ብርቱካን ያስጠላው ብርቱካናማ እንቅስቃሴ!

መቼስ የእኛ ዘመን ከእናቶቻችን ዘመን የተሻለ ነው፡፡ የልጆቻችን ደግሞ ከእኛ የተሻለ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ብዙ ነገሮች ሲታወሱ የኑሮ ውድነትን ጨምሮ ድሮ በሚሻልበት ዘመን ስለምን እያወራሁ እንደሆነ ጥያቄ ሳይጭርባችሁ አይቀርም፡፡ ያው ለእያንዳንዱ ጽሑፌ መነሻ አለው አይደል! ለዚህኛው ያነሳሳኝን በመጀመርያ ልተርክላችሁ፡፡ አንዳንዶቻችሁ ታውቁኛላችሁ ብዬ አምናለሁ፤ ለማታውቁኝ ደግሞ ብዙ ቦታ ተሳትፎ አደርጋለሁ፣.በትስስር አምናለሁ፤ እማማራለሁ፡፡ እቤት ከመቀመጥ ወይንም ገለልተኛ ከመሆን ምንም አይገኝም ብዬ የማምን ሴት ነኝ፡፡ ይሄ በነገራችን ላይ የኤውበሮች አንዱ አስተምሮታችንም ነው፡፡  ታድያ በተለያዩ ቦታዎች በሚኖረኝ ተሳትፎ የአንዳንድ ሰዎች አስተሳሰብ ከመላቁ የተነሳ እንደሚያስደንቀኝ ሁሉ የአንዳንዶች ደግሞ አንሶ በማይገኝበት ቦታ በማነሱ እጅግ ያናድደኛል፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ ንዴቴን ለማብረድ እራሴን “ተረጋጊ ይሄንን ወይንም ይህቺን ሴት ከዛሬ ወድያ የለማግኘት መብቱ በእጅሽ ነው!” እላታለሁ፡፡

ወቅቱ በብርቱካናማ ቀለም የተሰየመው ፆታዊ ጥቃት እና ትንኮሳ ይቁም በሚል በአለም አቀፍ ደረጃ እየተደረገ የሚገኘው የ16 ቀን እንቅስቃሴ መሆኑን ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ ብርቱካናማ ቀለም የተመረጠውም ዛሬ የሴቶች ጥቃት. ትንኮሳና ብዝበዛ በዓለማችን ቢኖርም በትግላችን ነገ ብሩህ እንደሚሆን ለማመላከት ነው፡፡ ከሰሞኑ ውሎዬ በአንዱ ቀን እለት በዚህ ርእስ ላይ ሴቶችም ወንዶችም በነበርንበት ኢ-መደበኛ  ስብሰባ መወያየት ተጀመረ፡፡ አንደኛው ሰው “እኔ እኮ ይሄ ከዓመት ዓመት እየተጠበቀ የሚደረገው የ 16 ቀናት እንቅስቃሴ ለብዙ ሴቶች ቢዝነስ ለአንዳንዶች ደግሞ የፖለቲካ ግርግር ነው፤ ያካብዳሉ! ምናቸውም ያልተነካ ሴቶች በየሆቴሉ ተሰብስበው ያጯጯሀሉ፣ ደግሞ እኮ እንቅስቃሴያቸውን ብርቱካናማ ቀለም ብለውት የምወደውን ብርቱካን ሁላ ነው ያስጠሉኝ…ወዘተ” ከማለቱ ሌላኛውም “ምን በየሆቴሉ ብቻ፤ ጭራሽ ፊሽካ ይዘው በየቤታችን ሳይገቡ አይቀሩም” በማለት አዳበረለት፡፡ ተሳሳቁ፤ አብረውን የነበሩት ሁለት ሴቶች እንደመሳቀቅ ጭራሽ በሳቅ አጀቧቸው፡፡ ሴቶቹ  የእኔን ያህል የተቆጩ ያለመሆናቸው ብቻዬን የምጋፈጠው ውይይት ሆነብኝ፡፡ እኔ ይህን ጊዜ “ምን ብንመስላቸው ይሆን እንዲህ የእንቅስቃሴውን መንፈስ ማጣጣላቸው! ያን ያህልስ ብርቱካናማው ተጋኗልን? ገብቷቸው ይሆን ግን…” እያልኩ በዝምታ ማሰላሰል ያዝኩ፡፡ ያልተለመደው ዝምታዬን ተከትሎ የሆነ ነገር ዱብ እንደማደርግ የገባቸው ወንዶች ጓደኞቼ (ጓደኞቼ ልበላቸው እንጂ!) እየተጠባበቁኝ ይመስላሉ፡፡  እኔ ግን በዝምታዬ ፀናሁ፡፡

ያልተለመደውን ዝምታዬን ለመስበር በሚመስል አንደኛው ሰው “ፍፄ ዛሬ ገና እጅ ሰጠሸ!” በማለት የአሸናፊነት የሚመስል ዳግም ቅስቀሳ አደረገብኝ፡፡ እኔ እኮ አንዳንዴ የወንዶች ባህርይ አይገባኝም (የእኛ የሴቶች እንደማይገባቸው ሁሉ)፡፡ እንዴ ዝምታ ሁሉ እጅ መስጠት ነው እንዴ! አንዳንዴ እኮ በርእሰ ጉዳዩ መነጋገር ሳንፈልግ፣ አካሄዱ ሳይመቸን፣ ብናስረዳቸው ላይገባቸው ወይንም እንዳይገባቸው አቋም መያዛቸውን ተረድተን…ወዘተ እኮ ዝም እንላለን፤ እኛ ሴቶች፡፡

እኔ እንደዚያ ሲናገሩ በሀሳቤ ሲመላለስ የነበረው በተለይ በእኛ ሀገር ከማናቸውም ጊዜ በተለየ በአሁኑ ሰዓት በጦርነቱ እና ያንን ተከትሎ በተከሰተው ስደት እንዲሁም ከዚህ ቀደም ተከስቶ በነበረው የኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት እጅግ በጣም ብዙ ሴቶች ጥቃት እና መደፈር ደርሶባቸዋል፣ እየደረሰባቸውም ነው፡፡ በየቤቱስ በባሎቻቸው ጥቃት የሚደርስባቸው፣ በቤተሰብ አባል ሳይቀር መደፈር የሚፈፀምባቸው ሴቶች ሰው አይደሉም ይሆን? መቼስ አልሰማንም እንዳንል በየጊዜው በተለያዩ የመገናኛ ሚዲያዎች እየተነገረ እና እየታየም ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ግን ደግሞ “መርጠው ለሚያዳምጡ ጓደኞቼ ምን ብዬ ባስረዳቸው ይገባቸው ይሆን?” ብዬ ሳውጠነጥን መላ ቢጤ መጣልኝ፡፡ እና ውስጤ ሲንቦለቦል የነበረውን ስሜት እንደዚህ አወጣሁት፡-

“እስቲ በቀን በቀን በየሚዲያዎቻችን ለእንግሊዝ ወይንም ለአውሮፓ ፕሪሚየር ሊግ የሚሰጠውን የአየር ሽፋን እና የሀብት ፍሰት እንመልከት እና በዓመት እናባዛው፤ ተጠቃሚውስ ማነው? ኳስ የሚወዱ እና የሚጠቀሙት  ሰዎች ጾታቸው በአብዛኛው ወንዶች አይደሉምን!? ሌላዎቹ ተጠቃሚዎች ፕሮግራሞቹን ስፖንሰር የሚያደርጉ ድርጅቶች ናቸው፡፡ እነዚህም በአብዛኛው የወንዶች ናቸው፣ ምክንያቱም ቢዝነሱን በብዛት እየመሩት ያሉት ወንዶች ናቸውና! በሌላ አቅጣጫ ደግሞ እንመልከት፤ ለምን የሴቶች እና የሕጻናት ጥቃትና መደፈር እየበዛ መጣ!?” ከሚዲያዎች ሰዓታቸውን ይህንን አስከፊ ተግባር መከላከል እና ግንዛቤ መፍጠርን የሚያስተምሩ ስንቶች ናቸው? ማንስ ነው የሚያዳምጣቸው? በዓመት ምን ያህል ግንዛቤ ማስጨበጥ እና ማስተማር እየተደረገ ነው?” ሀሳቤ ጥያቄ ይሁን ትንተና ያልገባቸው እስኪመስል ከዝምታ ውጪ መልስ የሚሆን ነገር የሚያፈልቅ ጭንቅላት አጠገቤ አልነበረም፡፡ እኔም ይህንን አጋጣሚ ለማብራራት ተጠቀምኩበት ምናልባት ትንሽ ቢከሰትላቸው፤

“ታድያ በዓመት 16 ቀናት ስለዚህ ጉዳይ ያውም ሚዲያዎች ሳይሆኑ የሴቶች መደፈር እና ጥቃት ያገባናል የሚሉ ቢንቀሳቀሱ ክፋቱ ምኑ ላይ ይሆን? እናንተንስ ይጎዳችሁ ይሆንን!? እህት ባትኖራችሁ ሚስት፣ ሚስት ባትኖራችሁ እናት፣ እሷም ባትኖር እኛ እኛ ጓደኞቻችሁ አለን፡፡ የምታውቋት ሴት ብትጠቃ ወይንም ብትደፈር ቢዝነስ ነው ወይንም ፖለቲካ ነው ብላችሁ ታልፉት ይሆን? ምን ብንመስላችሁ ነው እንደዚህ የምትፈርጁን? ክርክር አልፈልግም የእንቅስቃሴውን ክፋቱን ብቻ አስረዱኝ፡፡” በማለት ምላሻቸውን መጠባበቅ ያዝኩ፡፡ ለተወሰኑ ሰኮንዶች ፀጥታ ሰፈነ፡፡ “በነገራችን ላይ በዚህ ዓመታዊ እንቅስቃሴ ምክንያት ብርቱካንን አትጥላው፤ አቅምህ ከፈቀደ ዓመቱን ሙሉ ብላ እና ባይሆን 16ቱን ቀን አትብላ፤ ፁምበት!” በስመ አብ ትንፍስ ብዬ ወጣልኝ እኮ!

የመጨረሻዋ አባባሌ ፈገግ ብታስብላቸውም የስሜቴ ግለት ወንዶቹንም ሆነ አባሪ ተባባሪ  የሆኑትን ቀልደኛ ሴቶች ሳያስደነግጣቸው አልቀረም፡፡ አንደኛው ጓደኛችን ቀልደኛ ቢጤ ነውና “ፍፄ አወሳሰብሽው እኮ! በነገርሽ ላይ ፕሪሚየር ሊጎች እኮ የገንዘብ ምንጮቻችን ናቸው፡፡ ምን ያህል እየተቆመረ እንደሆነ አታውቂም እንዴ!” በማለት የከረረውን ሀሳቤን ማፍረሻ ይሁን ማጠናከርያ ብቻ ፈገግ የሚያስብል ሀሳብ አከለበት፡፡ ወንዶች የከረረ ወይንም የጠጠረ ሀሳብ ከሴቶች ሲመጣ ላለመሸነፍ ወይንም ላለመቀበል በቀልድ የሚያዋዟት ነገር ትመቸኛለች፡፡ እውነት እኮ ነው ሁለት የከረረ ነገር ይበጠሳላ! በነገራችን ላይ ወንዶች ብዬ በጅምላ ስናገር ፈራጅ እንዳታደርጉኝ፤ እጅግ በጣም መልካም የሆኑ ሴትን ልጅ ሊደፍሩ እና ሊያጠቁ ይቅርና በተቃራኒው ለሴት ልጅ መብት የሚከራከሩ ብዙ ወንዶች አሉ፤ እነሱ ይብዙልን፤ ይኑሩልንም! ያለ እነሱ ተሳትፎ ብቻችንን ለውጥ አናመጣምና!

ከማጠቃለያዬ በፊት ግን አንድ ጥቆማ አለኝ፤ በተለይ እንደነዚያ አብረውኝ እንደበሩት ሴቶች የወንዶች ንግግር፣ ቀልድ እና ፌዝ ገባቸውም አልገባቸውም በፈገግታ ለሚያጅቡት፡፡ ለመብታችን የማንታገል ከሆነ የሚታገሉልንን ሴቶች ባናግዛቸው ወይንም ባናጅባቸው እንኳን አናደናቅፋቸው፡፡ ከመነሻዬ የእኛ ዘመን ከእናቶቻችን ዘመን የተሻለ ነው ያልኩት እኮ በምክንያት ነው፡፡ እናቶቻችን እኛ ያገኘነውን ግንዛቤ እና እውቀት ስላላገኙ በግዞት አልፈዋል፡፡ እኛ በተለይ ፊደል የቆጠርነው ለእራሳችንም ለሌሎችም ድምጻችንን የማሰማት እድል አግኝተናል፤ ለውጥ እስኪመጣ፡፡ ለውጥ ደግሞ ሂደት ነው፤ ውጤቱ ልክ ዛሬ ችግኝ ተተክሎ ከዓመታት በኋላ ዛፍ ሆኖ እንደሚያፈራው የዓመታት ትግል ውጤት ነው፡፡ እኛ እንደ እናቶቻችን ዝም ስለማንል ነገ ለልጆቻችን የተሻለ ነገ ይሆናል፡፡ እኛም እንቅስቃሴአችን ወንድሞቻችን ከአጥቂነት ወደ ተከላካይነት (በእነሱ የኳስ ቋንቋ) እንዲሸጋገሩ አይደለም፤ ይሄ ጉዳይ ፕሪሚየም ሊግ አይደለምና! ዓለም የሁላችንም ስለሆነች ማንም አጥቂ ማንም ተከላካይ የማይሆንባት በአብሮነት የምንኖርባት ናት፤ እኛ ሴቶች እንደወንድሞቻችን ሰው መሆናችን ለመጠቆም ብቻ  ነው! ይሄንን ብቻ ነው እኛ ሴቶች የምንፈልገው፡፡  ለዛሬ ተንፍሼ ጨረስኩ! እነሆ በብርቱካናማ ገጽታዬ!

Written by: Fitsum Atenafework Kidanemariam

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *