ሲስተሙ (ክፍል ሁለት)

ብዙ መሥሪያ ቤት እንደመሥራቴ መጠን የብዙ ሰዎችን ባህርይ ለማወቅ ጠቅሞኛል ብዬ አምናለሁ፡፡ በእርግጥ ሰውን ሙሉ በሙሉ ማወቅ የማይደረስበት ጥበብ ነው፡፡ ፊት ለፊት የሚታየውን እና የሚታወቀውን ባህርይ ማለቴ እንጂ፡፡ ዛሬ ከሥራ ሕይወቴ ካጋጠሙኝ ለየት ያሉ ባህርያት በተለይ አዲስ ሠራተኛ በተቀጠረ ቁጥር በፍጥነት ተዋውቀው መረጃ የሚሰጡ እና የሚቀበሉትን በቁጥር ትንሽ የማይባሉትን ላውጋችሁ፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹ ሠራተኞች ብዙዎቹ የጠለቀ ወዳጅነት ፈልገው እንዳይመስላችሁ፤ አላማቸው መረጃ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም አዲስ ሆናችሁ መ/ቤቱን ስትቀላቀሉ አላማጅ ሆነው ይቀርባሉ፤ ስለእራሳቸው በተቻላቸው መጠን ጥሩ ጥሩውን ያወራሉ፤ እንዲያውም መ/ቤቱ ያለ እነሱ እንደማይቆም እራሳቸውን ምሶሶ አድርገው ያስተዋውቃሉ፤ ከዚያማ በቆይታቸው ያካበቱትን ምስጢር ዝርግፍ ነው፡፡ የሰው ሰምቶ ዝም የለምና የእናንተንም ለመዘርገፍ ትገደዳላችሁ፡፡ በእርግጠኝነት እንደዚህ ያሉ ሰዎችን በዓይነ ልቦናችሁ እያስታወሳችሁ ነው፡፡ በዙሪያችን ሞልተውናላ! እኔ በተለይ አንዷን ባልደረባዬን በዚህ ባህርይዋ መቼም አልረሳትም፡፡
ባልደረባዬ ድጋፍ ሰጪ ከሚባሉት በአንደኛው የሥራ ክፍል ውስጥ ትሠራ የነበረች ስትሆን በአብዛኛው አዲስ ተቀጣሪ ሠራተኛ ለሥራ ጉዳይ ያገኟታል፡፡ ታድያ ፊርማቸው ያልደረቀ ሠራተኞች ለመጀመርያ ጊዜ የሻይ ቡና ግብዣ የሚያገኙት ከእሷ ነበር፡፡ ከዚያ እነሱም በማላመድ ቅልጥፍናዋ ደስ እያላቸው ይከራርሙ እና ከሌሎች ሠራተኞች ጋር ሲላመዱ እሷን ብዙም አያገኟትም፡፡ እናም ብዙ ጊዜ ታጉረመርማለች “እኔ ድሮም እጄ አመድ አፋሽ ነው፤ እንዳላላመድኩት/ኳት ዛሬ ለእግዜር ሰላምታም ትዝ አልላቸውም” እያለች፡፡ እነሱም ያለ ይሉኝታ ይርቋታል፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ለአዲሶቹ ሰዎች ስለእራሷ መልካምነት ካስተዋወቀች በኋላ የሰዎቹን ማንነት፣ ከየት እንደመጡ፣ በማን እንደመጡ፣ በስንት ደመወዝ እንደተቀጠሩ…ወዘተ እና ከዚያም አልፋ ስለ ግላዊ ሕይወታቸው መረጃ ትጠይቃለች፤ ከዚያ ለጠየቃትም ላልጠየቃትም ስለ እነሱ ታወራለች፡፡ በዚህ ጊዜ አዲሶቹ ሰዎች ስለእራሳቸው ከሌሎች ሰዎች ሊሰሙ ሁሉ ይችላሉ፡፡ በዚያም ቅር ይሰኛሉ፡፡ አመድ አይደለም እንደዚህ ያለ ሰው የማይጨበጥ አየር ቢያፍስም (አይታፈስለትም እንጂ) አይገድም፡፡ እንደዚህ ያሉ ሰዎች ገደብ የለሽ ይባላሉ፡፡ ከሰዎች ጋር ገደብ አድርገን ገደቡ ካልገደበን እንደ እነዚህ ሰዎች መጨረሻችን አመድ አፋሽነት ነው፡፡ ማንም ሰው ለሥራ ጓደኝነትም ይሁን ለግል ጓደኝነት አይመርጠንም፡፡ ይሄ ደግሞ ከምንም በላይ ለሚከፋው ብቸኝነት ይዳርጋል፡፡ ይህ ሲሆን በዚያች የሥራ ባልደረባዬ እና ሌሎችም ፈጥኖ በመግባባት መረጃ የመሰብሰብ እና የመስጠት አመል (ብለው ይሻላል) ባላቸው ላይ ሲደርስ አይቻለሁ፡፡
በምንሠራበት መሥሪያ ቤት ወይንም ድርጅት ውስጥ አንዱ የድርጅት ፖለቲካ ጨዋታ አካል የሆነው ከሰዎች ጋር ሊኖረን የሚገባው ገደብ (boundary) ነው፡፡ ለነገሩ ገደብ ለሁሉም ዓይነት ግንኙነቶች ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ያለገደብ መቀራረብ ያለመከባበርን ያስከትላል፤ ምስጢር እንዲባክን ምክንያትም ይሆናል፤ የኋላ ኋላ ግንኙነትን ያሻክር እና መ/ቤቱን እስከ መጥላት አለበለዝያም ያለ ጓደኛ በብቸኝነት እስከመቅረት ያደርሳል፡፡ ገደብ ይገድበናል! ይከላከለናል፤ ከጥፋት ያድነናል፡፡
ገደብ በሥራ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ግንኙነት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ በትዳራችን ውስጥ በሚኖረን ግንኙነት ገደብ ወሳኝ ነው፡፡ ሚስት ለባሏ ያለ የሌላትን ዝክዝክ አድርጋ መንገር ያለባት አይመስለኝም፡፡ ባልም እንደዚያው፤ ለነገሩ ብዙ ባሎች እንደ ሚስቶች ሁሉን አያወሩም መሰለኝ፡፡ በአብዛኛው ባሎች ባያወሩም የሚያመሳስል ሌላ ባህርይ ግን አላቸው፤ አንዱ የጋባዥነት ባህርይ ነው፡፡ ያለገደብ እንግዳ እያመጡ በቤት ውስጥ መጋበዝ የሚስቶችን ገደብ እንደመጣስ ነው፡፡ እነዚህን ለምሳሌነት አቀረብኩ እንጂ ከትዳር በተጨማሪ በቤተሰብ፣ በልጆች እና በወላጆች፣ በጓደኛማቾች፣ በእህትማማች እና ወንድማማቾች…ወዘተ ብዙ የሚጣሱ ገደቦች አሉ፡፡ እናም ይህ ባህርይ ትክክል አይደለም፡፡ ይህንን በእርግጥ ለእናንተ መንገር ለቀባሪ እንደማርዳት ነው፡፡
አሁን ወደተነሳሁበት የመ/ቤት የሥራ ግንኙነት ገደብ ልመለስ እና አንዳንድ ሠራተኞች ከኃላፊዎቻቸው ጋር ያላቸውን ከገደብ ያለፈ ግንኙነት ታዝባችሁልኛል? ብዙ ጊዜ የሥራ ቦታ ግንኙነቶች ገደባቸውን ከጣሱ ከገንፎ ውስጥ እንደሚገኘው ስንጥር መጠርጠር ነው፡፡ ሠራተኛ እና ኃላፊ ጥሩ የሥራ ግንኙነት ሲኖራቸው ለሥራውም፣ ለእነሱም ስኬት ነው፡፡ ነገር ግን ጥሩ ግንኙነት እና ገደብ የሌለው ግንኙነት መለየት አለበት፡፡ ገደብ የለሽ ግንኙነት መግባባትን የሚያሳይ የሚመስለው ከላይ ከላይ ሲያዩት እንጂ ተጠግተው ሲያዩት በሆነ በአገም-ጠቀም የተሳሰረ ነው፡፡ ይህም ሠራተኞች በተለይ በእራስ ያለመተማመን ችግር ሲኖርባቸው ኃላፊዎችን ከመታዘዝም አልፈው ሲያነጥሱ መሀረብ ላቅርብ ባዮች ናቸው፡፡ ኃላፊዎችም ከተወሰኑ ሠራተኞች ጋር የተለየ ግንኙነት የሚፈጥሩት በጥቅማጥቅም ወይንም በማይታወቅ (እነርሱ ብቻ በሚያውቁት) ምክንያት ስለተሳሰሩ እንጂ የጤና እንዳልሆነ ከልምድ እና ከገጠመኝ አይተነዋል፡፡
ሀሳቤን ስጠቀልለው መከበር የሚጠላ የለም፡፡ ለመከበር ደግሞ ሌሎችን ማክበር ግድ ይላል፡፡ የማክበር አንዱ ማሳያ የሰዎችን ገደብ በመጠበቅ እና የእራስንም ገደብ በማስጠበቅ ነው፡፡ ስለሆነም በሥራ ቦታም ሆነ በማንኛውም ከሰዎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት ገደብ እንዲገድበን እድል እንስጠው፡፡ ገደብ ይገድባል፤ ያከብራል፤ ያስከብራልም፡፡ ለዛሬ ጨርሻለሁ!
Share on your socials!