ሲስተሙ (ክፍል ሁለት)

ትልቁ መጽሐፍ ወንዱን “በላብህ ጥረህ ግረህ ብላ” ሲለው ሴቷን አትጣሪ አትጋሪ (ይባላል ግን?) ያላት አይመስለኝም፡፡ ከላይ የታዘዘ ይሁን ከታች የተመደበልን እንጃ ብቻ እኛም ከወንዶቹ ባልተናነሰ (ትሁት ልሁን ብዬ እንጂ በባሰ ሳይሆን አይቀርም) እንጥራለን፣ እንግራለን፣ እንደናገራለንም፡፡ ሰሞኑ የሠርግና የግብዣም አይደል! በየሆቴሉ እና መናፈሻው በአማሩ አልባሳት፣ መጫሚያዎች፣ ጌጣጌጦች እና መዋቢያዎች ዝንጥ ያሉ ሴቶች አያለሁ፡፡ መቼስ ለኢትዮጵያውያን ቁንጅና በአሥር ጣቴ እፈርማለሁ፡፡ ወፍራሟም፣ ቀጭኗም፣ ቀይዋም፣ ጠይሟም፣ ቀይ ዳማዋም፣ ወጣቷም፣ ጎልማሳዋም፣ ሽማግሊቷም ሁሉም ያምራሉ፡፡ አሮጎቷ ያላልኩት የሰው አሮጌ ስለሌለው ነው፡፡

በአብዛኛው እይታዬን ከሚሰርቁኝ ነገሮች ውስጥ አንዱ የሴቶቹ ጫማ ነው፡፡ ብዙዎቹ ከምድር ከፍ ያለ ባለትልቅ ተረከዝ ስላደረጉ አረማመዳቸው ምቾት አልባ ነበር፡፡ አንዳንዶቹማ እንጨት ላይ ቆመው ሰርከስ እንደሚሰሩት ወጣቶች በጥንቃቄ ከመራመዳቸው የተነሳ ፊታቸውን በጫማቸው ቁጥጥር ሥር ያደረጉታል፤ ማለትም ቅጭም አድርገው ያልተመቻቸው መሆኑን ከፊታቸው ላይ በትልቁ ተጽፎ ይነበበኛል፡፡ ከፊት ለፊታቸው የሚመጣ ሰው ሲያዩማ ልክ ያስገደዳቸው እሱ/እሷ  ይመስል በኩስትሪያ መሬት ያፈርጧቸዋል፡፡ እኔ እንደዚህ ያሉ ፊቶች ሁልጊዜ ነው የማስተናግደው፤ ጫማ ያልተመቻቸው ፊቶች፡፡ እስቲ ማን ያንን ጫማ አድርጉ አላቸው! ከፍታ ያለው ጫማ ልብስ ያሳምራል አራት ነጥብ፡፡ ታድያ እኮ “ሲያጌጡ ይመላለጡ”  የሚለው ብሂል ከጎኑ የተለጠፈው ሁላችንም አውቀን እንድንገባበት ነው፡፡

ለነገሩ ጫማችንን አልኩ እንጂ ብዙ ነገራችን እኮ ምቾት አልባ ነው፤ የእኛ የሴቶች፡፡ ልጅ ለመውለድ ከእርግዝና እስከ ግልግልና ምቾት የለውም፡፡  የቤት ውስጥ ሥራ ደስ ይላል፡፡ ሰው ለቤቱ ካልሠራ ለማን ሊሠራ ነው፡፡ ነገር ግን ከጠዋት እስከ ማታ እኛ ትተነው ካልተኛን ማለቅያ የለውም፡፡ በዚያ ላይ ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገም ያው እራሱ ነው፣ ድግግሞሽ፣ በገንዘብ ያልተተመነ ነጻ ሥራ፣ ምስጋና እንኳን የማይሰጥበት፣ እንደውም በግዴታ የተጣለብን ነው፡፡ ቅድም “የቤት ውስጥ ሥራ ደስ ይላል ያልኩት ምን ሆኜ ነው?” ይነሳልኝ! ብቻ ለእኛ ለሴቶች የተባሉ ብዙዎቹ  ምቾት የሌላቸው ናቸው፡፡

ለነገሩ ጫማችን ብቻ ሳይሆን የጸጉራችን አሠራርም ምቾት አልባ ነው፡፡ ጸጉርን አሳምሮ መሄድ ደስ የሚል ቢሆንም ከማማሩ በፊት በእሳት መጋየት ይጠበቅብናል፡፡ እኔ አንዳንዴ “ካስክ የወንዶች ቢሆን ከፍጥረቱ እስከሁን እንዲህ እየተለባለበ ይኖር ይሆን?” ብዬ እራሴኑ ጠይቄ መልስ ሳላገኝ ስለምቀር እተወዋለሁ፡፡ ፀጉር ቤት ውስጥ መደዳውን ካስክ ውስጥ የተቀመጥን እለት “ተቃጠልኩ ይቀነስልኝ?”፣ “ደርቋል እኮ አይበቃኝም?”፣ “ቀዝቃዛ ውሀ አቀብይኝ?”…ወዘተ የመሳሰሉትን እሮሮዎች ስናሰማ ገሀነብ ውስጥ ያሉ ሀጥያተኛ ነፍሶች ትውስ ይሉኛል (አጋነንኩ!)፡፡ “ሲያጌጡ ይመላለጡ” ያሉት የተረት አባት ይሆኑ የተረት እናት ብቻ በጣም ብልህ ነበሩ! በአጠቃላይ ለእኛ ለሴቶች የሚያስፈልጉ ነገሮች ምቾት የሌላቸው ናቸው፡፡

ይሄንን ሁሉ እንደ መግቢያ ያተትኩት ስለምን ማውራት ፈልጌ እንደሆነ የገባችሁ አንባብያን ካላችሁ ድንቅ ብያችኋለሁ፡፡ አመራር እና እኛስ እንመቻቻለን? ማለቴ ከፍታው የአመራር ቦታ ለእኛ ለሴቶች ምቾት አለውን? እስቲ እውነቱን ከልባችን እናውራ! አመራር ላይ ከሚገኝ ወንድ እና ከምትገኝ ሴት የትኛቸው በእፎይታ ስሜት ውስጥ ያሉ ይመስላችኋል? በእርግጥ አመራር ቦታ ላይ የምንቀመጠው ለእፎይታ አይደለም፤ ኃላፊነት ለመውሰድ፣ ተጠያቂ ለመሆን፣ ወሳኝ ለመሆን፣ የተሻለ ሀሳብ ለማፍለቅ፣ ላለመታፈን፣ ተጽእኖ ለመፍጠር፣ የተሻለ ገቢ ለማግኘትና የተሻለ ኑሮ ለመኖር…ወዘተ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች እኛ ሴቶች ወደ አመራር ላይ ስንመጣ ሙሉ በሙሉ የሚሳኩ ናቸው? ለነገሩ ለወንዶችም ሙሉ በሙሉ ላይሳኩ ይችላሉ፡፡ ግን በአንጻራዊነት በአብዛኛው በሚባል መልኩ የአመራር ቦታ ለእኛ ለሴቶች ምቹ ሁኔታዎች የሉትም የምል ነኝ፡፡

ይህን ስናገር ኃላፊነት መውሰድ፣ ተጠያቂ መሆን ወይንም የተሻለ ሀሳብ ማፍለቅ ለእኛ ለሴቶች ያስቸግረናል ብዬ አይደለም፡፡ በአብዛኛው እኛን እያስቸገሩን ካሉት በተለይ ውሳኔ መስጠት አንዱ  ይመስለኛል፡፡ ይህም ደግሞ እኛ ስላቃተን ሳይሆን በሌሎች ተጽእኖ ውስጥ ስለወድቅን ነው፡፡ ሴቶች እንደምንችል ጥያቄ ውስጥ መግባት የለበትም፡፡ ጥያቄ ውስጥ መግባት ያለበት ውሳኔ ለመስጠት ወሳኞች ያለመሆናችን ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በኃላፊዎቻችን፣ በድርጅቱ ፖለቲካ እና ተዛማች ኩነቶች ይሄ ነው የማይባል ጫና ስለሚደረግብን ነው፡፡ ለነገሩም እኮ እዚያ ለመድረስም ፍዳችንን በልተን ነው፡፡ አንዳንዴማ የአመራር ቦታ ላይ ሲደረስ ያለው ፈተና “ለዚህ ኖሯል እንዴ በሬዬን ያረድኩት!?” ያሰኛል፡፡ በሬ ማረድ እና መሪነት ምን አገናኘው እንዳትሉኝ፡፡ ወግ በተረት ሲደገፍ ያምራል ወይንም ግልጽ ይሆናል ብዬ ነው፡፡ ያው ለማለት የፈለግኩት ግልጽ ነው፡፡ የበለጠ ግልጽ ለማድረግ ሌላ ተረት ልጨምር መሰለኝ፤ ” እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው” የሚባል ሹመት ይሰጠን እና ልክ እንደጫማችን የምንፈልገው፣ የምንደሰትበት ወይንም የሚያምርብን  ነገር ግን የማይመቸን ይሆናል ማለት ነው፡፡

ጠቅለል ሳደርገው ብዙ ነገሮች ለእኛ ለሴቶች ምቾት የላቸውም፡፡ ይህንን ስል ደስታ እና ምቾትን እንዳላቀላቀልኩ ልብ በሉልኝ፡፡ ቆንጆ ጫማ ከፍታ ያለው ስናደርግ ደስ ይለናል ግን ምቾት የለውም፤ ትዳር ስንይዝ ደስ ይለናል፤ የቤት ውስጥ ሙሉ ሰዓት የማይከፈልበት ሥራ ግን ምቾት የለውም፤ ልጅ መውለድ ደስ ይላል እርግዝናው እና ምጡ  ምቾት የለውም፤ አመራር ላይ መድረስ ደስ ይለናል፤ ፖለቲካው፣ ተቀባይነት ማጣቱ እና በሴትነታችን ምክንያት የሚደረገው ጫና ምቾት አይሰጥም፡፡ በአጠቃላይ ከጥቃቅን እና አነስተኛ ጉዳዮቻችን እስከ ከፍተኛ ጉዳዮቻችን ብዙ ነገሮች ምቾት የላቸውም፡፡ እናም አንዳንዴ መጽሐፉ እኛ ሴቶችን ምን ብሎን ይሆን እላለሁ! ምናልባት ምቾቱን እርሱት፤ በሚኖራችሁ ነገር ተደሰቱ ብሎን ይሆን? ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም አብዛኛዎቻችን ከወንድ አቻዎቻችን በተሻለ ደስተኞች ነን፡፡ ታድያ ምቾት ቢቀርስ!  ለማንኛውም እንዲህ ማለቴ የአመራር ወይንም የከፍታ ቦታ ቢቀርብኝስ! ብለን ለምቾታችን ብለን ደስታችንን ወይንም ስኬታችንን ወደጎን እንዳንተው! ሁልጊዜ ወደፊት ወይንም ወደላይ መጓዝ ደስታ ይሰጣል! ለማንኛውም ሀሳቤን አልጨረስኩም!

Share on your socials!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *