ለውጥማ ያስፈራል!

የዛሬ ጽሑፌ መነሻ ሰሞኑን ከድሮ መ/ቤት ባልደረባዬ የተደወለልኝ ስልክ ነው፡፡ ይህቺ የሥራ ባልደረባዬ ደውላ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ በተለያየ ሚዲያ እያየችኝ እንደሆነ እና እድገቴ እንደሚያስገርማት በመግለጽ አድናቆቷን ካርከፈከፈችልኝ በኋላ ጨዋታውን አደራነው፡፡ አመስግኛት ሳበቃ ስለቤተሰብ፣ ስለ ሥራ ወዘተ ተጠያየቅን፤ ወግ ነውና፡፡ ይህች የቀድሞ የሥራ ባልደረባዬ ስትደውልልኝ ተጠንቅቄ ነው የማናግራት፤ ከቀድሞ ባህርይዋ በመነሳት፡፡ የፈለገውን ዓመት ፈጅቶ ባገኛት ምንም የተሻሻለ የባህርይ ለውጥ የማይታባት ናት፡፡ አሁንም እዚያው ከእኔ በፊት ተቀጥራ የምትሰራበት መ/ቤት እየሠራች መቆየቷ ነው መሰለኝ የተግባቦት ስልቷ አልተለወጠም፡፡ የዚያ መ/ቤቱ ብቻ ሳይሆን የባህርይዋም ታማኝ እና ቅን አገልጋይ እንበላት ይሆን!?  በደወለችባቸው ወይም ባገኘኋት አጋጣሚዎች ሁሉ ታጉረመርማለች፡፡

እኔ እንደዚህ ምክንያት እየፈለጉ በዓመታት ቆይታ በስልክ ይሁን በአካል ለሚያገኙኝ ሰዎች ምክር ለመስጠት አንደበቴን አልከፍትም፡፡ ደግሞስ ባለፈው ጽሑፌ ላይ ምክር ሳንጠየቅ መምከር አግባብ ያለመሆኑን እኔው አውግቼ የለ! እናም እሷ ብሶት መሰል ወግ ስታወጋኝ ከማዳመጥ ውጪ ለምን ይህን አታደርጊም፣ ለምን ያንን አታትሞክሪም ማለት እንደሌለብኝ ስለተረዳሁ በዝምታ ነው የማዳምጣት፡፡ አሁንም ስትደውል ይህንኑ ነበር ያደረግኩት፡፡ ታድያ እንዲህ እንደቀድሞ ባልደረባዬ በአንድ መ/ቤት ቁጭ ብለው ሆድ እየባሳቸው እና እያጉረመረሙ ጡረታቸውን በመጠበቅ የሚኖሩ ሰዎች “ለምን ለውጥ አልፈለጉም?” ብዬ አስባለሁ፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው! ለብዙ ሰዎች ለውጥ ያስፈራል አይደል!?

በሕይወታችን ብዙ የለውጥ ሂደቶችን አስተናግደናል፤ በውዴታም በግዴታም፡፡ ለውጥ የማይቀር የተፈጥሮ ሂደት ነው፡፡ ሌላው ቢቀር እኛ መ/ቤት፣ ቤት፣ ወይንም ሌላ መለወጥ ያለብንን ነገር ፈርተን መለወጥ ቢያቅተን እንኳን እድሜ፣ ጊዜ እና ሌሎችም ከእኛ ቁጥጥር ውጪ የሆኑት ነገሮች መለወጣቸው እና መንጎዳቸው አይቀርም፡፡ ለነገሩ እኮ ለውጥ መፍራት የሚጀምረው ከሕጻንነታችን ጀምሮ ነው፡፡ ድሮ ሕጻን እያለሁ፣ እናቴ የራሷ ቤት እስኪኖራትና እስክንረጋ ድረስ ቤቶች ቀያይረናል፤ የተለያዩ ሰፈሮች ኖረናል፡፡ እናም እቃችን ሲሸከፍ አዲስ ቤት ልንገባ መሆኑ ቢያስደስተኝም ከሠፈር ጓደኞቼ መለያየቴ ያሳዝነኝና አለቅሳለሁ፡፡ ግን ታድያ በቀየርን ማግስት ከዚያ ከአዲሱ ሠፈር ልጆች ጋር ተዋህጄ  አገኘዋለሁ፡፡ አፍታም ሳይቆይ እላመዳለሁ፡፡ ይህ ግን እያደግን ስንሄድ ይቀየራል፡፡ ያቺ የመጀመርያዋ የለውጥ ፍራቻ ትከርምብናለች፣ ታረጅብናለች፡፡ ለውጥን ፈጽሞ አንለምድም፡፡

ስለዚህም ያለንበት ሁኔታ ባይመቸንም እንኳን ለውጡን ፍራቻ እርምጃችንን የምንገታ ብዙዎቻችን ነን! እኔ እንደዚህ ያሉ ሰዎች ዙርያዬን ሞልተውታል፡፡ አንቺስ ካላችሁኝ በተወሰነ መልኩ እኔም ለውጥን እፈራለሁ፤ ግን በአንጻራዊነት ደግሞ ተለዋዋጭ ነኝ፡፡

በሥራ ዘመኔ ለረዥም ዓመታት (10 ዓመታት) በሥራ የቆየሁት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነው፡፡ ያን ጊዜ ታድያ ከቀደሙት ወይም ከአንጋፋዎቹ የሥራ ባልደረቦቻችን የምንሰማው ስለ ለውጥ ሳይሆን ስለ ጡረታ ማስከበር ነበር፡፡ ሥራ ስለመቀየር የሚያስብ ሰው እንደ ጤነኛ ላይታሰብ ይችላል ወይንም ጡረታን የመሰለ እድሉን እንደሚያበላሽ ሞኝ ሰውን ይመስላል፡፡ ሰዎች በባህርያችን መማር የምንፈልገው በአካባቢያችን ከምናየው ነው፡፡ ከማንበብ እና ሌሎች አማራጮችን ከመፈለግ የምናገኘው እውቀት እና የምንወስዳቸው እርምጃዎች የተገደቡ ነው፡፡ ስለዚህም ሥራም ሆነ ማንኛውም ነገር እያንገሸገሸን እድሜ ዘመናችንን እንጨርሳለን፡፡ ስናሳዝን! ለነገሩ የሥራ ቦታ መቀየር ይቅር እና የምንቀመጥበትን ወንበር እኮ መቀየር ያስፈራናል፡፡ እስቲ ልብ በሉ፤ ኋላ መቀመጥን ጥሩ ምርጫ አድርገው የደመደሙ ሰዎችን (በተለይ ሴቶችን) ወደፊት ማምጣት የማይታሰብ ነገር ነው፤ ከሆነም በግዳጅ እንደሆነ ቁጠሩት፡፡

“እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል!” የሚለው አባባል የዋዛ አይደለም እኮ! ለእኔ እውነትነት አለው፡፡ ከዩኒቨርስቲ የሥራ ዘመኔ በኋላ ብዙ ስለተማርኩ ለውጥን እንደ መልካም አማራጭ እየወሰድኩ ሕይወቴን ቀጥያለሁ፡፡ አንድ መ/ቤት ለዘመናት ተመሳሳይ ሥራ እየሰራሁ ብቀመጥ ኖሮ አሁን ያለኝ በእራስ መተማመን፣ ለእውቀት መጓጓት ፣ነጻነት እና እድገትን መፈለግ ከየትም አይመጣም ነበር፡፡ በእርግጥም እስኪለመድ ለውጥ ያስፈራል፡፡ አንዴ ፍሬውን ከቀመሱት ደግሞ ሁሌም የሚፈልጉት እና የሚጓጉለት ነገር ነው፡፡

ለነገሩ ተወልደን ካደግንበት ቤት ትዳር ይዘን ለመውጣት በስንት ፀሎት እንዳልተማጸንን ልክ የመውጫችን እለት እዬዬ እንል የለ! “ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀስ” ይባላል እንጂ ወግ ብቻውን አይመስለኝም፡፡ ለውጥን ፍራቻም ጭምር እንጂ!  በወላጆች ወይንም አሳዳጊዎቻችን የነበረውን ኃላፊነት ተጋፍጠን ወደራሳችን ስናመጣው እንደምን አንፈራ! አውራ ለውጥ በሉት፡፡

በነገራችን ላይ አንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ ለዓመታት መቆየት ክፋት የለውም፣ እስከተመቸ ድረስ፡፡ በተለይ መ/ቤቱ የመጨረሻ ከፍተኛ ከፋይ ከሆነ ማን ይለቃል! የተሻለ ክፍያ ሁሌም የተሻለ አቅም ነዋ! ግን ደግሞ የተሻለ ክፍያ ብቻውን ደስተኛ እንደማያደርግ የምናይበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዝቅተኛ ተከፋይ ሆኖ እዚያው ከርሞ ጡረታ መውጣት ከሁለት ያጣ መሆንም አይደል! በእነዚህ ሁለት ጥግ ሁኔታዎች መ/ቤት የማይቀይሩ ሰዎች ደስተኛ መሆን ያልቻሉት ተመሳሳይ ሥራ፣ ተመሳሳይ የሥራ ባልደረባ፣ ተመሳሳይ አለቃ፣ ተመሳሳይ ኮሚቴ፣ ተመሳሳይ ወዘተ በሕይወታቸው ስለሚደጋገም ነው፡፡ ሕይወታችን ልዩ ልዩ ነገር (variety) ይፈልጋል፡፡ እናም ለውጥ የሌለው የሥራ ሕይወት ይሰለቻል! እና መፍትሔው ለውጥ ነው፤ ለውጥን በተለያየ መልኩ ማምጣት ይቻላል፡፡

ሥራ መለወጥ ብቸኛ መፍትሔ ስላይደለ በመጠነኛ ለውጥ ለሕይወት ሰላም እና ደስታ መስጠት ይቻላል፡፡ ይህም የተለያዩ የሙያ ማህበራትን በአባልነት በመቀላቀል ከተለያዩ ሰዎች ጋር በመተሳሰር (Network)፣ የተለያየ ልምድ እና ተሞክሮ ካላቸው ሰዎች ጋር በመማማር እና ለየት ያሉ ልምዶችን በማግኘት ባሉበት ቦታ ሆነው መለወጥ ይችላሉ፡፡ እርግጠኛ ነኝ ማጉረምረሙ፣ ደስታ ማጣቱ፣ መሰላቸቱ ሁሉ ሙሉ በሙሉ ባይጠፋም እንኳን በተወሰነ መልኩ ይቀንሳል፡፡ በዚህ መልኩ የሚያስፈራውን ለውጥ በማያስፈራ መልኩ ማስተናገድ እና ለሕይወት ቀለም መስጠት ይቻላል! ለውጥ ያስፈልገናልና! ለዛሬ ጨርሻለሁ!

Written by: Fitsum Atenafework Kidanemariam

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *