ጋለሞታ ማናት!

ሰብሰብ ብለን ወግ ይዘናል፤ በቁጥር ወንዶች ቢበዙም ሴቶችም የተወከልንበት ወግ፡፡ በጣም የምንግባባ ስብስቦች ስለነበርን ያንንም ይህንንም ርእስ እንደመጣልን እናነሳለን፤ ሀሳባችንን በነጻነት እናፈሳለን፡፡ ርእሳችን ሄደን ሄደን ሁላችንም በጋራ የምናውቃት አዲስ ቢዝነስ ጀምራ የምትታትር ሴት ጋር ደረሰ፡፡ ያቺ በሌለችበት እና ባልዋለችበት የተነሳችው ሴት በብዙ የሕይወት ፈተና አልፋ አሁን በእግሯ ለመቆም እየተውተረተረች ነው፡፡ ባለፈ ታሪኳ የአንድ ልጅ እናት ስትሆን  ያልዘለቀው ትዳሯ ብቸኛ እናት (single mother) እንድትሆን አስገድዷታል፡፡ ከቀድሞ ባሏ ጋር  በጋራ ያፈሩትን ልጅ በብቸኝነት ለማሳደግ  እጅግ የምትጥር አንዲት ሴት አጀንዳ ሆነች፡፡ ከመሀከላችን አንዱ ስለዚች ሴት ረዘም ያለ ደቂቃዎች መወራቱ ጊዜ ማባከን መስሎ የታየው አባላችን “ምን ሆናችሁ ነው ስለአንዲት ጋለሞታ ይህን ያህል ሰዓት ወስዳችች የምታወሩት፤ የተሻለ ርእስ አምጡ እንጂ!” አባባሉ በፈጠረው ደማቅ ሳቅና ፈገግታ ታጅቦ ርእሱ ወደሌላ ተቀለበሰ፡፡ አዲስ ርእሰ ጉዳይ ተነሳ! ደግሞ ለርእስ ምን ችግር አለ!

በአዲሱ ርእስ ዙርያ እስክቀላቀል ግን እኔ ከስብስቡ እኩል መጓዝ ተሳነኝ፡፡ በዝምታ ደቂቃዎች ማባከኔ ያልተለመደው ሆኖባቸው ግራ የገባቸው የጭውውቱ አባላት “የት ሄድሽ? ደህና አይደለሽም እንዴ!?” በማለት አብሮነቴን ሲጠይቁኝ ወደኋላ መለስኳቸው እና እኔ ብቻ ግራ የተጋባሁበትን አባባል እንዲብራራልኝ ጠየቅሁ፤ “ሴት ልጅ ጋለሞታ ማናት? ሴት በዚህ ጥቅል ስም የምትጠራው ምን ስትሆን ነው!?” በማለቴ “አሁንም እዚያው ርእስ ላይ ነሽ? አንቺ ጋለሞታ አይደለሽ ምን አሳሰበሽ? ወዘተ” ካሉኝ ጀምሮ የዚያች ሴት እንደዚያ መባል ያልደነቃቸው ሁሉ እኔን እንደስራ ፈት እና በዘመኑ አባባል “አካባጅ” አድርገው መመልከታቸው በጣም ግርታን ነበር የፈጠረብኝ፡፡ እኔም እኮ ግን ሳላበዛው አልቀርም፡፡ አንዳንዴ ነገሮችን ማለፍ ብችል ምናለበት!? አብሮአደግ ባህርይ እኮ ቶሎ አይለቅም አይደል!  ከልጅነቴ ጀምሮ አንድ አባባል ለእኔም ይሁን ለሌላ ሰው ሲሰነዘር በተለይ አሉታዊ ከመሰለኝ እና ካልገባኝ ያለማለፍ እና ጠይቆ ለመረዳት መጣጣር አባዜ አለብኝ፤ ብዙ ጊዜ መጨረሻው እንደማያምር እያወቅሁ፡፡ እንዳየሁት በአብዛኛው (ሁሉም አላልኩም) ማህበረሰባችን ቃላት አጠቃቀም ላይ ችላ የሚለውን ያህል የቃላቱ ግድፈት ላይ የሚሰጠውን ሂስ ችላ አይለውም፤ ይልቁንም ወደቁጣ እና ቅይማት ይሄዳል እንጂ፡፡ በዚህ ብዙ ሰዎች ተቀይመውኛል፤ ምን ይሻለን ይሆን!?

ጋለሞታ የሚለውን ቃል ማህበረሰባችን ባሏ ሞቶባት ወይንም በፍቺ ተለያይታ ልጅ/ልጆች ብቻዋን ለምታሳድግ ሴት ይጠቀመዋል፡፡ ከላይ እንደነገርኳችሁ ትዳሯ ስላልተሳካ ልጇን ለብቻዋን ለምታሳድገው ሴት ነበር አባላችን የተጠቀመው፤ ያው ንግግሩን በተመስጥዖ ያዳመጡና ፈገግም ያሉትን ሴቶችም ወንዶችም ጨምሮ፡፡ ጋለሞታ የሚለውን ቃል ትክክለኛ ትርጉሙን ለማግኘት የአማርኛ መዝገበ ቃላት እጄ ላይ ስላልነበረኝ እና አሉታዊነት እንዳለው ስለማውቅ ጉግልን ጠየቅኩት እና የሰጠኝ ምላሽ በጣም ነው ያደረገኝ፡፡ እንደወረደ ሴተኛ አዳሪ (prostitute) ብሎታል፡፡ ይሄን ትርጉም 100 ፐርሰንት ትክክል ነው ብለን ከተቀበልን ለዚያች ሴት የሚመጥን ትክክለኛ ቃል ይሆን!?  ይሄ አፀያፊ (እኔ ስለምፀየፈው) ቃል ታሪካዊ አመጣጡን እና አጠቃቀሙን እንኳን በደንብ የተረዳነው አይመስለኝም፡፡

ወንድ ልጅ ግን ሚስቱ ብትሞትበት ወይንም በፍቺ ቢለያይ እና ልጆቹን ብቻውን ቢያሳድግ (ብዙ ጊዜ መልሶ ያገባል እንጂ) ጋለሞታ ለምን አይባልም!? ትዳሩ ይሁን ግንኙነቱ የጋራ ነበር፤ ሲፈርስም ለመፍረሱ በተፈጥሮ ከሆነ (በሞት) ከአቅም በላይ ነው፤ በፍቺ ወይንም መጀመርያውኑም 80 ያልነበረ ከሆነ በስምምነት ለመፍረሱ የሁለቱም አስተዋጾ አለበት፡፡ እና ይሄ ሚዛናዊ የጎደለው ፈራጅ የሆነ አባባል ስለምን ለሴቷ ብቻ!?

ሴት ልጅ በሀገራችን “እንደ ሰው እየተከበረች ነው” ብለው የሚሞግቱ ሰዎች ማህበረሰቡን በጥልቀት ተረድተው ይሆን!? እንደዚህ ያሉ ፈራጅ ቃላት ምን ያህል ሰባሪ እንደሆኑ ያውቁ ይሆን!? በተለይ እኛ ከተማ ውስጥ የምንኖረው ትንሽም ቢሆን የዘመንን ሰዎች የሀገራችንን እና 80 ፐርሰንት የሚወክለውን የገጠሪቷን ኢትዮጵያ፣ ሴት ልጅ ከእንሰሳም በታች የምትታይበትን ድቅድቅ አለም አናውቀውም፡፡ ለነገሩ ይህ ጋለሞታን ያለቦታው የተጠቀመው እና ቃላት አሰካኩ የተደመመለት ሰው ትምህርት የዘለቀው፣ ዘመናዊነት ያልጎደለው አባላችን ነው፡፡ ነገር ግን ወዳ እና ፈቅዳ ብቸኛ ያልሆነችን እናት ጋለሞታ ሲላት፤  “ተሳስተሀል!” ያለውም ሰው አልነበረም፤ ምክንያቱ ደግሞ ብዙዎቻችን ፈራጆች ሆነናልና! ቆይ ወንዱ ትዳሩን ፈትቶ እሷ የሁለቱን ልጅ/ልጆች ይዛ እያሳደገችለት እሱ ለምን ሌላ ስም አልተለጠፈለትም? ጋለሞታ ባይባል እንኳን በቃ ሌላ ለእሱ ለወንዱ የሚመጥን ስም!?  አዎ ለእሱ ማህበረሰባችን ስም አላወጣለትም፡፡ ምክንያቱን ግን እኔም አላውቀውም፤ ማህበረሰቡም የሚያውቀው አይመስለኝም፡ የተዛባ ሚዛን!

እኔ ያልተማረው ማህበረሰብ ላይ ቅሬታ የለኝም፤ በቃ አልተማረም፤ ስለዚህም ሲወርድ ሲወራረድ የመጣውን ብኢል ተቀባብሎ ይጠቀምበታል፡፡ እኛ ተምረናል የምንለው ሰዎች ግን ምን ሆነን ነው!? በነገራችን ላይ እነዚህ ብቻቸውን ልጆች የሚያሳድጉ ሴቶች ብዙ ጊዜ (ሁልጊዜ አላልኩም) ጠንካራ ይሆናሉ፤ ጠንካራ ልጆችም ያሳድጋሉ፡፡ በፈረሰ ትዳር ወይንም በአባት ሞት ያደግን እና ዛሬ ላይ ጥሩ ዜጋ ከሚባለው ማህበረሰብ ውስጥ ያለን ስኬታማ ሰዎች ለዚህ ሕያው ምስክር ነን፡፡ አንዳንዴ የእግዚአብሔር ፈቃድ መኖሩንም እንዘነጋለን (ለአማኞች)፡፡ እናም ጋለሞታ የሚለው ስያሜ እንደ እኛ የሉ ዜጎችን ያፈሩ እናቶቻችንን አይወክልም! አንድ የልጅነት ገጠመኜን ልንገራችሁና ሀሳቤን ልጠቅልለው፡፡ አያቴ ቆፍጣና ነበረች፡፡ ታድያ በአንድ አጉል ቀን አንድ የእናቴ ጓደኛ (ሳያገቡ እና ሳይወልዱ ብቻቸውን የሚኖሩ የነበሩ) በ13 ዓመቴ ያጎጠጎጠውን ጡቴን አይተው “ኸረ ይቺ ልጅ ገና ካሁኑ ጋለሞታ ሆነችሳ፤ ክፉኛ አጎጠጎጠች እኮ!” ከማለታቸው እማማ አያቴ (ነፍሷን ይማርልኝ) ልጅ ፊት የማይባለውን እና የተዛባውን የቃል አጠቃቀም አርማ “አጎጠጎጠች ነው የሚባለው፤ ጋለሞታ አይባልም፤ ነውር ነው!” ብላ ተቆጣቻቸው፡፡ ሴትየዋ ከሄዱ በኋላ ስለከነከነኝ የጋለሞታን ትርጉሙ ጠየቅኳት! አያቴም አግብታ የፈታች ሴት መሆኗን በምታውቀው ልክ አስረዳችኝ እና የሴትየዋን አይነት ሳታገባ የቆየች ሴት ደግሞ ቆሞ ቀር እንደምትባል ነገረችኝ (የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች የሚለውን እያሰበች ነበር መሰለኝ)፡፡ ብቻ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ባጎጠጎጠው ጡቴ ከመሸማቀቄ የተነሳ ሰው ሁሉ ሲያየኝ እንደ እሳቸው ጋለሞታ የሚለኝ እየመሰለኝ ት/ቤት ስሄድ ሁሉ ቦርሳዬን ወደፊቴ አዙሬ ጡቶቼን እደብቅበት ነበር፡፡ እኛን ሴትዮም በዚያ አባባላቸው ያቄምኩባቸው ይኸው አሁንም አልረሳኋቸው፤ አቤቱ ይቅር በለኝ!  ለነገሩ እሳቸውም ባል ባለማግባታቸው እና ባለመውለዳቸው ማህበረሰቡ ሲያሸማቅቃቸው ስለኖረ አሸማቃቂነቱን ወርሰው ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ሴት ልጅን እንደሰው የምናከብርበት ዘመን ገና አልመጣም እና በተለይ እኛ ዘምነናል፣ ተምረናል፣ መሪዎች ነን፣ ተከታይ አለን የምንል ሰዎች ከቃላት አጠቃቀማችን ጀምሮ ጥንቃቄ ብናድርግ ጥሩ ነው፡፡ ሚዛን የዘለቀን ሰዋዊ እንሁን! ለዛሬ ጨርሻለሁ!

የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

Share to your circles!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top