አለማድነቅ እራስን መንፈግ ነው!

አንድ የከተማችን ታዋቂ ካፌ ውስጥ ከሰዎች ጋር ቁጭ ብለን የሥራ ጉዳይ ላይ ስንወያይ ለሥራችን ሙያዊ እገዛ እንደሚያስፈልገን አምነን ምክረ ሀሳብ እንዲሰጡን የሰዎችን ሥም “እከሊት እና እከሌ” እያልን ሀሳብ እያውጣጣን ነበር፡፡  ከመሀከላችን አንዱ ወይንም አንዷ እከሌን ብናማክረውስ ብለው ሀሳብ ሲያቀርቡ “በነገራችን ላይ እሱ እኮ የተተኮሰው ዓይናችን እያየ ነው! የሆነ ነገርማ ከጀርባው አለ!…ወዘተ” ደግሞ ሌላዋ  እከሊት ለፕሮጀክቱ በሚኖራት ፋይዳ ትነሳና ብዙም ሳይቆይ “እሷ እኮ ማለት…” ወዘተ፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ ውይይታችን እየደራ ሲሄድ እና ሰዓቱ መንጎዱን ሳስተውል ነበር የውይይታችን ጭብጥ ፈር እንደሳተ ያስተዋልኩት፡፡ ሳናውቀው ከሥራው ይልቅ ስለ እከሊት እና እከሌ ግላዊ ሕይወት ሳይቀር ማውራት ይዘን ነበር፤ በሌሉበት እና በማይመለከታቸው፡፡ በሕይወታችሁ ስንት ጊዜ እንደዚህ ያለ ጊዜ አሳልፋችሁ ይሆን? ያው ጊዜ አቅም ካለው እራሱ ይቁጠረው!

በእርግጥ መቼስ ጭውውትን ጣዕመኛ የሚያደርገው የሌሎችን ሥም እያነሱ ማውራት ሲታከልበት ነው፡፡ ስለ ሌላ ሰው ማውራት ደግሞ ምን  አለበት! ሰው ከሰው ጋር አይደል እንዴ የሚኖረው! ደግሞስ ስለ ሰው ያልተወራ ስለማን ሊወራ ይችላል! ከምር ግን ሰው የተፈጠረው ስለሰው ለማውራት እስኪመስል እኮ ነው የምናወራው፡፡ ድሮ ድሮ በዚህ የምንታወቀው ሴቶች ነበርን፤ አሁን ግን  ሴት ወንድ ሳይል ሁሉም ያወራሉ፤ ማለቴ እናወራለን፡፡ ማውራቱስ ባልከፋ! ግን የምናወራው ወሬ ዋጋው ስንት ይሆን! ማለቴ ስንት ዋጋ እያስከፈለን እንደሆነ አስባችሁታል?

ከላይ በጠቀስኩላችሁ የካፌ ቆይታ በሥራ ጉዳይ ተሰብስበን ለጠጣናቸው ቡና እና ማክያቶ ውድ ዋጋ ከፍለን የምንቋጨውን ቋጭተን በይደር የምናንጠለጥለውን አንጠልጥለን ከተለያየን በኋላ ከእራሴ ጋር በወሬአችን ዙርያ እያቀነቀንኩ ነበር ወደ ቤቴ የተጓዝኩት፡፡ ከምር በጣም ነው ያሳፈረኝ፡፡ ወሬአችን ለሥራ በሚል ርእሰ ጉዳይ ተንተርሶ ሰው ተኮር ሆኖ ተጠናቀቀ፡፡ በዚያ ላይ ሀሳባችን ሁሉ ጉድለት ተኮር ነበር፤ ማለቴ በሌሉበት የተረክናቸው ሰዎች ሁሉ በሞላላቸው ወይንም በሞሉት መጠን ሳይሆን ባጎደሉት እና በጎደለባቸው፡፡ አስቡት ከመነሻው ስማቸው የተነሳው የተሻለ እውቀት ወይንም አቅም አላቸው ተብሎ ነበር እኮ! ዋና ርእሰ ጉዳይም አልነበሩም እኮ! የዚህ ዓይነት ውሎ የመጀመርያዬ አልነበረም፤ የመጨረሻዬም እንደማይሆን አውቃለሁ፡፡ ውይ እዚህ እና እዚያ ከምል ለምን ፍርጥ አላደርገውም፤ በቃ ማድነቅ አልለመደብንም ወይንም ባህላችን አይደለም፡፡ ይልቁንም በጎደለ ማብጠልጠል እንጂ፡፡   

እንደውም ካለማድነቃችን ብዛት ድንገት ብናደንቅ ያደነቅናት ወይም ያደነቅነው ሰው ሳይደነግጡ አይቀሩም፡፡ በተለይ እኛ ሴቶች እርስ በእርሳችን የማንደናነቀው ነገር ሁሌም ያስገርመኛል፡፡ እኔ በበኩሌ ለማድነቅ እጣጣራለሁ፡፡ ግን አድናቆቴ የሚያስደስታቸው ሰዎች በመኖራቸው ልክ የሚያስደነግጣቸውም ብዙ ናቸው፡፡ ምን ያድርጉ አልለመዱትማ! ዘለፋ፣ ሀሜት አልያም በዝምታ ማለፍ በተለመደበት ማህበረሰብ ውስጥ አድናቆት እኮ ያስፈራል፡፡ ይሄ እንግዲህ በግላዊ ሕይወታችን እየኖርነው ነው፡፡ እንዲያው ምን ዓይነት ጎጂ ባህል እና ልምድ ነው! ስናየው እያማረን፣ ችሎታ አይተን ሲገዝፍብን፣ ደግነት ከምናስበው በላይ ሲሆንብን በአጠቃላይ መልካምነትን ማድነቅ ሲያቅተን የምንነፍገው ማንንም እንዳይመስለን፤ እራሳችንን እንጂ፡፡ እኔ እንደዚህ ነው የሚሰማኝ፡፡

በዚህ ምዕራባውያኑ ታድለዋል፡፡ እነሱም ሰው ስለሆኑ ያው ስለሰው ያወራሉ፤ እንክት አድርገው፡፡ ግን ደግሞ እንደ ባህል እና ልምድ ብዙ ጊዜ በፊት ለፊት እንደሚደናነቁ ባለኝ ትንሽ ተሞክሮ እና አብረዋቸው ከሚኖሩ ወዳጅ ዘመዶችም ሰምቻለሁ፡፡ ማድነቅ፣ ይቅርታ መጠየቅ እና ምስጋና መስጠት  ፊት ለፊት የሚታይ ቋንቋቸው ነው፡፡

እኔ እንደማህበረሰብ ታመናል ሲባል አይገባኝም ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን የሆነ የጎደለን እንዳለ ፍንትው ብሎ ይታየኛል፡፡ እኔ በታየኝ ልክ አልያም ከእኔ የተሸለ የታያቸውም ብዙ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ችግር አለ ማለት ነው፡፡ መልካም ነገርን አይቶ ያለማድነቅ እኔ እንደ ችግር ነው የማየው፡፡ ለዚህ ችግር ደግሞ መፍትሔ በእጃችን አለ፤ አርአያ መፈለግ፣ የሚደነቅ ከሚታያቸው ጋር መቀላቀል፣ ማድነቅ እና መደነቅ! ለሌሎች ብርታት መስጠት፣ ብርታት ሰጪዎችን መቀላቀል እና ብርታት ማግኘት! እፎይ እንዴት የአእምሮ ሰላም እንዳለው እኮ!

በነገራችን ላይ ስለሰዎች መልካምነት እያየን ያለማድነቅ እራሳችን ላይ የምንጥለው የንፉግነት ማእቀብ ነው፡፡ ንፉግ በሆንን ቁጥር ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ በጥቂቱ የተሰራንባቸው ሴሎች ሁሉ ኩምትርትር ነው የሚሉት፣ ከሰዎች ጋር የሚኖረን ግንኙነት የሰመረ አይሆንም፣ ጥሩ ግንኙነት በሌለበት ደግሞ ደስተኝነት፣ መተማመን እና መልካም ትዝታ አይኖርም ማለት ነው፡፡

ኤውብ በማድነቅ የአሥር ዓመታት ስኬት ያስመዘገበች ብቸኛ የሴቶች ማህበር ናት ብዬ ብናገር የዋሸሁ አይመስለኝም፡፡ በሴቶች ተመስርታ፣ ለማህበረሰቡ በጎ ሥራ የሠሩትን ብቁ ተብለው በማህበረሰቡ የተጠቆሙትን ታደንቃለች፤ ታበረታታለች፤ ለሕዝብም ታስተዋውቃቸዋለች፡፡ በየዓመቱ በኦክቶበር ወር ላይ በሸራተን አዲስ በሚደገስ የበቁ ሴቶች የሽልማት መርሀ ግብር ብዙዎችን የበቁ ሴት አውጥታለች፡፡ ኤውብ ማህበር ብትሆንም በግለሰቦች የምትመራ ናት፡፡ ይህ ማለት አድናቂ ሴቶች አሏት ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሴቶች ለሁላችንም አርአያ ናቸው፤ የማድነቅ እና የመደናነቅ አርአያ፡፡ እንደ እነዚህ ያሉትን ሴት መሪዎች ያብዛልን! እኛ አለማድነቅ እራስን መንፈግ መሆኑን አምነን እናደንቅ ዘንድ! ለዛሬ ቋጨሁ!

Written by: Fitsum Atnafework K/Mariam, Author at AWiB Ethiopia

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *