ሙስና ግን ይጣፍጣል እኮ¡

ወቅቱ የትንሳኤ በዓል ዋዜማ ነበርና አንዱ የድርጅታችን ደንበኛ የነበረ ዕቃ አቅራቢ (ነጋዴ) ለኃላፊያችን የምግብ ቅቤ ይዞላቸው ይመጣል፡፡ ነጋዴው ኃላፊያችንን ከቢሮአቸው ያጣቸዋል፡፡ እንዲያው ስገምት ሁለቱ የቢሮአችን ፀሐፊዎቻቸው ያልተረከቡት ሆነ ብለው እኔ እንዳውቅ (እንዳየው) ስለፈለጉ ይመስለኛል፤ ይህ የሆነው እኔና ኃላፊያች በስራም በባህርይም የማንግባባ ይልቁንም አንዳችን የሌላችንን ስህተት አድፍጠን የምንጠባበቅ ሰዎች ስለነበርን ይመስለኛል፡፡ በዚያ ላይ ኃላፊያችን ከሁላችንም ጋር ፀብ ያለሽ በዳቦ አይነት ጨዋታ ላይ ነበሩ፡፡ እናም ፀሐፊዎቹ ”እኛን ስለማያምኑን ፍፁም ቢሮ ሂድና ስጣት፤ እሷ ትሰጥልሀለች” ይሉታል፡፡ ቅቤውን ዝም ብዬ ተቀብዬ ልሸኘው አልወደድኩም ነበርና ትንሽ ተጨዋወትን፡-
እኔ፡- ኃላፊያችን (ስማቸውን እየጠራሁ) ቅቤ ግዛልኝ ብለውህ ነው?
ነጋዴው፡- እኔ እኮ ትልቅ የቅቤ ንግድ አለኝ አታውቂም እንዴ? ከፈለግሽ ላምጣልሽ? (የተደራረበውብ ላስቲክ ከአናቱ ሸንቁሮ እየቆነጠረ) ይሄ ደግሞ ለጋ ነው አሽቺው!
እኔ፡- ኸረ እኔ ለጋና ብስል ቅቤ በማሽተት አልለይም! ግን ለጋ ቅቤ በኪሎ ዋጋው ስንት ነው? (ስጦታውን በብር ለመተመን)
ነጋዴው፡- እንዴ ደግሞ ከእናንተ ሒሳብ እቀበላለሁ እንዴ! የበዓል ስጦታዬ እኮ ነው!
እኔ፡- ውይ አላወቅኩም! ለእሳቸውም ይህንን ሁሉ ቅቤ በስጦታ ነው ያመጣህላቸው?
ነጋዴው፡- እንዴ ይቺ ምን አላት! አምስት ኪሎ ብቻ እኮ ናት! አንቺም ከፈለግሽ አመጣልሻለሁ!
እኔ፡- (ቅቤውን ተቀብዬ ለኃላፊዬ በአደራ ካስቀመጥኩ በኋላ ሳቄን አፍኜ) እኔ እንኳን እሳቸው ቤት ሄጄ እበላለሁ!
ነጋዴው፡ እንዴ እኛ እያለን! ምን በወጣሽ፤ አሁን ነው በሹፌር የምልክልሽ፡፡
እኔ፡- (በወቅቱ 5 ኪሎ ቅቤ የሚያጓጓ መሆኑን ልቤ እያወቀው) ኸረ በጭራሽ! ደመወዜ እኮ ለቅቤ መግዣ ከበቂ በላይ ነው፡፡ ለማንኛውም መልእክትህን አደርስልሀለሁ! በማለት ቆፍጠን ብዬ አሰናበትኩት፡፡
ኃላፊያችን ሲመጡ ወደ ቢሯቸው በመሄድ (ሳቄን አፍኜ) ” እነሆ የእርስዎ ቅቤ ነው፤ እከሌ የሚባለው ነጋዴ ”ለዓመት በዓልህ በጠየቅከኝ እና ቃል በገባሁልህ መሰረት አምጥቼልሀለሁ ብሏል” ብዬ የእንግዳ መቀበያ ጠረጴዛቸው ላይ ዘጭ አድርጌ አስቀመጥኩላቸው፡፡ ኃላፊያችን (ብስጭታቸው ይታወቅባቸዋል) “አንቺ ጋር ምን ሊያደርግ አመጣው? ነው ወይንስ አንቺም አዝዘሽው ነበር?” አሉኝ አጃቢ ሙሰኛ ፈልገውና ብቸኛ ያለመሆናቸውን ለማረጋገጥ፡፡
እኔም (እያማተብሁ) “ኸረ በስመ አብ ይበሉ! ደግሞ ለመ/ቤት ዕቃ አቅራቢ “ቅቤ አምጣልኝ” የምለው ቆሜ ነው ሞቼ?” በማለት ነውራቸውን ለማጉላት በቀለሉኝ ልክ ተሳለቅኩባቸው እና ቢሯቸውን ለቅቄ ወጣሁ፡፡ ያን ጊዜ ኃላፊያችን በተነቃብኝ ስሜት ወድያው ነጋዴው ጋር ደውለው በማመስገን ፋንታ ቅቤውን እኔ ዘንድ መስጠቱ አግባብ እንዳልነበር አስረግጠው እንደጮኹበት ፀሐፊዎቹ ነገሩኝ፡፡ ስጦታ መቀበል በግዥ ሙያ “የጥቅም ግጭት- conflict of interest” ስለሚያስከትል ያስጠይቃል፡፡ ግን በዚያን ዘመን ”የቅቤ ጉቦ ተቀበለ” ብሎ አንድ ትልቅ ቢሮን የሚመራ ኃላፊን ማጋለጥ ለእኛም ከሙያችን አንፃር ስላነሰብን አለፍነው፡፡ እያለ ገጠመኙም ታሪኩም ይቀጥላል፡፡
ይህ ከላይ የተረኩላችሁ “የሕይወቴ ቅኝት” ከሚለው መጽሐፌ ስለሙስና ከጻፍኩት እውነተኛ ገጠመኝ አንዱ ነው፡፡ በግዢ ኃላፊነት ባገለገልኩበት ዘመኔ በግዢ ሰበብ የሚደረገውን ሌብነት (ሙስና) ለማስቀመጥ ሞክሪያለሁ፡፡ እኔ የማውቀው በግዢ ብቻ ያለውን እንጂማ ጣፋጩ ሙስና የተለያየ ፍሌቨር ያለው ብዙ አይነት ነው፡፡ ለነገሩ እኮ ሙስና ባይጣፍጥ ነው የሚገርመኝ፡፡ አስባችሁታል መንግስት ወይንም መንግስታዊ ያልሆነ መ/ቤት እየሰራችሁ ደመወዛችሁ ከወር እስከወር ለመድረስ በሰቀቀን ሲጨርሳችሁ እንዲህ ያሉ የቅቤ ነጋዴዎች የደረቀ አንጀታችሁን በቅቤ ሲያረሰርሷችሁ!? እንዴ አይደለም የመ/ቤቱን ንብረት መ/ቤቱንስ እራሱን ቢወስዱት! እናንተ እንደሆነ ቅቤ አላችሁ! ማን ያውቃል ጤፉም አስቀድሞ ተጭኖ ገብቶ ይሆናል! ይሄ እንግዲህ ለከስከስ ያለው የጓዳ ጎድጓዳ ሙስና እንጂ በጣም በትልልቁ የሚፈፀሙ ሙስናዎች ሲፈፀሙ በአይናችን ባናይም በጆሯችን እንሰማለን፤ የኑሮ ደረጃ ለውጦችም ሲመሰክሩ እናስተውላለን፡፡ ትናንትና አንድ ጃኬት ወር እስከወር ከመልበሱ ብዛት ከእሩቅ ነጥላችሁ የምታውቁት ሰውዬ ከጥቂት አመታት በኋላ የሆነ በቀን ሳይቀር መብራት በመብራት የሆነ መኪና ሲያሽከረክር ታገኙታላችሁ፡፡ እሱ ሲገርማችሁ የትልቅ ሕንጻ/ሕንጻዎች ባለቤት ሆኖ ሕንጻው ጫፍ ላይ ያለው ቢሮው ላይ ሲገማሸር ታገኙታላችሁ፡፡ ታድያ ሙስና ይጣፍጣል ቢባል ውሸት አለው!? እኮ! የለውም! የሚያሳዝነው በግዢ ስርዓት ውስጥ በኃላፊነትም ይሁን በሰራተኝነት የሚያልፉ ከሙስና የፀዱ ቁጥራቸው ኢምንት ስለሆነ በቃ ግዢ ካለ ሙስና አለ አራት ነጥብ!
በሀገራችን እንደ ድህነት ያለ ከባድ ጠላት የለንም፡፡ ድህነት ደግሞ እንደዚህ በተናጠል ለግል ጥቅማቸው የሚሮጡ ሰዎችን በሙስና እንዲዘፈቁ ያበረታታል፤ ይደግፋል፤ ምክንያቱም የተናጠሉት ሰዎች አብረውና ተባብረው ለሀገር የሚበጅ ስራ ቢሰሩ ገጽታ ይቀየራላ! ድህነት ከምድረ ገጽ ይጠፋላ! ከምድረገጽ መጥፋትን ደግሞ እንኳን ግዙፉ ድህነት ይቅርና ትንሽዬዋ ትንኝም የምትፈልገው አይመስለኝም፡፡ ሁሉም ተንሰራፍቶ ለመኖር ይፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያን የመሰለች ሀገር እንዲህ በየመስሪያቤቱ እና በንግድ ተቋማት አማካይነት በከፍተኛ ደረጃ በሙስና እየተጋጠች ነው ያለችው፤ ተግጣ ያለማለቋ እራሱ ተአምራታዊ ጥንካሬዋን የሚያሳይ ነው፡፡ ይሁንና ዛሬ የቆመች የሚመስለን ሀገር ነገ አበዳሪዎቿ በባለእዳነት ሲያዋክቧት ተንገጫግጫ መውደቅ ይቀርላት አይመስለኝም፡፡ አሁንስ ቆማለች ወይ ለምትሉኝ መልስ የለኝም፡፡ ግን ያው በሙሰኞች ምክንያት አዘቅት ውስጥ እየኖርን እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡
በተለያዩ መ/ቤቶች ስሰራ ድሮ ድሮ ሙስና በመብላት ይታሙ የነበሩ ሰዎች ብዙዎቹ የት እንደደረሱ አይታወቅም፡፡ በእርግጥ በሰላም እየኖሩ ይሆናል፡፡ ግን የሰረቀ ሰው በሰላም ይኖራል የሚል እምነትም የለኝም፡፡ እነሱስ ቢሆኑ ሞራሉን ከየት ያመጡታል! በዘረፉት ገንዘብ ልጆቻቸውን የተሻለ ት/ቤት አስተምረው የተሻሉ የሚባሉ ሀገራት ልከውም ከፍተኛ ትምህርታቸውን እያስተማሩ ይሆናል፤ ሕንጻ ሰርተው እያከራዩ ከፍተኛ ገቢ እያገኙም ይሆናል፣ ጥሬ ስጋ አፍቃሪዎች የነበሩ ስለሚበዙበት በየቀኑ እየቆረጡ ውስኪም እየጠጡ ሊሆን ይችላል፤ በሕይወት የሌሉም አሉ በቃ ጨክነው ጥለውት የሄዱ! (እነሱስ ምስኪኖች!)
እኔ በበኩሌ ሙስና ከሚበላ ወይም ከበላ ሰው ይልቅ የተፀየፈ እና በስርዓት እና በልክ የኖረ ሰው የበዛ ነጻነት እንዳለው አምናለሁ፡፡ ነጻነት ደግሞ የአካል ብቻ ሳይሆን የህሊና ነጻነት ያውም በእራሱ የሚዳኘው! ሄዶ ሄዶ ከ100 ለማያልፍ እድሜ ዘርፎ ከመክበር በንጽሕና ምጥን ያለች ኑሮ በሰላም ማለፍ ከምር ሰላም አለው! አቦ ለጊዜው ከሚወሰውስ እና ከሚጣፍጥ ሙስና ይጠብቀን! አሜን በሉ ግድየላችሁም! ለዛሬ ጨርሻለሁ!
የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም
Share with your Circle!
