አልሞተችም!

በዚህች ምድር ላይ ስንኖር መቼስ ይሆናል ካልነው ይልቅ አይሆንም ያልነው እየሆነ ማየትን ተለማምደነዋል፡፡ ይሄ ግጥምጥሞሽ ሲደጋገም ነው ከእኛ በላይ ሌላ ትልቅ አዛዥ ናዛዥ፣ ተቆጣጣሪ እና ወሳኝ ኃይል እንዳለ የማንጠራጠረው(የማልጠራጠረው በሚለው ይታረምልኝ)፡፡ ለነገሩ እኮ ሕይወትም የሚያጓጓው የገመትነው ሳይሆን ቀርቶ በድንገቴ (surprise) በመታጀቡ ነው፡፡ ታድያ ክፉውን ድንገቴ ያርቅልን!

ምን ሆነ መሰላችሁ፡፡ ዛሬ ላወራችሁ የፈለግኩት ለእኛ ጠቃሚ የሆነ ታሪክ ስላላት ሴት ነው፡፡ ውልደቷ እና እድገቷ እዚሁ አዲስ አበባ ነው፡፡ እናቷ ከወለደቻቸው አራት ሴቶች  የመጨረሻዋ ልጅ መሆኗ እናትየውም ሆኑ በዙርያዋ ያሉ ሁሉ እርግጠኛ ናቸው፡፡ ለአባቷ ግን እሳቸው ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡  ምክንያቱም አባትየው የውል ባለቤታቸው መካን ስለነበሩ የልጅ አምሮታቸውን የሚወጡት ሌሎች ሴቶችን እያማለሉ፣ እያባበሉ ነበር እና ይቺ ልጃቸው ከተወለደች በኋላ የሆነውን እሳቸው ናቸው የሚያውቁት፡፡ በንግድ ስራ የተሰማሩት እኒህ አባት መልከ መልካም እና ደግነትም ስለነበራቸው በለስ ቀንቷቸው በጣም ብዙ ልጆችን ከተለያዩ ሴቶች ወልደዋል፡፡ እቤት ከነበረችው ባለቤታቸው ጋር ውለታ ያላቸውም ይመስላል፡፡ ምክንያቱም የወለደችላቸው ሴት ፈቃደኛ ከሆነች ወስደው ለባለቤታቸው በማስረከባቸው በቤት ውስጥ ያደጉ ልጆችም ነበሩ፡፡ ለነገሩ የድሮ ባሎች ፍቃድ ባይጠይቁስ መብታቸው እኮ የትየለሌ ድረስ ነው፡፡ እንኳን ለመካን ሚስት ለወላዷ ሚስታቸውም ተጨማሪ ልጅ እንደ ቦነስ የሚያስታቅፉም ነበሩኮ! የዚች ባለታሪክ እናት ግን ልጇን ለአባትየው አልሰጠችም፣ እራሷ ይዛ እያሳደገቻት አባትም እየደገፏት እንደነበር አውግታኛለች፡፡

ይህቺ ሴት የተወለደችው ከዘጠኝ ወር ቀድማ ያለጊዜው (Premature) ስለነበር  ሕጻንነቷ ሕመም የሚያጠቃው ነበር፡፡ ስትታመም፣ ስታለቅስ፣ በየጊዜው ሆስፒታል ስትወሰድ፣ መርፌ ስትወጋ በቃ ማልቀስ መደበኛ መለያዋ ነበር፡፡ የእናትየው ጓደኞች እና ቤተዘመድ ሁሉ “በመጨረሻ መጥታ የስለት ልጅ ይመስል አሰቃየችሽ፣ ይቺማ አታድግም እኮ እንዲሁ ነው የምታለፋሽ!” ይሏታል፡፡ እናት በልጅ ተስፋ አትቆርጥም እና ለማሳደግ መክፈል ያለባትን ዋጋ እየከፈለች ባለችበት ሁኔታ አባት ይህቺን ሕጻንነቷን ያልጨረሰች እና ሌሎችንም ልጆቻቸውን ሳያሳድጉ በድንገት በሞት ተነጠቁ፡፡ እጅግ አስደንጋጭ ነበር ምክንያቱም ምንም ዓይነት የቆየ ሕመም ያልነበራቸው፣ በጣም ታታሪ ባለሀብት ነጋዴ፣ በወቅቱ የወንድነት መለክያ በነበረው አዳኝነት ከጃንሆይ እጅ ሽልማት የተቀበሉ ድንቅ ጎልማሳ ነበሩ፡፡ “አዳኝ” የሚለው የዱር አራዊት አደን ማለቴ ነው ስለሌላ ነገር አይደለምì ታድያ አባቷ በሕጻንነቷ የሞቱባት ጨቅላ ሕመሟ እየጠና ማልቀሷን ቀጠለች፡፡ ብዙም ሳይቆይ፣ በወራት ልዩነት ወላጅ እናቷን ያሳደጉ አያት ሞቱ፡፡ በባህላችን አልቃሻ ልጅ “ገፊ” እንደሚባል ታውቃላችሁ አይደል!? ልክ ውሻ ሲያላዝን ትልቅ ሰው ይሞታል እንደሚባለው አይነት ማለት ነው፡፡ ሕመሟ ባሰቃያት ቁጥር ስታለቅስ “ደግሞ አሁን ማንን ልትገፋ ይሆን!?” ይባላል፡፡ እናት በልጇ አባት ሞት እና በአሳዳጊ አያቷ ሞት ሀዘኗ የከፋ ሆነ፡፡

የልጇን አባት ማሳደግያ ውርስ ለማግኘት ፍርድ ቤት በመመላለስ ላይ እንዳለች ደርግ ከቤተሰቧ የወረሰችውን መሬት እና ሀብት ወሰደባት፡፡ ይህንን ተከትሎ የተበሳጩት ወላጅ እናቷ (የባለታሪኳ አያት) ስትሮክ መታቸው፣ ልብ በሉ ልጅት ታለቅሳለች፣ በቤተሰቡ መዓት እየወረደ ነው፡፡ በቃ ያቺ ገፊ ልጅ እንደሌሎች ልጆች የራሷን ፀጋ ይዛ አልመጣችም፡፡ እድሏ ነው!

የልጅቷ እናት በመጨረሻ ሀብት ንብረቷም ቀረ፣ የልጇንም ማሳደግያ ውርስ ሳታገኝ ቀረች ፓራላይዝድ የሆኑትን እናትዋን ከገጠር አምጥታ እያሳከመች ሕይወትን “ሀ” ብላ በአሳር መግፋት ተያያዘች፡፡ ያቺ “አታድግም” የተባለችው ገደቢስ ልጅ እያደገች ሄደች፡፡ አልሞተችም! ለአቅመ ትምህርትም ደርሳ ት/ቤት ገባች፡፡

እናቷ በደረሰባት የተደራረበ መገፋት ለመማር የነበራት ሕልም በመጨንገፉ ልጆቿን ያለመታከት የምትመክረው “የእኔን ሕይወት እንዳትደግሙ ጠንክራችሁ ተማሩ፣ ለሴት ልጅ የሕይወቷ ግብ መማር እና እራሷን መቻል ብቻ መሆን አለበት!” እያለች ነበር፡፡ የእራሷን ሕይወት ምሳሌም እንዲህ እየሰጠች “የምወደውን የነርሲንግ ኮርስ መጨረስ ያልቻልኩት በልጅነቴ በመዳሬ እና በመውለዴ፤ ሳልበስል የገባሁበት ትዳር ባለመዝለቁ፣ ከዚያም ከፍቺ በኋላ የጀመርኩትን ትምህርት በማታ እንኳን ተምሬ ባለመጨረሴ ሌሎች ውጣውረዶች በመምጣታቸው ምክንያት የጤና ረዳት ሆኜ በመቅረቴ ነው” እያለች በቁጭት ትነግራቸው ነበር፡፡

ምክራቸው የዘለቃት ይቺ ባለታሪኳ ሴት ልጅ ንቁ እና በትምህርቷም ጎበዝ ሆነች፡፡ ከትምህርቷም በተጨማሪ በት/ቤትም ሆነ በሰፈር ውስጥ በሚደረጉ ጨዋታዎች እና ውድድሮች ተወዳዳሪ የሌላት ድንቅ ሆነች፡፡ ያ ሁሉ ለቅሶ በሳቅ እና በጨዋታ ተቀይሮ የቤቱ አድማቂም ሆነች፡፡ በትምህርቷ ገፍታ ኮሌጅ በጠሰች፤ ደጋገመችው፤ ጠንካራ ሰራተኛም ሆነች፡፡ ወጣትነቷን በስራ እና በትምህርት ከመጥመዷ በተጨማሪ በበጎ ፈቃደኝነት ስራዎች ላይ ተሳታፊ በመሆን የማህበረሰብ አገልግሎቷን ተያያዘችው፡፡ በእናቷ እና በእራሷም የደረሰባት የሴትነት እና የወጣትነት ፈተናዎች በሌሎች ላይ እንዳይደገም ወጣቶችን ሜንቶር ማድረግ እና ማብቃትን የመደበኛ ስራዋ አካል አደረገችው፡፡ ሕይወትን በደንብ ተጋፈጠቻት፣ ተናነቀቻት፡፡ አልተሸናነፉም፡፡ እናም አሁን ሕይወት ጥሩ ጓደኛዋ ሆናለች፡፡ ይህቺ ሴት እየኖረች ነው፤ አታድግም የተባለችው ሴት አልሞተችም!

ይህቺ ባለታሪካችን ሴት በአሁኑ ሰዓት ስራዋ አሰልጣኝ እና አማካሪ ብትሆንም በተጨማሪ መጽሐፎችን እየጻፈች እና እርቅ ከእራስ ይጀምራል በሚል መድረኮችን እያዘጋጀች ትውልዱን ከሚያንፁ ዜጎች ጋር ተቀላቅላለች፤ ለውጥ በጋራ ለማምጣት፡፡ በሙያ ማህበራት ውስጥ ጽኑ ተሳትፎ በማድረግ እራሷን ከማሳደግ አልፋ ለሌሎችም እያገለገለች ትገኛለች፡፡ ከሰዎች ጋር ጥሩ ተግባቦት እና የመተሳሰር (Networking) ክህሎት ስላላት የምትፈልገውን ጠይቃ ለማግኘትም ለማጣትም ብርቱ ናት፡፡ የተለያዩ እውቅናዎችን አግኝታለችም፡፡

ከሰሞኑ ደግሞ እንቁ ሴት፣ ንቁ ሴት፣ ጠንካራ ሴት” የሚል እውቅና አግኝታለች፡፡ ይህንን እውቅና የሰጣት ደግሞ እንቁ ኢቬንት እና ማማከር ኃ/የተ/ ማህበር ነው፡፡ “ጠንካራ ሴት!” ማለት አይበገሬ፣ በፈተናዎች ውስጥ የምታልፍ፣ እራሷን የቻለች፣ በእራስ መተማመን ያላት፣ ሁልጊዜ አዲስ ነገር መማር የምትፈልግ፣ በእውቀት የታነጸች፣ ከስህተቷ የምትማር፣ ሰው አክባሪ፣ የምትኖርበትን አላማ የምታውቅ፣ እራሷን እና ሌሎችን የምትወድ፣ የምትንከባከብ፣ ታማኝ፣ አገልጋይ፣ ቁርጠኛ፣ ትኩረት (ፎከስ) ያላት፣ የማታወላውል ይቅርታ መስጠትም መቀበልም የምታውቅ ሴት ማለት ነው፡፡ “ይህንን አሟልተሻል!” ተባለች፤ ይህቺ ባለታሪካችን፡፡ እንግዲህ ከመነሻዬ እንደነገርኳችሁ ይሆናል ካልነው ይልቅ ያልጠበቅነው ይሆናል እና ይህቺ ባለታሪካችን ገፊ ብትባልም፣ አታድግም ትሞታለች ብትባልም አልሞተችም፡፡ የሚገርመው ደግሞ ወላጅ እናቷ በልጇ ተስፋ ቆርጣ አታውቅም ነበር፤ ልጇ በትምህርት ቤቶቿ እውቅና እና ሽልማት እያገኘች እንዳደገችው ሁሉ በሕይወት ዘመኗ ተሸላሚ እንደምትሆን ህልም ነበራት! የእናት ሕልም! እና ምን ለማለት ነው ይህንን ታሪክ የምትጽፍላችሁ እሷ ባለታሪኳ እኔ ነኝ!

የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

Share to your circles!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *