ትልቁ ኮንፈረንስ!

በሕይወቴ ብዙ የመጀመርያ እና አስደናቂ የሚባሉ ገጠመኞች ሞልተውኛል፤ በአብዛኛው ድንቅ የሚባሉ ሲሆኑ በተቃራኒውም ድንቅ ያልሆኑ ገጠመኞች አሉኝ፡፡ መጀመርያ ድንቅ ያልሆነውን አንዱን ልተርክላችሁ፡፡ ለረዥም ዓመታት የሰራሁበት እና በተለይ በወጣትነቴ ብዙ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በማገልገል የምታወቅበት መሥሪያ ቤት በወቅቱ መሀከለኛው የአመራር ደረጃ ላይ ለነበርነው ኃላፊዎች በአውሮፓ ሀገራት የልምድ መጋራት እና የአጭር ስልጠና እድል ይሰጥ ነበር፡፡ ከእኔ በወቅቱ በእድሜ እና በልምድ አንጋፋ የነበሩት ሁሉ እየተላኩ በእድሉ እየተጠቀሙ በተዋረድ የእኔ ተራ ደረሰ፡፡ እንደሚልኩኝ እርግጠኛ ስለነበርኩ ፓስፖርትም ስላልነበረኝ ለመዘጋጀት ፈለግኩ፡፡ ይሁንና የዚያን ጊዜ በመ/ቤት የድጋፍ ደብዳቤ በአጭር ቀናት ስለሚደርስ እድሉ እስኪሰጠኝ መጠበቅ ያዝኩ፡፡ ብጠብቅ፣ ብጠብቅ ጭራሽ እኔ ተዘልዬ በእድሜ የሚበልጡኝ ግን በኃላፊነት የሚያንሱኝ ሁለት ሠራተኞች እንዲሄዱ ተደረገ፡፡ ምክንያቱ (አፈትልኮ ሲወጣ እንደሰማሁት) እኔ ወጣት ስለነበርኩ “ሄዳ ትቀራለች” በሚል ግምት ነበር፡፡ እኔም የዚያ መ/ቤት እህል ውሀዬ ሲያልቅ ሌላ መ/ቤት ገባሁ፡፡


ሌላው ድንቅ ገጠመኝ ታድያ ይሄኛው አዲሱ መ/ቤቴ ገና ፊርማዬ እንኳን በቅጡ ሳይደርቅ በገባሁ በስድስተኛ ወር የዓለም አቀፍ የሴቶች ኮንፈረንስ እንድሳተፍ ያውም በልዩ ተወካይ (ዴሊጌት) ሆኜ ከአውሮፓም አልፎ አውስትራልያ ተላኩኝ፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኳችሁ ወቅቱ እ.አ.አ. በ 2003 ስለነበር ፓስፖርት እንኳን አልነበረኝም ነበር፡፡ በዚያ ላይ ከሀገር ውጭ መብረር የመጀመርያዬ ነበር እና ሁሉ ነገር ብርቅ ሆኖብኝ ነበር፤ ለነገሩ ምን ይደንቃል! ዋናው አስደናቂ እና ላወራ የፈለግኩት ነገር ምን መሰላችሁ፤ በዚያ ኮንፈረንስ ላይ ወደ 1500 የሚሆኑ ከተለያዩ ሀገሮች የተውጣጣን ሴት ተሳታፊዎች ነበርን፡፡ እያንዳንዳችን እንደየበረራ ሰዓታችን እና የመድረሻ ቀናችን ከኤርፖርት ጀምሮ ነበር አቀባበል እየተደረገልን የገባነው፡፡ ወደ ስብሰባ አዳራሹ ስንገባ በየስማችን የመጀመርያ ቃላት እየተሰለፍን የተዘጋጀልንን መታወቅያ (መለያ ባጅ) ከተቀበልን በኋላ የተለያዩ መስተንግዶዎች ተደረገልን፡፡ ዋናው ኮንፈረንስ ከመጀመሩ አጥቢያ ምሽት በሀገር ልብሶቻችን እና በባንዲራችን ደምቀን የኮክቴል ግብዣ ተደረገልን፡፡ በማግስቱ ዋናው የእንኳን መጣችሁ ንግግር ሲደረግ የተጀመረው አንዲት ደቂቃ እንኳን ሳይዘገይ በተመደበለት ሰዓት ነበር፡፡ ምን አለፋችሁ ዝግጅቱ በሴቶች ተዘጋጅቶ፣ በሴቶች ተመርቶ፣ በሴቶች ታጅቦ በአጠቃላይ የተዋጣለት ምንም ያልተዝረከረከ እንከን የለሽ ነበር፡፡


እኔ በዚያ ወቅት የተለያዩ ኮንፈረንሶችን በሀገሬ ተሳትፌ ባውቅም እንደዚያ ያለ በሰዓት ተጀምሮ በሰዓት የሚጠናቀቅ፣ ሁሉ ነገር የተዋጣለት ዓይነት ኮንፈረንስ ቀርቶ ትንሽ ተሳታፊ የሚገኝበት ስብሰባ እንኳን ገጥሞኝ አያውቅም ነበር እና በእኛ እና በአደጉት ሀገራት መካከል ካሉት ልዩነቶች አንዱ መሆኑን በደንብ ተረድቻለሁ፡፡ የሚገርማችሁ በዚያ ኮንፈረንስ አርፍደው የሚመጡ ሰዎች ካያችሁ አፍሪካውያን ናቸው፤ ያው እንግዲህ በቀለም ስለምንለይ ግምቴ ብዙ የተሳሳተ አይሆንም፡፡ ግን ዛሬ ይህን ገጠመኝ ያወጋኋችሁ በምክንያት ነው፡፡
ወደ ሀገሬ ተመልሼ ከመጣሁ በኋላ ቁጭት በደንብ አድርጎ ነው ያንገበገበኝ፤ እስካሁንም እየቆጨኝ እና ጥያቄ ሆኖብኝ የቀረ ነገር፡፡ እኛ በሀገራችን ላይ በሚደረጉ ኮንፈረንሶች ይሁን ስብሰባዎች መቼም ሰዓት ሳናከብር ይህ የእኛ ትውልድ አልፎ ለቀጣይ ከነ እፀፃችን ልናስረክብ ነው፡፡ ምን ይሆን እንዲህ ከደማችን የተያያዘ የሚመስለው የሰዓት ገዳይነታችን መንስሄ? ይህንን ነጥሎ ያጠና ተመራማሪ ይኖር ይሆን!? ለነገሩ ማን ቁብ ሰጥቶት!


በዚህ መልስ በሌለው ጥያቄዬ ውስጥ እየዋኘሁ የዛሬ አስራ ሦስት ዓመት የመጀመርያውን የኤውብ ሜይ ፎረም ለመካፈል ትኬት ገዝቼ ገባሁ፡፡ መግቢያው ላይ የነበረው ጥንቃቄ የአድናቆቴ አካል ቢሆንም በወቅቱ እዚያው ኢሲኤ እሰራ ስለነበረ ብዙም አልተገረምኩም፡፡ አዳራሹ ጋር የነበረው ድባብ ግን አስር ዓመታት (በዚያ አቆጣጠር ከ2003- 20013) ወደ ኋላ ነበር የወሰደኝ፤ በአግራሞት እና በአድናቆት፡፡ አውስትራልያ ተነጥቄ የሄድኩ ሁሉ ነበር የመሰለኝ፡፡ በሕይወቴ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ ሀገሬ በሴቶች ለሴቶች የተዘጋጀ እጅግ የተቀነባበረ እና የተዋጣለት ኮንፈረንስ አየሁ፡፡ እንባዬ በደስታ ዱብ ዱብ ነበር ያለው፤ ያለማጋነን ስነግራችሁ እመኑኝ፡፡ የሰው ሀገር ሴቶችን ስኬት አይቼ መቼም አንደርስበትም ብዬ ተስፋ ከመቁረጥ በተጨማሪ “ታድለዋል!” ብዬ እቀና ነበር፡፡ መንፈሳዊ ቅናት!


ያቺ ቀን የኤውብ መስራቿ (ባለፈው ሴትየዋ ያልኳችሁ) ነጣ ያለ ሙሉ ልብስ (ኮት እና ጉርድ) ለብሳ በፍጥነት እየተራመደች መመርያዎችን ታስተላልፋለች፤ አልፎ አልፎም በቡድን የቆምነውን ሰላም ትላለች፡፡ ከዚያም ከምሣ በኋላ በነበረው የትስስር ስነ ስርዓት ላይ መልእክት ለማስተላለፍ እንዲመቻት አንድ ጠረጴዛ ላይ ያለምንም ድጋፍ በመውጣት ቀጥ ብላ ቆማ “አንዴ አቴንሽናችሁን ስጡኝ፤ አዲስ አባላትን እዚህ ጋር እየመዘገብን ነው፤ አባል መሆን የምትፈልጉ ወደእዚህ ኑ እና እየከፈላችሁ ተመዝገቡ!” አለች፡፡ ሁለቴ እንኳን አላሰብኩም ከፊት ከተሰለፉት ተርታ ስገኝ፡፡ ከዚያማ ማን ያስቁመኝ! ከጥቂት ወራት አባልነት ወደ ቦርድ አመራርነት ከፍ አልኩኝ፤ ከዚያም በሜንቶርነት የስትራተጂ አመራር አባል ሆኜ በመጨረሻም በመሪነት የተሰጠኝን የኃላፊነት ድርሻዬን ተወጣሁ፡፡ በኤውብ ውስጥ በብዙ አቅጣጫ አድጊያለሁ ብዬ አምናለሁ!


የኤውብን ሜይ ፎረም ያደነቅኩት የውጭውን ኮንፈረንስ በማየቴ እና መሰል ዝግጅት በሀገሬ የመሳተፍ እድል ስላልገጠመኝ ነው፡፡ አሁንም ደፍሬ የምናገረው እንደ ኤውብ ያለ ሰዓት እና አጀንዳ አክባሪ ኮንፈረንስ እስካሁን ብዙም አልገጠመኝም፡፡ አጋንኜ ይሆን!? የእኔ ነገር! ብቻ ኤውብ እንደ ውጭው አለም መስራት ከፈለግን እንደሚቻል አሳይታናለች፡፡ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ብዙዎቻችሁም የምትደግፉኝ ይመስለኛል፡፡ እንድትደግፉኝ እያስገደድኳችሁ ከሆነ ይቅርታ ይደረግልኝ፤ ለማህበሬ ካለኝ ጽኑ ፍቅር እና ክብር የመነጨ እንጂ ለክፋት አይደለም! ለሁሉም ግን እንኳን ለአመታዊው የሜይ ፎረም አደረሰን!


እኔ የምለው ከማጠቃለሌ በፊት ከላይ የቀድሞ መ/ቤቴ ኃላፊዎች “በዚያው ትጠፋለች” ብለው እኔን ትተው አጣምረው የላኳቸው ሁለት ታላላቆች ሠራተኞች በዚያው ጠፍተው መቅረታቸው ሳልነግራችሁ ብቀር ይቆጨኛል፤ ለመ/ቤቱ ትልቅ ቁጭት ለእኔ የጭቡ አምላክ ሆኖ በትዝብት አስታውሰዋለሁ! ለዛሬ ጨርሻለሁ!

የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

Share with your circle!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *