ከእሷ ጀርባ

ብዙ ጊዜ ከጠንካራ ወንድ ጀርባ ጠንካራ ሴት እንዳለች ይነገራል፡፡ በእርግጥም ሐቅ ነው፡፡ ይህንንም ያስተዋሉ ሰዎች ሊመሠገኑ ይገባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ለዘመናት ሴቷ ትደክማለች ግን ከጓዳ አውጥቶ ያሞገሳት እምብዛም አልነበረም፡፡ እንኳን እሷ ከጓዳ ልትወጣ ስሟ እንኳን አይነሳም ነበር፡፡
አስታውሳለሁ ልጆች እያለን አንዳንድ ውድድሮች ካደረግን በኋላ ላሸነፍነው ልጆች አድናቆት ይሰጠን እና ቀጣዩ ጥያቄ የወላጆቻችን ማንነት ነው፡፡ የሚያሳዝነው ታድያ እናታችንን ሳይሆን አባታችንን ነበር የሚጠይቁን፡፡ እኔ ታድያ “የማን ልጅ ነሽ? እንደዚህ አድርጎ ያሳደገሽ አባትሽ ማነው?” የሚባለው ጥያቄ ልክ በልጅነቴ እንደምወጋው የቶንሲል መርፌ ያመኝ ነበር፡፡ አባቴ በሕጻንነቴ ስለሞተ በእኔ ማንነት ላይ አሻራ ለመተው ባለመታደሉ አልነበረም፡፡ ልጅን አንጾ ለማሳደግ የእናት ድርሻ ከቁብ አለመቆጠሩ እንጂ፡፡ በዚህ ስሜት ውስጥ ያለፍን ወይንም እያለፍን ያለን ቤት ይቁጠረን፡፡ ሴትን ያለማወደስ ግን መሠረቱ ምን ይሆን!
ሴት እናትም አባትም ስትሆን በጣም ጠንካራ ለመሆኗ በሴት እጅ ያደግን ልጆች እናውቀዋለን፡፡ ሰዎች በባህርያችን ረዳት ወይንም አጋዥ ሲኖረን ሸክማችንን እናካፍላለን፡፡ የተካፈለ ሸክም ደግሞ ክብደት ስለማይኖረው ጥንካሬን አይጠይቅም፡፡ ሸክማችንን የምናካፍለው ከሌለን ግን የበለጠ እንጠነክራለን፤ ላለመውደቅ፡፡ ይህ የትዳር አጋራቸውን በሞት የተነጠቁ ወይንም በፍቺ የተለያዩ አልያም ደግሞ ከትዳር ውጪ በተደረገ የፍቅር ግንኙነት ልጅ/ልጆች ወልደው የሚያሳድጉ ሴቶች ሕይወት ነው፡፡ እንደዚህ ያለች ሴት ሸክሟ አጠንክሯታል፡፡ ስለሆነም ከእሷ ጀርባ ያለው ጥንካሬዋ ነው፡፡ በእሷ ጥንካሬ ልጆቿም ጠንክረው ይወጣሉ፡፡ ለልጆቿ ጥሩ አርአያ ናት፡፡ ያቺ ብቸኛ ሴት በማህበሩ ያልተዘመረላት! ለነገሩ ብቸኛዋን ብቻ ሳይሆን ማህበሩ ለየትኛዋም ሴት ገና አልዘመረም፡፡
በትዳር ውስጥ ሆናም ብቻዋን የምትደክም ሴት ቤት ይቁጠራት፡፡ በአንድ ወቅት በሥራ ያወቅኳት ሴት ነበረች፡፡ ብሯን ባንክም ሆነ ቤቷ ማስቀመጥ ስለማትፈልግ እናቴ ጋር ታስቀምጥ ነበር፡፡ ምክንያቷ ደግሞ ባሏ ብር እንዳላት ካወቀ በጉልበት (ደብድቦ) ስለሚቀማት ለሁለት ልጆቻቸው እና ለእሱም ጭምር ምግብ ማብላት ይቸግራታል፡፡ እንደዚህ በስስት ያሳደገቻቸው ልጆቿ ግን በትምህርት ጥሩ ነጥብ ሲያመጡ እሷን ከቤት ቁጭ በይ ብሎ እሱ ት/ቤታቸው ድረስ በመሄድ ሽልማታቸውን ይቀበል ነበር፡፡ ዓለማችን ብዙ እንዲህ ያሉ ወንዶች አሏት፡፡
ማህበረሰባችን የሴቶችን ጥንካሬ ገና አልተቀበለውም፡፡ ሌላው ቢቀር ከእያንዳንዱ ጠንካራ ወንድ ጀርባ ያለችውን ጠንካራ ሚስት እንኳን ለአባባል እንጂ በቁም ነገር አጉልተው ሲናገሩት አይሰማም፡፡ እንዲያው እንዳይከፋት የሚናገሩት ይመስላል፡፡ በሴቷ ድጋፍ የደረሱበት ከፍታ የደረሱትም ወንዶች ከጥቂቶች በስተቀር አጽንኦት አይሰጡትም፡፡ በተለይ ደግሞ ሚስት ከሆነች አጉልቶ የማሳየቱ ነገር እምብዛም አይደለም፡፡ እንዲያውም እናት ከሆነች በመጠኑ ይነገርላታል፡፡ ለምን ይሆን ግን አንዳንድ ወንዶች ሚስቶቻቸውን አጉልተው ማመስገን የሚያስፈራቸው! እሱን ለእነሱ እተወዋለሁ፡፡ በእኔ አተያይ ደግሞ ሴቶች አባቶቻቸው፣ ባላቸው እና ወንድሞቻቸው ያደረጉላቸውን እገዛ በደንብ አጉልተው ያሳያሉ፤ ልክ እናታቸውን እና እህታቸውን ባወደሱት መጠን፡፡ ተወደሰም አልተወደሰ እሷ የሌለችበት ስኬት የሌለ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ እሷ እናት፣ ሚስት፣ እህት ወይንም አያት ልትሆን ትችላለች፤ ግን በእያንዳንዱ ወንድ ስኬት ውስጥ አሻራዋ አለ፡፡
እንደ እኛ ባሉ ባላደጉ ሀገራት ብዙ ነገር በሴቶች ትከሻ ላይ እንዳለ እየታወቀ እሷን የሚያመሰግን ወይንም የሚያወድስ ማህበረሰብ ግን የለም፡፡ አርግዞ መውለድ እና ተንከባክቦ ማሳደግ የስንት ዓመት ሥራ ነው ብለን ካሰብነው ብቻ በቂ ነው፡፡ የሰው ልጅ አድጎ እራሱን የሚችለው በስንት ዓመቱ ነው ብለን ካሰብን ደግሞ የትየለሌ! እህት ሆና እናቷን ከማገዝ ጀምሮ የእራሷን ቤተሰብ መስርታ ባሏን እና ልጆቿን የምትንከባከበው ሴት የትም ስትመሰገን ወይንም ስትሸለም አናይም፡፡ ለነገሩ “ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ” የሚለው አባባል የሴቷ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ውዳሴው ቀርቶባት በሰላም በኖረች! ፈተና የማይበግራት፣ ከውዳሴ ጋር የማትተዋወቅ፣ የራሷን ኑሮ ችላ ብላ ለሌሎች የምትኖር እልፍ ሴት አለች፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ከጀርባዋ ያለው ጽናቷ እና ጥንካሬዋ ድንቅ ነው! ሴት ልጅ እድሉን አግኝታ ከሠራች ወይንም ከነገደች ለሀገርም ለወገንም እንዲሁም ለእራሷም የሚገርም ለውጥ እንደምታመጣ እያየን ነው፡፡
ብዙዎቻችን እንደምናውቀው በሀገራችን ብዙ የሽልማት ድርጅቶች አሉ፡፡ ብዙዎቹ ወንድ ተኮር ይመስላሉ፡፡ ምናልባትም አርቲስቶችን የሚሸልመው የጉና አዋርድስ ላይ ጥቂት ሴት አርቲስቶችን እናያለን፡፡ በተረፈ ግን የበጎ ሰው ሽልማት ይሁን ሌሎች የሽልማት ድርጅቶች እስካሁን ለሽልማት ያበቋቸውን ሰዎች ደምረን የሴቶች ተሸላሚዎችን ቁጥር ብናይ ከመቶ 10 እጅ ካገኘን እኔ እቀጣለሁ፡፡ ሌላው ቀርቶ እጩ ሆነው የሚመጡት እንኳን በአብዛኛው ወንዶች ናቸው፡፡ እውን የሚሸለሙ ሴቶች ጠፍተው ነውን!? እውን እነዚያ ተሸላሚ ወንዶች በተሰማሩበት የሙያ ዘርፍ የበቁ ሴቶች ለውድድር ሳይበቁ ቀርተው ነውን!? መልሱን እራሴው እንደጠየቅሁ ልመልሰው፤ ሴቶች አሉ፡፡ ነገር ግን ማህበረሰባችን ሴትን ማወደስ የማይወድ ነው!!
ብቁ ሴቶች እንዳ ያሳየን አንዱ አጉሊ መነጽራችን በኤውብ በየዓመቱ የሚደረገው የበቁ ሴቶች የሽልማት መድረክ ነው፡፡ አቤት ስንቷን ጀግና ሴት አየን! በየዓመቱ በሚዘጋጀው የበቁ ሴቶች ሽልማት መድረክ ላይ ለማህበረሰቡ ፋይዳ ያለው አበርክቶ ያላቸውን ሴቶች እያየን እኮ ነው፡፡ ተሸላሚዎቹ ሴቶች በየተሰማሩበት መስክ አስደናቂ ሥራ የሠሩ ናቸው፡፡ እንዲያው ለምሳሌ አንዷን እንይ እና ጽሑፌን ልቋጭ፡፡ ዛሬ በከተማ አቀፍ የተማሪዎች ምገባ ሀሳብ መነሻው ከየት እንደሆነ ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ? ፍሬአለም ሽባባው ናት የጀመረችው፡፡ ፍሬአለምን መንግስት ሳያውቃት በፊት ኤውብ የበቁ ሴቶች ሽልማት ተሸላሚ አድርጋታለች፡፡ እንግዲህ ለምሳሌ አነሳሁላችሁ እንጂ ከ50 በላይ ሴቶች በኤውብ የበቁ ሴቶች መድረክ ተሸልመዋል፤ ለሕዝብም ይፋ ተደርገዋል፡፡ ሴቷ ማህበረሰባችን እስኪነቃ ውዳሴ እና ሽልማት ባይሰጣትም ቅሉ ከእሷ ጀርባ ማንም የማይቀማት ጥንካሬዋ እና ጽናቷ አሏት! ለዛሬ ጨረስኩ፤ ግን ተመልሼ እመለሳለሁ!!
ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም: Fitsum Atnafework K/Mariam, Author at AWiB Ethiopia