ለምስጋና እንፍጠን!

እንደ ልማድ ይሁን ባህል እርግጠኛ አይደለሁም ግን ብዙ ጊዜ ሰዎችን በበጎነታቸው የምናመሰግናቸው ከሞቱ በኋላ ነው፡፡ ብኢልም አለው፤ \”ሰው ካልሞተ ወይም ካልሄደ አይመሰገንም\” ይባላል፡፡ እርግጥ አሁን አሁን ጥቂት የሽልማት መድረኮችን የሚያዘጋጁ ተቋማት ሞትን ሲቀድሙ እየታዩ ነው፡፡ የእኛዋ ኤውብ ከእነዚህ አመስጋኝ ተቋማት አንዷ በመሆኗ እጅግ በጣም ነው ደስ የሚለኝ፡፡ አመስጋኝነትን ማን ይጠላል ትሉኝ ይሆናል፤ ማንም!

ኤውብ ለማመስገን ከሚፈጥኑት አንዷ መሆኗን ለማስታወስ እስቲ የላቁ ሴቶች ሽልማት (WoE Award) አከባበርን እንቃኘው፡፡ አሁን ከፊታችን በጥቅምት ወር ለ9ኛ ጊዜ ሊከበር ነው፡፡ በቦርድ አባልነቴ እና በቀድሞ የስትራተጂክ ቡድን አባልነቴ በየዓመቱ በሚደረገው የላቁ ሴቶች ሽልማት የሚመለመሉትን ሴቶች ቃለመጠይቅ በማድረግ እና እነሱን ለምርጫ በማቅረብ እንዲሁም በቅድመ ውድድሩ ላይ በሚደረገው ዳኝነትም ላይ ተሳትፊያለሁ፡፡ ያንን ሁሉ አልፈው ወደ መጨረሻው ውድድር የሚመጡት ጥቂቶች ናቸው፡፡ የዚያን ቀን እኛም ከእነሱ እኩል እንደሰታለን፡፡ ምን መደሰት ብቻ በደማቁ ዝግጅት ላይ ለመታደም ከመቼውም በተለየ በዲዛይነር አልባሳት ዝንጥ ብለን ቀድመን እንገኛለን፤ የተመረጡት ሴቶች ሲመሰገኑ እና ሲሸለሙ ለማየትና የደስታቸው ተካፋይ ለመሆን፡፡ ካረፉበት ሆቴል ዝግጅቱ ወደሚካሄድበት ወደ ሸራተን በሊሙዚን  ሲመጡ ግር ብለን ወጥተን እንደሙሽራ እናጅባቸዋለን፤ አብረናቸውም ፎቶ እንነሳለን፡፡ \”እንደእነሱ ባደረገን\” ብለንም እንመኛለን፤ እንተጋለንም፡፡ አዳራሹ ከመከፈቱ በፊት በሚደረገው አጠር ያለ የመተዋወቅያ ፕሮግራም ላይ እንከባቸውና እንጠይቃቸዋለን፤ እናደንቃቸዋለንም፡፡

አዳራሹ ተከፍቶ እንግዶች ቦታቸውን ከያዙ በኋላ በእርጋታ እየተራመዱ ታዳሚውን ሲቀላቀሉ አዳራሹ በጭብጨባና በእልልታ ድብልቅልቅ ይላል፡፡ ታድያ አንዳንዶቹ የላቁ ሴቶች እና ቤተሰቦቸው ላይ ያየሁት የደስታ የእንባ ዘለላ መቼውንም አይረሳኝም፡፡ ለእኛም ይተርፋል፡፡ ደስታ የማያደርገው የለ!

ታሪካቸው በቪዲዮ ሲተላለፍ ደግሞ ሌላ ስሜት ነው፤ \”እነኚህ ሴቶች የት ነበሩ?\” የሚለው ጥያቄ የየዓመቱ ተደጋጋሚ ጥያቄ ነው፡፡ ኤውብ ፍልፍል አድርጋ ታወጣቸዋለች፤ በሕዝብ/በጠቋሚዎቿ እየታገዘች፡፡ ልክ አንዱ ቪዲዮ ሲያልቅ \”ከሁሉም ደግሞ ይቺ ትልቃለች\” የሚል ግምት በሽበሽ ነው፤ የአንዳቸውን ሥራ ከአንዳቸው ማወዳደር እስኪቸግር፡፡ መጨረሻም ከላቁት ሴቶች የዓመቱ የበለጠ የላቀች ሴት ወይንም ልዩ ተሸላሚዋ ከመሀከላቸው የሚመርጡት ዳኞች ውጤት ይዘው እስኪመጡ በየጠረጴዛው ግምት መስጠት ይቀጥላል፤  \”ዳኞቹን አያድርገኝ\”  የምንለው እንበዛለን፡፡ በመጨረሻም ውጤቱ ሲታወጅ አዳራሹ በደስታ ጩãት ይናጣል፡፡ ታድያ የአንዷ በልዩነት መመረጥ የሚያስደስተው ታዳሚዎችን ብቻ ሳይሆን እራሳቸው የላቁት ሴቶች እንደእራሳቸው ይደሰታሉ፤ ይተቃቀፋሉ፤ ይሳሳማሉ! ሴቶች ሴቶችን የሚያደንቁበት፣ የሚሸልሙበት ልዩ መድረክ፤ የኤውብ የላቁ ሴቶች ሽልማት መድረክ!!!

የእኔ ነገር አዳራሽ ውስጥ ገብቼ ስምጥ ብዬ ቀረሁም አይደል! ወደ ተነሳሁበት ርእስ ስብስብ ልበልና \”ለምስጋና እንፍጠን\” ያልኩት በምክንያት ነው፡፡ በእዚሁ የሽልማት መርሀ ግብር ላይ ኤውብ ሳትቀደም በመፍጠኗ ዛሬ ላይ በሕይወት ያሌሉትን መመስገን የሚገባቸውን በጊዜ በማመስገኗ አይቆጫትም፡፡ እነማን ይሆኑ ለምትሉ ላስታውሳችሁ፤ እንድታዝኑ ሳይሆን እንድትጽናኑ እና እንድትደሰቱ፤ በዚያውም እንድንማርበት፡፡

ትርሀስ መዝገቡ በቤኒሻንጉል በሴቶች ላይ የሚደረገውን ግፍ (ሴቶች በጫካ ውስጥ ወልደው አራስ ቤታቸውን በዚያው የሚያሳልፉበትን ጎጂ ባህል) ለማስቀረት የታገለች የማይደፈረውን የደፈረች እና ትልቅ ለውጥ ያመጣች ድንቅ ሴት ነበረች፡፡ በ2014(እ.አ.አ.) የአሸናፊዎች አሸናፊ ነበረች፡፡ በወጣትነቷ ብዙ ሥራ የሠራች ገና እየሠራች ባለችበት እድሜዋ ከዚህች ዓለም በሞት ተለየች፡፡

ዘሚ ዩኑስ ያልተለመደውን እና ብዙም የማይታወቀውን ኦቲዝም ለሕዝብ በማስተዋወቅ፣ አርግማን ያይደለ የተፈጥሮ ክስተት መሆኑን በማስተማር ኦቲስቲክ የሆኑ ልጆች እንደማንኛውም ልጆች ትምህርት እንዲያገኙ ግንዛቤ ከመፍጠር ባሻገር ተቋም ከፍታ የብዙዎችን ሕጻናት እና ወላጆች ሕይወት ያቀናች ድንቅ ሴት ነበረች፡፡ እሷም ገና ብዙ ሕልም የነበራት ብዙ መስራት በምትችልበት ዘመኗ ኮቪድ ምክንያት ሆኖ በሞት አጣናት፡፡

ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ ከጎጂ ባህል አንዱ የሆነውን የሴት ልጆች ግርዛት በሀገር ደረጃ በተለይ በወላይታ ጠንባሮ ለማስቀረት የታገለች፤ ለውጥም ያመጣች ድንቅ ሴት ነበረች፡፡ መድረክ ስትይዝ ከአፏ ማር ጠብ የሚለው ዶ/ር ቦጋለችም በአንድ ወቅት የኤውብ ልዩ ተሸላሚ ነበረች፡፡ እሷንም እንዲሁ በሞት አጣናት

ጋዜጠኛ እሌኒ መኩርያም በድንቅ ጋዜጠኝነቷ የተከበረች ነበረች፤ ብዙ ወጣት ጋዜጠኞችን አፍርታለች፤ በበጎ ስራዎችም ላይ በመሳተፏ ትታወሳለች፡፡ በደማቁ ፈገግታዋ ደስታዋን የገለፀችበት ስሜት አሁንም ከዓይኔ አይጠፋም፤ ዛሬ ግን በሞት ካጣናቸው አንዷ ናት፡፡

ካትሪን ሀምሊን በፉስቲላ የሚሰቃዩ ሴቶችን ሕክምና እና ማገገምያ በመስጠት ለዳግም ሕይወት እያበቃች የነበረች ድንቅ ሴት ነበረች፡፡ ከሆስፒታሉ በተጨማሪ አዲስ መንደርን በመክፈት እነዚህ ሴቶች ከማገገማቸው ጎን ለጎን ምርታማ እንዲሆኑ አድርጋለች፡፡ በዚሁ ግቢ የአዋላጅ ነርሶች የሚማሩበት ኮሌጅም በመክፈት ብዙ ሙያተኞችን እያፈራ ያለ ኮሌጅ ትታልን አልፋለች፡፡ ታድያ ካትሪን በዚሁ በኤውብ መድረክ ተዋውቃለች፤ ቁልፍ ተናጋሪም ነበረች፡፡

እንግዲህ ከመነሻዬ  እንደጠቀስኩት \”ሰው ካልሞተ ወይም ካልሄደ አይመሰገንም\” የሚለው ብኢል ኤውብን አይመለከትም፤ ፈጥና ደራሽ ናትና! በእርግጥ ባላው የአቅም ማነስ ሁሉን መድረስ ላይቻላት ይችላል፡፡ ያም ሆኖ ግን እነዚህም ላይ የደረሰችው ኤውብ ናት፡፡ ኤውብ ያልተዘመረላቸውን ትዘምርላቸዋለች፤ ታዘምርላቸዋለችም፡፡

በነገራችን ላይ እኛ ሀገር ሰው ሲሞት በቀብር ሥነስርዓቱ ላይ የሚነበበውን ታሪክ ሳዳምጥ ሰው ሁሉ ይመሳሰልብኛል፤ \”ቅን፣ ደግ፣ ሰው አክባሪ፣ አስታራቂ…ወዘተ ነበሩ\” ይባላል፡፡ አሁን ማን ይሙት ሟች ሁሉ እንደዚህ ያሉ ነበሩ ወይስ ሙት ወቃሽ ላለመሆን ነው! ለማንኛውም ይሄ እራሱን የቻለ ወግ ነውና በሌላ መስመር እንመለስበታለን፡፡

ኤውብ ግን የእዚህ ዓይነት ይሉኝታ ወይም ማስመሰል የለባትም፡፡ የሚመሰገኑትን ፈጥና ታመሰግናለች፤ ታስመሰግናለች፡፡ ይህ ከኤውብ የምንማረው ትልቅ ትምህርት ነው፡፡ የግድ ተቋም መሆን የለብንም፡፡ በግላችንም የምናመሰግናቸውን ሰዎች በሕይወታችን ይኖራሉ፤ ወላጆቻችን ሊሆኑ ይችላሉ፤ እህት ወንድሞቻችን፣ ጓደኞቻችን፣ የሥራ ባልደረቦቻችን አልያም አገልግሎት የሚሰጡን ሰዎችና ድርጅቶች፤ እናም ፈጥነን እናመስግናቸው፡፡ ይህንን በማድረጋችን እናስደስታቸዋለን፤ ቀዳሚው ባይታወቅም በሕይወት ከቆየን ከቁጭት እንተርፋለን፡፡ ለዛሬ ጨርሻለሁ!