እርጉዟን ማን ይቅጠራት!?

አንዳንድ የጦፉ ክርክሮች በአንድ ወገን አሸናፊነት ወይም አሳማኝነት ሳይቋጩ ሲቀሩ እንዴት ያንገበግበኛል መሰላችሁ፡፡ በጓደኛሞች ወይም በቤተሰብ መሀከል የሚደረግ ክርክር ወይም ቃሉን የተሻለ ለማድረግ ጭውውት (በዘመነኛው ጭዌ)፣ ምክክር  ወይንስ ውይይት እንበለው? ብቻ ስያሜው ማንም ይሁን መጨረሻው የአንዱ ወገን አሳማኝነት ሲነግስበት ፋታ ይሰጣል፡፡ ምክንያቱም ዋና አላማው ጦርነት መክፈት ሳይሆን ስምምነት ላይ መድረስም አይደል! ለጦርነትም ለስምምነትም ያልደረሰ ክርክር ወይንም ውይይት ላይ ጊዜ በማጥፋት የዛግኩበት ገጠመኝ ሲከነክነኝ “እስቲ አብረን እንዛግ?” አልላችሁም ግን ላጋራችሁ እና አብረን እናብላላው እስቲ! ማን ያውቃል የሆነ ነገር ይገለጥልን ይሆናል! ከተገለጠላችሁ ከወዲሁ ከአደራ ጋር የምጠይቃችሁ አንብባችሁ ስታበቁ እንደሌላው ጊዜ (አድንቃችሁ) ዝም አትበሉ፡፡ ይልቁንም ሀሳብ እንድትሰጡኝ (ኮሜንት እንድታደርጉልኝ) እፈልጋለሁ፤ ምናልባት በተመሳሳይ አጋጣሚ  ቀጣሪ ጓደኞቼን ወይንም የእነሱ አይነት መረዳት ያላቸውን ሰዎች ካገኘኋቸው እንዳሳምናቸው ወይንም እንድነግራቸው፡፡

ምን ሆነ መሰላችሁ ሴቶችም ወንዶችም ጓደኛሞች ሰብሰብ ብለን ወግ ይዘን የወጉ አቅጣጫ ወደ ስነ-ጾታ (Gender-ጄንደር) ያመራል፡፡ መቼስ ስለ ጄንደር ሲነሳ በብዙዎቻችን አእምሮ የሚከሰተው የሴቶች ጉዳይ ነው አይደል! ያው ስላልተረዳነው እኮ ነው እንጂ የሁላችንም ጉዳይ ነው፡፡ እናላችሁ (ይቺ አባባል ድሮ እናቶቻችን ወግ ሲይዙ ከቆሙበት ለመቀጠል የሚጠቀሙባት ቃል ናት) ነፍሰጡር ወይንም እርጉዝ ሴት የጭዌአችን ትኩረት ሆነች፡፡ ሁላችንም በተለያየ ሙያ የተሰማራን ስለሆነ ስብጥራችን ያላየነውን ሐቅ ያሳየን ይመስላል፡፡ እኔ የሰው ሀብትና ጄንደር፣ ሌሎች ደግሞ ከኢንጂነሪንግ፣ አካውንቲንግ (ኦዲት) እና ቢዝነስ ማኔጅመንት የተውጣጣን ስንሆን ከመሀከላችን የራሳቸው ኩባንያ (ካምፓኒ ወይንም ድርጅት) ያላቸው ባለሙያዎች አሉበት፡፡ ርእሰ ጉዳዩን ወደ ጠረጴዛው ያመጣው የኩባንያ ኃላፊ  “አዲስ ሰራተኛ ወደ ካምፓኒ ለማምጣት ፈታኝ የሆነ ጊዜ ነው፣ ልምድና እውቀት ያላቸው የት ገቡ!? ከስንት ድካም በኋላ አንድ ጥሩ ሲቪ ያላት ሴት አገኘን እና ለኢንተርቪው ስንጠራት እርጉዝ ናት፡፡ በጣም ደነገጥኩ፡፡ ስለጠራናት ብቻ ኢንተርቪውን ማድረግ ነበረብን፡፡

የሚገርመው ደግሞ በእሷ ልክ ኢንተርቪውን በብቃት የተወጣ ተወዳዳሪ አልነበረም፤ ግን ምን ዋጋ አለው፣ ለአራት ወራት የወሊድ ፈቃድ የምትወጣ ምናልባትም የ 6 ወር እርጉዝ ናት፤ የእኛ ሥራ ደግሞ ፕሮጀክት ያማከለ (Project based)  ስለሆነና የአንድ ዓመት ስራ ስለሆነ ሌላ ሰው መፈለግ ነበረብን” የሚል ነበር፡፡ “ውይ ይሄማ በጣም አስቸጋሪ ነው! ፕሮጀክቱ ላይ የምትቆየው እኮ ስምንት ወራት ብቻ ሊሆን ነው!” የሚሉ አጋዥ ሀሳቦችም ታከሉበት፡፡ ከእሱም ላይ ለስድስት ወራት በቀን ሁለት ሰዓት የማጥቢያ ሰዓት መፍቀድ እንዳለብህስ ታውቃለህ!? በሚል ቅብብሎሽ ጭውውቱ እየደራ መጣ፡፡ ከእኔ ጋር ሁለት ሴቶች ነበርን እና ሁኔታውን እየሳልን ነው መሰለኝ ለጥቂት ደቂቃዎች በግርታ  መንፈስ አዳማጮች ነበርን፡፡

ዝምታውን መስበር ነበረብኝ፤ የሴትነት ብቻ ሳይሆን የሙያ ግዴታዬም ነውና! “አንዲት ሙያተኛ ሴት ለቦታው ብቁ መሆኗ ከተረጋገጠ በእርግዝናዋ ምክንያት አለመቅጠር አግባብ አይደለም፤ በሕግም ያስጠይቃል” አልኩ፡፡ ሌላው ወንድ ጓደኛችንም አገዘኝ፡፡ ግን ደግሞ በሰዓት የተገደበ ፕሮጀክት ይዞ ሙያተኛ የሚፈልገው የኩባንያ ባለቤትም እውነት አለው፤ ልክ እሷ እርጉዟ ሴት መብት  እንዳላት ሁሉ፡፡ ሚዛናዊ ለመሆን በምናደርገው ጥረት መፍትሔ የሚሆን ሀሳብ ከማምጣት ይልቅ ተወዛገብን የሚለው ቃል ብቻውን አይገልጸውም፡፡ ምክንያቱም ማናችንም በዚህ መልኩ አስበነው አናውቅም ነበርና፡፡

ጥቂት ካሰብኩበት በኋላ አንድ ሀሳብ ብልጭ አለብኝ ወይም አለልኝ እና ወደ ጭውውቱ ጠረጴዛ አመጣሁት፤ “ቆይ ባለቤታችሁ ወይንም እህታችሁ እርጉዝ ናት እንበል፣ ወድያውም ሥራ እየፈለገች፡፡ አንድ ያመለከተችበት ድርጅት “ካሉት ተወዳዳሪዎች ያንቺ ልምድና ትምህርት ስለማረከን ኢንተርቪው ልናደርግሽ ፈልገናል፤ እናም በዚህ ቀን እና ሰዓት ድርጅታችን እንድትመጪ” ብለው ቢደውሉላት እና ብታማክራችሁ ይቺ በኢኮኖሚ እራሷን የቻለች አልፋም ቤቱን እንደ እናንተ የምትደጉመዋን ሴት “እርጉዝ ስለሆንሽ ኢንተርቪውን አታድርጊ ቅሪ እና ከወለድሽ በኋላ  ሥራ ፍለጋውን ትቀጥያለሽ!” ነው የምትሏት ወይንስ “መልካም እድል!” ብላችሁ ነው የምትሸኟት? በድጋሚ ለጥቂት ሰኮንዶች ጸጥታ ነገሰ፤ ማናቸውም ግን ምላሽ አልነበራቸውም፡፡ ጸጥታውም ያመጣው መፍትሔ አልነበረውም፤ ልክ እንደክርክሩ ወይም እንደ ውይይቱ ፍሬ አልባ ነበር፡፡

እናም ለዚህ ነበር  ከመነሻዬ የእናንተን ሀሳብ (ኮሜንት) ያለወትሮዬ የጠየቅኩት፡፡ ወደኋላ ሄጄ እናቴን አሰብኳት፡፡ አራታችንንም ስትወልድ የወሊድ ፈቃድ እየወጣች ነበር፡፡ ከዚያም ስትመለስ አንዳንድ ስልጠናዎች አምልጠው ይጠብቋት እና አቻ የስራ ጓደኞቿ የተሻለ እድገት ወይንም እርከን ላይ ሲቀመጡ እሷ ግን ባለችበት ትሄድ ነበር፡፡ ያ የእነሱ ዘመን ግን ተለውጧል፡፡ የእኔ ዘመን የተሻለ ሆኗል፡፡ ቋሚ ምስክር ነኝ!

እኔ ልጄን አርግዤ የወለድኩበት አለም አቀፍ ድርጅት (ኤንጂኦ) በጁላይ 21 2008 (እ.አ.አ) ተቀጥሬ በአመቱ በዚያችው ቀን በጁላይ 21 2009 ነበር የወለድኩት፡፡ በተቀጠርኩ በአመቱ ስወልድ የአራት ወር የወሊድ ፈቃድ እና ሙሉ ሁለት ወር የዓመት ፈቃድ ተሰጥቶኝ በስድስት ወሬ ነበር ወደ ስራ የተመለስኩት፡፡ አንድ ዓመት አገልግዬ ሁለት ወር ድፍን አይኖረኝም፤ ያለክፍያ ፈቃድ ለማግኘትም የአገልግሎት ዘመኔ አይፈቅድም ነበር፡፡ ነገር ግን ወደፊት የሚታሰብ ተብሎ ነበር የተሰጠኝ፡፡ ከዚያ በተጨማሪ የሚሰጠው ሁለት ሰዓትም ታሳቢ ሆኖ ነበር፡፡ ልጄ አንድ ዓመት ከሞላው በኋላ ቀጣሪ ድርጅቴ ለአንድ ወር ስልጠና ሙሉ ወጪዬን ሸፍኖ ውጭ ሀገር ሊልከኝ ወሰነ፡፡ እኔ ግን ሕጻን ልጄን ትቼ አልሄድም አልኩ፡፡ ተጠርቼም “እናትሽ እና ባለቤትሽ እንዲሁም ሞግዚት አለሽ፣ በልጅ ምክንያት ወደኋላ መቅረት የለብሽም!” ተብዬ ተመከርኩ፡፡ መንግስታዊ ያልሆኑ (አለማቀፍ ኤንጂኦዎች)፣ የመንግስት ድርጅቶች እና የግል ኩባንያዎችም ካሉ ሕጉን ተፈጻሚ በማድረግ የሴቶች መብት መከበር ላይ አስተዋጾ ለሚያደርጉ ቀጣሪዎች ትልቅ አክብሮት አለኝ!

ይሁን እና ይሄ ብዙ ቀጣሪዎች ጋር ተፈጻሚ እንዳይደለ እናውቃለን፤ በተለይ ለትርፍ የተቋቋሙ ድርጅቶች ምንም እንኳን የሰራተኛ ቅጥር መተዳደሪያ አዋጁ የሚመለከታቸው ቢሆንም ተፈጻሚነቱን ማንም እየፈተሸው አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ እርጉዝ ሴት አልቀጥርም ለሚሉ አስረጋዝ ቀጣሪ ወንዶች “ፍሬው ያማረ ዘር እንዲበዛለት፣ አባት ደስ ይለዋል ልጅ ሲወለድለት…” የሚለውን ዜማ እንዴት ያዩታል? እንዴ ደስታ እኮ ሙሉ የሚሆነው ከደስተኛ እርጉዝ ሴት በሚገኝ ልጅ እንጂ ከተገፋች ሴት በሚገኘው አይደለም! ለማንኛውም ይሄን ጉዳይ ግን እናስብበት፣ እናውጠንጥነው! የጄንደር እኩልነት እርጉዝ ሴቶችንም ያካተተ መሆን አለበት! ቀጣሪ እና አባት የሆናችሁ ወንዶች ደግሞ ደስታችሁ ሙሉ እንዲሆን ያስረገዛችኋት ወይም ሌላው አቻ ወገናችሁ ያስረገዛትን ሴት መብት ጠብቁላት! ያኔ ማድጋችሁም ሙሉ ይሆናል! ለዛሬ ጨርሻለሁ ስል ያልተቋጨውን ውይይት (ጭውውት፣ ክርክር) ለመጨረሽ ይረዳን ዘንድ ሀሳብቻሁን በጉጉት እየጠበቅሁ ነው!

የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

1 thought on “እርጉዟን ማን ይቅጠራት!?”

  1. ሰላም፡
    በነገራችን ላይ ጥሩ የውይይት ርዕስ ነው፡፡ እኔ ሚገርመኝ አንዳንድ ወንድ አለቆቻችን፣ ወንድሞቻችን፣ ባሎቻችን አንዳንዴ ሲናገሩ ወይም ውሳኔ ሲያስተላልፉ የኛ እናትነት ላይ እነሱ የነበሩበት፣ያሉበት አይመስሉም፤ ይረሱታል’ንዴ? ወደ ጉዳዩ ስመለስ (እናላችሁ ነው ያልሽው እኔም አልኩ) ስለዚች ብቁ ሴት ብቻ ሳተኩር የወሊድ ፍቃዱም ይገባታል ስራውም ይገባታልም ያስፈልጋታልም ፡፡ ምናልባት ለሁለቱም ሚዛናዊ ለመሆን ብሞክር በዚህ አሁን እኛ ባለንበት ዘመንኮ ስራ ከየትም ቦታ መስራት ይቻላል ለስራው አስፍላጊውን (ላፕቶፕ፣ ዋይፋይ/ዳታ ፓኬጅ እና ሌሎችም) ቢያመቻቹ ጊዜዋን አመቻችታ/አብቃቅታ የመስራት አቅሙ አላት ምክንያቱም ሴት ናት፡፡ አመሰናለሁ!!!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *