ሲስተሙ (ክፍል ሁለት)

የሰው ሀብት ማኔጅመንት ኮንፈረንስ ለመሳተፍ በላስቬጋስ የነበረኝ ቆይታ በድል ተጠናቅቋል፡፡ ይሁን እንጂ ይሄን ግዙፍ ሀገር ረግጦ ዘመድ አዝማድ እና ጓደኛ ያለማግኘት ብልህነት ስላይደለ ከላስቬጋስ መልስ በዲሲ እና አካባቢዎቹ ትንሽ ቆይታ እያደረግሁ ነው፡፡ እንደ እኔ አዲስ ለሆነ ሰው የሚታየው ነገር ብዛቱ! የሚታየውን ሁሉ አቅም በፈቀደ ዞር ዞር እያደረጉ እያሳዩኝ ነው፡፡ መቼስ ልምላሜ እና መንገድ የአሜሪካ ዜጎች ሳይሆኑ አይቀሩም፤ ተንሰራፍተውበት የለም እንዴ! ስለሱ ላውራ ካልኩ የተነሳሁበትን ስለምዘነጋ ስለ ሲስተሙ የጀመርኩትን ወግ ሁለት ልበላችሁ፡፡

ለመጀመርያ ጊዜ የተቀናጀ ትልቅ ኮንፈረንስ የተሳተፍኩት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2002 ዓ.ም. በአውስትራልያ ብሪስበን ከተማ ነበር፡፡ ወደ 2000 የምንሆን የወሴክማ ሰራተኞች እና አጋሮች ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የተሰባሰብንበት በሴቶች ተደግሶ፣ በሴቶች ብቻ ሲመራ የነበረ እጅግ የተቀናጀ እና ስኬታማ የነበረ ኮንፈረንስ፡፡ በዚያ ጊዜ በእኔ ደረጃ የማውቀው እና የተሳተፍኩት ኮንፈረንስ ውሱን  ከመሆኑ ባሻገር ሴቶች ብቻ ኃላፊነት ወስደው ያዘጋጁት ትልቅ መድረክ አይቼ አላውቅም ነበር፡፡ እናም ያንን የመሰለ ዝግጅት በሀገሬ ለማየት በጣም ተመኝቼ ነበር፤ እንደተመኘሁም አልቀረሁ  በ11ኛ ዓመቱ በ2013 (እ.አ.አ) የኤውብ ሜይ ፎረም ተደገሰና ወደ 500 ሰዎች በተሳተፉበት ዝግጅት ተሳተፍኩ፤ በዚያው ተጠምቄ ቀረሁ፤ ፍሬዋን እየበላሁ፡፡

የአሁኑ የላስቬጋሱ ደግሞ የበለጠ ይግረምሽ ብሎ 25000 ሰዎች የተሳተፉበት ነበር፤ እኔ እና ከእኔ ጋር የሄደውን የማህበሬ አባል ጨምሮ፡፡ እስቲ አሰቡት 25000 ሕዝብ ምን ያህል ግዙፍ እንደሆነ! እነሱ ግን አልተደነጋገራቸውም፡፡ አቀነጃጀታቸው  የትየለሌ መሰላችሁ! ኮንቬንሽን ሴንተሩ በሰሜን እና በምእራብ ተከልሎ እና ተከፋፍሎ ተሳታፊዎች ወደፈለግንበት አዳራሽ ምንም ሳንደነጋገር  እና ሳንቸገር እንድንደርስ አቅጣጫ አመላካች ተደርጎልናል፡፡ ብንደናገር እንኳን በቁጥራችን ልክ በሚመስል ሁኔታ በጎ ፈቃደኞች ተደርድረው የጠየቃቸውን መረጃ ሁሉ በመስጠት ይመሩናል፤ መታከት የለም፤ በትህትና እና በፈገግታ ማስተናገደ ብቻ!  ሌላው የሚገርመው ነገር ደግሞ የሰው ሀብት ማኔጅመንት ሶሳይቲው (SHRM) በአብዛኛው አዘጋጆቹ፣ በጎ ፈቃደኞቹ እና ተሳታፊዎቹም ጭምር ሲታይ የሴቶች ቁጥር ይበዛል፡፡ ለኢኮኖሚው እያደረጉ ያለውን አስተዋጾ ያለማድነቅ አይቻልም፡፡፡

የእኔ ቆይታ አጭር ቢሆንም ለትዝብት እንደመጣ ሰው ሁሉን በአትኩሮት እያየሁ እና እየተደመምኩ ነው፡፡ ስለሲስተሙ ሌላ ያስገረመኝ ነገር ያው በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ሕግ ማክበር ይታያል፡፡ ለማነጻጸር ቢከብድም አንዱን ገጠመኝ ላውጋችሁ፤ ከጓደኞቼ ጋር መንገድ እየሄድን ያልተጋነነ የትራፊክ መጨናነቅ ነበር፤ አረንጓዴ በርቶ በተራችን መሄድ ሲገባን ቆምን፡፡ ይህ የሆነው ቀድመው የተለቀቁት እና ከሌላ ቅያስ ቀድመውን ወደመንገዱ የገቡት በጠበቁት ፍጥነት መጓዝ ስላልቻሉ እነሱ እስኪያልፉ መጠበቅ ሲስተሙ ስለሚያስገድድ በራልኝ ብሎ ግር ብሎ መግባት የለም ማለት ነው፡፡ ከኋላ የነበሩት መኪናዎችም አንዲትም የልቀቁልኝ ጡሩምባ አልነፉም፡፡ ይህ እንዲሆን የሚያስተናግድ የትራፊክ ፖሊስም አልነበረም፡፡ በቃ እነዚያ እስኪሄዱ አረንጓዴውም ጠፋ፤ ሌሎች ተረኞች ወደየአቅጣጫቸው ተመሙ፤ እኛ ቆመን ሁለተኛ ተራ ጠበቅን፡፡ መንገዱም ክፍት ሲሆን ሄድን፡፡ ይሄ ሁሉ የደቂቃዎች ሰላማዊ ትእይንት ነበር ቀልቤን የሳበው፡፡ ይህ አጋጣሚ በእኛ ሀገር ሲገጥምስ? አረንጓዴ መብራት ስለበራ ብቻ መብታችን ነው ብለን ካላለፍን እንላለን፤ ከፊታችን የቀደሙት መኪኖች ላይ ጡሩምባ አንነፋለን መሄጃ እንደሌላቸው እያወቅን፤ መንገዱ ይዘጋጋል፤ ብዙ ጡሩምባዎች ይጮሀሉ፤ አንገቶች ለስድብ እና ለግብረ መልስ በመስኮት ይወጣሉ፤ አስፋልቱ የተረበሸ ከተማ ሆኖ ያርፋል፡፡ ትራፊክ ፖሊሶች ለማስተባበር ቢሞክሩም ሁሉ ቦታ የሉም፣ አንዳንዴ እነሱም ይደክማቸዋል መሰለኝ ቆመው ትእይንቱን ያያሉ፡፡  እና የሁለት አለም ሰዎች መሆናችን ግርምርም ብሎኛል፡፡ እኛ ሲስተሙ የሌለን እነሱ ግን ያላቸው፡፡ ይሄ አንዱ እይታዬ ነው፡፡

ሲስተሙ የሰጣቸውን ሕግ ማክበራቸው መከባበርን ስላተረፈላቸው ሕይወት ቀለል አድርጎላቸዋል፡፡ በየተሰማሩበት ሥራ ትሁቶች ናቸው፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩላችሁ ኮንፈረንሱን ሲያገለግሉ ከነበሩት ሠራተኞች ይልቅ በጎ ፈቃደኞች ይበዙ ነበር፡፡ እንኳን የመደናገር ዓይን አሳይታችሁ እንዲሁ እንኳን ምን እንርዳችሁ ሲሉ ነበር የከረሙት፡፡ ሥራቸው እንግዶችን ማገዝ ስለነበር ሌላ ሥራ ደርበው አይሠሩም፤ ሰዓታቸው እስኪያልቅ ዓይናቸው፣ ልባቸው ብቻ ሙሉ ቀለባቸው ከአኛ ከእንግዶች ጋር ብቻ፡፡ በዚያ ላይ የተጠየቁትን አመላክተው ሲያበቁ መልካም ቆይታ፣ መልካም ቀን የሚሉትን ቃላት በፈገግታ አጅበው ይመርቁላችኋል፡፡ ያው ማነጻጸሬ እንድንማርበትም አይደል! ወደ እኛዎቹ አገልጋዮች እንይ እስቲ! ሁለት ሶስት ሆነው ከቆሙ በወሬ እና በስልክ የሚጠመዱትን ነገር አስታውሱ፤ ከዚያስ ሲጠየቁ “ረበሽኝ እኮ!” በሚል ስሜት ይገላመጣሉ፤ ከሰጡም ሙሉ መረጃ ላይሆን ይችላል፡፡ ለሱም ደግሞ ሥራቸው እንደሆነ ሳይሆን እንደተባበሩን በመቁጠር ምስጋናው ከእኛ ይጠበቃል፡፡ ብቻ በሥራም ሆነ በባህርይ ሲስተሙ እነሱን ድንቅ አድርጓቸዋል፡፡ በእኛ እና ለእኛ እየሆነ ላለው ግን እውነቴን ነው ያለምንም ማጋነን ሥራን ነፍስ ይማር ብዬዋለሁ፡፡ ታድያ የሆንነውን ብንሆንስ ምን ይደንቃል!  ሥራ ቢያቅተን እንኳን በትህትና ማሸነፍ እንዳንችል አንዳች ጋንጩር አለብን፤ የማያስፈግግ፣ የሚያነጫንጭ፤ በአጠቃላይ የሚያሰናንፍ፡፡ ትህትና የበታችነት የሚመስለንም በጣም ብዙዎች ነን፡፡ ድሮ ድሮ እማይዬ ነፍሷን ይማረው እና “ኩራት ቁርሰ፣ ምሳ እራት አይሆንም” የምትለው አባባል ነበር፡፡ ታድያ እኔ “እማይዬ ኩራት እራት አይሆንም ነው የሚባለው እኮ ቁርስና ምሳን አይጨምርም!?” ስላት ደስ የሚል መልስ ነበራት፤ ለምንም ለማንም ስለማይበጅ መሆኑን አስረግጣ ታስረዳኝ ነበር፡፡ እንደውም ባዶ ኩራት የበታችነት ስሜት ውጤት መሆኑንም ጭምር፡፡

ከሁሉም በላይ የእነዚህ የኮንፈረንሱ አዘጋጆችም ሆነ የነዋሪዎቹ ስነ ምግባር እና ለሲስተሙ መገዛት ለሀገራቸው ምን ያህል ገንዘብ ይዞ እንደሚመጣ አስቡት፤ የተፈጠረውስ የሥራ እድል ቀላል ነው እንዴ! ሥራቸውን አክብረው ለሲስተማቸው ተገዝተው በመኖራቸው ሀብት ችግራቸው አይደለም፡፡ በልካቸው ይኖራሉ፡፡ እኛስ ልካችን እንደእነሱ ያለመኖር ይሆን? መከባበር፣ ትህትና፣ ሥራ ማክበር የአለት ከእለት እንቅቃሴአቸው አካል ናቸው፡፡ ይሄኔ ሌላም ያላየሁት ማንነት አላቸው፡፡በእርግጥ  ለእኛ አስደንጋጭ የሆኑ ልምምዶችም አላቸው፤ ትውልድ ላይ እያደረጉት ያሏቸው፡፡ ለእኛ የሚያስተምሩ እና የሚጠቅሙንን መርጬ አወጋኋችሁ እንጂ፡፡ የማይመለከተኝን እዘለዋለሁ፡፡

እንደ ማጠቃለያ ሀሳቤን ልሰብስብ እና ቢሆን የምለውን ላጋራችሁ፡፡ በሀገራችን በየትኛውም ተቋም ሄደን በትህትና፣ በሰዓት እንዲሁም በትጋት ተስተናግደን እና ጉዳይ አስፈጽመን ለመውጣት የሕልም እንጀራ ያህል ነው፤ ከምኞት በስተቀር የማይበላ፡፡ ደግሞ አኮ መመርያዎች እና ደንቦች ደግሞ በጽሑፍ ከአቅማቸው በላይ ተሰድረዋል፡፡ ማንም አይፈጽማቻም፤ አያስፈጽማቻም፡፡ ክፍተቱ እየታወቀ እንኳን ለለስልጠና የሚመደበው በጀት ከጠቅላላው 2% ከበዛም 5% ነው፤ እሱም ትክክለኛው ስልጠና፣ ትክክለኛው ሰልጣኝ እና አሰልጣኝ ሳይገናኙ ባክኖ ያልቃል፡፡ እናም በተለይ ይህንን የምታነቡ የኤውብ ቤተሰቦች ሴት መሪዎች እና ሲኢኦዎች ካላችሁ እራሳችሁን ጨምሮ ሠራተኞቻችሁን ደንበኛ አገልግሎት (Customer Service) ስልጠና ብታገኙ እና አሁን ያለውን አገልግሎታችሁን ተምሳሌት ብታደርጉት ቀላል ለውጥ አይሆንም፡፡  እኛ ከእኛ አንጀምር፤ ቢያንስ የእራሳችንን ቢዝነስ እናሳድጋለን፡፡ ሀገራችን ደግሞ ከት/ቤት ጀምሮ ቢሠራበት ለውጥ ይመጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ ያንን የሚያደርግ የትምህርት መሪ ያምጣልን፡፡ ለውጡን በእኛ ዘመን ባንደርስበትም ልጆቻችንንም  ኃላፊነት ወስደን እናሰልጥን፤ ስልጡን ዜጎች ይሆኑ ዘንድ፤ አለበለዝያ እንደ እኛ አይነቱን ኑሮ እንዲደግሙት እየፈረድንባቸው ነው፡፡ መልካም ሥራ በመልካምነት እየሠራችሁ ያላችሁትን ያብዛልን! ለዛሬ አበቃሁ!

Share on your socials!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *