የሥራ ቦታ የጨዋታ ሜዳ ነው!

የሥራ ቦታ የጨዋታ ሜዳ ነው Fitsum Blog Image

በሥራ ቅጥር ሕይወቴ ያሳለፍኩትን ጣፋጭ እና ጎምዛዛ ዘመን የመጀመርያው እና “የሕይወቴ ቅኝት” የሚል ርእስ የጻፍኩትን መጽሐፌን ለእራሴም ለአንባቢዎቼም ማስነበቤን እንደ ትልቅ ጀብዱ እቆጥረዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ሁላችንም እዚች ምድር ላይ የመጣነው ተከስተን ልንጠፋ አይደለም፡፡ ለእራሳችን ኖረን ለሌሎችም ልንኖር እንጂ፤ በእርግጥ አንዳንዶች ለእራሳቸው የማይኖሩ አኗኗሪዎች አይጠፉም፡፡ አኗኗሪ መሆን በጣም ያሳዝናል፡፡ ዋናው ነገር ትርጉም ያለው ኑሮ ኖረን ከዚያ ደግሞ ያንን ለእራሳችንም ለሌሎችም በሰነድነት ማስቀመጥ ደግሞ ጀብዱ ነው፤ እሱን ነው የምላችሁ፡፡ ብዙ ሴቶች ትልልቅ ስራ እየሰሩ “እኔ ገና ምን ሰራሁና፣ እኔ እኮ ያን ያህል የሚወራ ስራ የለኝም፣…ወዘተ” ይላሉ፤ ትሁት ለመሆን ብለው ነው ወይንም የራሳቸውን ዋጋ ሳይውቁት ቀርተው፤ ብቻ አይገባኝም፡፡ ለእኔ ግን የዚችን ሀገር ኢኮኖሚ ቀጥ አድርገው የያዟት ሴቶች ናቸው፤ ከወንዶቹ እኩል፡፡ ዛሬ እሱን ላወራ አይደለም አመጣጤ፤ ወደመጣሁበት ልመለስ እና ስንቶቻችን ነን የድርጅት ቅጥርም ይሁን በቢዝነስ ስንኖር  የሥራ የጫወታ ሜዳ መሆኑን የተረዳን!?

ከመነሻዬ “የመጀመርያ መጽሐፌ” ያልኩት ሁለተኛ መጽሐፍ ስለጻፍኩ ነው፡፡ ያው የምታውቁ ታውቃላችሁ፤ ምናልባት ላልሰማችሁ ስሙልኝ! ይህ ሁለተኛው እና ከጥቂት ወራት በፊት ለአንባቢ የደረሰው መጽሐፌ የትርጉም ሥራ ሲሆን ርእሱም “በመጨመቷ ለመሪነት አለመታጨቷ” ነው፡፡ ንዑስ ርእስም አለው፤ ይህም “ማህበረሰብ  በፈጠረባቸው ጫና ሴቶች (ባለማወቅ) የሚፈጽሟቸው እና ሙያቸውን አደጋ ላይ የሚጥሉባቸው ሰማንያ ሁለት ስህተቶች” ይላል፡፡ ዋናዋ ጸሐፊ አንድ መቶ አንድ ስህተታችንን ነበር ያስቀመጠችው፡፡ ግን ወደ እኛ ሀገር ሳመጣው አንዳንዶቹ እንደ ስህተት ሳይሆን ምናልባትም እንደ ግርማ ሞገስ ሊቆጠሩ ስለሚችሉ ተውኳቸው፡፡ እና ሰማንያ ሁለቱን ስህተቶች ከነመፍትሔ ሀሳባቸው ተርጉሜ ጋብዣችኋለሁ፡፡ የዛሬ ርዕሴ የማደርገው እና የማወጋችሁ የመጀመርያውን ስህተታችንን በመንተራስ ነው፡፡

ስህተት አንድ፡- “የሥራ ቦታ የጨዋታ ሜዳ መሆኑን ያለመረዳት!” እንግዲህ ጸሐፊዋ ይህንን በመጀመርያ ስህተትነት አስቀምጣዋለች፡፡ ስትተነትነውም ጨዋታ ሁሉ ውድድር ነው፣ በጨዋታው ውስጥ የሚገባ ሰው ሁሉ “ውድድር” የሚለውን ታሳቢ አድርጎ መሆን አለበት ትላለች፡፡ ብዙ ሴቶች ይህንን ስላልተረዱ “ሥራዬን እስከሰራሁ ድረስ ስለሌላው ነገር ምንም አይመለከተኝም” በማለት እራሳቸውን ከጨዋታው ያገልላሉ፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ምን እየተዶለተ እንዳለ ማወቅ የእነሱ ችግር አይደለም፡፡ የሥራ ኃላፊዎቻቸው ምን ዓይነት ባህርይ እንዳላቸው (የሚያስከፋቸውን እና የሚያስደስታቸውን፣ ትኩረታቸውን የሚስበውን እና ግድ የማይሰጣቸውን…ወዘተ) ጉዳዬ አይሉትም፡፡ ከዚያማ በተሰጣቸው የሥራ ዝርዝር ሥራቸውን ብቻ አድምተው ይሰራሉ፤ ከዚያ የሥራው ሰዓት ሲያልቅ ወደቤታቸው ወይም ወደጉዳያቸው ይሄዳሉ፡፡ በእነሱ ቤት ከእነሱ በላይ ታታሪ ለአሳር ነው ትላለች፤ በምሳሌም ታስረዳለች፡፡ እኔ ልክ ይህንን መጽሐፍ ከማንበቤ በፊት እንደዚህ ያለሁ ሰራተኛ ነበርኩ፡፡ በቃ ሥራዬን እሰራለሁ ከዚያ ውጪ ስለ ኃላፊም ሆነ ስለ የሥራ አጋር ብዙም አያስጨንቀኝም ነበር፡፡ ይህን ስላችሁ አልግባባም ማለቴ አይደለም፤ በጣም ተግባቢ ነኝ፤ ነገር ግን ስለ ድርጅቱ፣ ስለኃላፊዎች፣ ማን ከማን ጋር እንደሚውል፣ ማን ምን እንደሚያስደስተው/እንደማያስደስተው…ወዘተ ጉዳዬ ሆኖ አያውቅም፡፡ ታድያ እድገቶቼን ሁሉ ወደኋላ ሄጄ ሳስታውስ እኔ በጥረቴ ያገኘኋቸው አልነበሩም፤ እንዲያው የእግዜር ጣት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ ለረዝም ጊዜ ከሰራሁበት መ/ቤት ከወጣሁ በኋላ መ/ቤት መቀየር ስፈልግ ማስታወቅያ እያደንኩ እወዳደር ስለነበር ከነበርኩበት የተሻለ የሥራ መደብ አገኛለሁ እንጂ መ/ቤቶቹ ውስጥ ከገባሁ በኋላ ያገኘሁትን የእድገት ደረጃ እምብዛም አላስታውስም፡፡ ይህ ማለት ጨዋታውን አልተጫወትኩም ነበር ማለት ነው፡፡

ይልቅስ እነማን ያድጉ ነበር መሰላችሁ፤ ኃላፊዎች ስር ስር የሚሉ፣ ለሥራም ሆነ ለግል ጉዳያቸው ተፍ ተፍ የሚሉ፣ መረጃ የሚያቀብሉ፣ ኃላፊው/ዋ ቢሳሳቱ እንኳን ጭንቅላታቸውን ከፍ ዝቅ እያደረጉ ትክክል መሆኑን የሚሸነግሉ፣ እንደ መጣላቸው ሲቆጧቸው አሜን ብለው የሚቀበሉ፣ በሚያስቀውም በማያስቀውም የሚያጅቡ፣ ጥፋት እያዩ እንዳላዩ የሚሆኑ፣ ከተቻለ በትውልድ ቋንቋቸው ምስጢር የሚያወሯቸው፣ አንዳንዴም ትንኮሳ የሚታገሱ…ወዘተ፡፡ ለነገሩ ይሄ የእኛ ሀገሩ ጨዋታ እንኳን ቅጥ ያጣም ጭምር ነው፤ ይቅርታ ሁሉም መ/ቤት ወይንም ኃላፊ እንደዚህ ዓይነት ጨዋታ ያደንቀሉ ማለቴ አይደለም፤ ግን በአብዛኛው የምናየው ይህንኑ ነው፡፡ ግን እሱም ጨዋታ ከተባለ፡፡

ጸሐፊዋ የምታነሳው ጨዋታ ግን ከዚህም ይለያል፡፡ ሴቶች በመ/ቤታቸው ውስጥ ስለሚሆነው ነገር ለማወቅ ብዙም አይታትሩም ትላለች፡፡ ሴቶች ሥራቸው ላይ ያተኩራሉ፤ ከዚያ ውጪ አብረዋቸው ከሚሰሩ የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ጥሩ ግንኙነት ካላቸው ለእነሱ ድላቸው ይህ ብቻ ነው፡፡ የድርጅት ጨዋታ መጫወት ማለት የድርጅቱን ባህል፣ የድርጅቱን ፖለቲካ ጠንቅቆ ማወቅ ነው የሚል ምክር አላት፡፡ የድርጅቱ ባህል በኃላፊዎች መሪነት እንደ እለት ተእለት ተግባር የሚወሰድ እንቅስቃሴ ሲሆን ያንን ማወቅ እና ከባህሉ ጋር መጓዝ ግድ ይላል ትላለች፡፡ የድርጅቱ ባህል ደንበኛ ተኮር ከሆነ ለደንበኛ የሚመጥን ባህርይ ምን ዓይነት እንደሆነ እና ኃላፊዎች ደንበኞችን እንዴት እንደሚያስተናግዱ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ አንዳንድ መ/ቤት ደግሞ የሰራተኞችን ባህርይ ማጥናት እና ቆምጨጭ ማለት የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህን ጊዜ ፈገግተኛ ወይንም ቅልስልስ መሆን ሊያስደፍር ወይንም ላያስከብር ይችላል፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን ሜዳውን ማጥናት ግድ ይላል ትላለች፡፡ እናም ከላይ የጠቀስኩት የእኛ ሀገሩም የድርጅት ሜዳ የግድ እንደዚህ ዓይነት ጥናት ይጠይቃል ማለት ነው፡፡ መዋታው እንደሜዳው አይደለምን!

እስቲ በየመ/ቤታችሁ በምናባችሁ በመሄድ ከሰራተኞች ወይንም ከኃላፊዎች ጋር የነበራችሁን ግጭት ወይም ያለመግባባት አስቡ፤ ከዚያ መንስሔውን አስቡ፤ እናም የእናንተ ሚና ምን ይመስል እንደነበረ አስታውሱ፡፡ ከላይ ከጠቀስኳቸው ሁኔታዎች ጋር በተወሰነ መልኩ አልተመሳሰለባችሁም? በነገራችን ላይ እኛን የሚያጠቃን ግትርነት ነው፡፡ “ለማን እና ለምን ብዬ!” እንላለን፡፡ እኔም በቅጥር ዘመኔ እነዚያ ጨዋታውን በደንብ የሚጫወቱትን ሰዎች “አሸርጋጆች!” ነበር የምላቸው፡፡ አሁንም ቢሆን እንደ እነሱ በጣም ዝቅ ማለት የምችልበት አይመስለኝም፡፡ በተወሰነ መልኩ ድርጅትንም ሆነ የእራስን ስብእና በማይነካ መልኩ ዝቅታ ግን አስፈላጊ መሆኑን ከዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ተምሪያለሁ፡፡ በእርግጥ እነሱ ሀገር ጥሩ ሲስተም ስለተዘረጋ በአገም ጠቀም የሚሰጥ ሹመት ወይም የሚመጣ ሽረት የለም፤ እንደ እኛ ሀገር፡፡ ቢሆንም ግን በተወሰነ መልኩ አጠፍ ማለት ከመሰበር ያድናል፡፡

አንድ ምሳሌ ልስጣችሁ እና ልቋጭ፡፡ አንድ መስሪያ ቤት በምሰራበት ጊዜ አንዲት በስራዋ የሚተካት ያልነበረ በጣም ጎበዝ ሴት ነበረች፡፡ ይቺ ሴት በእራስ መተማመኗ ከምትችለው በላይ ከመሆኑ ብዛት ለማንም ትሁት አልነበረችም፡፡ ወይንም በግልጽ ሰው አታከብርም ነበር፡፡ የመሰላትን እና የመጣላትን ቃላት በመሰንዘር ትታወቅ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ እሷ እራሷም ጆሮ የደረሰ ቅጽል ስም ተለጠፈላት፡፡ እሷ ግን ያም ብዙ አላስደነገጣትም ነበር፡፡ ታድያ “የአህያ ስራውን እስከሰራች ተዋት” እየተባለ የሚያርማትም (ተይ ባይ ሳይኖራት) ብዙ ኖረች፡፡ ነገር ግን የሥራ መደብ እድገት ሲመጣ እሷን እያለፉ ከእሷ በታች፣ እሷ ላሰተማረቻቸው ሰዎች ይሰጥ ነበር፡፡ በስራዋ እንከን ሳይኖርባት ነገር ግን እድገቶች ለምን እሷን እንደሚዘሏት ስትጠይቅም የሚሰጣት “ባህርይሽን አስተካክይ!” የሚል አጭር እና ግልጽ ምላሽ ነበር፡፡ ይሄ ለዓመታት ሲንከባለል፣ እሷም አንዴ ከተዋሀዳት ባህርይ ሳትላቀቅ ጡረታ መውጣቷን ከጊዜ በኋላ ሰማሁ፡፡ ይሄ እንግዲህ የድርጅትን ባህል እና ፖለቲካ አንድም ያለማወቅ እና ያለመረዳት በሌላ በኩል ደግሞ ቸልተኝነት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ጨዋታውን አለመጫወት ማለት ነው፤ ይሄ ደግሞ እንዳየነው ከውድድሩ ውጪ አድርጓታል፡፡ እናም በማንኛውም ድርጅት ውስጥ ተቀጥረንም ይሁን ቀጥረን የምንሰራ ሰዎች ወይንም የራሳችንን ቢዝነስ የምንመራ ሰዎችም ብንሆን የድርጅት ጨዋታ ችላ የምንል ሰዎች ከሆንን ስህተት ነውና ከዚህ በኋላ  የጨዋታ ሜዳውን በመጠቀም ተወዳዳሪ መሆን እንዳለብን ልብ ልንል ይገባል፡፡ ብዙ የሚታረሙ ስህተቶቻችንን ለማወቅ እና ለመሻሻል መጽሐፉን እናንብበው! ለዛሬ ጨረስኩ!

Written by: Fitsum Atenafework Kidanemariam

Share on your page!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *