አይነኬ!

በአንድ ወቅት እሰራበት የነበረ መ/ቤት ውስጥ እንደልቡ እንዲሆን ልዩ መታወቅያ የተሰጠው የሚመስል የስራ ባልደረባችን ነበር፡፡ ታድያ ይሄ ሰው አለቃ ከምንዝር ሳይለይ ሁሉንም ሰው አፉ ያመጣለትን ሲናገር ልቡን እንኳን የሚያማክር አይመስለኝም፡፡ ብዙ የማይረሱኝ አስከፊ፣ አናዳጅ እና አንዳንዴም አስገራሚ የሆኑ ንግግሮቹ ከነስሜታቸው በአእምሮዬ ተቀርፀው ቀርተዋል፡፡ ከማይረሱኝ ንግግሮቹ ለምሳሌ አንዱን ላጋራችሁ፤ የስራ ኃላፊያችን የብዙ ልጆቻቸው እናት ከነበሩት የ80 ሚስታቸው ተደብቀው በቢሮ ውስጥ በፈጠሩት ጾታዊ ግንኙነት አንድ ልጅ ወለዱ እና ያቺን ያስወለዷትን ሴት ለመካስ ከነበረችበት ዝቅተኛ የስራ መደብ ከፍ አስደርገው እሳቸው በኃላፊነት በሚመሩት እና እኛ የምንሰራበት ክፍል አስመድበዋት ነበር፡፡ ድርጊቱ ድብቅ ይሁን እንጂ ሰራተኛው ሁሉ በጭምጭምታ እየተቀባበለ አውቆታል፤ ግን ማንም ምንም አይናገርም ነበር፡፡ ታድያ በአንዱ ቀን ያቺ እናት ልጇን የመ/ቤቱ ክሊኒክ ለማሳከም ታመጣ እና ምርመራው ካለቀ በኋላ ቢሮ ይዛው ትመጣለች፡፡ ያ እንደልቡ የሚናገረው ባልደረባችን ሰራተኛው ሰብሰብ ባለበት ልጁን ለመሳም ሳብ እያደረገ “አንበሳው ምናለ እናትህን እንኳን ብትመስል! ከማርገዟ በስተቀር እናትነቷን የሚያረጋግጥ አንድ ነገር እንኳን የላትም እኮ፤ ይሄኔ እነዚያ ከቤት የተወለዱት ልጆቹ እንዲህ እንደ አንተ ቁርጥ አባታቸውን አይመስሉም እኮ!” በማለቱ እኛ ተሳቀቅን እንጂ እሱ ምንም አልመሰለው፡፡ አለቃችን ሽምቅቅ እሷ ደግሞ ቁጥት ቢሉም ቃል አላወጡም፡፡ “አሁንስ አበቃለት!” ያልነው ያ እንደልቡ ተናጋሪ ሰራተኛ በማግስቱ ከኣለቃችን ጋር በወቅቱ ያካሄድ ስለነበረው የአፍሪካ ዋንጫ የእግር ኳስ ቅልጥ ያለ ጭውውት ሲያደርጉ ስሰማቸው “ወንዶች ስለሆኑ ነው እንደልቡ ተናግሮ ያልተኮራረፉት?” ብዬ በሀሳቤ ሳውጠነጥን ሰውየው ለካ አይነኬ ስለሆነ ነው፡፡ እሱ ጋር ያለን ምስጢር ለመጠበቅ ባላየ ይታለፋል፡፡ ታድያ በየመ/ቤቱ እንደዚህ ያሉ ስለስራም ይሁን ስለሰዎች ግላዊ ሕይወት የመሰላቸውን የሚናገሩ ሰራተኞች ገጥመውኛል፤ ግን ማንም ምንም አይላቸውም በቃ አይነኬ ናቸው፡፡ እኔ ዛሬ ላይ ቆሜ ሳስታውሳቸው ግን ግርም ድንቅ ይለኛል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አይነኬዎች መጠቀሚያዎች ስለሆኑ ነው፡፡
በሴቶችም እንደእነዚህ ያሉ ሰራተኞች ነበሩ፡፡ በአብዛኛው ከአለቆች ጋር በሚኖራቸው ዝምድና (ጾታዊ ወይንም ኢ-ጾታዊ) የሚያጋጥም ነው፡፡ ኢ-ጾታዊ ያልኩት የጾታ ንክኪ ያሌለው ነገር ግን በዝምድና ወይንም በሌላ አገም ጠቀም ዝምድና ማለት ነው፡፡ እንደእነዚህ ያሉ አይነኬ ሴቶች በስራቸውም ብዙ የማይጨነቁ ናቸው፡፡ እነሱ ደግሞ ጥቃታቸው አለቆች ላይ ሳይሆን ሌላው ሰራተኛ ላይ ያነጣጠረ ነው፤ የበላይነት ወይንም የተሻለ ቀረቤታ ያላቸው መሆኑን የሚያሳዩበት መሳሪያቸው ነው፡፡ ታድያ የማይረሳኝ ሁለት አይነኬዎች የከፈቱት ጦርነት ነበር፤ ወንዱ እና ሴቷ አይነኬ፡፡ እንደ አጋጣሚ ወንዱ አይነኬ ኃይሉን ያካበተው በፖለቲካ ተሰሚነት ሲሆን ሴቷ ደግሞ በጾታዊ ግንኙነቷ ነበር፡፡ እኛ ግን ይህንን ሁሉ ጥግ ይዘን የምናየው በአሉባልታ በሚመጣልን መረጃ እንጂ ተጨባጭ ነገርማ ከየት ይገኛል፤ ተጨባጩ አይነኬነታቸው ያደረሰብን መገለልና መድልዎ እንጂ፡፡ ታድያ ብዙዎቻችን በዚያ ጦርነት የተደሰትን ነበርን፡፡ በተለይ ሴቷ ክብሯን ሸጣ ባመጣችው የአይነኬነት ስልጣን እኛን እውቀት እና ጉልበታችንን ሸጠን ለምናድረው ስጋት ሆናብን ነበር፡፡ ነገሩ ተቀጣጥሎ ተቀጣጥሎ ሄደ እና አለቃችንን የሚያስጠይቅ ሆኖ በመገኘቱ በመጨረሻም እሳቸው ከቦታቸው እንዲነሱ ተደረገ፡፡ አቤት ስንቱ ተነካካ መሰላችሁ! በነገራችን ላይ አይነኬ ሴቶች ቁጥራቸው ከአንድ በላይ ሆኖ ፍንትው በማለቱ እርስ በእርስ ባለመግባባታቸው ብተና ተካሂዶ አንጻራዊ ሰላም ያገኘንበት አጋጣሚ ሆኖልን ነበር፡፡ ዛሬ እነዚያ አይነኬ ሴቶች እና ወንዶች የት ደርሰው ይሆን!? ለኃላፊዎች በሚያደርጉት ማሽቃበጥ ብቻ ለጊዜው ተሰሚነትና የበላይነት ቢያገኙም ተጠቃሚነታቸው ዘላቂነት ያልነበረው እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡
አይነኬዎች በየመስሪያ ቤቱ አሉ፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት አይነኬዎች መጠቀምያ ናቸው፡፡ ፖለቲከኛውም መረጃ አቀባይ ነው፣ በጾታዊ ግንኙነት ይህንን ማዕረግ ያገኘችው ሴቷም ቅምጥ ናት፡፡ እንደ ድርጅት ወይንም እንደ ሀገር ስናስበው የሚየሳዝነው እነሱ ባሉበት ስራ በትክክል እንደማይሰራ ስናቀወቅ ነው፡፡ አንድ ሰው ለተቀጠረበት መ/ቤት የድርጅቱን አሰራር መመርያና ደንብ ተከትሎ ከመስራት ይልቅ “አይነኬ ነኝ!” በማለት ለአለቃ ወይንም ለሌሎች የበላይ አካላት እያሸረገደ እና እያጎበደደ የሚኖር ከሆነ ስራ እየሰራ/እየሰራች አይደለም፡፡ ሁለተኛ የሚሰሩ ሰዎችንም ሞራል የሚገድል ነው፡፡ ትዝ ይለኛል እኛ የተሰጠንን ስራ ጨርሰን ለማረፍ ስንፈልግ እነ እንደልቡ (አይነኬዎች) ወይ ከስራ በመቅረታቸው አልያም እያሉ ለሌላ ተልእኮ (mission) በመሰማራታቸው ምክንያት ያለውዴታችን የእነሱንም ስራ ደርበን እንሰራ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ለጽድቅ ወይንም ለተጨማሪ ክፍያ ስላይደለ እጅግ ያበሳጨንና ያነጫንጨን ነበር፡፡ አንዳንዴ ልክ የመ/ቤቱ የእንጀራ ልጅ የሆንን አይነት ስሜት ይሰማን ነበር፡፡
ታድያ ጊዜ ለኩሉኩሙ እንዲሉ ዛሬ ላይ እነአይነኬዎች የሚያልፍ ሹመት፣ የሚያልፍ ውበት እና የሚያልፍ ጥቅማጥቅም ጠለላ በማድረጋቸው ወርቃማ ጊዚያቸውን ባለመጠቀማቸው ከነበሩበት የስራ እርከን ብዙም ከፍ አላሉም ነበር እና ዛሬ ላይ ባለህበት ሂድ እንደተባለ ወታደር ቆመው የቀሩ ሆነዋል፤ በለስ ቀንቷቸው ከነቁት በስተቀር አልያም የውጪ እድል አግኝተው በስደት ከሚኖሩት በስተቀር፡፡ በየትኛውም እምነት ካሰብነውም የአይነኬዎች ግፍ ቀላል አይደለም! ሕሊናም ይጠይቃልኮ!
አይነኬነት የሕልም እንጀራ ነው፡፡ በእውን የሚኖር ሰው አይነኬነትን ተገን ባያደርግ ብልዕነት ነው፡፡ ዛሬ ላይ ቆሜ በነጻነት እየሰሩ እና እየተማሩ የነበሩትን ሰዎች ሳስተውል በአብዛኛው ደህና ደረጃ የደረሱ ናቸው፡፡ አለም ሁሉንም በነጻ እንድንመርጥ አቅርባልናለች፤ ያለክፍያ፡፡ ብልዕ ሰው አይነኬ አይሆንም፤ ማናለብኝ አይልም፣ ለጊዚያዊ ጥቅም ስብእናውን አይሸጥም፣ የሌሎችንም ስብእና አይነካም፡፡ ለጊዜው እሩቅ የሚመስለውን የሕይወት ጎዳና አንድ ብሎ ጀምሮ ርቀት ይጓዛል፤ ካላቋረጠ ያሰበበት በነጻነት ይደርሳል፡፡ በነገራችን ላይ አይነኬዎች አንዳንዶቹ በሰው ተገፋፍተው የገቡበት ማንነት ስለሆነ ከገቡ በኋላም የአቋራጭ ክብርናው ስለሚያማልላቸው እራሳቸውን እንዳጡ ይኖራሉ፡፡ ከዚህ ደግሞ ይሰውረን!
በተለይ ወጣት ሆናችሁ ይህንን የምታነቡ እህቶችም ሆናችሁ ወንድሞች አይነኬነት ለጊዜው ሊያማልል ይችላል፡፡ የሰዎች መጠቀምያ በመሆን ጥቅማጥቅም ሊገኝ ይችላል፡፡ ነገር ግን ልክ እንደ ዛፍ ላይ እንቅልፍ ማለት ነው፡፡ ዛፍ ላይ የሚተኛን ሰው አስቡት፡፡ ለሽ ብሎ አይተኛም፤ መውደቅን ስለሚፈራ፡፡ ስለዚህ ስጋት የሌለበት አልጋ ላይ ለመተኛት ተግታችሁ ተማሩ፤ ተግታችሁ ስሩ፤ ያለአቋራጭ ጊዜውን ጠብቆ የሚመጣ ክብር ዋጋው ከቀይ እንቁ እኩል ነውና! ለዛሬ ጨርሻለሁ!
የተፃፈው በፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም
Share with your Circle!
