ሲስተሙ (ክፍል 4- የመጨረሻ)

በአሜሪካ በነበረኝ ጥቂት ግን ጥፍጥ ያለ የቀናት ቆይታዬ ያልተደነቅኩባቸው ነገሮችም አሉ፡፡ ቀጥታ ወደ እነሱ ከመግባቴ በፊት ካለፉት አድናቆቶቼ ለማጠቃለያ ሰብሰብ ላድርጋቸው፡፡ በዋናነት የእኛ ብርቅዬዋ መሳለጫ መንገድ ዓይነት ሳላጋንን በየ ኪሎ ሜትሩ አልያም በ 500 ሜትር ርቀት ይገኛል፡፡ ይህ ማለት መተንፈሻ እና ማስተንፈሻ መንገዶች እንደሸረሪት ድር ይመስላሉ፤ በተለይ በዋና ከተሞች፡፡ መንገድ የሀገር ደም ሥር መሆኑን ያየሁበት ነው፡፡ እኔ ከቤቴ ተነስቼ የ10 ኪሎ ሜትር ርቀት እየነዳሁ ለመጓዝ ልቤ እስኪመታ ነው የምጨነቀው፤ ያው መንገዱ አንድ ወይንም ሁለት ስለሆነ የትራፊክ መጨናነቁን እያሰብኩ፡፡ መንገድ ሠርተዋል፤ አሁንም እየሠሩ እና ከስር ከስር እያደሱም ነው፡፡ ታድያ መንገድ ሲሠሩ መጨናነቅ ፈጥረው አይደለም፤ አስቀድመው ተለዋጭ ሰርተው እና እየሠሩ መሆናቸውንም አሳውቀው ነው፡፡ ይህንን በደንብ አይቻለሁ፡፡ ሲስተሙ ለሰዎች ምቾት ቅድምያ ይሰጣል፡፡

በአረንጓዴ ውበቱ ላይ ሌላው ውበት ደግሞ አንድም ቆሻሻ የሚጥል ሰው የለም፡፡ እንኳን የበሉበትን እና የጠጡበትን ትርፍራፊ ማሸግያዎች፣ የውሀ ላስቲኮች፣ የጫት ገረባዎች፣ የሽንኮራ  ምጣጮች…ወዘተ ሊጥሉ ቀርቶ ውሻቸውን ይዘው ሲሄዱ እንኳን በአስገዳጅ የተፈጥሮ ጥሪ የጣለውን/የጣለችውን ቆሻሻ በኪሳቸው ይዘው በሚዞሩት ላስቲክ ልቅም እና ጽድት አድርገው ነው ጉዟቸውን የሚቀጥሉት፡፡

ውሻ ካነሳሁማ ስለውሾቻቸው ሳላወራ ማለፍ ንፉግነት ነው፡፡ ያው ያያችሁ አይታችኋል፤ የሰማችሁም ሰምታችኋል፡፡ ለጨዋታ ድምቀት የእኔን እይታ ላክልላችሁ፡፡  አንድ ማስታወቅያ ቀልቤን ስቦት ፎቶ አንስቼዋለሁ፡፡ የአፋልጉኝ ማስታወቅያ ነው፡፡ እዚህ እኛ ሀገር ሰው (ሕጻናት፣ አረጋውያን፣ የአእምሮ ሕመምተኛ የሆነ ቤተሰብ) ከቤት ወጥቶ በዚያው ሳይመለስ ሲቀር ማስታወቅያ በየመንገዱ ማንበብ የተለመደ ነው አይደል? እዚያ ለእነዚህ ሰዎች ማፈላለግያ ሲስተሙ ሥራውን ይሰራል፡፡ በሰፈሮች መንገድ ላይ ተለጥፎ ያየሁት ግን የውሻ አፋልጉኝ ማስታወቅያ ነው፤ ከነቁመናው ፎቶ ተነስቶ ያገኘ ሰው የሚደውልበት ስልክ ከታች ተቀምጦ ማለት ነው፡፡ አስቡት የውሻው ባለቤት እስኪገኝለት ሀዘን ላይ ነው/ናት ማለት ነው፡፡ በዚያ ላይ አንዴት እንደሚያሸልሏቸው ልነግራችሁ አልችልም፤ የአንገት ሀብሉ፤ ልብሱ፤ ጫማው፣ ሕክምናው፣ ጋሪው፣ ብቻ ስንቱን እነግራችኋለሁ፡፡ የት ነበር ያነበብኩት “የአሜሪካ ውሻ ባደረገኝ?” የሚል ጽሑፍ፡፡ እኔ ግን አንዳንዱ እንክብካቤ የተፈጥሮ ነጻነታቸውን ያሳጣቸው ስለሚመስል ቅጥ ያጣ ሆኖብኛል፤ ቅናት እንዳይመስልብኝ እንጂ በውሾቹ፡፡ ለምሳሌ ታኮ ጫማ ያደረገች ሴት ውሻ በተፈጥሮ ከተሰጣት እግር በምን ይመቻታል? በዚያ ላይ ጸጉራቸው የተሰራው ለብርዱም ለሙቀቱም ታስቦ ነው፤ ከፈጣሪ፡፡ እና በእሱ ላይ የሚደረብላቸው ልብስ ምን ያህል ተመችቷቸው ይሆን! ዳሩ እኔ ምን አገባኝ! ፎፎፎ! ሲስተሙ የፈቀደላቸው ነው፡፡

ታድያ የዛሬው የሲስተሙ ትርክቴ ማጠቃለያዬ ወደሆነው እና በዋናነት ላጋራችሁ ወደፈለግኩት እውነት  ልውሰዳችሁ፡፡ ሲስተሙ የነጭ እና የጥቁርን ልዩነት ወዶ እና ፈቅዶ አቅፎ እና ደግፎ ያቆየው ለምን ይሆን? ውሻ እንኳን እንደዚያ በሚከበርበት ሀገር እንዴት ሰዎች በሰውነታቸው እኩል አልሆኑም ይሆን? በዲሲ ያየሁት  የጥቁሮች መንደር ብለው ያስጎበኙኝ በነጩ ቤተመንግስት የቅርብ ርቀት የሚገኝ ከተመሰረተ እድሳት ጎብኝቶት የማያውቅ፣ ከመጠጥ ግሮሰሪዎች እና የመሳሰሉት ጎጂ ሸቀጦች ውጪ የረባ ነገር የማይሸጥበት ብሶት ያረገዙ ጥቁሮች በቀላሉ የሚገድሉበት እና የሚገዳደሉበት፣ ያደፈ ልብስ ለብሰው የሚታዩበት፣ ቆሻሻቸው የተዝረከረከበት ብቻ ምን አለፋችሁ በቀን እያያችሁት የሚጨልምባችሁ (በአንጻራዊነት ከዚያው ከአሜሪካ ማለቴ እንጂ በእኛ ሰፈሮች ማለቴ አይደለም) ያስፈራል፡፡

አደነጋገጤን ያስተዋለ አንድ እዚያው ሲስተሙ ውስጥ ነዋሪ የሆነ ዘመዴ “ይሄ እኮ ዓለም ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው! እንዲያውም የበለጠ እንድታውቂ ይህንን መጽሐፍ አንብቢው” አለና THE COLOR OF LAW በሚል ርእስ የተጻፈ መጽሐፍ ሰጠኝ፡፡ ከአንዱ ከተማ ወደሌላው ስዘዋወር በሚኖረኝ ጉዞ አልፌ አልፌ እና እንዲሁም ከመተኛቴ በፊት እያነበብኩ ባጋምሰውም ገና ሳልጨርሰው ከድኜ ቁጭ አደረግኩት፤ ከላይ ከላይ እያየሁ መደመሜን እንዳይቀንስብኝ፡፡

ሌላው አሜሪካ ካፒታሊስትነቷ ሁላችንም የምናውቀው ነው፤ ገንዘብ ተኮር ናት፡፡ የሀብታም እና ሀብታም ያልሆኑ ሰዎች (ደሀ ለማለት ስለቸገረኝ ነው) ልዩነት ጎልቶ የሚታይባት፡፡ እንዲያውም የገረመኝ ሰፊ ሆኖ በተንጣለለው ሀገሯ በስፋት የሚኖሩትን ሕዝቦቿን አብልታ ለማሳደር ተፈጥሯዊ (ኦርጋኒክ) ያልሆኑ በፍጥነት የሚደርሱ ምግቦችን ታቀርባለች፡፡ ማንም በምግብ እጦት አይሞትም ማለት ነው፡፡ ታድያ እነዚህ ምግቦች ለጤና ጠንቅ ናቸው ይባላል፡፡ ሲስተሙ ያተኮረው አጥግቦ ማሳደር ወይንም መሠረታዊ ነገሮችን ማሟላት ላይ እንጂ ጤና ላይ አይደለም ይላሉ፡፡ ታድያ ሀብታሞቹ እነዚህን ምግቦች አይበሉም፤ በብራቸው ኦርጋኒክ የሚባሉትን ውድ ምግቦች ገዝተው ይመገባሉ እንጂ፡፡ በነገራቸን ላይ እኛ ጠግበን አንበላም እንጂ ኦርጋኒክ ስለምንበላ ሀብታሞች መሆናችንን እንወቅ፡፡ ታድያ “በአሜሪካ የዜጎች ጤና ጉዳይስ?” ካላችሁ ያው እሱ ቢዝነስ ነው ይሏችኋል፤ ሲስተሙ ገንዘብ አምጪ እክሎችን ያበረታታል፤ እንደ ጤና ያሉትን፡፡  ብዙ ኢንሹራንሶች ብዙ መድሀኒት አምራቾች የገቢ ማግኛ ምንጭ ናቸው ይሏችኋል፡፡  ቀደም ሲል የማደንቀው ሲስተሙ ዥንጉርጉር ገጽታ አይገርምም? ከመገረምም ግራ የሚያጋባ ሲስተም፤ የአንድ ሳንቲም ሁለት የተራራቁ ገጽታዎች!!

በአሜሪካ የተማረ እና ያልተማረ የኑሮ ልዩነት በጉልህ ይታያል፡፡ በእርግጥ ነጋዴን አያካትትም፡፡ ግን በሲስተሙ የተማረ የተማረ ነው፤ ጥሩ ኑሮ የሚኖር፡፡ ለምሳሌ እኛ ሀገር እኩል የተማሩ ሰዎች እንደሚገቡበት መ/ቤት ገቢያቸው ይለያያል፤ ኑሯቸውም እንደዚያው፡፡ ብዙ አማራጭም ላይኖር ይችላል አይደል!? በእርግጥ በአሜሪካ ስራ አይናቅም፤ ያልተማረም በጉልበቱ የጉልበት ስራ መርጦ ሊሠራ ማንም አያግደው፡፡ ብቻ የሚሸጥ እውቀት ወይንም ጉልበት ካለ የሚኖርበት ሀገር ነው፡፡ ግን መማር በተለይ በሲስተሙ ከሆነ ዋጋው የተሻለ ነው፡፡

እንግዲህ በነበረኝ ቆይታ ለእናንተም ለእራሴም ይህንን በአራት ተከታታይ ጽሑፍ ሰንጃለሁ፡፡ ማየት አስወራኝ እኮ! ማየት ማመን ነው የሚባለውስ ለዚህም አይደል! ብዙ የሚወራለት እና የሚወራበትን ሀገር እንኳንም አየሁት! ብዙ ተምሬበታለሁ፤ ተዝናንቼበታለሁ፣ አትርፌበታለሁም፡፡  በሲስተሙ ያለኝ ወግ በዚሁ ተጠቃሏል፡፡

ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም: Fitsum Atnafework K/Mariam, Author at AWiB Ethiopia

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *