አይመቸኝም!

 “እዬዬም ሲደላ ነው!” ያሉት እነዚያ የድሮ አበዎች ምን ያህል እንደቀደሙን ሳስብ ግርም ይለኛል፡ ከምር ግን የድሮ ዘመን ተረተኞች ትንቢተኛ አይመስሏችሁም!? ይሄ ተረት እኮ ጥግ ድረስ የሄደ ነው፡፡ እዬዬ ከስሜቶች አንዱም አይደል! እና ካልደላን ስሜቶቻችንን እንኳን አናዳምጥም እያሉን ነው፡፡ በዚያውም ይሄ አባባል የሁነቶችን ለውጥ እና ለለውጥም መዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ማሳያ ይመስለኛል፤ ሲመቸን መመቻቸት ሳይመቸን መቀበል አልያም መቀየር እንደሚገባን፡፡

እኛ ግን አሁንም “አይመቸኝም!” በሚለው አባባል ውስጥ ድብብቆሽ እየተጫወትን ነው፡፡ ድሎት ላይ ነን ማለት እኮ ነው፤ ግን ነን እንዴ!? ለዚህ የአይመቸኝም አባዜ ብዙ ገጠመኞች እና ወጎች ቢኖሩኝም ግን ዛሬ ርእስ አድርጌ እንድጽፍ ያስታወሰኝ ከአንዲት ለረዥም ጊዜ ከተለያየን በኋላ በአጋጣሚ ያገኘኋት የቀድሞ ጓደኛዬ ጋር የነበረኝ የቡና ላይ ወግ ነው፡፡ ይህቺ ጓደኛዬ ተቀራራቢ ከነበረው አስተዳደጋችን ባሻገር ብዙ የምንጋራቸው እሴቶች ስለነበሩን በዚያው መንፈስ ነበር ከእሷ ጋር የማሳልፈውን ጊዜ አስቤ እና ናፍቄ ያገኘኋት፡፡ እኛ ሰዎች ደግሞ በአኗኗራችን፣ በብስለታችን እና በተለያዩ ምክንያቶች እሴቶቻችንም ተቀያያሪ ኖረዋል! በእርግጥ አንዳንዶች ድሮም ሆነ ዘንድሮ ስታገኟቸው ምንም ለውጥ አታዩባቸውም፤ ወይንም በተሻለ ብስለት ልታገኗቸው ትችላላችሁ፤ ታድለው! 

ታድያ ይህቺ ጓደኛዬ ድሮ ከማውቃት ማንነቷ የተወሰኑ አሉታዊ ለውጦችን ተላብሳ ነበር ያገኘኋት፡፡ መለወጥ እኮ ግን ተፈጥሯዊ ነው፤ ግን “ለውጡ ምን ዓይነት ነው?” የሚለው ነው የወጌ መነሻ፡፡ በምሳሌ ላውጋችሁና ካዘዝነው ማክያቶ ይጀምራል፤ የመጣልን ማክያቶ በነጭ የቡና ሲኒ ነበረና አስተናጋጇን ጠርታ “ውይ እኔ ማክያቶ መልኩን እያየሁ ካልጠጣሁ አይመቸኝም! በሌላ ሲኒ ይቀየርልኝ!” አለቻት፡፡ ከመነሻው ያልተነገራት አስተናጋጅ ምላሽ ፈጣን ነበር፤ ” የቡና እና የማክያቶ ሲኒዎቻችን አንድ ዓይነት ነጫጭ ናቸው፤ ምናልባት የሻይ ብርጭቋችን አንቺ የምትፈልጊው ዓይነት ስለሆነ በእሱ ገልብጬ አስሙቄ ላምጣልሽ!?” ብላ ላቀረበችው ጥያቄ አዎንታ የሚመስል ነገር ስላገኘች  የጓደኛዬ ማክያቶ በሻይ ብርጭቆ ተደርጎ ዶሮ በጋን ሆኖ መጣላት፡፡ “ውይ ይሄማ ለመጠጣት አይመቸኝም” አለችና እንደ መቆጣት ብላ መጠጣቱንም ተወችው፡፡ ባትፈልግ ይሆናል፡፡ ወይም እንደ ልምዷ ነው!

ከዚያም በደራው ጨዋታችን መሀከል ስልክ ተቀብላ በቁጣ ስሜት ካናገረች እና ከዘጋችው በኋላ “ሀገር ልብስ አዝዤ አይደርስም እያለኝ እኮ ነው፣ ሰርግ አለብኝ ብዬ ደጋግሜ አስጠንቅቄው ጠላፊው ስላመመው የሚደርስ አይመስለኝም ነው እኮ የሚለኝ፣ እዚህ ሀገር እኮ በቃ ቀብድ እስኪቀበሉ አደርሳለሁ ይላሉ ግን…” አለች ቀዩ ፊቷ በንዴት ቲማቲም እየመሰለ፡፡ እውነቷን ነው አገልግሎት ሰጪዎች ጋር ቀጠሮ ያለማክበር የተለመደ ችግር ነው፡፡ እናም ተለዋጭ ሀሳብ ያቀረብኩ መስሎኝ “ካልሆነ ታድያ ከቁምሳጥንሽ ለሰርግ የሚሆን ሌላ ሀገር ልብስ ምረጪና ልበሺ!” ከማለቴ “ውይ እኔ ከዚህ ቀደም ሌላ ሰርግ ላይ የለበስኩትና የታየ ሀገር ልብስ ለሌላ ሰርግ መልበስ አይመቸኝም” አለችኝ፡፡

ድሮ ሳውቃት እንደዚህ ያልነበረችውን ጓደኛዬን ምን ቢያስነኩብኝ ነው ብዬ (በሆዴ) ዝም አልኩ፡፡ የእሴት ለውጥ ይሏል ይሄ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ጽሑፌ የእራሴን ተሞክሮ አስታወሰኝ፡፡ በተለይ ድሮ ድሮ የዓመቱ የሠርግ ልብስ የሚባል አዘጋጃለሁ፤ ከዚያ ደጋግሜ ከመልበሴ የተነሳ አንድ ጊዜ አንድ ጓደኛችን ሰርጉ በተከታታይ ለሁለት ቀን  ነበረና ሌላኛው ጓደኛችን አሳስቦት “ፍፁም ሁለቱንም ቀን አንድ ልብስ ልትለብሺ ነው?” ያለኝን መቼም አልረሳውም፡፡ እና ያን ጊዜ መቀየሬ ትናንት የተጨፈረበት ሆኖብኝ እንጂ የታየሁበት መሆኑ ለእኔ አሳሳቢ አልነበረም ፡፡

ብቻ “አይመቸኝም!” የሚለውን ብኢል የሚያበዙ ብዙ ሰዎችን አውቃለሁ፡፡ በሥራ ላይ እያለሁ አንዳንድ የሥራ ባልደረቦቼ በተለይ ወንዶቹ ለምሳ የሚያወጡትን ከገቢያቸው ጋር ያልተመጣጠነ ወጪ በማየት እና በልተውም ከጤናቸው እና ከገንዘባቸው አኳያ የሚያሳዩትን ምሬት በመስማት “ለምን ምሳ ከቤታችሁ ይዛችሁ አትመጡም?” ስላቸው ብዙዎቹ የሚመልሱልኝ “የቀዘቀዘ ምሳ አይመቸኝም፣ ባደረ ወጥ ስለሚፈተፈት ያደረ ወጥ አይመቸኝም፣ ምሳ ተሸክሞ መምጣት አይመቸኝም…” ብቻ ምላሻቸው አይመቸኝም ይበዛበት ነበር፡፡

እንግዲህ ወጪውም ሳይመች ይዞ መምጣቱም ሳይመች አስቡት! የሆነ ነገር ለመሥራትም ስንፈልግ ብዙዎቻችን የምንመርጠው ብቻችንን መሥራት ነው፡፡ “ከሰው ጋር መሥራት አይመቸኝም ምክንያቱም ያጓትቱብኛል፣ ሐሳቤን ያጣጥሉብኛል፣ ሐሳቤን ይቀሙኛል፣ …ወዘተ”፡፡ ውጤታማ ያለመሆናችን ዋናው ምክንያት እንዲያውም ይሄ “አይመቸኝም!” የምንለው ጎታች ወጋችን ይመስለኛል፡፡ ደግሞ እኮ በአናቱ የመጣ ነገር መሆኑ ነው፤ ዘመን ያመጣው በሉት፡፡ ድሮ ድሮ ዛሬ ላይ በማይመቹን እውነታዎች ተመቻችተን እና ተረጋግተን ኖረን ነበር እኮ!

እስቲ በተለይ በእኔ ዘመን የኖራችሁትን ወደኋላ ልመልሳችሁ እና ላስታውሳችሁ፡፡ ለምሳሌ ስንቶቻችን ቤት ነው የምግብ ማቀዝቀዣ ፍሪጅ የነበረው? እስቲ ስንቶቻችን ቤት ነበር ወጥ በየቀኑ የሚሰራው? በትልቅ ሸክላ ድስት አንዴ የተሰራው ወጥ ምቅ እየተደረገ ለሁለት ሦስት ቀን ሲበላ ያውም እየጣፈጠን ነበር እኮ! በእርግጥ ያን ጊዜ ባይጣፍጥም አርፎ መብላት ግድ ይላል፡፡ ባለመቀመጫው መጸዳጃስ ስንቶቻችን ቤት ነበር? ግን ተጠቅመንበታል፤ ያው እንደ ጊዜው ነውና! ታድያ በዚያ ጊዜ የነበርን ሰዎች ነን ዛሬ ላይ ብዙ ነገር የማይመቸን፡፡ ሰዎች አይደለን፤ እንረሳለና! እኔ ምቾት አይገባንም የምል አይደለሁም፡፡ የምንሠራው፣ የምንጣጣረው እኮ በድሮ በሬ ለማረስ አይደለም፤ የተሻለ ኑሮ ለመኖር እንጂ፡፡ እናም ምክንያታዊ፣ አሳማኝ እና ልማታዊ የሆነ “አይመቸኝም!” ለእኔም፣ ለእሷም፣ ለእሱም፣ ለሁላችንም በጣም ይመቸናል! 

እኔ ደሀዋን ሀገራችንን አለማወቅ አለብን ባይ ነኝ፡፡ ብዙዎቻችን በተለይ ከተማ ተወልደን ያደግን እና በመስክ ሥራ ወይንም በተለያየ ምክንያት ወደ ገጠር ካልወጣን ሀገር ማለት አዲስ አበባ ብቻ ሳይመስለን አይቀርም፡፡ የሀገራችን አብዛኛው ክፍል ገጠር ነው፤ የእኛ ምቾት በፊልም ወይንም በቴሌቭዥን መስኮት ብቻ የሚታይበት፡፡ ለዚያውም መብራት ስለሌለ በጀነሬተር በሚገኝ ሀይል ካዩት ነው፡፡ እዚያ እኮ መጸዳጃ ቤት በስልጡኖቹ ገጠሬዎች ጓሮ በጉድጓድ ተቆፍሮ አልያም በየሜዳው የሚወጣበት፣ የት/ቤት ዴስክ ስለማይኖር ድንጋይ ለወንበርነት የሚጠቅምበት፣ ውሀ በቧንቧ ሳይሆን ከከብት ጋር እየተሻሙ ከጉድጓድ የሚጠጣበት፣ ከዚህ በላይ መቀጠል አይመቸኝም! ምክንያቱም ማድረግ በማልችለው ነገር ላይ ብዙ ማውራት ሆድ ያስብሰኛል፡፡

እና ይህንን ምሳሌ ያመጣሁት እኛ መመቻቸት ያለብን ከሀገራችን እና ከሕዝባችን የኑሮ እና የኢኮኖሚ ደረጃ እንጂ ላይ ላዩን (superficial) ባንሆን ለእራሳችንም ጤና ነው፡፡ ልብ በሉ እንደ ገጠሩ ሕዝባችን ሜዳ ላይ እንፀዳዳ፣ የጉድጓድ ውሀ እንጠጣ እያልኩ ደግሞ አይደለም፡፡ ነገር ግን ቢያንስ ሀገራችን እና ሕዝባችን ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት “አይመቸኝም!” የምናበዛባቸውን ቅንጦታዊ ነገሮቻችንን (ቁሳቁሶቻችንን) እናራግፍ እያልኩ ነው፡፡ ለራስም ጤና ነው!

በዚያ ላይ እኮ ሁላችንም “ኑሮ ተወደደ!” የሚለውን ነጠላ ዜማ በድርብርብ ዜማነት እያንጎራጎርነው ነው፤ ተወጥረናላ! ታድያ ከኑሮ ውድነት ጋር ” አይመቸኝም!” የሚሳለጥ ሀሳብ ይሆን? ከምር እናስብበት እስቲ፡፡ ወደ ቀድሞ ማንነታችንን እና እሴቶቻችንን ወደኋላ ጎራ በማለት፣ የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ በመቀበል፣ ትክክለኛ ማንነታችንን አመጣጥነን ሚዛናዊ ኑሮ መኖር እውነቴን ነው የምላችሁ እንዳይቆጨን ይረዳናል፡፡

እስቲ ቆም ብለን ከቀልባችን እንሁን እና በትክክል የማይመቸንን፣ የሚመቸንን እና ባይመቸንም ከመቀበል ውጪ መለወጥ የማንችላቸውን ነገሮች እንለይ፤ ያን ጊዜ የራሳችንን ኑሮ እራሳችንን ሆነን በመኖር እናጣጥመዋለን፡፡  ለይስሙላ ወይንም ላይ ላዩን “አይመቸኝም!” የምንላቸውን ነገሮች ሙሉ በሙሉ ባንተዋቸውም እንኳን እንቀንሳቸዋለን፤ ጤና ይሆነን ዘንድ! ለዛሬ ቋጨሁ!

Written by: Fitsum Atenafework Kidanemariam

Share on your page!

2 thoughts on “አይመቸኝም!”

  1. Tseganesh Getachew

    It is very interesting Fitsumye. Thank you for sharing!! Yaw yetinant yiresal, sewnetachin hormon yikeyral, lewtim yimetal. ya new zare hulun asresito aymechegnm miyasbilew….. gn eski enkensew, lesemim kebad new yemilew mikrshin enem likebelew.

    Thanks again for sharing!!!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *