እንደ ሁኔታው!

በአንድ ወቅት እሰራበት የነበረ አንድ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት የመዋቅር ለውጦችን አደረገ እና ለረዥም ዓመታት ያገለገሉትን ሰራተኞች የአገልግሎት ዘመን ያላማከለ ስለነበር እጅግ አስቆጣቸው፡፡ በወቅቱ የነበረው የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የውጭ ሀገር ዜጋ ስለነበረ የእኛን ሀገር ውስጠ ወይራዊ ንግግር አያውቃትም እና ያመነበትን ፊት ለፊት ነበር የሚናገረው፡፡ ታድያ ከንግግሩ የማይረሳኝ “እናንተ ነባር ሰራተኞች ሆይ! ተጎድተናል ካላችሁ መሥሪያ ቤቱን ለቃችሁ መሄድ ትችላላችሁ፤ እንዲያውም ለመ/ቤቱ አዳዲስ ሠራተኞች (New blood) ያስፈልጋል” በማለት እንደ ዋዛ ተናገረ፡፡ አንዳንድ ዋዛዊ አነጋገሮች አጥንት ይሰብራሉ፤ እንደማይጠገን አድርገው፡፡ ብዙዎች አዘኑበት፡፡ እኔ በመ/ቤቱ ብዙም ስላልቆየሁ ካላዘኑት ውስጥ ብሆንም ጓደኛ ያደረግኳቸው ነባሮቹ ጓደኞቼ ለመ/ቤታቸው ልክ እንደቤታቸው ነበርና ተግተው የሚሰሩት በመጠኑ ሀዘናቸውን ተጋራኋቸው፡፡ ግን በመጠኑ ያው ሀዘናቸው ሀዘኔ ብዬ እንጂ የኃላፊው ሀሳብ ሙሉ በሙሉ ስህተት ነው ብዬ አልነበረም፡፡ ምናልባት የእሱ ስህተት እንደ ባህላችን ያለማዋዛቱ ነው፡፡ በዚያም ላይ ነባር ሠራተኛ እኮ የድርጅቱ ታሪክ ነው! ጥሩ ታሪክ ይከበራል እንጂ አይጣልም! ጥሩ ያልሆነ ግን ያው…!

 እኔ በሥራ ቅጥር ዘመኔ ብዙ መስሪያ ቤት መቀያየሬን እንደ ጥቅም ነው የማየው፡፡ ከሚገኘው እውቀት በተጨማሪ የተለያዩ መ/ቤቶችን ባህል እና ፖለቲካ ምን እንደሚመስል አይቼበታለሁ፤ ተምሬበታለሁም፡፡ መ/ቤት ውስጥ ያሉ ሰዎች ናቸው፤ እናም ስለ ሰዎች ባህርይ እኔንም ጨምሮ በደንብ ያወቅኩበት የሕይወቴ አጋጣሚ ነው፡፡ በእኛ ሀገር አኗኗር በተለይ ደግሞ የሥራ እድል እንደ ልብ ያለመገኘት ብዙዎች ልክ “ብልጥ ልጅ የያዘውን ይዞ ያለቅሳል” ዓይነት የሥራ ሕይወት እንዲኖሩ አስገድዷቸዋል፡፡ ብልጡ ልጅ እኮ የያዘውን ይዞ የሚያለቅሰው ሌላ እየፈለገ ነው! ብዙዎቻችን አዲስ የሥራ ለውጥ የምናደርገው ተገፍተን ስንወጣ ብቻ ነው፡፡ እስከዚያ እንደሁኔታው እራስን እየሸነገሉ መኖር ብቻ፤ እንደሁኔታው! በነገራችን ላይ መ/ቤቶቻችን እኛ ብንወጣ ወድያው የመተካት አቅም አላቸው፡፡ አንዳንድ ሰዎች እነሱ የማይኖሩ ከሆነ ሰማይ የሚደፋ ይመስላቸዋል፡፡ የሚገርማችሁ ነገር ግን በጭራሽ ሰማይ አይደፋም! በተለይ ኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ሰዎችማ አምነው መደበኛ የዓመት እረፍታቸውን እንኳን መውጣት ይቸግራቸዋል እኮ! አንድ መስሪያ ቤት ስትሰሩ እስካላችሁ ድረስ እንጂ ባትኖሩ ወድያው የምትተኩ መሆኑን በደንብ ማወቅ አለባችሁ፡፡ እስቲ የሰራችሁባቸውን መ/ቤቶች ወደኋላ ሄዳችሁ አስቧቸው! የእናንተ ያለመኖር መ/ቤቱን አላዘጋውም አይደል!? እንዲያውም ያ የድሮ ኃላፊያችን (ፈረንጁ) ያለ ይሉኝታ አዲስ ሰራተኛ ያስፈልገናል እንዳለው የእናንተን( የእኛን) ከቦታው ዞር ማለት አድፍጠው የሚጠብቁም አይታጡም፡፡ እንዴ ዛሬ እኮ እንኳን ሰው በሰው ቀርቶ በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስም እየተተካ ነው፡፡ ምንጊዜም በቀላሉ ተተኪ (የምትተኩ) እንደሆናችሁ አስቡ!  

ይሁን ሁሉ የማወራው ከምትወዱት እና ከሚወዳችሁ ሥራ ላይ ተነስታችሁ ሌላ ሥራ ፈልጉ እያልኩ አይደለም፡፡ ነገር ግን እኔ የለፋሁበት ነውና ባይመቸኝም እንደ ሁኔታው ችዬና ተቻችዬ እየሠራሁ እቀመጣለሁ የሚለው ከፍርሀት ወይንም በእራስ ካለመተማመን የሚመጣ እሳቤ እየተፈታተናችሁ ከሆነ ማለቴ ነው፡፡ እንደ ሁኔታው የሚባል ነገር እኔ በበኩሌ አይመቸኝም፡፡ ከሁኔታው በላይ መሆን አለብን የምል ነኝ፡፡ እርግጥ ነው እንደ ሁኔታው የሚባልላቸው አስገዳጅ እና ከአቅም በላይ የሆኑ ነገሮች እንዳሉ አይካድም፡፡ ለምሳሌ አንድ ቤተሰብ የማስተዳደር ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ ያለባቸው ሠራተኞች የተሻለ የሥራ አማራጭ እስኪያኙ እንደ ሁኔታው እየቻሉ እና እየተቻቻሉ መኖር ግድ ይላቸው ይሆናል፡፡ 

አንድ ገጠመኜን ላውጋችሁ፡፡ በቅጥር ከሠራሁባቸው በአንደኛው ዓለም አቀፍ መ/ቤት ውስጥ ብዙ የውጭ ዜጎች ነበሩ፡፡ ታድያ እነዚህ ሰዎች ደህንነታቸው እና ምቾታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ በዋናነት ኃላፊነት ያለበት እኔ የምሠራበት የሥራ ክፍል ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ በተለይ የእኔ እና የተወሰንን ኃላፊዎች ስልክ ለ24 ሰዓታት ክፍት መሆን ነበረበት፡፡ ወቅቱ ብዙም ኮሽታ የነበረበት ስላልነበረ በሌሊት የደወሉበት ቀን ብዙም አይደለም፡፡ ከሆነም መብታቸው ነው! አልፎ አልፎ ግን በረራቸው ሌሊት ከሆነ ትራንስፖርታቸው ሳይቀር ስለሚመለከተኝ ሊደውሉ ይችላሉ፡፡ ጥሩ የአሰራር ስልት ስለነበረ በሥራችን ቅሬታ አሰምተው አያውቁም፡፡ ታድያ በጣም ተከባብረን እየሠራን ባለበት አንድ ያልጠበቅኩት ወቀሳ ደረሰኝ፡፡ ይህም “ፍፁም ቴክኒካል ናት፤ በኢሜል ለምትጠየቀው ጥያቄ በኢሜል፣ በስልክ ለምትጠየቀው በስልክ፣ በደብዳቤ ለምትጠየቀው በደብዳቤ ብቻ ትመልሳለች፤ በአካል አናገኛትም” የሚል ነበር፡፡ እናም በወቅቱ ለወቀሳ ያበቃኝን ነገር ማወቅ ብቻ ሳይሆን መቀበልም ተሳነኝ፡፡ ምክንያቱም በአካል ላገኝሽ እና ስለ ሥራ ላነጋግርሽ እፈልጋለሁ የሚል ጥያቄ ካልቀረበልኝ ለምን አገኛቸዋለሁ!? 

ነገሩ ለካ ወዲህ ነው! በወቅቱ ሌሎች የሥራ ባልደረቦቼ ከተጠየቁት በላይ አገልግሎት መስጠት አስለምደዋቸዋል፡፡ ለምሳሌ መርካቶ በየት በኩል ነው ሲሏቸው “እኔ ገበያ አደርግልሻለሁ/አደርግልሀለሁ” እስከ ማለት እንደሁኔታው እራሳቸውን አስገዝተዋል፡፡ እዚህ ላይ እንግዳ ተቀባይነት የሀገራችን ባህል ቢሆንም እራስን እዚያ ድረስ ማስገዛት ለእኔ የማይዋጥልኝ ነበር፡፡ ለምሳሌ ለመጀመርያ ጊዜ ማለማመድ፣ ማሳየት የአባት ይሁን የእናት ብቻ ወግ ነው፤ ግን ደግሞ ቋሚ ገበያተኛ (አስቤዛ ሽማች) መሆን የሚጠይቅ ሁኔታን እንደ ሁኔታው ብሎ በየጊዜው ለመተግበር ለእኔ ነውር (taboo) ነበር፡፡ በተቃራኒው ለኃላፊዎች እና ለሥራ ባልደረቦቼ ትክክል ነበር፡፡ ታድያ እዚያ መ/ቤት ድርጅቱን እየወደድኩት የድርጅቱን ባህል ስላልተቀበልኩት መውጣት ነበረብኝ፡፡ ለሥራው በጣም ታታሪ እና ጠቃሚ የነበርኩ ቢሆንም እንኳን መውጣቴ ያንን ያህል አላጎደለም ነበር፡፡ ሁሌም ተተኪ አለና! 

ይሄ አንድ ምሳሌ የብዙዎቻችንን ገጠመኝ የሚያስታውስ ይመስለኛል፡፡ ሁኔታዎችን እያዩ መፍሰስ በብዙ ድርጅቶች የተለመደ ባህል ነው፡፡  እንደሁኔታው መሆንን አንድ እና ብቸኛ አማራጭ መስሏችሁ በያዛችሁት ሥራችሁ ላይ ለረዥም ጊዜ የቆያችሁ እስቲ ነቃ በሉ፡፡ ሕይወት እኮ አንዴ ናት!  ሁኔታው ሳይሆን ገዢው መተዳደርያ ደንቡ ነው፡፡ ደንብ እና መመርያ ማክበር ሁኔታዎችን እንደማክበር ተፈላጊ ካልሆነስ! በነገራችን ላይ የተለያዩ መ/ቤቶች እየተወዳደሩ መግባት የራስን የዋጋ ተመን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ከዚያም ባለፈ ለመወዳደርያ የሚያበቁ መስፈርቶችን ለሟሟላት እራስን ማጎልበት እና ማስተማር ተያያዥ ስለሆኑ መገላበጡ መልካም ነው፡፡ ያልተገላበጠ ምን ይሆናል እንዲሉ! እንደ ሁኔታው ከመኖር ሁኔታዎችን ማመቻቸት ብልህነት ነው! 

ማሳሰብያ፡- ይህ ጽሑፍ በተሰማራችሁበት የሥራ መስክ እና በመ/ቤታችሁ አሰራር እና ባህል ደስተኛ እና ስኬታማ የሆናችሁትን አግላይ ነው! ለዛሬ ጨርሻለሁ!

Written by: Fitsum Atenafework Kidanemariam

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *