ሥራ እና ሀሜት

በአንድ መ/ቤት አብረን እንሰራ የነበረ የቀድሞ ባልደረባዬን ከዓመታት በኋላ አገኘሁት፡፡ እድሜው ከመጨመሩ እና ገጽታውን ከመቀየሩ በስተቀር ባህርዩ እድገቱን ተከትሎ የተሻሻለ አይመስልም፡፡ በ \”የሕይወቴ ቅኝት\” መጽሐፌ ውስጥ የመ/ቤት ሰዎች ባህርይ ስዘረዝር አንደኛው የእሱ ነበር፡፡ ለመጽሐፌም ግብአት ሆኖኛል ማለቴ ነው፡፡

ይሄ ባልደረባዬ ምን ያደርግ ነበር መሰላችሁ፤ በጠዋት ቢሮ ለመግባት ማንም አይቀድመውም ነበር፡፡ አስታውሳለሁ የሚጠቀመው አንበሳ አውቶቡስን ነበር እናም ሁልጊዜ የመጀመርያዋን አውቶቡስ ተሳፍሮ መ/ቤት ግቢ ውስጥ ከጽዳት ሰራተኞች ሳይቀር ቀድሞ የሚገባው እሱ ነበር፡፡ ታድያ በጠዋት መግባቱን የሚጠቀምበት ለሥራ ሳይሆን ለመረጃ መሰብሰብያ ነው፡፡ የመግቡያ ሰዓት ላይ እየተንጠባጠብን ከምንደርሰው ሰራተኞች ቢሮ በጠዋት እየገባ በወሬ ይጠምደናል፤ \”የእንትናን ጉድ ሰማሽ? እሷማ/እሱማ ምን ሆነ/ች መሰለሽ… እንትና ደግሞ ከማን ተሸሎ/ላ ነው… ያ ማነው ስሙ ምን ሆኖ ነው እንዲህ የሚለጥጠው…ወዘተ፡፡ በቃ ሥራችንን ሳንጀምር በወሬ ስልችት ያደርገናል፡፡ ከዚያማ ልክ አለቃችን ሲገቡ እጅ የሚነሳ መስሎ ገብቶ የቃረመውን ያቀብላል፡፡ ታድያ ከእኔና ከመሰሎቼ ብዙም መረጃ ስለማያገኝ እኛን ለመወስወስ እና ያገኛትን ታህል ለማግኘት እንደ ቀብድ የሌሎችን ሰዎች መረጃ ዘርግፎ ይሰጠናል፡፡ ያው ያማልናል ማለት ነው፡፡ ወሬ ቀምሞ ከማውራቱ የተነሳ ያለውዴታቸው የሀሜት ሱሰ ያስያዛቸው እንደነበሩ ትዝ ይለኛል፤ እሱን ካላገኙና ካልቃረሙ ስራው የማይሳለጥላቸው፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ ከእሱ ጋር የሚታይ ሰው አንድም መረጃ እየሰበሰበ ነው አልያም መረጃ እየታለበ ነው፡፡

በተለይ ኃላፊዎች ለመረጃ ማሰባሰብ በራቸውን ክፍት ስለሚያደርጉለት የተለየ የተፈላጊነት ስሜት ይሰማው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በዚህ የተነሳ ባህርዩ ለእንደ እኔ ላለነው ብዙም የሚመች አልነበረም፡፡ እኔ በመ/ቤቶቼ ሰራተኛ በነበርኩ ጊዜ ስለ ሰዎች እራሳቸው ሰዎቹ ከሚነግሩኝ ውጪ እና በጣም ቅርበት ካለኝ የሥራ ጓደኞቼ  በስተቀር  የሌላ ሰው ወሬ ወይንም ሀሜት መስማትም ማውራትም አልፈልግም ነበር፡፡

ታድያ ይህ ሰው የትምህርት ደረጃ ወይም ሙያ ሳያንሰው፣ የሥራ ዘመኑን ሰርቶ ሳያሳይበት፣ እውቀትና ልምድ ሳያካብትበት፣ በዚሁ በባህርዩ ምክንያትም ከጊዚያዊ መሳርያነት ባለፈ ለእድገቱ የሚጠቅም ነገር ሳያገኝ አሁን ላይ የከሰረ ጡረተኛ ሆኗል፡፡ እንደዚያ ሳይጠሩት አቤት እያለ ሳምሶናይታቸውን ተቀብሎ መረጃ ወይም ሀሜት እየሰጠ ይሸኛቸው የነበሩት አለቆች አልጠቀሙትም፤ ምናልባትም በዚያች ወቅት ብቻ ተጠቅመውበት ይሆናል እንጂ፡፡ እንደ አገልግሎቱ ጓደኞች አላፈራም፤ አሁንም ግን በቁጭት አልተለወጠም፡፡ ከስንት ዘመን በኋላ ሳገኘው የረባ እንኳን ሰላምታ ሳንለዋወጥ በዚያን ጊዜ ይጠቀምበት በነበረው ቋንቋ ስለማላገኛቸው እና ግማሾቹንም ስለረሳኋቸው ሰዎች ወሬ ሊጀምርልኝ ሲል ቅንጣት ይሉኝታና እፍረት ሳይሰማኝ ነበር ያስቆምኩት፡፡ በነገራችን ላይ ይህንን ሰው አልኩ እንጂ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ብዙ አሉ፡፡  አይ አጉል አመል!

መቼስ የጥንቱ የሥራ ባልደረባዬ ባለውለታዬም ነው፤ ቢያንስ ወደኋላ ሄጄ የተለያዩ ቢሮዎች ውስጥ የነበሩ እንደ እሱ በወሬ እና በሀሜት ይተዳደሩ የነበሩትን ሰራተኞች አስታወሰኝ፤ ዛሬ ለእናንተ የማስተላልፈው መልእክትም አቀበለኝ፡፡ በሚገርም ሁኔታ በሰራሁባቸው መስሪያ ቤቶች ሁሉ ማለት እችላለሁ እንደዚህ ያሉ ሰርተው በስራቸው ከሚታወቁ በሀሜተኝነታቸው የሚታወቁ በተለይ ደግሞ ለኃላፊዎች እንደ እንባ ጠባቂ ዓይነት የነበሩ ሰራተኞች ነበሩ፡፡ እነዚህን ሰዎች በልዩነት የሚያመሳስላቸው ቴክኒካል እውቀት ላይ ክፍተት ያላቸው መሆናቸው ነው፡፡ ምናልባትም በአብዛኛው ጊዜ ፍትሀዊ የሆነ የሥራ ምዘና ስለማይደረግ እድሜያቸውን አራዝመዋል፤ አንዳንዱ ኃላፊማ ከቦታው ሲነሳ እንደ አደራ ልጅ ለቀጣዩም ያስረክባቸዋል፡፡ ግን የሚያሳዝነው ከዚያ መ/ቤት ውጭ በሌላ መ/ቤት ለተሸለ የሥራ መደብ ተወዳድረው እንዳይገቡ እንኳን እነዚያ ኃላፊዎች ቢያንስ እንዲማሩና እንዲሻሻሉ አልያም ስራቸውን በትጋት እንዲሰሩ አላበቋቸውም፡፡ ስለሆነም ብዙ ጊዜ ነጭናጫ፣ አጉረምራሚና የባከኑ ናቸው፡፡

በተቃራኒው ደግሞ በሥራ ዘመናቸው ጠንካራ ሠራተኞች የነበሩ ሙያተኞች (ፕፌሽናሎች) በጡረታ ዘመናቸው እንደውም የተሻለ ተከፋይ እና ተፈላጊ የሚያደርጋቸውን ሥራ እየሰሩ የሚገኙ ጥቂት አይደሉም፡፡ መሆን የምንፈልገውን የምንሆነው በምርጫ ነው፡፡ ለእኔ እነዚህኞቹ አርአያዎቼ ናቸው፡፡

የዛሬ መልእክቴ ገጸ ባህርይ የድሮ የሥራ ባልደረባዬ ይሁን እንጂ ዋና መልእክቴ እሱ አይደለም፡፡ መልእክቴ በተለይ ለወጣቶች እና አዲስ ሥራ ለምትጀምሩ እንደእነዚህ ሰዎች የባከናችሁ እንዳትሆኑ ነው፡፡ ቁሳዊ ሀብት ሲባክን ከእለታት አንድ ቀን ጥሩ አመራር ሲገኝና ሥርዓቱ (ሲስተሙ) ሲሻሻል በሌላ ቁስ ይተካል፡፡ ነገር ግን እኛ የሰው ሀብቶች ስንባክን ለባከነው ጊዚያችን፣ እድሚያችን በአጠቃላይ ማንነታችን መተክያ የለንም፡፡ ምናልባት እኛ ባክነን ስንቀር በአዲስ ሰዎች እንተካ እንደሆነ እንጂ፡፡

የሥራ (የቢሮ) አካባቢ ሀሜት ሱስ ያስይዛል፡፡ ማንኛውም ነገር ደግሞ ሱስ ከሆነ አያሳድግም፣ አያሻሽልም፣ ሕይወት አይለውጥም፡፡ ሀሜተኛ ሰራተኞች የሰው መጠቀምያ እንጂ ለራሳቸው የሚጠቀሙት ነገር የለም፤ ካለም እጅግ ጊዚያዊ ነው፡፡ አንድ ሰራተኛ ደግሞ ትጉህ ሰራተኛ የሚያሰኘው/የሚያሰኛት እና ለትክክለኛ እድገት እጩ የሚያደርገው/ጋት በሥራቸው የሚያስመዘግቡት ውጤት ላይ የሚያሳዩት ስነ ምግባር ተደምሮ ነው፡፡ እናም ሀሜትን እንፀየፈው! በሥራችን እና በሥነምግባራችን ብቻ ተለይተን እንታወቅ!