አግቢ!

Thank you so much for giving me advice that i did not ask for [or want]...

የእኛ ማህበረሰብ መቼስ ደግ ነው! ይሄ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ አንዳንዴ ግን ደግ የማይሆንባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ እንደማህበረሰብ ነው የማወራው እና በጅምላ ጭፍጨፋ እንዳይመስልብኝ ልጠነቀቅ ፈልጌ ነበር፤ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ አማረጭ የለኝም፡፡ ጉዳዩ ምን እንደሆነ ከጽሑፌ ርእስ ሳይገባችሁ አይቀርም፡፡ እና የእኛ ማህበረሰብ ደግነት ሳያንሰው “አግቢ!” የሚለውን አባባል እርግፍ አድርጎ ቢተወው እኔ በበኩሌ ደስ ከሚላቸው አንዷ ነኝ፡፡ አንዳንዶቻችሁ በተለይ የምታውቁኝ “አግቢ!” የሚለው ምክር ይሁን ትእዛዝ እንደማይመለከተኝ በማሰብ ወይም በማብሰልሰል ላይ ናችሁ አይደል!? አይገርማችሁም እኔ በዚህ ገጽ ላይ የምጽፈው ለእራሴ ብቻ ሳይሆን ለሚመለከተው ሁሉ ነውና ከወዲሁ እሮሮዬን አንዳታጣጥሉብኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ፤ ከሰላምታ ጋር!

“አግቢ” አንዱ ትህዛዝ መሳይ ምክር ይሁን እንጂ ለሴቷ አነቃቂ ሳይሆን አንዳንዴ አሰቃቂ ሊሆን እንደሚችል ማህበረሰቡ አልተረዳም፡፡ ሴት ልጅን በተመለከተ በግላዊ ጉዳዮቿ ላይ በአብዛኛው ሰው በያገባኛል ስሜት እራሱን የሰየመ ይመስለኛል፡፡ ደግሞ እኮ “ያገባኛል” በሚያስብሉ እና ከሸክሟ በላይ በሆኑት ጉዳዮች ለምሳሌ እንደ ጥቃት እና ትንኮሳ ላይ አግብቷቸው የመፍትሔ አምጪ አካል ቢሆኑ ወግ ነውና ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ለነገሩ እኮ የማህበረሰቡ ጣልቃ ገብነት በሴቷ ሕይወት የበዛ ይሁን እንጂ ወንዱም በተወሰነ መልኩ አይቀርለትም፡፡ በሴቶች ላይ መበርታቱ ከፋ እንጂ፡፡ ለነገሩ ይሄ የአግቢ ምክር በሴቷ ላይ የሚበረታው እንደውሀ ቆጣሪ በተገጠመላት (ነው በተገጠመባት?) የእድሜ እርከን ምክንያት መሆኑ እሙን ነው፡፡ ግን ደግሞ “አግቢ!?” ስለተባለች ብቻ ያገባች ወይንም ባል ማግባትን እንደ ግብ ቆጥራ ያገባች ካለች እስቲ እጅዋን ታውጣ!? መቼስ ባል በገንዘባችን እንደምንገዛው ቁሳቁስ ተገዝቶ አልያም ተፈጥሮ እንደለገሰን የመልካም ቅጠል ዘር ተሸምጥጦ የሚመጣ ግሁዝ አይደል!

በነገራችን ላይ እኔም “አግቢ” የሚለው ምክር ሰለባ በነበርኩ ጊዜ የታዘብኳቸው ገጠመኞች አሉኝ፡፡ በዚህ ቃል እንማረር የነበርን ኮበሌዎች ማህበረሰቡ በጣም ስለሚያማርረን “ኑሯችንን የሚኖሩልን አይመስሉም? ምን አገባቸው? ለእራሳችን አንሰን ነው የሚመክሩን? ማን ምከሩን ብሎ ጠየቃቸው…ወዘተ” እያልን ስናጉረመርም እንከርምና ልክ ከመሀከላችን ልክ ሲያገቡ ያንን ሁሉ ቃላቸውን እና ምሬታቸውን ይረሱና  እዚያው ማህበረሰብ ማጥ ውስጥ ገብተው “አግቢ፤ አግቡ!” ማለታቸው ሳያንሳቸው “ዋ ተናግሪያለሁ!” የሚለውን ማስፈራርያ ያክሉበታል፡፡ እናንተ እንደዚህ የምትሉ እህቶቼ ሆይ የነበሩበትን መርሳት፤ የተጸየፉትን እና የጠሉትን አጉል ባህል መቀላቀል አስጸያፊ ባህርይ ነው፡፡  በማንም ባያምርም በእናንተ ግን የበለጠ አያምርም፤ “አግቢ” አትበሉ እሺ!?

ትዳር ጥሩ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ እኔ በትዳር ሕይወት ውስጥ ከገባሁ 18 ዓመቴ ነው፡፡ በትዳር ሕይወቴ ከትዳር በፊት ከነበረኝ ሕይወቴ ባልተናነሰ ደስተኛ ነኝ፡፡ ነገር ግን “አግቢ” ስለተባልኩ ተሯሩጬ የፈጸምኩት ውል ሳይሆን እግዚአብሔር የምወደውን እና ስለወደደኝ ለትዳር የጠየቀኝን ሰው ስላገናኘኝ ነው፡፡ እዚህ ላይ ልብ በሉ፤ “የጠየቀኝ” ነው ያልኩት፡፡ በጓደኝነት ምንም ያህል ጊዜ ብንቆይ እኔ ማግባት ብፈልግም እንኳን “እንጋባ!” ብዬ መጠየቅ የማልችልበት ማህበረሰብ ውስጥ ነው ያለሁት፤ ስለዚህ ተጠይቄ ነው ያገበሁት፡፡ ይህ ማለት ምናልባትም 95% (100% ላለማለት) ሴቶች ለጋብቻ ካልተጠየቅን እኮ አናገባም! ምንም ያህል ብንማር፣ ብንሰለጥን፣ በኢኮኖሚ ብንልቅ እና ቁመናችን ቢያምር በተለይ በእኛ ዘመን  የነበርነው የዚያን ጊዜ ወጣት ሴቶች የአሁኑ ጎልማሶች ወንድ ልጅን ለትዳር አንጠይቅም፡፡ የአሁኖቹም ቢሆኑ “የተሻሻለ ዘመን ነው” ይባል እንጂ በየፊልሙና ቲክቶኩ የምናየው ወንዶቹ እየተንበረከኩ ሲጠይቋቸው ነው፤ የተንበረከከች ሴት አጋጥማኝ አታውቅም፡፡ እናም ማህበረሰቡ ይህንን እውነታ እያወቀ ነው “አግቢ” የሚለን፡፡ እኔ በበኩሌ ይህንን አሳቢ ወይንም ለጋስ ምክር አልለውም፤ ጭፍን ምክር እንጂ፡፡ በዚያ ላይ ያለማወቅ እንጂ “ምከሩኝ!” ተብሎ ሳይጠየቅ መምከርም እኮ አግባብ አይደለም፡፡ እኔ ይህን አልኩ፤ እናንተ ግን የፈለጋችሁትን የማለት ማህበረሰባዊነት መብታችሁ የተረጋገጠ ነው፡፡

ማህበረሰባችን ሆይ! እስቲ ሴትን ልጅ ለመረዳት እና ለመርዳት ማሰብያ ፣ማሰላሰያ እና ማገናዘብያ ጊዜ ውሰዱ! እሷም እኮ ሙሉ ሰው ናት! የሚያስፈልጋትን እና የማያስፈልጋትን ታውቃለች፡፡ ለምሳሌ ትዳር ብትፈልግ ማድረግ የሚኖሩባትን ውሱን (ይሰመርበት) ነገሮች ታውቃቸዋለች፡፡ ያው የመጨረሻው ቁልፍ የወንድየው “ታገቢኛለሽ ወይ?” የእንብርክክ ይሁን የቁም፣ የቴክስት ወይንም የምልክት አልያም ደግሞ በሆነ መንገድ የሚገለጽ ቁልፋዊ ጥያቄ ስለሆነ፡፡  

ስለ ሴት ስብእና ግን ማህበረሰባችን ማወቅ ያለበትን ሳልናገር ባጠቃልል ቅር ይለኛል፡፡ ሴት ልጅ ለአቅመ ሔዋን ደረሰች ወይንም በሰለች የሚባለው በእራሷ እርግጠኛ ስትሆን፤ በእራሷ እና በችሎታዋ ስትተማመን፣ ጥንካሬና ደካማ ጎኗን ለይታ ስታውቅ፣ በእራሷ የምትቆም እና በሌሎች ማረጋገጫ ጥገኛ የማትሆን ስትሆን…ወዘተ ነው፡፡ ይሄ በጥቅሉ ነው፡፡ ስብእናን ( Personality) ስንመለከት  ሁላችንም ሰዎች (ወንድ እና ሴት) የየራሳችን ስብእና አለን፡፡ በስድስት የስብህና ዓይነቶች እንደምንመደብ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ እነዚህም  አልፋ፣ ቤታ፣ ጋማ፣ ኦሜጋ፣ ዴልታ እና ሲግማ ይባላሉ፡፡ አንድ ለየት የሚያደርገን ወንዶች ላይ ዜታ የሚባል ተጨማሪ ስብእና እንዳለ ጥናቱ ያሳያል፡፡ እያንዳንዱን የስብእና ዓይነት እናንተው አንብባችሁ ትደርሱበት ዘንድ የቤት ስራ ይሁንልኝ፡፡ እንግዲህ ይህንን የስብእና ነገር ያነሳሁበት ምክንያት ሁሉም ሴቶች ወይንም ሁሉም ወንዶች አንድ ዓይነት ሰብእና የሌለን መሆናችንን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መጀመርያ የራሳችንን ስብእና ፈልገን እናግኝ፤ “ሌሎችን መካሪ” ከመሆናችን በፊት፡፡  ከርእሰ ጉዳያችን ጋር ስናገናኘው ለምሳሌ አልፋ ባህርይ ያላት ሴት በነጻነቷ የማትደራደር፣ በራሷ የምትተማመን፣ ቆፍጣና፣ ሕልመኛ፣ ሰው በቀደደላት የማትገባ፣…ወዘተ ናት፡፡ የዚህ ዓይነት ስብእና ያላትን ሴት ታድያ ለመምከር ምን ያህል ብቁ ነህ/ ነሽ/ ናችሁ!?

ከማጠቃለሌ በፊት ለወጣቷ ሴት ምክር ሳይሆን የማስታውስሽ ነገር አለ፤ “አግቢ!” በዚህ ምድር ላይ የመጣሽበት ዓላማ አለሽ (The purpose of your life!)፡፡ ያው ታውቂዋለሽ፤ ዓላማሽን ለማሳካት የሚያስችልሽ ደግሞ በጊዜ ቀመር የከፋፈልሽው ግብሽ ነው፡፡ እናም ስኬታማ የሚያደርግሽን “ግብ አግቢ!”  ለምሳሌ “በዚህ ዓመት ኮሌጅ እገባና በሚቀጥለው እጨርሳለሁ!” ብለሽ ከሆነ ትምህርትሽን ወጥረሽ በመያዝ ጨርሺ፤ አንድ ግብ አገባሽ ማለትም አይደል! “በዚህ ጊዜ ስራ እሰራለሁ ወይንም ቢዝነስ እሰራለሁ ከዚያም ለኑሮዬ የሚያስፈልገኝን ገቢ አገኛለሁ እናም በአቅም እደራጃለሁ!” ይህም ግብ ነውና አግቢ! ብቻ በሕይወት ስትኖሪ ዓላማ አለሽ እና ዓላማሽን የምታሳኪበትን ግቦችሽን አግቢ! እነዚህ እንደ ምሳሌ የጠቀስኳቸው ጥቂቶቹ እና በራስሽ ጥረት ልታሳኪያቸው የምትችያቸው ናቸው፡፡ ከዚያ ውጭ ያለውን የ “አግቢ” እና ተመሳሳይ ማህበረሰባዊ ልማድ የወረራቸውን አባባሎች ማንም ስለነገረሽ እና ስለመከረሽ ሳይሆን የአንቺ ልብ የሚልሽን እና ማድረግ የምትችይውን ብቻ አድርጊ! እልሻለሁ!  ማለቴ እላችኋለሁ! ለዛሬ ጨረስኩ!

Written by: Fitsum Atenafework Kidanemariam

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *