አማጭ-አዋጭì

ትዳር ከሚመሰረትበት መንገድ አንዱ በአማጭ በኩል የሚደረግ መጣመድ (matchmaking)  ነው። “እከሌና እከሊት ቢጋቡ ጥሩ ይጣነዳሉ” ብሎ/ላ በጥሩ መንፈስ የተነሳሳ ሰው ለሁለቱ ተጣናጆች እንዲተያዩ፣ እንዲተዋወቁ ሁኔታውን ሲያመቻቹላቸው ማለት ነው። በቅን ልቦና ተነሳስተው እራሳቸውን የአማጭ መንበር ላይ ያስቀመጡ ሰዎችን የማደንቅ ነኝ፤ እኔ በግሌ፡፡ “ለምን?” ካላችሁ ሁለት አጣናጅ ፈላጊዎች ጥርጊያ መንገዱ ተሰርቶላቸው ሲገናኙ እንደማለት ነዋ! በማንኛውም አጋጣሚ ለምሳሌ በመንገድ፣ በካፌ፣ በትራንስፖርት፣ በላይብራሪ፣ በገበያ፣ በጥምቀት፣ በስራ ቦታ ወይንም በሆነች አንዲት ቅጽበት ተያይተው ልባቸው ፈቅዶ እና ተዋውቀው ለትዳር የሚበቁ ያሉትን ያህል በአማጭ አንድ ዙር ጥናት የተደረገበት ጥምረት ምን ክፋት አለው!? እኮ የለውም አይደል? ለእኔ ስትሉ “አዎ” እንድትሉ እየገፋፋኋችሁ መሰለብኝ ይቅርታ! ለነገሩ እኔ አማጭ-አዋጭ አልኩ እንጂ ብሂሉማ አማጭ-ረማጭ ነው፡፡ ረማጭ ማለት ስርወ ቃሉ መረመጥ ሲሆን እሳት ውስጥ መክተት ማለት ነው፡፡ ግን ከዚህ ቀደም ስለአባባሎቻችን ነካክቻለሁ፤ ትክክል የሆኑም ያልሆኑም በማን አለብኝነት አንድ ላይ ዘመን ተሸግረዋል፤ ገና ይሻገራሉም፡፡ ስለዚህ ረማጭ የሆኑትን ሳይሆን አዋጮቹን ነው የማደንቀው፡፡

በአማጭ የታጨሁበትን አንድ አጋጣሚ እስቲ ዛሬ ላውጋችሁ። ወቅቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በላይብራሪ ሳይንስ በቀኑ መርሀ ግብር ሁለት ዓመት ተምሬ እና በዲፕሎማ ተመርቄ በብር 347 (ሶስት መቶ አርባ ሰባት) ስራ ተቀጥሬ ከሱውም ላይ እየከፈልኩ በማታው የትምህርት ክፍል አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለድግሪ በመማር ላይ ባለሁበት ወቅት ነበር፡፡ (በነገራችን ላይ ሁለት ዓመት ከፍዬ ተማርኩ እና በሶስተኛው ዓመት ላይ ዩኒቨርስቲ ላይብራርያን ሆኜ ስለተቀጠርኩ ክፍያ ተነሳልኝ!)  እናላችሁ ያ ዘመን በሰፈራችን ኮሌጅ ተመርቃ ስራ የያዘች ብቸኛ ወጣት መሆኔ ብዙዎች እይታ ውስጥ እንድገባ ያደረገ ዘመን ነበር፤ ወቅቱ ደግሞ እራሷን ችላ ገቢ የምታመጣ ሴት ዋጋ የተሰጠበት ሆኖ እንጂ በእድሜ እና በመልክ ከእኔ በእጥፍ የተሻሉ በሽበሽ ነበሩ፡፡

ታድያ በሰፈራችን አንድ ታዋቂ ሴት ነበሩ፡፡ ጠንካራ ሰራተኛ እና ኃይለኛም ነበሩ፡፡ ከእናቴ ጋር “በሀገሬ-የወንዜ ልጅ” ስም ደህና ይግባባሉ፡፡ ቤታቸው ብዙ ወንድ እንግዶች ነበሯቸው፡፡ ምሳ እያዘጋጁ በክፍያ ይመግቡ ነበር፡፡ አካባቢያችን ጦር ኃይሎች ሆስፒታል፣ ሚኒቴሪ ፖሊስ፣ አዋሽ ወይን ጠጅ፣ አንበሳ ዱቄት የመሳሰሉት ድርጅቶች ስለነበሩ እዚያ የሚሰሩ ሰዎች የተወሰኑት በምሳ ሰዓታቸው እሳቸው ቤት ይመገቡ ነበር፡፡ ታድያ እኚህ ሴት አንድ ሰሞን እናቴን በጥብቅ ይፈልጓትና ቤታችን አጥብቀው ይመላለሳሉ፡፡ እናቴ በወቅቱ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ትሰራ ስለነበር የተለያየ የስራ ሰዓት (shift work hour) ነበራት:: ተመላልሰው ሰዓቱ አልገጥም ሲላቸው አንድ ቀን በማታ ሲመጡ አዳሪ ሆና አጥተዋት ብስጭት ሲሉ እኔ መልእክታቸውን ነግረውኝ እንዳስቀምጥላቸው ስጠይቃቸው “ለልጅ አይነገርም!” ቢሉኝ ለአያቴ እንዲነግሯት ከአያቴ ጋር አገናኘኋቸው፡፡ እሳቸው እቴ፤ መጨረሻ እናቴ ከስራ ስትመጣ ነገሩ ስላሳሰባት ቤታቸው ድረስ ሄደችላቸው፡፡ እናም ሲያወጉ (ሲዶልቱ) ቆይተው አርፍዳ መጣች፡፡

ከቀናት በኋላ እናቴ ሴትዮዋ ቤት ጥሪ እንዳለ እና አብረን የምንሄድ እንደሆነ ነገረችኝ፡፡ የእማዬ ትእዛዝ ሁሌም ይከበር ነበረ እና “እሺ” ብዬ ለበስኩ፡፡ በዚያ ታሪካዊ እለት ያነሳሁት ፎቶ ስለነበረኝ የለበስኩት ጥቁር ዘመናዊ ቱታ እናቴ ደግሞ ቢጫ ጥለት ያለው የሀገር ልብስ ነበር፡፡ ታድያ እናቴ ያለወትሮዋ “ልብስ ቀይሪ፣ እንዲያውም ለምን ቀዩን ቀሚስሽን አትለብሽም ቀይ ያምርብሻል፣ ፈካም ያደርግሻል” አለችኝ። እኔ ደግሞ ዘመናዊ አለባበሴን ስለወደድኩት ክችች አልኩ። እናቴ ለምን ልብስ እንደመረጠችልኝ የገባኝ በኋላ ነው፡፡  አንድ ሚስት ፈላጊ እኚህን ሴት ያማክራቸዋል። ከዚህ በኋላ “አማጭ” እንበላቸው፡፡ እሳቸው ደግሞ እኔ ላይ ቀልባቸው አርፎ ኖሮ በድብቅ ለሰውዬው ያሳዩኛል፤ ሰውዬውም ይስማማል፣ እናም እናቴን ያማክሯታል። እናቴም “ትንሽ ትቆይ ድግሪዋንም ትጨርስ፣ በሰል ትበል…ወዘተ” ብላ ብትከራከርም አማጫችን  “ሰውየው ቀላል ሰው እንዳይመስልሽ፣ ፓይለት ነው፣ ምን የመሰለ ቤት አዲስ አበባ አለው፣ ከጉያሽ አትወጣም፣ ትምህርቷም አይቋረጥም፣ እድሏን አትዝጊባት፣ በዚያውም አንቺም ልጆችሽ ጋር በነጻ ትኬት ትመላለሻለሽ…ወዘተ” በሚል እንኳን እናቴን ዘር ማንዘራችንን የሚያማልል ማሳመኛ አዘነቡላት። እናቴም ተረታች፡፡ የጥሪው ቀን አማጯ ሴት ከሰውየው ሊያስተዋውቁኝ የተቆረጠው ቀን ስለነበረ ነው እናቴም አለባበሴ ቅር ያላት። እኔ ነገሩ ስላልገባኝ (እንኳን አልገባኝ) ሙጭጭ አልኩ እና አማጯ ቤት በድግስ ስም ሄድን።

ልክ ስንገባ ወደ 8 የሚሆኑ ሰዎች በድምሩ 16 አይኖች ሁሉ እኔን እና እንቅስቃሴዬን ነበር የሚያዩት። ከእናቴ ነጥለው በሰውየውና በጓደኛው መሀከል አስቀመጡኝ። ለምን እንደሆነ ስላልገባኝ ትንሽ ጨነቀኝ። እንደወትሮዬ ፈታ ማለት አቃተኝ። በእርግጥ አለባበሴ ከነበሩት ጥቂት ሴቶች የተለየ ዳያስፖራዊ ነው። ኮፍያዬን እንዲመቻቸው አውልቂያለሁ። ምግብ ቀረበ። መጎራረስ ተጀመረ። እኔ አስቀድሜ ጉርሻ እንደማልወድ አወጅኩ። ጥሩ የመወያያ ርእስ ሆነልን።

ሰውየው:- ጉርሻ እምቢ ይባላል እንዴ?

እኔ:- አዎ (ቀጥተኛ ነበርኩ/ነኝ)፣ ስለማልወድ ነው!

ሰውየው:- ለምን? መጎራረስ እኮ ባህላችን ነው፣ ኢትዮጵያዊት አይደለሽም እንዴ?

እኔ:- ነኝ፣ ግን ጉርሻ ለእኔ መታረም ያለበት ባህላችን ነው። አፌ መቀበልና ማላመጥ ከሚችለው በላይ ስለሚመጣ አልወደውም።

ሰውየው:- ጉርሻና ፍቅር ሲያስጨንቅ ነው ሲባል አልሰማሽም?

እኔ:- እሱም ትክክለኛ ካልሆኑት አባባሎች አንዱ ነው። ፍቅር የሚያስደስት እንጂ የሚያስጨንቅ መሆን የለበትም።

ሰውየው:- ትፈላሰፊያለሽ ልበል? እናንተ ሴቶች ስትማሩ እኮ! (አልጨረሰውም፣ ግን አምባገነን መሆኑ ታይቶበታል)።

እኔ፡- ገና ተማሪ ነኝ፤ ግን ባህላችን ውስጥ ጥሩ ነገር እንዳለ ሁሉ ጥሩ ያልሆነ ነገር ስላለ የማልቀበለውን አልቀበልም! 

ሰውየው፡- (ቢራውን በላይ በላዩ እየኮመኮመ) እንዴት የአዲስ አበባ ልጅ ሆነሽ ቢራ አልጠጣም ብለሽ ኮካ ትጠጫለሽ? ነው ወይንስ እናትሽ እንዳይቆጡ ነው?”  

እኔ፡- መጠጣት እና ያለመጠጣት ከክልል ጋር አያገናኘውም፤ የምርጫ ጉዳይ ነው!

አማጭ አሁንም አሁንም “ተጫወቱ፣ ምን ጎደለ?” እያሉ ይመላለሳሉ። እኔ ሰውዬው ላይ ብዙ ነጥብ ጥዬበታለሁ። በተለይ ጅምላ ፍረጃው (generalizations) ድክም ብሎኛል፡፡ ብቻ ባልተዋዛው ወጋችን እየተጨዋወትን ከነጓደኛው የጦር ጀት አብራሪዎች እንደሆኑ ነገሩኝ። አድናቆቴን እና አክብሮቴን ገለጽኩላቸው። ሙያው ስለሚገባው! ከኋላዬ የተዶለተውን አለማወቄ ጠቀመኝ። ሰውየው ደብረዘይት (ቢሾፍቱ) ትልቅ ቤት እንዳለው እና ደብረዘይትን ሊያስጎበኘኝም ቃል ገባልኝ፡፡ እኔ ለዚያች ቀንም ስለደከመኝ ዳግም የማላገኘው ሰው ነበር፡፡

ወደቤታችን እየሄድን ከእማ ጋር ስንጨዋወት እናቴ:-“መቼስ ከሰው ጋር የመግባባት ችሎታሽ በቤታችን የለም!” ስትለኝ “ኧረ ሰዎቹም ጋዜጠኛ ይመስል ያልጠየቁኝ የለም። እነሱ እኮ የጦር ጀት አብራሪዎች ናቸው አይገርምሽም?” ስላት እናቴ ደነገጠች፡፡ አሰባችሁት አማጭ የጦር ጀት አብራሪውን ነበር “ፓይለት ነው” ያሏት፡፡ እሷም አመነችና ልጇን ፈቀደች፡፡ በነገራችን ላይ የጦር ጀት አብራሪነት የተከበረ ሙያ እኮ ነው፡፡ ብቻ “ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው” እንዲሉ ነገሩን ያወቅኩት እናቴና አማጯ ሴት ተቀያይመው እና ተኮራርፈው ለወራት ዘልቀው ነው። ቅያሜው ደግሞ “ፓይለት ነው” ብለው መዋሸታቸው ሳያንስ ሰውየው የልጆቹ እናት የነበረችዋን ሚስቱን እየደበደበ ሲያስቸግራት ሁለት ልጆቹን ጥላበት የሄደች መሆኑን እያወቁ ሊድሩኝ ማግባባታቸው ነበር፤ ያቺን ወጣት እኔ! አስቡት ስንቶች የእንደእነዚህ ያሉ አማጮች ሰለባ ሆነዋል! እውነትም አማጭ-ረማጭ!

ወጌን ሳጠቃልለው አማጭ ያመጣው ትዳር ሁሉ መጥፎ ነው እያልኩ አይደለም። ነገር ግን በትውውቁ ጊዜ ከሚነገራችሁ ባሻገር በእራሳችሁ ጊዜ ወስዳችሁ ስለተጣማጃችሁ በቂ መረጃ ማግኘት ይኖርባችኋል፣ በዚያውም ልክ ደግሞ የእራሳችሁንም ማንነት አትደብቁ። ትዳር የእለት አይደለማ! ለትዳር ፈላጊዎች ጥሩ አማጭ ይግጠማችሁ በማለት ለዛሬ ቋጨሁ!

የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

Share to your circles!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *