ተጋልጠናል!

ማህበራዊ ሚዲያ (social media) ተጠቃሚ ከሚባሉ ሰዎች አንዷ ነኝ፡፡ በተለይ ፌስቡክ በጣም ጊዜ ካጣሁ እንኳን በቀን አንዴ ገብቼ ትንሽ መልእክት እጽፋለሁ፤ የሌሎችን ጽሑፎች አነባሁ፤ ሀሳብ እሰጣለሁ፣ እቀበላለሁም፡፡ ብዙ ሰዎች ፌስቡክን የስራ-ፈት ሚዲያ አድርገው ስለሚቆጥሩት እንደተዉት ሲናገሩ እሰማለሁ፡፡ እኔ ደግሞ በተቃራኒው ምንያህል እየተጠቀምኩበት እንደሆነ ቤቴ ይቁጠረው፡፡ ዋናዎቹን ብነግራችሁ ሥራዬን የማስተዋውቅበት እና ቢዝነስ የማገኝበት ነው፣ በጣም ጥሩ ጓደኞች አፍርቼበታለሁ፣ በጎ ስራ (ደጋፊ እና ተደጋፊ ማገናኘት) እሰራበታለሁ፣ የልጅነት ጓደኞቼን፣ አስተማሪዎቼን እና በሕይወቴ ውስጥ ዋጋ አላቸው የምላቸውን ሰዎች ዳግም አግኝቼበታለሁ፤ እንዲሁም ሜንቶር የማደርጋቸውን ወጣቶች በመገናኘት አገልግሎት እሰጥበታለሁ፡፡
ይሁንና ፌስቡክ አጠቃቀም ስልጠና ሳያስፈልገው አይቀርም፡፡ አለበለዝያ ገበና አውጥቶ ቁጭ ነው የሚያደርገው፡፡ እጅግ በጣም ተጋልጠናል ማለት እደፍራለሁ፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት በጣም ድንቅ ሰዎችን በፌስቡክ ተዋውቄ በገአድ ዓለም ወርደን ሻይ ቡና የተባባልን፣ ቢዝነስ (ስልጠና) የሰራን፣ ከዚያም አልፈን ሰርግና ለቅሶ ሳይቀር የተደራረስን አለን፡፡ የተሳካለትስ ትዳር ይመሰርት የለ! (እኛን ባለትዳሮችን ባይመለከትም!) ታድያ የዚያን ያህል ደግሞ ሰው የምትታዘቡበት ሚዲያ ነው፡፡ በጣም የተከበረ የሚባል ሰው ወርዶ (ዘጭ ብሎ) ታገኙታላችሁ፡፡
ሰሞኑን የገጠመኝም ይህ ነው፡፡ ሰውዬው የራሱ ድርጅት መሥራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ (CEO) ነው፡፡ ፌስቡክ ላይ ስለድርጅቱ ብዙ ስለሚጽፍ እና ስለምከታተለው የዚህ የዲጂታል ሲስተም አልጎሪዝም ልጥፎቹን ((post) ፊትለፊት ያመጣልኛል፡፡ ይህ ማለት በየጊዜው የምታዩትን ልጥፍ እንደምትፈልጉት ስለሚያውቅ ወይም ስለሚገምት ፌስቡካችሁ ፊትለፊት ገጽ ገጭ ያደርግላችኋል ማለት ነው፡፡ ታድያ ይሄ ሰው በሙያ ተግባባን እና ማውራት ጀመርን፡፡ በዚህ አጋጣሚ ድርጅቱን የሚሸጥበትን መንገድ በጣም አደንቅለታለሁ፡፡ የስልጠና ማእከላቸው ትልቅ እንደሆነ እና ጉምቱ አሰልጣኞች አብረውት እንደሚሰሩ ነገረኝ፡፡ “እኔም እኮ ጉምቱ ነኝ” ብዬ ለመጠጋት ተወሰወስኩ፡፡ ግን ከዚያ በፊት በደንብ ልወቀው ብዬ እራሴን መከርኩ፡፡ እንግዲህ የፌስቡክ ጓደኛ ለማወቅ የግድ መገናኘት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ፕሮፋይሉ ውስጥ ገብታችሁ ቀደም ያሉ ልጥፎችን በተለይ ሳታነቧቸው ያመለጧችሁን፣ ከእራሳቸው ጓደኞች ጋር የተመላለሱትን (የተጻጻፉትን ሀሳቦች)፣ የለጠፏቸውን ፎቶዎች ሁሉ ስትበረብሩ ትንሽ ወይንም በቂ ፍንጭ ታገኛላችሁም፡፡ ይህ በእርግጥ ሁልጊዜ ላይሳካ ይችላል ግን በተወሰነ መልኩ ይገኛል፡፡
ታድያ ይሄ ትልቁ ያከበርኩት ሰው እኔ ጋር ከሚያወራው ጋር ፈጽሞ የማይሄድ ማንነቱን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየኝ የጽሑፍ ልውውጦች አይቼ ዓይኔን ማመን ስላልቻልኩ ደጋግሜ አነበብኳቸው፡፡ “አድኛ ብላሽ!” ብዬ (በሆዴ) ተስፋ በቆረጠው ስሜቴ የሀሳብ ልውውጤን ቀጠልኩ፡፡ ከዚያም የተወጠነው የቢዝነስ ወግ ዳር መድረስ ስለነበረበት የእነርሱ ድርጅት የሚሰጠውን የስልጠና ዓይነት ጠየቅኩት፡፡ ዝርዝር መስጠት የድርጅታቸው አሰራር የማይፈቅደው መሆኑን ሲነግረኝ ምናልባት የስሜት ብስለት (Emotional Intelligence) ከዝርዝሩ ውስጥ ያለበት መሆኑን ማወቅ መፈለጌን ነገርኩት፡፡ እሱም በኩራት “እንዴ እሱማ ከዋናዎቹ ስልጠናዎቻችን አንዱ አይደለም እንዴ!” በማለት ለብዙ ድርጅቶች እንደሰጡም አስረግጦ ነገረኝ፡፡ በዚህ በኩል ደግሞ ፌስቡክ ያጋልጣል!
መቼስ ስልጠና ለአንዳንድ ሰው ቢዝነስ (የገንዘብ ምንጭ) ብቻ ነው! የምናሰለጥነውን ስልጠና እራሳችን ላይ ካልተገበርነው ምን ዋጋ አለው! በዚያ ላይ አንድ ድርጅት የሚመራ ሰው በሶሻል ሚዲያም ሆነ በገአዱ ዓለም ብቁ የሚያደርገው የስሜት ብስለት (Emotional Intelligence) ሲኖረው ነው አይደል እንዴ! ሰዎች አውርደው ቢጥሉን እንኳን በእርጋታ መገሰጽ እንጂ በአደባባይ ኃይለ-ቃል መሰናዘር ያለንበትን ኋላቀርነት ፍንትው ነው የሚያደርግብን እኮ! በዚያ ላይ እንደዚህ አመራር ቦታ ላይ ያለን ሰዎች የሶሻል ሚዲያ አጠቃቀማችን ላይ ጠንቃቃ ካልሆንን ሰራተኞቻችንም አያከብሩንም፤ አርአያ መሆንም አንችልም ማለት እኮ ነው፡፡ እንዲያው ለራስም ክብር እና ደስታ ሲባል ጥንቅቅ ጽድት ማለት አያስፈልግም ትላላችሁ!?
በነገራችን ላይ እንደዚህ ያለ የድርጅት ባለቤት ወይም አመራር ላይ ያለ ሰው በሶሻል ሚዲያ ኃይለ-ቃል (ስድድብ) ሲፈጽም ስመለከት የመጀመርያዬ አይደለም፡፡ በተለይ በኳስ ጨዋታ ውርርዶች እና አንዳንድ ማህበራዊ ጭውውቶች ላይ በሚኖሩ ምልልሶች ላይ ይገጥመኛል፡፡ እሩቅ ሳንሄድ መኪና በማሽከርከር የሚሰነዘሩ የስድብ ልውውጦች ከየመኪናው ተመዝግበው የቀን ስሌት ቢወጣላቸው (ከስራ ኃላፊዎች ብቻ) በአማካይ ከአንድ አሽከርካሪ ሁለት ስድቦች በቀን አይመዘገብም ይሆን?! ይመዘገባል! የስሜት ብስለት ደግሞ ቦታ፣ ጊዜ እና ሁኔታ የሚመርጥ አይደለም፡፡
ሶሻል ሚዲያውን ብዙ ሰው የጠላው ሁሉም ሰው በቀላሉ የሚጠቀመው እና በአብዛኛው ደግሞ የስሜት ብስለት የሌላቸው ሰዎች የተቆጣጠሩት በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የማይተዋወቁ ሰዎች የቃላት ጦር ሲማዘዙ ማየት የተለመደ ነው፡፡ የሚተዋወቁትም ቢሆኑ ወደ ሶሻል ሚዲያው ሲመጡ ብዙም ያለመከባበር ሲዘላለፉ እናያለን፡፡ በነገራችን ላይ እንደሀገር ወይንም እንደዜጋ በባህል፣ በስልጣኔ፣ በእውቀት…ወዘተ የት ጋር እንዳለን ሶሻል ሚዲያው በደንብ ያጋለጠን ይመስለኛል፡፡
አንዳንዴ እኔንም ውስጣዊ ስሜቴ “ተይውና ቁጭ በይ!” ይለኛል፡፡ ግን ደግሞ ባለውለታዬ ነው ብያችሁም አይደል! እንዴት ጥዬው ልውጣ! በእርግጥ እኔ በተለይ ልዩነታችንን አጉልተው የሚያሳዩት እንደ ፖለቲካ፣ ብሔር እና ኃይማኖት ያሉት አንኳር ነገሮች ላይ ተሳትፎ የለኝም፡፡ እኔ ለዚያ የሚሆን ቆዳ ነው ጫንቃ የሚባለው ብቻ ሁለቱም ስለሌለኝ አልመረጥኳቸውም፡፡ ባይሆንም ግን የሚሳተፉ ሰዎች የሚለዋወጡትን ሀሳቦች (ዱላ ቀረሽ ክርክሮች እና ስድድቦች) በአጋጣሚዎች ማየቴ አይቀርም፡፡ አንዳንዴ እንደዚህ በድንገት ሲገጥማችሁ ብዙ ትታዘባላችሁም! ከምር በጣም ተጋልጠናል! ሳጠቃልለው ማህበራዊ ወይም ሶሻል ሚዲያውን ባንጠቀም ምንም አይደለም! ከተጠቀምን ምርጫው በእጃችን ነው፡፡ መልካሙን ብቻ መርጠን መጠቀም አቅማችንን (energy) ይቆጥብልናል! እኛም በብስለት እና በጥንቃቄ ሀሳባችንን መስጠት ይጠበቅብናል! ከተጋላጭነት ይሰውረን ዘንድ! ለዛሬ ጨርሻለሁ!
የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም
Share with your circle!