አግብታለች?

ስኬታማ ሴቶች የሆኑትን የሆኑት ብዙ ወድቀውና ተነስተው ነው! ለነገሩ ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ ወንዶችም ጭምር፡፡ የእኔ ነገር በቀላሉ ሰዎች ብዬ እኮ ማጠቃለል እችል ነበር አይደል! ግን ማውራት የፈለግኩት ስለስኬታማ ሴቶች ገመና ነውና ነው፡፡ ወንዶች ስኬታማ ሲሆኑ ጎበዝ ነው፣ ባለሀብት ነው፣ ታድሎ፣ ከምን ተነስቶ ይሆን እዚህ የደረሰው፣ ወዘተ የመሳሰሉት እሱና እሱ ላይ ያተኮሩ አስተያየቶች እና አድናቆቶች ሲሰጡ ከመስማት ያለፈ ብዙም ስለ እሱ (ስለስኬታማው ሰውዬ) ግላዊ ማንነት ገፋ ተደርጎ ሲጠየቅ ወይንም ሲወራ አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ ቢጠየቅም ለአመል እንጂ ያንን ያህል እርቀት አይኬድም፡፡ 

ዛሬ ብሶት የሚመስል ነገር ነው የምጽፍላችሁ፤ የምር ሆድ እየባሰኝ ነው፤ ለነገሩ ብሶ ሲያበቃ ይወጣልኛል ግን እስከዚያ እስቲ ትንፍስ ልበለው ብዬ ነው ለጽሑፍ የማበቃው፡፡ ምን ሆነ መሰላችሁ፤ አንድ የታዘብኩት ነገር እኛ ሴቶች በጣም ብዙ ጥሩ ስነምግባራት እንዳሉን ሁሉ መሻሻል ያለባቸው ጥሩ ያልሆኑ ወይም በእኔ አተያይ ብልሹ ስነምግባራት አሉን፡፡ ተሳስቼ ከሆነ ካነበባችሁ እና ከጨረሳችሁ በኋላ ይቅርታ እንድታደርጉልኝ ከወዲሁ እጠይቃችኋለሁ!

ነገሩ እንዲህ ነው፤ ጥቂት የማይባሉ ሴቶች ያውም እራሳቸውም ስኬታማ የሚባሉ ሴቶች ሌላዋን ስኬታማ ሴት የበለጠ ግለ-ታሪኳን ለማወቅ ከመጓጓታቸው የተነሳ “አግብታለች? ወልዳለች?” የሚሉትን ጥያቄዎች ይጠይቁኛል፡፡ እንደዚህ ያለውን ጥያቄ የሚጠይቁኝ ደግሞ አብዛኞቹ እነሱ አግብተው ልጅ የወለዱቱ ናቸው፡፡ ይሄ ነገር ከምን የመጣ እንደሆነ የሚያውቅ እና የሚያስረዳኝ አለ? እኔ አንድ የሚገባኝ ወይም የምጠረጥረው ነገር አለ፡፡ ይህም ምን መሰላችሁ አንዲት ሴት ካገባች እና ከወለደች ሚስት ሚስት እና ልጅ ልጅ ብቻ የመጫወት ሚና ስለሚኖራት የስኬት ማማ ላይ ለመውጣት አቅም አይኖራትም ብሎ መደምደም ያውም ከወንዶች ሳይሆን ከራሳችን ከሴቶች የመጣ እራስን አሳንሶ የመገመት የበታችነት ስሜት ነው አራት ነጥብ! ትንሽ ስሜታዊ ሆንኩኝ መሰለኝ! ተደጋገመብኝ እና እኮ ነው፡፡

በዚህ ብቻ የሚያቆም መሰላችሁ? ስኬታማዋ ሴት እንደ አጋጣሚ ሆኖ ትዳሯ የፈረሰ ከሆነች ቀድሞ የሚነገረው እሱ ነው! በዚያ ላይ ቀድመው እያወቁት ለማረጋገጥ ይሁን ወይም ለማናውቀው ለማሳወቅ “ተፋታለች አይደል!?” የሚሉ አስተያየቶች ከተቻለ በ”ታሳዝነኛለች!” ታጅቦ ይነገራችኋል፡፡ ãረ ወየው የት አለም ላይ ይሆን ተንጠልጥለን የቀረነው!? ሲጀመር ስኬት እና ግላዊ ሕይወት ለየቅል ሆነው ሳሉ አንደኛው ሌላኛውን ለማደብዘዝ ለምን አስፈልጎ ይሆን! ደግሞስ ማግባት እና መፋታት የሥራ ስኬት መገለጫ ሆነው መቅረባቸው ለምን ይሆን!? ይሄ ነገር ከእኛ ሀገር ውጭ ባሉት ዓለማት እንደዚህ የተዛዘለ ይሆንን?

ለነገሩ ጥግ ጥጉን ከምሄድ ለምን ፍርጥርጥ አላደርገውም፤ ያው መጨረሻ ላይ ይቅርታ ስጡኝ ብዬ የለ! እኛ ሴቶች (አብዛኛዎቻችን-ሁላችንም አይደለንም) ኃይለኛ ያለመደናነቅ ሕመም (ሲንድሮም) ተጠቂዎች ነን! እኛ የማናውቀው ነገር ግን በእጅጉ መታከም ያለበት ያለመደናነቅ ስቃይ ያለው ሕመም! አንዲት ስኬታማ ሴት ፊት ለፊታችን ስትቆም ወይም መድረክ ላይ ቆማ ንግግር ስታደርግ ወይንም በሌለችበት ስሟ ከፍ ብሎ ሲነሳ በጣም ደስ ሊለን እኮ በተገባ ነበር! ስኬትን ተጎናጽፋ ስታሳየን፣ መሆንን ስታሳየን አርአያ አገኘን ማለት እኮ ነው! “ሴቶች ይችላሉ!” የተባልነው እኮ እንደእነዚህ ያሉ ሴቶች ባስመዘገቡት ስኬት እና ድል ነው! 

በነገራችን ላይ በእርግጠኝነት የማወራው አንድ ነገር አለ፡፡ ሴት ስለሆንኩ እና በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ስለኖርኩ አውቀዋለሁ፡፡ እንዲያው ከማጠቃልለው በፐርሰንት ስገልፀው 95% የምንሆነው ባል ያገባነው ጠይቀን (Propose አድርገን) ሳይሆን ተጠይቀን ነው፡፡ በተለይ ትዳሩን በጉጉት የምንጠብቀው ከሆነ ፕሮፖዝ ስንደረግ በደስታ ፈንጥዘን እና አንብተን ነው የምንቀበለው፤ እኛ ምን ያህል ብንወድና ዝግጁ ብንሆን ፕሮፖዝ የማድረግ ባህሉ ስላልተሰጠን፡፡ እናም ልክ ጥረን ግረን ወጥተን ወርደን ያመጣነው ስኬት ማድረጉ ብዙም አላምንበትም፡፡ እኔ ትዳር እና ልጅ የእግዚአብሔር ፈቃድ ናቸው ብለው ከሚያምኑ ስለሆንኩ ግላዊ አመለካከቴን እዚህ ላይ እንደ ሐቅ ማስቀመጥ አልሻም፡፡ ለማለት የፈለግኩት “አግብታለች? ወልዳለች? ተፋትታለች?” የሚሉት ጥያቄዎች ስኬታማ ከሆኑ ሴቶች ጋር ምንም አያገናኛቸውም! ግለ-ታሪካቸውን ለእራሳቸው እንተውላቸው! ምናልባት ወሳኝ ኩነት ሄደን ጥናት ብናደርግ ፍቺ የሚፈፀመው ሴቷ ስኬታማ ስለሆነች ነው የሚል ድምዳሜ ላይ እንደማንደርስ ከማውቃቸው ፍቺዎች ተነስቼ መገመት አያቅተኝም፡፡

በዚያ ላይ ይሄ ነገር እኮ ሄዶ ሄዶ የወንዶችንም ስነ-ልቦና የሚነካ ጉዳይ ነው! በከተማችን በኃይለኛ የሚናፈሰው አንዱ የአደባባይ ምስጢር ምን መሰላችሁ? “ወንዶች ስኬታማ፣ የተማረች፣ የነቃች፣ እራሷን የቻለች፣ በእራሷ የምትተማመን…ወዘተ ሴት ለትዳር ይፈራሉ!” ይባላል፡፡ ይሔ ክብረ-ነክ አስተሳሰብ ነው! አባት እኮ ነው ሴት ልጁን አቆፍጥኖ የሚያሳድግ፤ ልክ እናት እንደምታቆፈጥነው! ታላቅ ወንድም እኮ ነው እህቱ እንዳትሰናከልበት እግር እግሯ ስር እየተከተለ የሚገራት! ሚስቱን ያስተማረ፣ እንድትማር እና እንድትበቃ እገዛ ያደረገ ባል ቤት ይቁጠረው! መቼስ በእራሷ የማትተማመን፣ የማትማር፣ መብቷን የማታውቅ፣ ከእኔ ከምትጠብቅ የእራሷን ሥራ ሰርታ እራሷን የምትሞላ ሴት ለትዳር አልፈልግም ብሎ መስፈርት ያወጣ ወንድ ካለ እኔ እቀጣለሁ፡፡ ãረ የእራሴው ባለቤት በሴት ልጅ መብቃት የሚያምን ቋሚ ምስክር ነው!

በዚህ አጋጣሚ ስኬታማ ሴትን የምታደንቁ፣ አርአያ የምታደርጉ፣ እራሳችሁም ለስኬታችሁ የምትሰሩ፣ የስኬታማዋን ግለ-ታሪክ ሳይሆን ለስኬት ያበቃትን ታሪክ ለማወቅ የምትታታሩ ሴቶች ትክክለኛው መንገድ ላይ ናችሁ! መንገዳችሁን አልጋ በአልጋ ያድርግላችሁ! 

እናንተ ሌላኞቻችሁ ለዛሬ ጽሑፌ መነሻ የሆናችሁኝ ስኬታችሁን ማጣጣም ያቃታችሁ፣ ከሌላዋ ስኬታማ ሴት ጋር ያልሆነ ፉክክር (ውድድር) ውስጥ የገባችሁ፣ እናንተ የቆማችሁበት ቀጠና ብቻ ስኬት የሚመስላችሁ፣ የሚደነቀውን ከማድነቅ ይልቅ እፀፅ እየፈለጋችሁ እራሳችሁን የምታረጋጉ እና ሌሎችን አጃቢ ለማድረግ ባህርያችሁን ለማጋባት የምትጥሩ ሴቶች ልቦና ይስጣችሁ!

እንደ ማጠቃለያ መናገር የምፈልገው እስቲ አንዳንዴ ለእራሳችን ጊዜ እንስጥ እና እራሳችን ላይ ክትትል እና ግምገማ(Monitoring & Evaluation) እንስራ! እድገት በእድሜ፣ በእውቀት፣ በአስተሳሰብ (በተለይ በስሜት ብስለት)፣ በልምድ፣ በስነምግባር፣ በቀናነት፣ በአቅም (በገንዘብ) ተመጣጥኖ እና ተከሽኖ እንዲዋሀደን ሳናሰልስ እንጣጣር፤ እድገታችን ግንጥል ጌጥ እንዳይሆን! እስከዚያም የበቁትን ሴቶች እናድንቅ!  ለዛሬ ጨርሻለሁ!

የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

Share with your circle!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *