ሙሉ ሴት?!

ልክ ርእሴን ስታነቡ \”ግማሽ ሴት አለ እንዴ?; ሳትሉኝ አትቀሩም፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በአንደኛው መ/ቤቴ ተቀጥሬ ስራ እንደጀመርኩ ስለመ/ቤቱ በአጠቃላይ የሚያስተዋውቀኝ ሂደት (orientation) ላይ እያለሁ  የገጠመኝን መነሻ አድርጌ ላውጋችሁ፡፡ ድርጅቱ መንግስታዊ ያልሆነ ዓለም አቀፍ ድርጅት ስለነበር ዜግነታቸው ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ሰራተኞች ነበሩ፡፡ ከእነዚያ ውስጥ አንደኛዋ ቋሚ ምድቧ ኢትዮጵያ ሳይሆን  የፕሮግራም ክፍተት ለመሙላት በጊዚያዊነት ወይም በተለመደው አጠራሩ በሁለተኛ ሰራተኛነት (Secondment) የመጣች ነበረች፡፡  እናም ከጥቂት ቀናት መለማመድ በኋላም \” ገና እንዳየሁሽ እና በመጨባበጥ ሰላምታ እደተለዋወጥን ነበር ይህቺ ሴት ለየት ትላለች ያልኩት\”  አለችኝ፡፡

በዚህ አባባሏ የተነሳ ተቀራርበን በማክያቶ ዙርያ የሕይወት ልምድ መለዋወጥ ጀመርን እና  ገና ስንተዋወቅ \”ለየት ያልሽ ነሽ\” ያለችበትን ምክንያት ጠየቅኳት፡፡ ያንን ለማስረዳት አንድ መጽሐፍ  ከአዋሰችኝ በኋላ \”በይ በደንብ አንብቢው እና እንወያይበታለን\” አለችኝ፡፡ ያቺ ሴት በኢትዮጵያ ቆይታዋ ቢሮ ውስጥ  አልያም  በአረፈችበት ሆቴል የሚሰሩትን ሴቶች ካጤነች በኋላ  የዚያ መጽሐፍ ጸሐፊ ጭራሽ ጥናቷን ያደረገችው በኢትዮጵያ ሴቶች እስኪመስላት መገረሟን ነበር የተረከችልኝ፡፡  በእርግጥ እሷ ያደገችበትም ማህበረሰብ ከእኛ ብዙ የራቀ አልነበረም፡፡ ነገር ግን የእኛን ሴቶች በአጠቃላይ ቢሮ ውስጥ የምናሳየውን ባህርይ (Character) ስታይ  ተገርማ ነበርና ልታጋራኝ ፈልጋ ነው፡፡

አዲስ መ/ቤት ሥራ መለማመድ፣ ሰው መለማመድ እና ወደ ሲስተሙ መቀላቀል ዋናው ግዴታዬ ሆኖ ሳለ እሷም መሄጃዋ ደርሶ መጽሐፉን አንብቤ ሳልጨርስ እና ሳንወያይ እንዳንቀር ሌላ ጉጉት ፈጥሮብኝ ስለነበር ሌሊት እየተነሳሁ ፈተና እንዳጣደፈው ተማሪ አነበብኩት እና ጨርሼ ለውይይቱ ደረስኩ፡፡

የመጽሐፉ ርእስ  \”NICE GIRLS DON’T GET THE CORNER OFFICE: 101 Unconscious Mistakes Women Make That Sabotage Their Careers” የሚል ሲሆን ጸሐፊዋ ዶ/ር ሎዊስ ፒ. ፍራንኬል ትባላለች፡፡  አሰልጣኝና የሕይወት ክህሎት አስተማሪ ናት መጽሐፏ ጥናታዊ ይዘት ሲኖረው እኛ ሙያተኛ ወይንም ቢሮ ውስጥ የምንውል ሴቶች ያለማወቅ ስለምንፈጽማቸው 101 ስህተቶች እና መፍትሔ ያቸው (Tip) ትተነትናለች፡፡   መነሻ ሀሳቧ በአጠቃላይ ሴቶች የሆንነውን ሆነን እንድናድግ በማህበረሰባችን፣ በባህላችን፣ በኃይማኖት ተቋማት እና በኢኮኖሚ ደረጃችን ከወንድ አቻዎቻችን አነስ እንድንል ጫና ተደርጎብናል የሚል ነው፡፡ ስለዚህም አንዲት ሴት ሙሉ ሴት ሆና ሳለች  እንደ ልጃገረድ (girlish) ባህርይ ታሳያለች፡፡ ምክንያቱም የልጃገረድ ባህርይ ያላትን ሴት ወንዶች ይወዷታል፤ ይንከባከቧታልም፡፡ ይህ እንክብካቤ የምቾት ቀጠና (comfort zone) ውስጥ እንድትሆን ያደርጋታል፡፡  ስለዙህም በስራዋ ወይም በሙያዋ ላይ ፈታኝ የሆኑ ሥራዎችን (Challenging tasks) እራሷን ችላ የማትወስድና የማትወጣ፣ ብሎም ለኃላፊነት የማትበቃ ተደርጋ ትወሰዳለች ትላለች፡፡

ዶ/ር ፍራንኬል ምንም እንኳን መነሻው ከላይ የጠቀስኳቸው አካላት ለእኛ ለሴቶች የጫኑብን ቢሆኑም ቅሉ እኛም እንደወረደ ከመቀበል ይልቅ ብዙዎቻችን እራሳችንን ለማውጣት ጥረት ስናደርግ አንታይም ትላለች፡፡  ምክንያቱም ሙሉ ሴት ስንሆን  የመጎልበት (empowered) የመሆን ባህርይና ተግባር ስለምንላበስ በወንድ ይመስሉናል፤ ምቾት የማንሰጥ ኃይለኞች ተደርገን ስለምንፈረጅ ያንን መባልን እንፈራዋለን ትላለች፡፡ በነገራችን ላይ እሷ ከዚህ መረብ ወጥታ፣ ሙሉ ሴት ሆና፣ ጎልብታ፣ ምርምር አድርጋ በመጽሐፍት ከማጋራት አልፋ አሰልጣኝ ሆናለች፡፡ መልእክቷ ለእኛ ሙሉ ሴት መሆን ላልቻልነው ነው፡፡

እንግዲህ \”ሙሉ ሴት መሆን አልቻላችሁም\” ያለችንን የጽሑፏ የመግቢያ ትንታኔ  እስቲ ሁላችንም በውስጡ እራሳችንን እንይበት፡፡ ብዞዎቻችን ሴቶች በቢሮ አካባቢ ከወንድ አቻዎቻችን እኩል እንደማንችል ሲነገረን መቻላችንን ቆፍጠን ብለን ከማሳየት ይልቅ \”አትችይውም፣ ይከብድሻል፣ ይበዛብሻል….\” በሚሉን ጊዜ አዘኔታ ስለሚመስለን መስማማታችንን በመለሳለስ፣ በመሽኮርመም፣ በፈሪነት ወይም በእንክብካቤ ፈላጊነት ስሜት እንገልጸዋለን፤ በመሆኑም ፈታኝ (challenging) የሆኑት ስራዎች ለወንዶቹ ይሰጡና ቀለል ቀለል ያለው ለእኛ ለሴቶቹ ይተዋሉ፡፡ ይህ እንደሙሉ ሴት ሳይሆን እንደ ትንሽ ሴት (girlish) የምናሳየው ባህርያችን  ኃላፊነት መውሰድ የማንችል፣ ቁርጠኛ (Assertive) ያልሆንን እና የአመራር ብቃት የጎደለን ሆነን እንድንፈረጅ አስተዋጾ አድርጓል ትለናለች፡፡ በመሆኑም  የተሻለ የሥራ እድገት ሲመጣ በሙያ አቻችን ለሆነው ለወንዱ  ይሰጠዋልል፡፡ እንግዲህ ይህ ጥናት ቁጥራቸው በጣም ዝቅተኛ የሆኑትን ያወቁበትን ቁርጠኛ (Assertive) ሴቶች አያካትትም፡፡

የጸሐፊዋን ጥናት እስቲ ከእራሳችን የዘውትር  የሥራ ባህርይ ጋር አያይዘን  እንመልከተው!? የመስክ ስራ የሚያስፈልገው ሙያ ላይ ያለን፣ የጉልበት ስራ የሚያስፈልገው የግንባታ ሙያ፣ ማሽን መፈታታትና መገጣጠም ንብረት ማስተዳደር፣ የሰው ሀብት ማስተዳደር እና ሌሎች ከሰዎች ጋር በቡድን የሚሰሩ ስራዎች ላይ የተሰማራን ብዙዎቻችን ሴቶች አይመለከተንም ትላላችሁ?

እኔ በበኩሌ አምኛለሁ፡፡ በብዙ ዓመት የሥራ ላይ ቆይታዬ የጸሐፊዋን እይታ  በእራሴም በሌሎችም የሴት የስራ አጋሮቼ ያየሁት ክፍተት ነው፡፡ የወንዶች የተንከባካቢነት እና የሴቶች ከፍተኛ የእንክብካቤ መሻት ሲንድሮም (syndrome) ከጥያቄ ውጭ ነው፡፡ እንግዲህ ጸሐፊዋ ይህንን የምክር ቅምሻ (coaching tip) ብላ ያቀረበችው እንጂ 101 ስህተቶቹ ደግሞ ሌሎች ናቸው፡፡ በደንብ  እኛን ሴቶችን ( የቀድሞ እራሷንም ጨምራ) አጥንታናለች፡፡ በበኩሌ ብዙ ተምሬበታለሁ! ገናም እየተማርኩበት ነው፡፡ ያቺ ለወራት ያወቅኳትን የሥራ ባልደረባዬንም ስላስነበበችኝ እና እራሴን እንድፈትሽ ስላደረገችኝ ሳመሰግናት እኖራለሁ፡፡ ያን ጊዜ (ከ12 ዓመታት በፊት) ነበር ያገኘኋት፡፡  እንዲህማ እንደ አሁኑ ኤውብ ማህበራችን ብትኖር ኖሮ ብዙ ሙሉ ሴቶች እንዳሉን በአሳየኋት ነበር፡፡  ይህም ሆኖ ግን አሁንም  በቂ ሙሉ ሴቶች አሉን ብዬ አልልም፡፡ ብዙ ይቀረናል!

በእራሳችን ላይ በመስራት መለወጥ አለብን፡፡ ሙሉ ሴቶች ወይም ቆራጥ ሴቶች (Assertive Women) በመሆን  ትንሽ ሴት ልጅ (girlish) ከሚያስመስመሉን ባህርያት እና ተግባራት መላቀቅ አለብን፡፡ ለዚህም አውቀን የምንገኝ፣  ሰርተን የምናሳይ፣ እራሳችንን የምንችል፣  እንክብካቤ የማይደልለን፣ ኃላፊነት የምንወስድ፣  ቆፍጣኖች፣ በእራሳችን የምንተማመን፣ ከፊት የምንቀመጥ (ኮርነር ፈልገን የማንደበቅ)፣ ሀሳባችንን በነጻነት የምንገልጽ…ወዘተ  መሆናችንን በተግባርም በባህርይም ማሳየት ይኖርብናል!