ወይኔ ጉዴ ፈላ!

በቀደም እለት አዲስ ዓመት የነበረው 2018 ዓ.ም. ከምኔው ተሯሩጦ አልቆ አሮጌ እንደሆነ አልገረማችሁም!? ደግሞ እኮ እራሱን ችሎ ቢያረጅ እኛ ምን ቸግሮን! አባሪ ተባባሪ አድርጎ እኛንም ማስከተሉ ከፋ እንጂ፡፡ ለነገሩ በዚህ መኖር ተአምር በሆነበት ዘመን እየኖሩ ማርጀት እኮ ፀጋ ነው፡፡ ጥያቄው ግን እየኖርን በጊዜው ያቀድነውን ለመከወን እድል አግኝተን ይሆን ወይ? የሚለው ነው፡፡ የጊዜው ሩጫ እንደ ድሮ አይመስለኝም፡፡ አንዳንዴ ነዳጅ ልቀዳ ነዳጅ ማደያ ስቆም ማሽኑ ሲከፈት ቁጥሮቹን በቅጡ ሳላያቸው የነዳጅ መጠን ማሳያ (ጌጅ) ጋኑ መሙላቱን የሚያሳየው ፍጥነት እና የጊዜ መሮጥ ይመሳሰሉብኛል፡፡ እናንተስ!? እንደ እኔ ነው የሚሰማችሁ ወይንስ ጊዜው አላልቅ እያለ አዲስ አመት እየናፈቃችሁ ነው? ያው ለሁላችንም አዲስ አመት መጣሁላችሁ እያለን ነውና እኛም እንኳን ደህና መጣህ እንለዋለን፡፡
አዲስ አመት በመጣ ቁጥር ሁላችንም በሳህናችን ላይ ያለው ችግር ነው የሚታየን፡፡ ዛሬ በሀሳቤ የመጣችው ወጣት ሴት ናት ምናልባትም ሃያዎቹን ጨርሻ 30ዎቹን ለመቀላቀል ያኮበኮበችው ወይንም የተቀላቀለችው፡፡ እሷን ሳስታውስ የእራሴን ዘመን ወደኋላ ሄጄ እቃኛለሁ፡፡ በእርግጥ ሕይወት ለየትኛውም ጾታ አልጋ በአልጋ አይደለችም፡፡ ወንዱም ቢሆን በእነዚያ እድሜው ጥሩ ስራ እየሰራ እራሱን አደራጅቶ ለቀጣይ ቤተሰብ ምስረታ መዘጋጀት ይጠበቅበታል፤ ብቸኝነት ምርጫው እስካልሆነ ድረስ፡፡ ይሄ ተፈጥሯዊ፣ መሰረታዊ እና ማህበራዊ እውነታ ነው፡፡ አቤት የሴት ልጅ ሲሆነ ደግሞ አከፋፉ! እሷ ለእራሷ ከምትጨነቀው በላይ እንጨነቅልሻለን የሚሉ ሰዎችን መቋቋም እንዴት ከባድ መሰላችሁ!
በሃያዎቹ መጀመርያ ላይ ብዙዎቻችን ኮሌጅ ጨርሰን፣ ኮሌጅ የመግባት እድል ያልነበረን ወይንም ያልፈለግን ካለን ደግሞ በንግድ ወይንም በምንፈልገው ሙያ ተሰማርተን ገቢ በማግኘት እራሳችንን መቻል እና ቤተሰባችንን መደጎም የሚያስደስተን ዘመን ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ ደግሞ ከጓደኞቻችን ጋር የምንዝናናበት እና በአጠቃላይ አለምን የምንተዋወቅበት እድሜ ነው፡፡ ልክ ሃያዎቹን አጋምሰን ወደ ሰላሳ እድሜ ስናቀና ቤተሰብም ከድጎማው ይልቅ “አጀባዬ አጀባ ሆኗል ሰርግሽ እንዴት ልይሽ!” የሚባልልን ቀን ይናፍቃቸዋል፡፡ ዘመድ አዝማዱም በየሰርጉ እና በየድግሱ ስንገጣጠም “አለ ገና አለ ገና…” እያሉ ጣታቸውን ይቀስሩብናል፤ በአይናቸው ይሸነቁጡናል፡፡ እኛም ምን ጠንካራ ብንሆን የማህበረሰቡ አካል ነንና እንደየአፈጣጠራችን ያሳስበናል፡፡
አሮጌ አመት ሊያልቅ ሲል ያቀድነውን ስንከልስ በስኬታችን ስንደሰት ባልተሳካልን ስንቆጭ ይሄም ከላይ ያነሳሁት ጉዳይ ተያያዥ ነገር መሆኑን አስባችሁት ታውቃላችሁ!? እኔ ያንን የወጣትነቴን ዘመን ሳስታውስ የማልደብቃችሁ ሐቅ ነው፡፡ በስራ፣ በትምህርት፣ ቤተሰብ በመደጎም፣ ከጓደኞች ጋር ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ፣ በበጎ ፈቃደኝነት በመሳተፍ፣ የመዝናናት እና እንዲሁም በቤተ እምነቴ የሚደረጉ ጉዞዎችን በማድረግ ብቻ ያላደረግኩትን ጠይቁኝ፤ እጅግ በጣም ስኬታማ የወጣትነት ዘመን ነበረኝ፡፡ለዚህ በጣም አመስጋኝ ነኝ፡፡
በዚህ ሁሉ ስኬት ውስጥ ግን “ማን ይሆን የሚያገባኝ!? ወይኔ ጉዴ ፈላ ቆጣሪው እየሄደ ነው እኮ!…” እያልኩ በልቤ መጨነቄን ይኸው ዛሬ ለእናንተ ተናዘዝኩላችሁ፡፡ እርግጥ ያን ጊዜ ምንም የማትጨነቅ ስኬታማ ሴት መስዬ ነበር የምታየው፤ ለማን ደስ ይበለው ብዬ! በነገራችን ላይ እኔ ባል አግብቼ የራሴ የሆነ ኑሮ መመስረት ምኞት እና ፍላጎት ስለነበረኝ እንጂ ሁሉም ሴት ይጨነቃል እያልኩ ግን አይደለም፡፡ እንደ እኔ ለምንፈልገው እና አዲስ አመት መጣሁ ባለ ቁጥር ቆጣሪው ለሚያሳስበን ብቻ ነው፡፡
ይሄ ሁሉ ሲሆን እኮ ደግሞ የምወደው የወንድ ጓደኛ ነበረኝ፡፡ በዚያን ጊዜ እሱም እንደሚወደኝ አውቃለሁ እኮ ያው እርግጠኛ ባልሆንም፡፡ እኛ ሴቶች (የእኛ ዘመኖቹ) ደግሞ የፈለገ ብንወድ እና ለትዳር ዝግጁ ብንሆን አፍ አውጥተን “እስከመቼ በጓደኝነት ልንዘልቅ ነው፤ መዋደዳችንን እርግጠኞች ከሆንን ለምን ተጋብተን ሕይወትን በፍቅር ለሁለት አንጋፈጥም!?” አንልም፡፡ እንላለን እንዴ? ኸረ በስመ አብ አይታሰብም፡፡ ደግሞ “ጠይቃኝ እንቢ አልኳት!” ብሎ ቢጎርርብንስ (ቢኮፈስብንስ ማለት ነው)! አቤት ይቺን ኢጎ ሰብራ ያለፈች እና የወደደችውን እና የወደዳትን ወንድ ጠይቃ ያገባች ሴት ካለች ለእኔ እሷ ጀግና ናት፤ እኔ በዚህ ጉዳይ ጀግና ስላልነበርኩ የሚበልጡኝን አደንቃለሁ፡፡
ትዝ ይለኛል ቅድስት ሥላሴዎች የትዳር አማካሪዬ ስለነበሩ ቤተክርስትያን ሄጄ “ሥላሴዎች እኔን ጥሩ ሚስት የምትሆን ሴት አድርጉኝ እና ጥሩ ባል ስጡኝ!” ብዬ ተንበርክኬ እንንልፀለይኩበት የያኔው ጓደኛዬ የዛሬው ባለቤቴ ለጋብቻ ሲጠይቀኝ እውነት አልመሰለኝ ይሁን ወይንስ ፀሎቴ ይደርሳል ብዬ አላሰብኩም ይሁን እንጃ ብቻ እሺ ለማለት እንዴት እንደታሸሁ (እንደተሸኮረመምኩ) እኔና ፈጣሪዬ ነን የምናውቀው፡፡ ይሄ ነገር የሁላችንም ሴቶች ችግር ነው ወይንስ የእኔ ብቻ!?
አስባችሁታል “በቃ ተይው እንዲያውም ሀሳቤን ቀይሪያለሁ!” ቢለኝ እኮ ሁለት ዓመት ሙሉ የገነባሁት የጓደኝነት እና የመጠናናት ዘመን ምስጥ ሊበላው ነበር! ይሄኔ እኮ ደግሞ ምስጥ የማታውቁ ትኖራላችሁ! አሁን ስለምስጥ ሳይሆን ስለ እኔ ነው የማወራችሁ፡፡ እስቲ ስንቶቻችሁ ናችሁ እንደዚህ ጫፍ የደረሰ ግንኙነት በሰራችሁት ጥቂት ስህተት ምስጥ የበላው ማለቴ የከሰመባችሁ!? ቤት ይቁጠረው! እኔ ግን ዛሬ ይህንን ጽሑፍ የምጽፍላችሁ 21 ዓመት ሊደፍን ሁለት ወራት የቀሩት ትዳሬ ውስጥ ሆኜ ነው፡፡ በእኔ ቁፍጥና ሳይሆን በእግዚአብሔር ቸርነት!
ዛሬ ይሄን የዘመን ለውጥ ስጋት ያጋራኋችሁ በምክንያት ነው፡፡ ዘመን በተለወጠ ቁጥር ያላሳካነው ትምህርት፣ ስራ፣ ገንዘብ መቆጠብ፣ ንብረት ማፍራት፣ ማህበራዊ ሕይወት ማሳካት፣ ትዳር መመስረት… ወዘተ የሚያሳስበን ከሆነ በእርግጠኝነት እኛ በጤንነት ነን፡፡ ቀደም ብዬ ያልኩትን አሁንም አላጥፍም፤ በመረጡት ሙያ መስራት እና መለወጥ/ማደግ እንደ ግዴታ ብናየው ጥሩ ነው፡፡ ሌሎቹ በተለይ ትዳር የማደግ እና የመለወጥ ግብአት ቢሆንም የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ “ማግባት አልፈልግም” የምትይ እህት ካለሽ ምርጫሽ ነው፤ እንደ ስራ መሰረታዊ ፍላጎቶችሽን የምታሟይበት መሳርያ ስላይደለ፡፡ ማህበራዊ ሕይወት አያስፈልገኝም ብቸኝነት ይበልጥብኛል ማለትም ምርጫ ነው፤ ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ እንዲሉ፡፡ መማርም ቢሆን ያለኝ ይበቃኛል ለሚል ሰው እሱም ምርጫ ነው፡፡ ከእነ አካቴው እቅድ ከሌለን ደግሞ አሳሳቢ ነው፡፡ ይሄ እንኳን ይህንን የኤውብ ገጽ ለተቀላቀልን ቤተሰቦች አይነገርም፡፡
ጠቅለል ሳደርገው ግን አዲስ አመት ሊመጣ ሲል እቅድን እያሰቡ በተሳካው በመደሰት ባልተሳካው “ወይኔ ጉዴ ፈላ!” ብሎ መደንገጥ ጤነኛ ስሜት ነው፡፡ ምክንያቱም ስንደነግጥ እንባንናለን፤ ስንባንን ከምቾት ቀጠናችን ወጥተን እቅዳችንን ለማሳካት እንውተረተራለን ማለቴ እንጣጣራለን፤ ጥረት ደግሞ የስኬት ቁልፍ ነው፡፡ እኔ ጽሑፌን ከእድሜ ጋር ተያያዥ ተደርጎ የተነደፈልንን ትዳር ተኮር አደርግኩት እንጂ ለማንኛውም የሕይወት ግብ ከአምና የተሻለ ስኬት እንዲኖረን መደንገጥ እና መባነን አለብን ብዬ የማምን ነኝ፡፡ ሲጀመር የትዳር በር ለምን በእድሜ ይታጠራል!? ይሄ ደግሞ ሌላ ርእስ ነው! ወይኔ ጉዴ ፈላ አንዛዛሁባችሁ አይደል! 2019 ዓ.ም. መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን! ለዛሬ ጨርሻለሁ!
Share with your Circle!

Fitse, what an inspirational work! Alertness is the key to success.
Weynae Gudae Fela, Aster Awekech I mean Fitsum Awekech.