አትተኙ!

እስቲ ስንቶቻችሁ ናችሁ “የሕይወቴ ቅኝት” የሚለውን መጽሐፍ ያነበባችሁ? ያላነበባችሁ እንግዲህ ተዋውሳችሁ አንብቡ ምክንያቱም ሁለተኛ እትም ለማሳተም “እቁብ ግቡልኝ?” ብዬ ጓደኞቼን በዚህ ዘመን አላስቸግርም፡፡ ድሮ የእኛ ዘመን፣ የእነሱ ዘመን ስንል አስር ወይንም ሃያ ዓመት ልዩነት እየፈለግን ነበር፤ ምክንያቱም ለውጦች አዝጋሚ (evolutional change) ናቸዋ፡፡ አሁን እኮ ዘመን ወደ ሳምንት ተቀይሯል መሰለኝ ባለፈው ሳምንት የነበረ ዛሬ ተለውጦ ታገኙታላችሁ፡፡ ነገር ሁሉ እንደቤት አስቤዛ ተለዋዋጭ ሆኗል፡፡ የዛሬ ሦስት ዓመት በኤውብ እቁብተኞቼ ድጋፍ አሳትሚያለሁ፡፡ እና ኑሮ ቀልብ ባሳጣበት እና አንባቢ በጠፋበት በዚህ ዘመን ወደ ማተምያ ቤት አልሄድም ለማለት ነው፡፡ ለማንኛውም መጽሐፌን ያነሳሁላችሁ ከዚያ ውስጥ አንዱን ሰበዝ መዝዤ ላወራላችሁ ፈልጌ ነው፡፡
በአንድ ወቅት ወጣት ሰራተኛ በነበርኩበት መ/ቤት ውስጥ አለቃ እና ምንዝር (የአለቃ ታዛዥ) ተከባብረው ብቻ ሳይሆን ተፈራርተውም ጭምር ነበር የሚኖሩት፡፡ የአለቃ ታዛዥ ያልኩት የበታች የምትለዋን ቃል ላለመጠቀም ነው፡፡ ምክንያቱም ያኔ የበታች ሰራተኞች እየተባልን ከምር ነው የምላችሁ እስኪበቃን ፈግተናል፡፡ በስራ ብቻ ሳይሆን ስራ ነክ ባልሆኑ ጉዳዮችም ጭምር፡፡ አሁን ወደ ጉዳዩ (ወደ ገደለው) ልመጣላችሁ ነው፡፡ ከላይ “ተፈራርተው” አላልኳችሁም? ይቅርታ ፈርተው ወይንም ፈርተን ነበር የምንሰራው በሚለው ይታረምልኝ፡፡ እንዴ ወንዶች አቻዎቻችን የሚያስፈራቸው ነገር እምብዛም በሌለበት የእነሱን መብት በፈሪነት መድፈር አግባብ አይደለማ! ግን እነማን ነበርን የምንፈራው? ለምንድን ነው የምንፈራው? ቆይማ በገጠመኝ አጅቤ ልንገራችሁ፡፡
እንደነገርኳችሁ ወቅቱ ያን ዘመን እና መ/ቤቱም የዚያ ዘመን ስመ ጥር እና ትልቁ መ/ቤት ነው፡፡ ለነገሩ የሰራሁባቸው ሁሉ ስመ-ጥር ስለሆኑ “ስለእኔ ነው የምታወራው?” ብሎ በስም አጥፊነት የሚከሰኝ መ/ቤት የለም፡፡ እና እዚያ መ/ቤት ኃላፊዎች ጎልማሶች የነበሩ ኮትና ሱሪ ለባሾች፣ የተማሩ የተመራመሩ(ይሄን እንኳን ለማለት ያህል ያልኩት ነው)፣ የተዳሩ፣ የወለዱ፣ የከበሩ( ግነት ያስፈልጋል ብዬ ነው!) (the c-suites) ነበሩ፡፡ ታድያላችሁ በአብዛኞቹ (ሁሉም ያለማለቴ ይሰመርበት) አዲስ ወጣት ሴት ሰራተኛ ወደ ክፍላቸው ስትመደብላቸው ደስ ይላቸዋል፡፡ እርግጥ ነው አዲስ ሰራተኛ ያልሰለቸው፣ ማደግን ሰንቆ የሚመጣ ነውና እንደልብ ማዘዝና ማሰራት ይቻላል የሚለው መንፈስ ስላለ ይሆናል፡፡ ይሄኛው ግን እንደ እሱ አይደለም፡፡ ቢሆንማ ኖሮ አዲስ ወንድ ሰራተኛም ይህንን ክራይቴርያ ያሟላል፡፡ ግን ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ ኃላፊዎቹ (አለቆቹ) ወጣት ሴት ይወዳሉ፡፡ በቃ ይወዳሉ አልኩ ይወዳሉ፤ አልገባችሁም? የገባችሁ ብቻ ማንበብ ቀጥሉ ከዚህ በላይ ገልቤ ማስረዳት ስለሚያሳፍረኝ፡፡ ለነገሩ እነዚያ አለቆችም በወጣት ዓይን ሲታዩ በጣም ግርማ ሞገስ ያላቸው ናቸው፡፡ እናም ስንቱን…
ያው መጽሐፌ የእኔ ታሪክ ስለሆነ እና የሰው ታሪክ መጻፍ እንዳይሆንብኝ ብዬ ያልጻፍኳቸው ብዙ ሚስጥራት አሉኝ፤ ይህን የመሳሰሉ፡፡ ያን ጊዜ ታድያ አንዷ የእንደዚህ ዓይነቱ አለቃ ሰለባ የነበረች ወጣት ያጫመተችኝ እና ከልቤ የማይጠፋ አስተማሪም አሳዛኝም ወግ እነሆ፡፡ ከትውልድ ቄዬዋ የወጣችው 12ኛ ክፍል ጨርሳ ለእሷ የሚሆን ስራ ስታፈላልግ ቤተሰቦቿ ደግሞ የደረሰች ልጃቸውን ለመዳር ሲቋምጡ የመማር እና የማደግ ሕልሟ እንዳይቋረጥ ወደ አዲስ አበባ ገብታ ዘመድ ተጠግታ (እያገለገለች) ስራ መፈላለግ ጀመረች፡፡ እዚያ በእኛ መ/ቤት ውስጥ የመላላክ ስራ ታገኝና ትቀጠራለች፡፡ ለኮሌጅ ዝግጅትም 12ኛን ደግማ የማታ መማር ቀጠለች፡፡ አለቃችን በወቅቱ የተከበሩ፣ ባለትዳርና እሷን የሚያካክሉ ልጆችም ለሀገር ያበረከቱ (??) ሰውዬ ቀልባቸው አረፈባት፡፡ ስራዋ የማያስመሽ ቢሆንም ወጥመዳቸው ባስገቧት እለት ግን ቢሯቸው ጠሯት እና “ብዙ ፎቶ ኮፒ የሚነሱ ሰነዶች ስላሉ አምሽተሸ እንድትሰሪ እፈልጋለሁ፣ ትርፍ ሰዓት ክፍያው በእኔ ነውì” ይሏታል፡፡ የአለቃ ትእዛዝ ነው እና አመሸች፡፡ በቃ ቀጥሎ ያለውን እናንተ ጨርሱታ!
እኔ የጭብጡን መጨረሻ ልንገራችሁ፡፡ እንግዲህ በአንድ ምሽት የተጀመረ ግንኙነት እየቀጠለ ሄዶ እሷ ግን ሚስት መሆን ስለማትችል ቅምጥ ሆነች፡፡ ወሬው የአደባባይ ምስጢር ሆነና ውሎ እያደር ማንም ለትዳር (ለቁምነገር) ሳይጠይቃት ቀረች፡፡ በቃ ቁጭ ብላ ቀረች፡፡ እሷው ናት ይህንን ታሪኳን የነገረችኝ፡፡ የልጅነት ሕልሟ የነበረው በክብር ተድራ የወላጆቿን ጉልበት ስማ ይቅርታቸውን አግኝታ መመረቅ ነበር፡፡ እሱም እንኳን ወግ ነው ብንለው የእኔ የምትለው ነገር እንዳይኖራት አደረጓት እኛ ባለ ኮት እና ከረቫት ትልቁ አለቃ፡፡ ይህንን ታሪክ የነገረችኝ ደግሞ እየተንገበገበች ነበር፡፡ ምክንያቱም እሳቸው ወጣት ሴት ሰራተኛ በመጣ ቁጥር የማለማመጃው (Induction) አካል ይመስል እንትን ሲሉ ስሜቷን እንደሚጎዳው ትዝ ብሏቸው አያውቅም ነበር፤ በቢሮ ውስጥ መነካካት እኮ ሌላ የጎንዮሽ ጉዳቱ ይሄም ጭምር ነው ወገኖቼ!
እንደዚህ ያሉ ወጣት የስራ ባልደረቦቼ ቁጥራቸው ጥቂት አልነበረም፡፡ በተለይ የስራ ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑ ወጣት ሴቶች እድገት ለማግኘት እንደሚጓጉ ስለሚታወቅ እና የትምህርት ደረጃቸው የሚፈልጉትን ደረጃ ሊያስገኝላቸው ስለማይችል አቋራጭ መስሏቸው የገቡበትም አሉ፤ ተገደው እና ፈርተው የገቡበት ግን ይበዛሉ፡፡ ዛሬ ላይ እንደዚያ ተነካክታ “ተመስገን አምላኬ ከአለቃዬ ጋር በመተኛቴ ይህን የመሰለ የተሻለ ሕይወት አገኘሁ!” የምትል ሴት ትኖር ይሆን? እንጃ አይመስለኝም፡፡ ምናልባት ግን “በሴትነቴ በተሰጠኝ ጸጋ ተጠቀምኩበት እንጂ ምን አጠፋሁ!?” የምትል ላትጠፋ ትችላለች፤ በተለይ አለቅየው ያላገባ/ያላገቡ ወይንም የፈቱ እና ሚስት ፈላጊ ከነበሩ፡፡ ምክንያቱም እውነተኛ የትዳር ጓደኛ ስራ ቦታም ይገኛልና፡፡ ችግሩ ግን ወጣት እና የስራ መደብ ዝቅተኛ የሆነች ሴት የሚያባልጉ ወንዶቹ አንድም ትዳር ያላቸው ናቸው አልያም ትዳር ቢፈልጉ እንኳን ካማገጧቸው ሴቶች ውስጥ መርጠው የሚያገቡ አይደሉም፡፡ ስራቸውን ስለሚያውቁ ከሌላ ስፍራ ይፈልጋሉ፡፡ ምናልባት ፍቅሯ አይሎባቸው ቢያገቧት እንኳን “የእኔ ደሞዝ ይበቃናል፣ ያንቺ ሚጢጢ ደመወዝ መጥታ ቀዳዳ አትደፍንም፣ ስለዚህ ልጆች እየወለድን ቁጭ ብለሽ አሳድጊ” በሚል አሳማኝ ምክንያት ቤት ያስቀሯታል፡፡ ወገኖቼ ይሄ ፈጠራ አይደለም፡፡ የሆነውን፣ የደረሰባቸውን እና የነገሩኝን ነው የምነግራችሁ፡፡ እኛም ነቄ ሆነን እንጂ መች ይቀርልን ነበር!
ብዙ እንደዚህ አይነት ገጠመኝ (ታሪክ) ያላቸው ሴቶች ሕይወታቸውን እያማረሩ ሊጨርሱት ተቃርበዋል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ባለማወቅ ባለመረዳት የፈጸሙት ድርጊት መሆኑን አምነው የነቁ፣ የተጸጸቱ እና ዳግም ሰለባ ላለመሆን እራሳቸውን በትምህርት እና በተሻለ ሙያ አብቅተው በእራሳቸው የቆሙ አሉ፡፡ ድርጊቱን ፈጻሚው ሰውዬ (አለቅየው) ደግሞ በስራ ላይ ከሆኑ ትልቅ አለቃ ሆነዋል፤ አልያም ጡረታ ላይ ከሆኑ ደግሞ ዋና አሸማጋይ (የተከበሩ) ሆነው ኑሯቸውን ቀጥለዋል፡፡
ትኩረቴን ሁሉ በስራ መደብ ዝቅተኛ ወይንም ስራ ጀማሪዎች ላይ ያደረግኩት በአብላጫ የጉዳዩ ተጠቂ ስለሆኑ እንጂ የብዙ ሰራተኛ ሴቶች ችግር ነው፡፡ ደግነቱ እንደዚህ አይነት ዓመል ያለባቸው አለቆች ቁጥራቸው ትንሽ ነው፡፡ ብዙዎች ወንድ የስራ ባልደረቦች እና አለቆች ይህን አስጸያፊ ተግባር የሚቃወሙ ናቸው፡፡ እናም በተለይ ወጣት ተቀጣሪዎች ሁሉም አንድ መስለዋችሁ አትሸማቀቁ፡፡ አትርበትበቱ፣ “ስራውን አጣዋለሁ ይሆን?” ብላችሁ ያለፍላጎታችሁ ከአለቃችሁም ይሁን ከአቻ ወንድ የስራ ባልደረባችሁ ጋር አትተኙ! እናንተም እነሱም በድርጅቱ ውስጥ እኩል መብት ነው ያላችሁ፡፡ ሌላው ቢቀር ድርጅቱ የግል ኩባንያ ሆኖ ድርጊቱን ሊፈጽምባችሁ ዳር ዳር እያለ ያለው የኩባንያው ባለቤት ቢሆንም እንኳን ያለውዴታችሁ በግዴታ ምንም የማድረግ መብት የለውም፤ ሕጉ እኩል አድርጓችኋልና!
ውይ ዛሬ ደግሞ ግልብ አድርጌ ጻፍኩ መሰለኝ! እውነታው ነው ያስለፈለፈኝ፡፡ ምን ላድርግ ወጣት ሴቶችን ሜንቶር አደርጋለሁ እናም ይሄ ነገር አሁንም እንኳን ንቃታችን ከፍ ባለበት ዘመን ተባብሶ መኖሩ እየገረመኝ ነው፡፡ አብሪያቸው የሰራኋቸው ከላይ የተረኩላችሁ ታላላቆቼም ድርጊቱ ተፈጽሞባቸዋል፡፡
እህቶቼ እንዲሁም ልጆቼ ሆይ፡- በዚህ ቀሽም መንገድ ሄዳ ንፁሕ ህሊና ያላት ሴት የለችም፣ ለጊዜው ብታድግም እንኳን ከፍታ ላይ አትወጣም! እናንተ ከፍታውን በግላችሁ ተጣጥራችሁ፣ ተምራችሁ፣ ጠንክራችሁ ሰርታችሁ እና ቆፍጥናችሁ ታገኙታላችሁ! እና ያለፍላጎታችሁ ከወንድ የስራ ባልደረባችሁ ይሁን ከአለቃችሁ ጋር በግዳጅ አትተኙ! ለዛሬ አቋርጫለሁ!
የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም