ብቁነት ትኩረት ይስባል!

እራሴን ለማስተዋወቅ እና ለገበያ ለማቅረብ (ለመሸጥ) ከምጠቀምባቸው አንዱ እና የምኮራበት በኤውብ እና በሌሎችም የሙያዊ ትስስር የሚያበረታቱ ማህበራ አባል መሆኔን ነው፡፡ ይህም በሰዎቹ ዘንድ ዋጋዬን ከፍ ሲያደርገው እና የመጀመርያ እይታቸውን (first impression) የተሻለ ሲያደርገው አስተውላለሁ፡፡ እናም በልቤ “እውነትም ሰዉ እራሷ ላይ የምትሰራ ሴት ማድነቅ ጀምሯል” ብዬ በማህበረሰባችን የእድገት ለውጥ እኩራራለሁ፡፡ የዚያን ያህል መኩራራቴ እንዳይዘልቅ የሚያደርጉ ኩነቶች ያጋጥሙኛል፡፡ ከልክ ያለፈ ትችት፤ በተለይ ደግሞ በሌሎቹ ማህበራት ሳይሆን የሴቶችን እምቅ ችሎታ እያወጣች እና እያበቃች ባለችው ማህበር በኤውብ፡፡
ነገር በምሳሌ ሲሆን ግልጥልጥ ይላል እና ከገጠመኞቼ አንዱን ላጋራችሁ መሰለኝ፡፡ ምን ሆነ መሰላችሁ፤ አንዲት ጓደኛችን ከባለቤቷ ጋር የሰሩትን ቤት እንድንመርቅላቸው በተለያዩ የሕይወታቸው ጉዞ የሚያውቋቸውን እና የተጎዳኟቸውን እንዲሁም ቤተዘመዶቻቸውን ድል ያለ ግብዣ አድርገው ይጋብዛሉ፡፡ አኔም ከተጋባዦቹ አንዷ ሆኜ ተገኘሁ፡፡ ቀድሞውኑም በቡድን የመጡት ሌላ ሰው በመሀከላቸው ሳይቀይጡ ጭውውታቸውን ተያይዘውታል፡፡ እንደ እኔ በተናጠል የመጣነው እንደ አማራጭ “ተጫወች” “ተጫወት” እየተባባልን በመግባባት መቧደን ጀመርን፡፡ አዲሱን ቤት አደናንቀን ስናበቃ ሳናስበው እርስ በእርሳችን በጥልቀት ወደመተዋወቅ ገባን፡፡ ብዙ ጊዜ የእኔን ፊት የሚመስል ብዙ ፊት አለ መሰለኝ “አንቺ ግን አዲስ አልሆንሽብኝም?” የሚሉኝ አንድ ሁለት ሰዎች መኖራቸውን ሳስተውል “ምናልባት ብዙ ቦታ ስለምሳተፍ ይሆናል፣ ቶስትማስተርስ፣ ኤውብ፣ ሻርም…” ከማለቴ ተጠለፍኩ፡፡
ኤውብ ማለት ይሄ የሴቶች ምናምን ነው? ክላስ ያለን ኤሊቶች ነን የሚሉት ሴቶች የሚሰባሰቡበት ነው? ኢትዮጵያዊ ቀለም የሌለው ነው? ሁልጊዜ ሂልተን የሚሰባሰቡት ናቸው…ወዘተ”፡፡ ለካስ ስለማያውቁት ነገር በድፍረት ማውራት እንደዚህ መልከ ጥፉ ነው?! ብቻ ምን አለፋችሁ እኔ ከ10 ዓመት የዘለለ የቀደምት አባልነት መታወቅያ ያለኝን ሴት “እስቲ ስለኤውብ አስረጂን?” ከማለት ይልቅ የማጥላላት ናዳቸውን አዘነቡት፡፡ ምናልባትም ከስሚ ስሚ ውጪ የአንድ ወቅት አባልነት እንኳን የሌላቸው ሴቶች እና ፕሮግራሙ ላይ በጭራሽ ተሳትፈው የማያውቁ ወንዶች ነበሩ፡፡ እኔ ለእነሱ ሽምቅቅ አልኩኝ፤ ከምር፡፡ ነገሩ እኛ ማህበረሰብ ውስጥ በጅምላ እየተቀባበሉ ስለማያውቁት ነገር አሉታዊ አስተያየት መስጠት አዲስ አይደለም፡፡ ግን በኤውብ ሲመጡብኝ የምር በሀገሬ የመጡ የውጭ ወራሪዎች ነው የመሰሉኝ፤ አጋነንኩ እንዴ?
በቅርቡ እያዳበርኩት ያለውን ክህሎት መጠቀም እንዳለብኝ ተሰማኝ፤ የስሜት ብልህነት (Emotional Intelligence) ድሮ ድሮ እንደምናገረው “ኤውብን ሳታውቁ ለምን እንደዚህ ትላላችሁ? ለመሆኑ የት መጥታችሁ ያያችሁትን ነው…ወዘተ” ከማለት ይልቅ በጥሞና እና በዝምታ ካዳመጥኳቸው በኋላ ልክ የቅብብል ጥልሸታቸውን ሲጨርሱ ወደ ሌላ ርእሰ ከመግባታቸው በፊት እኔ ደግሞ ተራዬን እንዳወራ እድል እንዲሰጡኝ በእርጋታ ጠየቅሁ፡፡ ከቀድሞው የተሻለ ፀጥታ ሆነ፡፡ “ለካስ አብሮ ከመጯጯህ ይልቅ መጨረሻ ላይ አስፈቅዶ ጊዜ ወስዶ መናገር ዋጋ አለው!” አልኩና በልቤ ማስረዳቴን ቀጠልኩ፡፡ ማራኪ በሆነ አጀማመር እንደገባሁ ያወቅኩት ከማስረዳቴ በኋላ ሳያውቁት ልክ ስብሰባ ላይ የተደረገ ንግግር ይመስል ሲያጨበጭቡ ነበር፡፡ አገባቤ እንዴት ነበረ መሰላችሁ፡-
“እስቲ ስለ የበቁ እና የላቁ ሴቶች ሽልማት (Women of Excellence) ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ?” ብዬ ለጠየቅኩት ጥያቄ የእናውቃለን ምላሽ ስላላገኘሁ ቀጠልኩ፤ “ስለ ኤውብ አስተያየታችሁን ስትሰጡ የነበረው ታድያ ይህንን ትልቅ የኤውብ ፕሮግራም ሳታውቁ ኖሯል እንዴ!?” በሚል ፊቴ ላይ የወቃሽ ሳይሆን ለማሳወቅ የሚተጋ ፊት አሳየኋቸው፡ የውስጤ ሀሳብ ደግሞ “አይ የእኛ ነገር! መቼ ይሆን ጠንቅቀን በማናውቀው ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠትና ፍረጃ የምናቆመው? ይሄ ባህርይ ግን የዓለም ይሆን ወይ የእኛ የኢትዮጵያውያን?” ይሞግተኝ ነበር፡፡ ዋናው ነገር እነዚህን በአጋጣሚ ያገኘኋቸውን ሰዎች አመለካከት ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ መምራት ነበር እና ሀሳቤ ላይ ብዙም አልቆየሁም፤ ይልቁንም መለስ ብዬ ማብራራቴን ቀጠልኩ፤ ለማዳመጥ እንደጓጉ እርግጠኛ በመሆን፡፡
“ኤውብ ለማህበረሰቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ እና በአገልግሎታቸውም የላቀ አስተዋጾ ያደረጉትን ሴቶች በየዓመቱ በሸራተን ሆቴል ውድ የሆነ የክብር የእራት ግብዣ (Gala Dinner) ዝግጅት በማድረግ ልዩ ሽልማት እና እውቅና የምትሰጥ ብቸኛ የሴቶች (ምናምን ያሉትን ለማፍረስ) ማህበር ናት፡፡ እነኚህ ሴቶች ደግሞ ሕዝብ እንዲጠቁም በየሚዲያው እየተነገረ በጥቆማው መሰረት የሚሰሩት ሥራ እና ያመጡት ልዩነት ጥናት ተደርጎ ከዚያ ውስጥ ጥቂቶቹ በፕሮፌሽናል ዳኞች አጋዥነት ተመርጠው ይሸለማሉ፤ ለሕዝብ ይተዋወቃሉ፡፡ ይሄ እንግዲህ ቀደም ሲል ምን እየሰራ እንደሆነ የማይታወቅ፣ ጥቂቶችን ያውም ኤሊቶችን ብቻ አቃፊ የሆነ…ወዘተ፡ ላላችሁት ምላሽ እንጂ ኤውብ ከዚህም በላይ ናት!” ዝምታቸው ከፈራጅ ማንነታቸው ጋር እየሞገታቸው መሆኑ ስለገባኝ ቀጠልኩ፡፡
“የላቁ ሴቶችን ከመሸለም እና ለሕዝብ ከማስተዋወቅ በተጨማሪ ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው በቀጣይ ሕይወታቸውን እንደምን መቀጠል እንዳለባቸው ብዙም እውቀት የሌላቸውን ወጣት ሴቶች መሪ ሜንቶርሽፕ በሚባለው ልዩ ፕሮግራም የተለያዩ የሕይወት ክህሎት እና ሙያዊ ስልጠና በመስጠት ወደሚፈልጉት የስራ መስክ በአፋጣኝ እንዲቀላቀሉ እያደረገች ያለች ማህበር ናት”፡፡ ዝምታቸው እና አድናቆታቸው ቀደም ሲል ያለ በቂ እውቀት ፈራጅነታቸውን እንዲጸጸቱበት ያደረጋቸው ስለመሰለኝ ርእሳችንን እንደምንም ብዬ እንድንቀይር መንገድ ከፈትኩ፤ እነሱ ግን ከመውጣት ይልቅ የበለጠ ለመረዳት እንደጓጉ ከሁኔታቸው ስለተረዳሁ ስልክ ተለዋወጠን፡፡ እርግጠኛ ነኝ እነዚህ ሰዎች ስለኤውብ ብቻ ሳይሆን ስለማንኛውም ማህበር ይሁን ግለሰብ በቂ መረጃ ሳይኖራቸው ከመተቸት እና ከመፈረጅ በመጠኑም ቢሆን ይታቀባሉ፡፡ በነገራችን ላይ ይሄ ነገር እንደማህበረሰብ ሁላችንም ልናስብበት እና ልናሻሽለው የሚገባን መልእክቴ ይሁንልኝ! ሳጠቃልለው የበቁ እና የላቁ ሴቶች ሽልማት ትኩረት ይስባል፡፡ ይህንን ደግሞ እንደ ኤውብ ባለች ማህበር ሴቶች አደራጅተውት ሴቶችን መሸለማቸው የባህል ለውጥ ከማምጣትም አንጻር ብናየው ቀላል አይደለም፡፡ እኛ ሴቶች እኮ እርስ በእርስ መረዳዳታችን እና መሸላለማችን በይበልጥ ጎልቶ የወጣው እና እየዳበረ የሄደው በኤውብ ነው፡፡ ኤውብ ለአስረኛ ጊዜ በተለመደው ሥነ-ስርዓት ልትሸልም እየደገሰች ነው፤ በብዙ የአቅም ፈተና ጋር! እርግጠኛ ነኝ እንደ እኔ የእናንተንም ትኩረት የሳበ ዝግጅት ነው፡፡ አስረኛው የበቁ እና የላቁ ሴቶች የሽልማት መርሀግብር በጥሩ ሁኔታ ይከናወን ዘንድ እምነቴ ነው! አሥራ አንደኛው የበቁ እና የላቁ ሴቶች ሽልማትስ ይከናወን ይሆን? ለዚያ ደግሞ የዓመት ሰው ይበለን!
Written by: Fitsum Atenafework Kidanemariam