የእድገታችን ምስጢር?

እድገታችን የሚለው ቃል ሁላችንንም በሀሳብ በየአቅጣጫው እንደወሰደን አልጠራጠርም፡፡ የቱን እድገት ይሆን ደግሞ ዛሬ የምታወራልን፤ የሀገራችንን? የልጅነታችንን? የድርጅታችንን? እድገት በየፈርጁ በአእምሯን ውስጥ ተመላለሰ አይደል! እኔ ግን ማውራት የፈለግኩት የስራ ቦታ እድገት (promotion) ነው፡፡

የሰው ሀብት የአንድ ድርጅት ወይንም ኩባንያ የጀርባ በሉት የፊት ብቻ የሁሉም አጥንቱ ነው፡፡ ድርጅትን ድርጅት የሚያደርገው ትልቁ ሀብቱ (Asset) ሰው ነው፡፡ ድርጅት ወይንም ኩባንያ ፈጣሪዎች ወይንም መስራቾች ተልእኮ፣ ራእይ፣ ግብ…ወዘተ እያሉ የሚቀርፁት ያንን ለማሳካት የሚቀጥሯቸውን ሙያተኛ ሰዎች በመተማመን ነው፡፡ አስባችሁታል ሁሉም ሰው ስራ ፈጣሪ ሆኖ ተቀጣሪ ባይኖር ምን ሊሆን እንደሚችል? ያንን ማን አስቦት ያውቅና! ምድሪቷም ቀጣሪና ተቀጣሪ እንዲጠቃቀሙ አድርጋ ነው የተዘራችው እና የበቀለችው፡፡ ይሄ ባይሆን መልከ ጥፉ ትሆን ነበር ብዬ አስባለሁ፤ ሁሉም ለእራሱ የሚሮጥባት ጥፉ ነገር፡፡

ታድያ የቢሮ ሠራተኛ በነበርኩበት ዘመን የተለያዩ ማንነቶች ውስጥ የታጨቁ ባህርያትን አይቻለሁ፡፡ ዛሬ ደግሞ ከመነሻዬ ስለእድገት ስለሆነ ማውራት የፈለግኩት ትኩረቴን እድገት አድርጌ ላውጋችሁ፡፡ እድገት በቅጥር ስንሰራ አንዱ ጥቅማጥቅማችን እና መብታችን ነው፡፡ ከመነሻው ተደራድረን የሚከፈለን ደመወዝ ለዘላቂነት መቀጠል አይኖርበትም፡፡ እንደ ድርጅቱ አይነት እና አቅም የሥራ ምዘና ውጤታችን እየታየ እድገት ይኖረናል፡፡ ይሄ የማወራው ጤነኛ የሰው ሀብት ማኔጅመንት ባለበት መስሪያ ቤት ውስጥ ያለውን አካሄድ ነው፡፡ እኔ እንደመታደል ሆኖ ብዙዎቹ የሰራሁባቸው ድርጅቶች ይሄ ጤነኛ ሲስተም ያላቸው ነበሩ፡፡ የሌላቸውም ግን አጋጥመውኛል፡፡ ለምሳሌ አንዱ የሰራሁበት መ/ቤት የደመወዝ እድገትም ሆነ የኑሮ ውድነት ማስተካከያ (cost of living adjustment) ሲስተም አልነበረውም፡፡ ታድያ ቀደም ሲል ከድርጅቱ ጋር የቆዩ ሰራተኞች አንዳንዶቹ ዝም ብለው ይሰሩ ነበር፤ ነቃ ያሉት ደግሞ ድርጅቱን ቢወዱትም ገበያውን ያነፈንፉና “የተሻለ ደመወዝ አግኝቻለሁ እናም ያን ያህል ካልተከፈለኝ መልቀቄ ነው” ብለው ይደራደራሉ፤ ለእነሱ ዓይነቶቹ ታድያ በተናጠል ይጨመርላቸዋል፡፡ ይሄ ጤነኛ ያልነበረ አካሄድ የሚባለው ነው፡፡

እንዲህ ያለ ሚዛናዊነቱን ያልጠበቀ የደመወዝ እድገት አሰጣጥ በሰራተኞች ላይ መከፋፈልን በስራው ላይ በደልን ያስከትላል፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ሲያጉረመርሙ የድርጅቱ ልጆች እና የእንጀራ ልጆች በሚል ክፍፍል ይሰጡት ነበር፡፡ ሰራተኞችን ማበላለጥ በትጋታቸው፣ በአገልግሎታቸው እና በእውቀታቸው እንጂ በአገም ጠቀም መሆን የለበትም፡፡ ይሄንን የተረዱ አሰሪዎች ምስጋና ይግባቸው! ያልተረዱቱ ልቡና (እና እውቀት) ይስጣቸው! 

ሌላው ሰራተኞች(ተቀጣሪዎች) መብት እና ግዴታቸውን ጠንቅቀው ያለማወቃቸው ለተዛቡ አሰራሮች በር ከፋች ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ተቀጣሪ ሆናችሁ ወደ አንድ ድርጅት ስትገቡ ድርጅቱ ወይንም ኩባንያው የማስተዋወቅ መርሀግብር (Induction/Orientation) ከሌለው እንዲሰጣችሁ መጠየቅ አለባችሁ፡፡ አንድ ከጥቂት ዓመታት በፊት ትልቅ የሥራ ኃላፊነት ቦታ ላይ አዲስ እድገት (ሹመት) ያገኘች ሴት ለውጥ እንዴት እንዳመጣች ስታስረዳ አገባቧንም ጠቀስ አድርጋ ነበር እና ያኔ የደነገጥኩት ድንጋጤ አሁንም ከውስጤ አልጠፋም፡፡ እንዲህ ብላ ነበር “ቦታው ላይ ስመደብ የቢሮው ቁልፍ፣ ወንበር፣ ጠረጴዛ እና የተዝረከረኩ ፋይሎች ነበር ያገኘሁት፣ ከዚያ ውጪ ምን መስራት እንዳለብኝ፣ ከየት እንደምጀምር እንኳን አላውቅም ነበር! ከዚያ እንደምንም ሰነዶቹን አንብቤ…” ከዚህ በላይ ይቅርባችሁ! አስቡት ትልቅ የሥራ መደብ ላይ ስትሾሙ ወይንም ስትመደቡ ይህን የመሰለ ባይተዋርነት ከምን የመጣ ነው?! መብትን እና ግዴታን ካለማወቅ አይመስላችሁም? መብት ሲባል የስራ ዝርዝር መጠየቅ፣ ፖሊሲዎችን እና መመሪያዎችን መቀበል እና አንብቦ ማወቅ፣ የሥራ መደቡ ቀደም ሲል የነበረ ከሆነ ምን እንደተሰራ፣ ምንስ በእንጥልጥል እና በእቅድ የተያዘ እንዳለ…ወዘተ የሚገልጽ የርክክብ ሰነድ(Handover note)  መረከብ የመሳሰሉት ሲሆኑ ግዴታ ደግሞ ኃላፊነት የምትወስዱበትን ሥራ ጠንቅቆ ማወቅ፣ ለዚያም ከሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች/ክፍሎች መተዋወቅያ መርሀ ግብር (Induction or Orientation) ማግኘት ነው፡፡

የእድገታችን ምስጢር ቢፈተሸ ታድያ ብዙ አስገራሚዎች እንደሚኖሩ እሙን ነው፡፡ ድርጅቱ ወይንም ኩባንያው ሲስተም ካለው ምንም ምስጢር የለውም፡፡ ግልፅ(transparent) ነውና! ይሄ ሳይሆን ሲቀር ግን ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ልጅ እና እንጀራ ልጅ እስከሚያስብል አገም ጠቀማዊ የሆነ አደጋ አለው፡፡ ይሄ ደግሞ የድርጅቱን ባህል ያጠለሸዋል፡፡ ምስጢር ያልኩበት ምክንያት ገጠመኞች ስላሉኝ ነው፡፡ አንድ መ/ቤት በምሰራበት ወቅት የማልረሳት አንዲት በዚያው መ/ቤት ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የሥራ ደረጃ ያደገች የሥራ ባልደረባችን ነበረች፡፡ እድገቷን በተመለከተ ብዙ ምስጢራት ነበሩ፡፡ ሥራ እንደማንኛውም ሰራተኛ ትሰራለች፡፡ ለጋሚ የምትባል አይደለችም፡፡ ነገር ግን ከሌላው ሰራተኛ ልዩ የሚያደርጋት ክህሎት ብዙም አይታወሰኝም፡፡ ግን ቶሎ ቶሎ እድገት ታገኝ ነበር፡፡ መጨረሻ አድጋ አድጋ አንድ ቦታ ቆመች፡፡ የዚህን ጊዜ ሌላ ድርጅት ታመለክትና እዚህ በድርጅቱ ውስጥ ያገኘችው ፈጣን እድገት እንደ ልዩ ብቃት ስለታየላት በከፍተኛ ኃላፊነት ቦታ በጥሩ ደመወዝ ልትቀጠር የቅጥር ደብዳቤ ይሰጣታል፡፡ ያንን ትይዝ እና የመ/ቤታችንን ኃላፊ “እኔ ይህንን የመሰለ አዲስ ስራ (Job Offer) አግኝቻለሁ፤ ነገር ግን መ/ቤቴን በጣም ስለምወደው መልቀቅ አልፈልግም፤ ገንዘቡ ደግሞ ያስፈልገኛል፤ እና ደመወዜ በዚህ ይስተካከልልኝ እና እዚሁ ልቀጥል!?” በማለት አሳምና ያለአግባብ እና ያለጊዜው የሆነ የደመወዝ ጭማሪ ታገኝበታለች፡፡ ልጅት ዋዛ አይደለችማ፤ እዚያ ድርጅት የተሰጣትን ኃላፊነት እንደማትወጣው ለቅርብ ወዳጆቿ ሱክ ያለችው ወሬም ጆሮዬ ገብቶ ነበር፡፡ ለእሷ ብቻ በተደጋጋሚ በሚደረገው አግባብ ያልሆነ አሰራር ድርጅቱ እንቁ የሆኑ ሰራተኞችን ቀስ በቀስ እንዳጣ አስታውሳለሁ፡፡ ይሄ አንዱ እና ብዙ ድርጅቶች ውስጥ የሚያጋጥም ምስጢር ነው፡፡

ከማጠቃለሌ በፊት ሌላው ምስጢር ምን መሰላችሁ፤ አሉ ደግሞ ሕጻን ልጅ ሲርበው ለምቦጩን ጥሎ/ጥላ ሽልጦ (ጥቢኛ) እንደሚጠይቁት ዓይነት እድገትንም በዚያ መልኩ ማግኘት የሚፈልጉ እና ኃላፊዎች እግር እግር ስር እየተከተሉ የሚወተውቱ እና የሚሳካላቸው ወይንም ግምት ውስጥ የሚወድቁ፡፡ እድገት የሚገባ ሲሆን መጠየቅ ያለበት አግባብ ወይንም ስርዓት ባለው መንገድ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ  በድርጅቱ ውስጥ ያለውን የሰው ሀብት ማኔጅመንት መተዳደርያ ደንብ (HR Procedure guideline/manual) ጠንቅቆ ማወቅ፤ ቀጣሪዎችም በሙያተኝነት የበቁ ሰራተኞች እንዲኖሯችሁ ማሳወቅ/በየጊዜው ማስገንዘብ አለባችሁ፡፡ ግልጽነት ያለው አሰራር ለጋራ ጥቅም (ለቀጣሪም ለተቀጣሪም ጥቅም) ነውና!  ለዛሬ ጨርሻለሁ!

የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

Share with your circle!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *