የአይምሮዬን ህመም ለሆዴ አቀበልኩት

ጊዜው አመሻሽ ላይ ነው። አልጋዬ ላይ ተኝቼ እንባዬ ያለማቋረጥ ይፈሳል። ምን እንዳጋጠመኝ እንኳን አላውቅም። ደሞ ይሄ ለሊት ተጀመረ። ስልኬን አነሳሁ። ማህበራዊ ድህረገጽ ከፍቼ አውራ ጣቴ እስኪዝል በስልኬ መስታወት ላይ ከላይ ወደ ታች ቀጥዬም ከታች ወደላይ እሱም አልበቃ ብሎኝ ማቃቸውም ማላቃቸውም ሰዎች የለጠፉትን እንደወደድኩ ለማሳወቅ ስልኬን እጠቀጥቀው ይዣለሁ። ችግሩ ግን እንባዬ ስልኬ ላይ እየተንጠባጠበ ይህን ተግባሬን እየገታኝ መሆኑ ነው።በእንባዬ ተናደድኩ፤ “አረ አሁን እንኳን ሰላም ስጠኝ፣ ምን አርጊ ነው ምትለኝ?እና እኔ እንዴት እነሱን ልመስል እችላለሁ? እንዴት እንደዚ ወገቤ ሊቀጥን ይችላል? እንዴት እንደዚ ወብ ልብስ ሊኖረኝ ወይ ደሞ የውጪ ሀገር ጉብኝትላይ ልገኝ እችላለሁ?” የእንባዬ ወንድ መሆን ገረመኝ፤ፈገግም አልኩና “እኔ ግን እንደ አብዛኛው ሰው መጥፎውን ነገር በወንድ የምመስለው ለምን ይሆን\” ብዬራሴን ጠየኩ……

ወንድ  ወንድ ስል ትዝ አለኝ፤ ያ የማይረባ እስካሁን የፅሁፍ መልዕክቴን ማይመልሰው ይሄኔ እኮ ከአንዷ ጋር አጥር ላይ ተንጠልጥሎ ስልክ እያወራ ይሆናል። ቆይ እኔ ምን ይጎለኛል? ከኔ ምን አጥቶ ነው ያኔ በኔ ላይ ሌላ ሴት የደረበው? አሁንም ሳቄ አመለጠኝ…. እያሰብኩ ያለሁት እኮ የዛሬ 5 አመት ታሪክነው። እና ይሁና እስከ ዛሬ ጥፋቱን ይቅር ብዬ እንደ ጓደኛ አብሬው ስለቆየሁነው? “እውነት ይቅር ብለሽዋል ግን?” ራሴ ነበርኩ ለራሴ ጥያቄ ያቀረብኩት። አሁንማ ሳስበው ትንሽም አይምሮዬ ለቀቅ ያረገ ይመስለኛል። ግን እኔ ሳልሆን ብዙ ሰው አንቺ ልጅ ለቀቅሽ እንዴ ስለሚሉኝ በግዳጅ ሆነ በውዳጅ አምኜ ሳልቀበል የቀረሁ አይመስለኝም።

“አሁን ወሬ አትቀይሪ፤ ይቅር ብለሽዋል ወይስ ይቅር አላልሽውም?” “ኡፋ.. ” ቁጣ ቁጣ ይለኝ ጀምሯል። ”ይቅር ባልለው እንዴት አሁንም ድረስ ጓደኛው ሆናለሁ?” “አሁንም ያኔ በተፈጠረው ጉዳይ እንደ አዲስ እንደምትሰበሪ ልትክጂ ነው?” ከአልጋዬ ተስፈንጥሬ ተነሳሁ፤ አይኔ ቀልቷል፣ ቁና ቁና ተነፍሳለሁ……………. ”ስንቴ ነው እኔ በወንድ ጉዳይ ተጎድቼ

እንደማላውቅ ምነግርሽ? ማን ስለሆኑ ነው እነሱ?” ልቤ በጣሙን ይመታል፤ “ውሀ ውሀ”አልኩኝ ጨጓራዬ ሲነድ ተሰምቶኝ። የለሊት ጋዎኔን ከወንበር ላይ ስቤ ለበስኩና የክፍሌን በር ከፍቼ እየተጣደፍኩ ከማድቤት ውሀ ፍለጋ ወጣሁ።

ሰአቱ አመሻሽ 4፡30 አካባቢ ነበር። ቤተሰቦቼ ተኝተው ስለሚሆን እንዳልቀሰቅሳቸው በባዶ እግሬነበር የወጣሁት። ሆኖም እናቴ አሁንም እዛው ጓዳ ውስጥ ናት። ወደኋላ አፈገፈግኩና ወደመታጠቢያ ቤት አመራሁ። አይገርምም ሳለቅስ መቆየቴ ሳይበቃኝ ምክንያት አልባ ለምለው እንባ ምን ሆነሽ ነው ተብዬ እንዲ ሆኜ ማለት ስለማልችል ብቻ እንባዬንም ከፊቴ ላይ በውሀ ማስለቀቅ አለብኝ። እናቴ እንደሆነች በልቼ ማደሬና ምጠለልበት ጣራ እንዲሁም የምለብሰው ልብስ እስካላጣሁ ድረስ አንድም የማዘን መብት እንደሌለኝ በደንብ አስተምራ ነው ያሳደገችኝ።

አዎ….. እኔ በምኖርበት ሀገር ማዘንም ሆነ ድባቴ የአካባቢውን ማህበረሰብ ፍቃድ ይጠይቃል።አለዛ “ያቺ ቀበጥ” ፣ “ምን አጣሁ ብላ ነው ቆይ”፣“አዪዪ እቺ ልጅ ሳታረግዝ አትቀርም”…….. ብቻ በፍቃድ የመከፋት አልያም በፍቃድ የመደበት ብቻ መብት ይኖርሻል። ይህን እያሰብኩ ራሴን ዘናእያረኩ በሉት ብቻ ፊቴን ታጠብኩ። አይኔ ያለቀሰይመስላል?” አዎ ከአይኔ ስር ያሉት ከረጢቶችያሳብቃሉ። እና እናቴ እንዲ መስዬ ስታይ ምን ትለኝይሆን? መስታወት ፊት ሆኜ እናቴን ማስመሰሉንተያያዝኩት……..

”አንቺ ምን ሆንኩ ብለሽ ነው ደሞ ምትነፋረቂው? ቅድም ያቺን ተናገሩኝ ብለሽ ነው? በዚ እድሜሽ ታገቢያለሽ፣ ስራትይዢያለሽ ብለን ስንጠብቅ ይሀው እዚ ተዘፍዝፈሽ ነው ምትውዪው። ቆይ ምን አምጡ ነው? እኛ ጡሪን አልን? ራስሽን እንኳን አሻሽዪ እንጂ፤ሆኦኦኦኦኦኦኦ”…..

በትወናዬ ተደምሜ መሳቅ ጀመርኩ፤ ቀስ በቀስ ሳቄበእንባ ተተካ፣ አልቻልኩም፣ ለካ በብዙ ነገርተጎድቻለሁ…….. ለካ እንባዬ ሚፈሰው ዝም ብሎ አይደለም። ማንም የማይረዳው ራሴም በቅጡ ማላቀው ህመምተኛ ነኝ። አሁን እንባዬ ቆመ። መታመሜን ያመንኩ ሰአት በትንሹም ቢሆን ብርታትን አገኘሁ። አሁንም ቢሆንግን እናቴ ያለችበት ጓዳ ሄጄ ውሀ መጠጣትን አልፈቀድኩም። ዞር ስል ባሊ ውስጥ የተጠራቀመ ውሀ አየሁ። አላንገራገርኩም የልብሴን እጀታ ሰብስቤ በሁለቱም እጄ ውሀውን ቀዘፍኩት፣ አይኔንም ጨፍኜ ጥሜን ቆረጥኩበት። አልጋዬ ላይም ሄጄ ተዘረርኩ። ሆዴ ሲጎራበጥ ተሰማኝ። ተመስገን………………………….. ለመጠጥነት በማይውል የተጠራቀመ ውሀ የአይምሮዬን ህመም ለሆዴአቀበልኩት።

ይሄን ድርሰት ስጽፍ በውስጡ ባሉ ሀሳቦች በአንዱ ቢያንስ የአንዲትን ሴት የአይምሮ ጤንነት ያቃወሰ ሀሳብ እንዳካተትኩ ይሰማኛል። በሀገራችን የአይምሮ ደህንነት ወይም mental health ብዙ ያልተባለለት፣ እንደ ትክክለኛ በሽታም የማይታይበትና ሰዎች ብቻቸውን እንዲሰቃዩበት የተውነው ሀሳብ ነው። ግፋ ቢልም ሴጣን ነው በሚል ፀበል ከመውሰድ ውጪ የስነልቦና አማካሪዎች ጋር በመሄድ ለችግሩ እልባት ለማግኘት መሞከርን እንደ አማራጭ ማየት አይዘወተርም። ሌሎች ህመማችንን እንዲያቁልን ብቻ ሳይሆን ራሳችን ራሱ በዚ በሽታ እየተሰቃየን መሆኑን ለማመን በጣሙን እንቸገራለን። ምግብ፣ መጠለያና ልብስ እስካልጎደለብን ድረስ ሌላው ትርፍ ነው ብለን እንድናምን ማህበረሰቡ አስገድዶናል። በዚህም ምክንያት ብዙሀን ወጣቶችን በራስ ማጥፋት ከጎናችን አጥተናል። ወላጆችም ቢሆን ልጆቻቸውን እንደማያውቋቸው ማመንና ሁሌም ቢሆን ልጆቻችን እንዴት ናቸው፣ ያጋጠማቸው ፈተና አለ ወይ፣ በምንስ ላግዛቸው እችላለው የሚለውን አትኩሮት ሰጥተው ቢሰሩበት ያለው አዎንታዊ ተጸኖ ሰፊ ነውና ቢታሰብበት ጥሩ ነው። በድባቴ፣ በጭንቀት እንዲሁም በተመሳሳይ የአይምሮ ጤንነት እክል የምትሰቃዩ ሰዎች ካላችሁበት ስቃይ እንድታገግሙ መልካም ምኞቴ ነው።