የምቾት ቀጠና ለዘላለም ይኑርì

AWiB, Fitsum Atenafework Kidanemariam Blog የምቾት ቀጠና

አንዳንድ ቃላት ከአማርኛ ስያሜያቸው ይልቅ በእንግሊዝኛ ተለማምደናቸዋል፡፡ የምቾት ቀጠና በእንግሊዝኛው comfort zone በሚል የምናውቀው ነው፡፡ ወደ ዝርዝር ሀሳቡ ከመግባቴ በፊት በትርጉም መጀመሬ ፈገግ አስባለኝ፤ ሁለተኛው መጽሐፌ ትርጉምም አይደል፤ ወደዚያ ወሰድ እያደረገኝ ነው መሰለኝ፡፡ ለነገሩ የዛሬ ሀሳቤም ከዚህ ቀደም እንዳደረግኩት “በመጨመቷ ለመሪነት አለመታጨቷ” የሚል ርእስ ከሰጠሁት የትርጉም መጽሐፌ የፈለቀ ነው፡፡ ዛሬ የምመዝላችሁ ስህተት ሁለት ላይ የተቀመጠው “በምቾት ቀጠና መቆየት” የሚለው ይሆናል፡፡ ጸሐፊዋ “የእኛ የብዙ ሴቶች ስህተት” ካለችው በኋላ እኔም አምኜበት ወደ እኛ አማርኛ ሳመጣው በምክንያት ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን የምቾት ቀጠና የሚለው ሀሳብ በደንብ ግልጽ እንዲሆንልን በዚህ መጽሐፍ ትርጓሜው መደላደል ወይም ተመቻችቶ በአንድ ቦታ ለረዥም ጊዜ መቆየት፣ ሀሳብ አለመሞገት፣ ስጋትን (Risk) አለመጋፈጥ እና ነገሮችን ቸል ማለት የሚሉት ናቸው፡፡ ጸሐፊዋ ከሰጠችን ትንተኔ ጋር አያይዤ እኔ የማውቀውን እና በአንዱ የሥራ ቦታ የገጠመኝን ላጋራችሁ ወደድሁ፡፡ መቼስ የእራስ ስህተት ለእራስ ብዙም አይታይም አይደል!

አንድ የሥራ ባልደረባዬ ከእኔ ጋር በሥራ ከመገናኘታችን በፊት በአንድ የዓለማቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት (International Non-government Organization) ለአስራ ሰባት ዓመታት ተደላድላ ሰርታለች፡፡ በኋላ ድርጅቱ በዋናነት ገንዘብ የሚመድብለት መንግስት የፋይናንስ ቀውስ ያጋጥመውና ድርጅቱ እያነሰ ሄዶ ሄዶ መጨረሻ ላይ ይዘጋል፤ እናም ዘግተው ከወጡት የመጨረሻዎቹ ሠራተኞች አንዷ ነበረች፡፡ ታድያ እኔ የነበርኩበት መ/ቤት በወራት እድሜ ቀድማኝ ተቀጥራ ተገናኘን፡፡ የሥራ ክፍላችን አንድ ባይሆንም የሥራችን ባህርይ እና የሥራ ደረጃችን ቶሎ ቶሎ ያገናኘናል፡፡ ታድያ በሥራችን ላይ እሷ ከምታውቀው መንገድ ውጪ አማራጮችን የማየት፣ አዳዲስ ሀሳቦችን የማመንጨት ወይንም ከሌሎች የመነጩትን ሀሳቦች የመቀበል ከፍተኛ ችግር ነበረባት፡፡ ሁልጊዜ በውይይት ወይንም በሥራ ምክንያት ክርክር ከተጀመረ የድሮ መ/ቤቷን ትጠቅስና “እኛ እዚያ እያለን እንደዚህ ነበር የምንሰራው፤ ልኩ ይህ ነው!” በማለት ፍርጥም ያለ አቋም ትይዛለች፡፡ ጠንከር ያለ አቋም ይዞ የሚሞግታት ሰው ከመጣ ያንን የቀድሞ መ/ቤቷን ስም በመጥራት “መ/ቤቴ ይግደለኝ!” ማለት ቋሚ መቃወሚያዋ ነበር፡፡ ስብሰባ ሲጠራ የምትሳተፈው ግዳጅ ከሆነ ብቻ ነው፤ ለዚያውም ደግሞ አንዲት ሀሳብ ሳትሰጥ በተሰጠው ሀሳብ ተስማምታ ትወጣለች፡፡ አንዳንዴ ስብሰባ ሊጀመር ሲል ዘግይታ ስለምትመጣ “ማነው የጎደለው!” ይባልና እሷ መሆኗ ሲታወቅ “መጣችም አልመጣችም ችግር የለውም” በሚል እሳቤ ስብሰባው ይጀመራል፤ በመሀከል ስትገባም መግባቷ ሳይታወቅ ጥግ ተቀምጣ ሲያልቅ ትወጣለች፡፡ ይሄ የዘወትር ተግባሯ ነበር፡፡

ታድያ እኔም አዲስ መሆኔን እና እሷም በቆይታዋ መልመድ አለመቻሏን ተከትሎ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የማኔጅመንት ስልጠና እንድንወስድ መ/ቤቱ ወጪውን ሁሉ ሸፍኖ አመቻቸልን፡፡ ስልጠናው ከአዲስ አበባ ውጭ ስለነበር በወቅቱ ሳትሳተፍ ቀረች፡፡ ምክንያቷም “ከቤቴ ውጪ ሳድር እንቅልፍ አይወስደኝም!” የሚል ሰበብ ነበር፡፡ መቅረቷንም ቀደም ብላ ባለማሳወቋ እና እድሉን ሌላ ሠራተኛ እንዲጠቀምበት ባለማስቻሏ የድርጅቱ ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት እጅግ ተቆጡ፤ እሷ ግን በወቅቱ ምንም የመሰላት አትመስልም፡፡ ብቻ ምናለፋችሁ የምቾት ቀጠና ለዘላለም ይኑር! በሚል ያወጀች ገራሚ ሴት እሷን አየሁ፡፡

በዚህ እና በመሳሰሉት የመደላደል ባህርይዋ ብዙ እድሎች አመለጧት፤ ለምሳሌ እኔ የምመራው የሥራ ክፍል ወደ ከፍተኛ ማኔጅመንት አባልነት (ከጥቅማጥቅም ጋር) ሲቀላቀል እሷ የምትመራው ክፍል ባለበት ቆመ፣ የተለያዩ ስልጠናዎች ሲመጡ ከእሷ ይልቅ በስሯ ለሚገኙ ሰራተኞች እድሉ ይሰጥ ነበር፡፡ እናም ዘግይቶ የገባት ይቺ የሥራ ባልደረባዬ ኖራ ኖራ መበሳጨት እና መነጫነጭ ጀመረች፤ ሰው ነችና!  “እኔንማ ዞር ብሎ የሚያየኝ የለም፣ የቀድሞ መ/ቤቴ ይግደለኝ!…ወዘተ” በማለት፡፡ እኔም በአንዱ ቀን በቡና ዙርያ አመቻችቼ ያለባትን ክፍተት ነገርኳት፤ ሀሳብ ተቀበይ፣ ተከራከሪ፣ ተሳተፊ፣ ተግባቢ፣ ወደኋላ እየሄድሽ ለዘመናት አንድ ቦታ የቆየሽበትን ዘመን እንደ ጥሩ ምሳሌ አትጠቀሚ፣ ለውጥን ፈልጊ…ወዘተ፡፡ በወቅቱ ወድያው ባትቀበለውም ዛሬ ላይ ግን ወደ ኋላ ሄዳ ስታስበው እንደሚቆጫት ነግራኛለች፡፡ እና ምን ለማለት ነው እሷን በምሳሌ አነሳኋት እንጂ ሁላችንም መጠኑ ይለያይ እንደሆነ እንጂ የምቾት ቀጠና አድናቂዎች ነን፡፡ ስህተታችን የሚከሰትልን ካለፈ በኋላ ነው፤ ላይከሰትልንም ይችላል፡፡

“በመጨመቷ ለመሪነት አለመታጨቷ” በሚለው የትርጉም መጽሐፌ ዋና ጸሐፊዋ እንደ ስህተት አስቀምጣ ስታበቃ ምክሮቿን ለግሳናለች፡፡ እኛ ሴቶች የሥራ ቦታችን ሁልጊዜ ምቹ ስፍራ እንዲሆን ከመፈለጋችን የተነሳ አዳዲስ ነገሮችን ከመሞከር ይልቅ ሁልጊዜ ተመሳሳይ ነገር መሥራትን እንመርጣለን፤ የሥራ ቦታ የጨዋታ ሜዳ መሆኑን ብናውቅም እንኳን በብልሀት ከመጫወት ይልቅ በጥንቃቄ እና በፍርሀት እንንቀሳቀሳለን፤ የእራሳችንን ተነሳሽነት ከመውሰድ ይልቅ የኃላፊዎችን ትህዛዝ እና ውሳኔ እንቀበላለን፣ ተግዳሮቶችን ከመጋፈጥ እንሸሻለን ትላለች፡፡  ከዚህም ጋር አያይዛ ምክሮቿ ከምቾት ቀጠናችን ወጥተን በሥራ ቦታ የሚጠበቅብንን ጨዋታ እንድንጫወት፣ የሌሎችን ተሞክሮ መማርያ እንድናደርግ፣ ያልገባንን ከሌሎች ጠይቀን እንድንረዳ ወይም ምክር እንድናገኝ፣ እርምጃ እንድንወስድ እና ለወሰድነውም እርምጃ ኃላፊነት እንድንወስድ ትመክራለች፡፡

የእራሴን ስህተት አንድ ጓደኛዬ እንዲህ በማለት ነግራኝ ነበር፡፡ እኔ እንዲያውም የሥራ ቦታ በመቀያየር አልታማም፡፡ ረዥም ዓመት የሰራሁት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነበር፡፡ እሱም ድግሪዬን እስክጨርስ የተሰጠኝን የመማር እድል መጠቀም ስለነበረብኝ እያገለገልኩ መገልገል ስለነበረብኝ ነው፡፡ ከዚያ ከወጣሁ ግን አንድ ድርጅት ውስጥ ከሁለት እስከ ሦስት ዓመታት ብቻ ነበር የምቆየው፡፡ ታድያ በነበረኝ ቆይታ በጣም እደላደል እና የሆነ ነገር ቅር ሲለኝ (ሳይመቸኝ ሲቀር) ብቻ ነበር ሥራ መፈለግ የምጀምረው፡፡ ያንን ያስተዋለች ጓደኛዬ “የመደላደል ባህርይ አለሽ፤ የተሻለ እድል ልታገኚ ስለምትችይ ሁልጊዜ ፍለጋ ላይ ሁኚ!” ያለችኝን መቼም አልረሳውም፡፡ በእርግጥ እኔ የማምንበት ነገር አለ፡፡ አንድ መ/ቤት ገብቼ ወድያው ለውጥ በመፈለግ አላምንም፡፡ እዚያው መ/ቤት ውስጥ በተሰጠኝ ኃላፊነት ለውጥ ማምጣት፣ አስተዋጾ ማድረግ፣ የምታወስበት ነገር (legacy) መተው አለብኝ፡፡ ባልተመቻቸ የሥራ ባህል እና ፖለቲካ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ግን የገባኝ ዘግይቶ ነበር፡፡

እንግዲህ ይሄ ከምቾት ቀጠና የመውጣት ምክር ሁላችንንም የሚመለከት እና በሙያችን ማደግ ከፈለግን ልንተገብረው የሚገባ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሁልጊዜ ስጋ ወጥ ወይንም ሁልጊዜ ሽሮ ወጥ መብላት እንደሚሰለች ሁሉ ሕይወታችንን ጣእም እንዲኖረው ለማድረግ ከተደላደልንበት አንድ ቦታ ፈቀቅ እንበል፡፡ አበው ይሁኑ እማው ሲተርቱ ያልተገላበጠ ያራል፣ እልፍ (ዞር) ሲሉ እልፍ (ብዙ) ይገኛል ይላሉ፡፡ ሁልጊዜ ሀሳብ ተቀባይ ብቻ ሳይሆን ሀሳብ አመንጪ (ሰጪ) እንሁን፤ ሁልጊዜ ታዛዥ (አቤት-ወዴት) ብቻ ከምንሆን ለምን ብለን እንጠይቅ፤ ሁልጊዜ በአንድ መንገድ ብቻ ከምንሄድ አማራጮችን እንሞክር፤ ሁልጊዜ ፈሪ ከምንሆን ተጋፋጭም እንሁን! ጊዜው እንደድሮ ሁሉ ነገር ቀስ ያለ ሂደት ተከትሎ የሚሄድበት አይደለም፤ እናም ከጊዜው ጋር መፍጠን እና መራመድ ካልቻልን ተከታይ መሆን ቀርቶ የምንከተላቸውም ሰዎች ከዓይናችን ርቀው ብቻችንን ልንቀር ሁሉ እንችላለን፡፡ እናም ንቁ! እንንቃ! የምቾት ቀጠና ለዘላለም አይኑር!

ከማጠቃለሌ በፊት በዚህ በመጨመቷ ለመሪነት አለመታጨቷ በሚለው የትርጉም መጽሐፌ ውስጥ እስካሁን ያቀረብኩላችሁ ሁለቱን ነው፡፡ ሰማንያ ስህተቶቻችን ገና አልተዳሰሱም፡፡ ስለዚህ ይህንን መጽሐፍ የራሳችሁ አድርጋችሁ ብዙ ብትማሩበት ታተርፋላችሁ የምላችሁ ለማስተዋወቅ ብዬ ሳይሆን ለመምከር ነው! በቀጣይ ከሥራ ወይንም ከቢዝነስ ወጣ ብለን በሌላ ማህበራዊ ርእስ እንገናኛለን፤ የዚያ ሰው ይበለን!

Written by: Fitsum Atenafework Kidanemariam

Share on your page!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *