ሲስተሙ (ክፍል ሶስት)

ሰው ግን ዋጋው ስንት ነው!? እኔ የሰውን ዋጋ ለማወቅ በተለመደው ጉግል ጥናቶችን ፈልጌ ነበር፤ በእኛ ሀገር የተሠራ ጥናት አልገጠመኝም፡፡ ለነገሩ እኛ እኮ ባህላችን አንዳንድ ነገሮች ላይ ከገንዘብ በላይ ነው! የአሜሪካኖች እና የሌሎች አውሮፓውያንን የተለያየ ግምታዊ ዋጋ ግን አይቻለሁ፤ በሚሊዮኖችም በትሪሊዮኖችም ተመትሮ፡፡ ትክክለኛውን ቀምሮ ማስፈር ሳይቸግራቸው አልቀረም፡፡ ፈረንጆች በቋንቃቸው ከቃላት መጨረሻ Less ሲያስገቡ አፍራሽ ነው አይደል!? ለምሳሌ useful እና Useless ጠቃሚና ጥቅም የሌለው ተብሎ እንደሚተረጎመው፡፡  ግን በሌላ መልኩ price ወደ Priceless ሲቀየር ዋጋ የሌለው ማለታቸው ሳይሆን ከዋጋ በላይ ነው ማለታቸው እንደሆነ እንረዳለን፡፡ እንግዲህ ሰው ማለት እሱ መሆኑ ነው፡፡ ከሀብቶች ሁሉ አቻ የሌለው ውዱ የሰው ሀብት ነው፡፡ we humans are priceless! ያው ግን ይህም የሚሆነው በቦታችን ስንገኝ ነው ታድያ!

ስለ ሲስተሙ በሦስት ተከታታይ ጽሑፍ ያጻፈኝ ስለዋጋ የማወራበት ይሆናል ማለት ነው፤ በአሜሪካ በነበረኝ አጭር ቆይታዬ ባየሁት፣ በሰማሁት እና ባነበብኩት፡፡ በነገራችን ላይ የጉዞዬ ዋና ምክንያት የዓለም አቀፉ የሰው ሀብት ማኔጅመንት ያዘጋጀውን የ75ኛ ዓመት ኮንፈረንስ ለመሳተፍ መሆኑን ከመነሻዬ ተናግሪያለሁ፤ በክፍል አንድ፡፡ እግረ መንገዴን እዚያ ድረስ ሄጄ ወዳጅ ዘመድ ሳላገኝ እንዳልመጣ አሉኝ የምላቸውን (ሁሉንም ባይሆንም) አዳርሻለሁ፤ እነሱም ተንከባክበውኛል፡፡ ምስጋን ይግባቸውና! አሜሪካንን ለመጎብኘት የሀገሩ ነዋሪ ሰው ወሳኝ ነው፤ በተለይ እንደ እኔ መጠነኛ ፍራንክ ይዞ በድፍረት ለሄደ ሰው፡፡ በአጭሩ ቆይታዬ ያየኋቸው ከተማዎች ላስ ቬጋስ፣ ዲሲ፣ ቨርጂኒያ፣ ሜሪላንድ፣ ፊላደልፍያ እና ኒውዮርክ ናቸው፡፡ በላስ ቬጋስ የሚገኘውን የሁበር ግድብ ስጎበኝ አሪዞናንም ጫፏን ነክቻታለሁ፡፡ እና ምን ለማለት ነው ስድስት (ሰባት) ከተማ ጎብኝቶ ስለአሜሪካ ያለማውራት አይቻልም፤ ምክንያቱም ሲስተሙ በአብዛኛው አንድ እና ወጥ ስለሆነ፡፡

ስለተነሳሁበት የሰው ዋጋ ላወጋላችሁ የፈለግኩት መነሻዬ እነሆ፡፡ በኮንፈረንሱ ላይ የተላለፉት መልእክቶች ብዙ ቢሆኑም በተለይ እኔ ከተሳተፍኳቸው ውስጥ የሰው ሀብትን ከምንም በላይ አግዝፈው የቀረቡ ነበሩበት፡፡ ለምሳሌ በአንደኛው መድረክ ላይ የሠራተኞች ደህንነት አጠባበቅ ካነሷቸው ነጥቦች አንዱ ” ሠራተኞቻችሁን በዓመት ውስጥ ለምን ያህል ጊዜ የመዝናኛ ቦታዎች ትወስዷቸዋላችሁ?” የሚለው ቀልቤን እጅግ ሳበው፡፡ ጥያቄው ለተሳታፊዎች ቀርቦ እያንዳንዳቸው ኃላፊዎች ሀሳባቸውን ሲሰጡ በድንጋጤ ነበር የማዳምጠው፡፡ ተወያዮቹ ሠራተኞቻቸውን ሙሉ ወጪያቸውን እየሸፈኑ ለእረፍት እና ለጉብኝት በመረጧቸው፣ ከሚኖሩበት ከተማ እና ሀገር ውጪ ባሉ መዝናኛዎች እንዲሄዱ ያመቻቹላቸዋል፡፡ ከነቤተሰባቸው እንዲዝናኑ የሚያመቻቹላቸውም አሉ፡፡  ለዚህ ደግሞ የሰው ሀብት ስትራተጂያዊ እቅዳቸውን ሲሠሩ የሚያካትቱት ነው፡፡ ልክ እንደ ዋነኛ በጀታቸው በጅተው ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ሲስተሙ ነው ምን ማድረግ ይቻላል!

ይህንን የመሰለ የሲስተም ልዩነት በዚህ በአንድ ምድር ላይ መኖሩ አስገርሞኛል፡፡ እርግጥ ነው እኛ ገና ያላደግን በማደግ ላይም ያይደለን ሀገር ውስጥ የምንኖር ዜጎች ነን፡፡ ሀገራችን በጦርነት የምታወጣው ሀብት አለባት፣ በሙስና የሚዘርፏት ዜጎቿ አሉባት፣ የማይሠሩ ማለትም በሥራ ላይ ሆነው የሚቀልዱ በርካታ ዜጎችን በእቅፏ ተሸክማለች፡፡ ብቻ እንደ ሀገር ብዙ ቻይ ነች፡፡ እነሱ ጦርነት፣ ሙስና፣ የማይሠራ ሠራተኛ…ወዘተ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ሲስተሙ በጣም ጥብቅ እና ውልፍት የማያስብል ነው፡፡ ለእነሱ ሥራ ሥራ ነው፤ እረፍትም እረፍት፡፡ እኛ በስራ ሰዓት ብዙ እረፍቶች አሉን፡፡ ታድያ ያልሠራነውን ብሩስ ከየት ይመጣል! ያልዘራነውን ማፈስ አንችል!  ይሄ በዋነኝነት ችግራችን ሆኖ ሳለ አሠሪዎችም ሠርተው የማሠራት ችግር ሳይኖርባቸው ይቀራልን!? እኛ ሀገር አፈር ድሜ ግጠው ባቆሙት ድርጅት ውስጥ በሙያው ምንም እውቀት የሌላቸውን ዘመዶቻቸውን ከሰገሰጉ በኋላ “ትርፍ የለም” ብለው የሚያማርሩ፣ አልፈውም ከመንግስት ቋት የሚበደሩ፣ በኋላም መክፈል እያቃታቸው ሲቸጋገሩ የምናያቸው መዓት ናቸው እኮ!

እኔ መቼስ ቅናት የደም ዝውውሬን ርብሽብሽ አድርጎት ነው ወደ ምስኪኗ ሀገሬ የተመለስኩት፡፡ እኛው ያመሰከንናት እምዬ ኢትዮጵያ! እንኳን ቫኬሽን ማለቴ መዝናኛ ቀርቶ የዓመት እረፍትስ የሚገባን ስንቶቻችን ነን ይሆን! በተሰማራንበት የሥራ መስክ ደስተኞች ሆነን በትጋት እና በታማኝነት የምንሠራ ስንቶቻችን እንሆን! መቼስ ሙሉ በሙሉ ሠራተኛ የለም የሚለው ፍረጃ ትክክል አይደለም፡፡ ዞሮ ዞሮ ሀገሪቷ እኮ ቆማለች፤ በጥቂቶች ምሶሶነት፡፡ ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ አንዳሉት አበው/እመው  ድርጅቶቻችን ከፍለው ሽርሽር ባይወስዱንም መብታችን የሆነውን የዓመት እረፍታችንን በቅጡ የሚሰጡን ስንቶች ናቸው? ጠያቂ ሲስተም የለማ!

አንድ ግን የማይካድ ሐቅ እኔ እና መሰሎቼ ዘንድ አለ፤ በተለያዩ አጋጣሚዎች ለስልጠና፣ ለኮንፈረንስ  እና ለልምድ ልውውጥ በሚል የተለያዩ ሀገራት የመሄድ እድል የገጠመን፡፡ እኔ በዚህ እድል በመጠኑም ቢሆን ከተጠቀሙት አንዷ ስለሆንኩ ሀገሬን እና ድርጅቶቼን አመሰግናቸዋለሁ፡፡ እርግጥ ነው አንዳንድ ድርጅቶች የሚመለከታቸውን ሠራተኞች መላክ ሲገባቸው ያለአግባብ የማይመለከታቸውን (በአገም ጠቀም) እንደሚልኩ ይታማሉ፡፡ ሀብቱ ከኪሳቸው አልወጣማ!  እናም ሙሉ በሙሉ ሲስተሙ እኛ ዘንድ የለም ማለትም በልቶ ካሀጅ መሆን ነው፡፡ ይሁን እና እንደዚህ ለውይይት ሲቀርብ ደግሞ ሲስተም ውስጥ የማስገባቱ ነገር ቢታሰብበት ምን ይለናል ለማለት ነው፤ እኛም ተግተን እንሥራ፤ ድርጅቶቻችንም ይህንን ያመቻቹልን፤ ይህ ነው የመልእክቴ ጭብጥ፡፡ (የእኔ ነገር ለካስ አሁን በድርጅት አልታቀፍኩም!) በቃ ለሚመለከታቸው ይመቻችላቸው!

ይህ ለጊዜው ከመልእክትነት ይልቅ ምኞት ቢሆንም የማይሳካበት ምክንያት ግን የለም፡፡ ቀጣሪዎች ኃላፊዎችም ሆናችሁ የድርጅት ባለቤቶች ሠራተኞቻችሁ ለድርጅቱ የእኔነት ስሜት እንዲሰማችሁ መፈለጋችሁ አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ ከየትም አይመጣም፡፡  ሰው የድርጅት ውድ ሀብት ነው! ሠራተኞችን እንደ ሰው ዋጋ መስጠት፣ እኩል ማየት፣ በሙያቸው ማክበር፣ የሥራ ባህልን በድርጅቱ ማስፈን፣ አገም ጠቀምን ማስወገድ የመሳሰሉትን ከተገበራችሁ/ከተገበርን ድርጅት ያድጋል፤ ሽርሽር እና ሌሎች የደህንነት ጉዳዮች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ይቻላል፡፡ ሀገራችን ይህ ሲስተም እንዲኖራት ደግሞ የእርስ በእርስ ጦርነቱን፣ ሙሰኞችን፣ ሰነፎችን ከምድረ ገጽ ያጥፋልን! እኛም እነዚህን እኩይ ተግባራት እንፀየፋቸው!

ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

1 thought on “ሲስተሙ (ክፍል ሶስት)”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *