ብዙዎቹ ሴቶች ንግግር በሚያደረጉ ቁጥር እራሳቸውን ያጡ ወይም ማንነታቸውን ፈልገው ማግኘት ያልቻሉ ዓይነት ስሜት እየተሰማኝ ነበር እና አንዳንዴም ወደ ቀልቤ ስመለስ “አንቺ ማነሽ እና ነው ፈራጅ ያደረገሽ?” ብዬ እራሴን እወቅሳለሁ፡፡  “መቼስ ትልልቅ ሰዎች መሆናችን ካልቀረ እንደ ትልቅ ስንሆን ሰዎች በቀላሉ ይረዱናልና ነው ሳላስበው ፈራጅ መሆኔ” ብዬ ደግሞ እራሴን አጽናናለሁ፡፡

ሰሞኑን ተርጉሜ ለንባብ ያበቃሁት “በመጨመቷ ለመሪነት አለመታጨቷ” በሚለው መጽሐፍ ውስጥ ፀሐፊዋ ሴቶች ካለማወቅ የሚሰሯቸው ብላ ካስቀመጠቻቸው ስህተቶች ውስጥ ከእነዚህ ሴቶች እና ወንዶች ጋር በነበረኝ ቆይታ ቢያንስ አንድ ሁለቱ በደንብ ሲተገበሩ ተመልክቻለሁ፡፡ አንደኛው የጠቀሰችው ስህተት “ሴቶች በሥራ ቦታ አልያም በስብሰባ ላይ ሲናገሩ ቃል አልባ ድምፀቶችን እንደ እእእ ያሉትን ወሬ ማራዘምያ ያዘወትራሉ፤ ይህ የሚሆነው ደግሞ በአብዛኛው በእራስ ያለመተማመን ስላላቸው ነው” ትላለች፡፡ ሌላኛው ፀሐፊዋ ስህተት ብላ ጠቅሳው እዚህ በአካል ያገኘሁት “ሴቶች ብቻቸውን ሲሆኑ እና ወንድ የሥራ ባልደረቦቻቸው አብረዋቸው ሲኖሩ የሚኖራቸው ተግባቦት የተለያየ ነው፡፡” ያለችው ስህተታችን ነው፡፡ አቤት እንዴት ፍንትው ብሎ እንዳየሁት! ሰው እንዴት በአንዴ ሁለት ዓይነት መሆን ይቻለዋል! ጥሩ ተዋናይ አይደለን እንዴ!

በአጠቃላይ እራሳችንን ያልሆንንበት የሁለት ቀናት ቆይታ ሲጠናቀቅ እንኳን ካርድ ለመለዋወጥ ይቅርና የምወደውን ፎቶ እንኳን አብሬ ለመነሳት ከፍተኛ ስንፈት ነበር የገጠመኝ፡፡ አንድ ነገር ግን ተምሪያለሁ፡፡ ሴቶች እራሳችን ላይ በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በእውቀትም ብዙ በመስራት ተመጣጣኝ የሆነ ማደግ እንደሚኖርብን ፡፡ አለበለዝያ እራሳችንን እናጣታለን፤ ለእራሳችን እንጠፋባታለን፡፡ ከእራስ ጋር እንደመጠፋፋት ደግሞ አሸባሪ ነገር የለም፡፡ እራስን መሆን ወይንም እራስን ማግኘት ደግሞ በተቃኒው ሙሉ ሰው ያደርጋል፡፡

አንድ ነገር ልጨምርላችሁ እና ወጌን ልቋጭ፡፡ ለነገሩ ዛሬስ ወግ ሳይሆን ሀሜት መሰለብኝ አይደል!? ምን ላድርግ ወድጄ አይደለም፡፡ ሴቶችን ለማጎልበት በከተማችን ጥቂትም ቢሆን ጥረት እየተደረገ ባለበት ክፍለ ዘመን ላይ ያልተመጣጠነ መጎልበት ያስከተለውን ቀውስ በቁሙ ስላየሁት በመጠኑ ተከፍቼ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ስልጠናው የነበረው በከተማችን ከሚገኙ ባለ አራት ኮከብ ሆቴሎች በአንዱ ሲሆን አገልግሎቱም የተዋጣለት ነበር፡፡ ነገር ግን ከእኔ፣ ከጥቂት ሴቶች እና ከወንዶቹ በስተቀር በአብዛኛዎቹ ሴቶች የየራሳቸውን የመጠጫ ማግ ይዘው የመጡ ሲሆን በሻይ ቡና የእረፍት ክፍለ ጊዜ እኛ በሆቴሉ የተዘጋጀውን የእረፍት ሰዓት ቁርስ እና ትኩስ መጠጦች ስንጠቀም እነሱ የአረንጓዴ ሻይ፣ የሎሚ ጭማቂ እና ሌሎችም ከጤነኛ ቅጠላቅጠል የተጠመቁ መጠጦችን ከየማጎቻቸው ይጎነጩ ነበር፡፡ ይህ ጤነኛ ነገር ደስ ያሰኛል፤ መብታቸውም ነው፡፡ ግን ደግሞ ድባቡ የፉክክር እና የደረጃ ማሳያ ይመስል ነበር፡፡ ታድያ አንዷ የያዘችው ማግ የስታርባክስ ነበረና ሌላኛዋ “በ666 እቃ መጠቀም አላቆምሽም!?” ስትላት የጥቂቶች ጓደኞቿ የስላቅ ሳቅ አጀብ ሆኖላት የልብ ልብ ስሜት ሲሰማት ለእኛ ለባይተዋሮቹ እንግዳ የነበረው የቡድን መነቋቆር የድባቡን ፕሮፌሽናል ገጽታ ጥፍት ነበር ያደረገብን፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ የማንነት ጥያቄ ያልተጠየቀበት ወይም ያልተመለሰበት ቆይታ ብዬዋለሁ፡፡ እኔ ለእራሴ የተማርኩትን ተምሬ፣ መድገም የሌለብኝን ስህተት ለይቼ፣ በከተማችን የጎላ የኢኪኖሚ እና የእውቀት ክፍተት መኖሩን ተረድቼ ከእራሴ ጋር እንዳልጠፋፋ የተቻለኝን ሁሉ ጥረት አድርጌ ያሳለፍኩበት ወርቃማ ጊዜ ነበር፡፡ ለዛሬ አደራ ከእራሳችን ጋር አንጠፋፋ! በማለት ሀሳቤን ልቋጭ፤ ተመልሼ በዚሁ ብህሬ እስከማገኛችሁ!

Written by: Fitsum Atenafework Kidanemariam

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *