The እኩያን

ማሳሰብያ ለመልካም ወንዶች፡- ይህ ጽሑፍ እናንተን ስለማይመለከት ለሚመለከታቸው ብቻ አንብቡላቸው!
ልጅትን ያወቅኳት በማህበራዊ ሚዲያ ነው፡፡ በአካል እንድታገኘኝ ደጋግማ ስትወተውተኝ “ያስጨነቃትን ነገር ለእኔ በመንገር ቀለል የሚላት ከሆነ የመገኘት መስዋእትነት ልክፈል” ብዬ ሰዓቴን ገድቤ ቀጠርኳት፡፡ ገደብ ያደረግኩት ያንን ያህል ከአቅም በላይ የሆነ ውጥረት ውስጥ ስለሆንኩ ሳይሆን “ብዙም ከማላውቃት ሴት ጋር ከዚያ በላይ ምንም መነጋገር አልችልም” ብዬ አስቀድሜ በመደምደሜ ነበር፡፡
የቀጠርኳት ግሮቭ ጋርደን ነበር (አሁን እሱ ቤት አለ ይሆን!?)፤ ነፋሻ እና አረንጓዴ መስክ እያየች በነጻነት እንድታወራ፡፡ የታሪኳ አስደንጋጭነት እና የእሷ በስሜት ውስጥ መሆን የመደብኩትን አንድ ሰዓት ለማሰብ ቀርቶ ጨርሰን ስንለያይ አራት ሰዓት ሙሉ እንዳዳመጥኳት እንኳን አልታወቀኝም፡፡ ታሪኳ መሳጭ ሆኖ ብቻ ሳይሆን አንድ ሰው ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ግዙፍና አስፈሪ ስለነበር እና መቼስ ባላውቃትም ያንን የመሰለ ታሪክ አምና ስትነግረኝ ከቀለላት ይውጣላት ብዬም ጭምር እንጂ፡፡ ደግምም በርካታ ሴቶች እያለፉበት ስለሆነ ለታሪኩ ባይተዋር አልነበርኩም፡፡
የታሪኳን አጢሪራ (በዩኒቨርስቲ አጭር ጽሑፎች ለማለት የምንጠቀምበትን ለማስታወስ) ባሏ የነበረ የልጇ አባት ምንም ሳይኖራቸው መሬት ላይ ፍራሽ አንጥፈው እየተኙ እሱ በደመወዝተኛ እሷ ደግሞ ያገኘችውን እየነገደች መኖር ጀመሩ፡፡ እሷ ጠንካራ ነጋዴ በመሆኗ በኢኮኖሚ ከእሱ የተሻለ አቅም ነበራት እናም ቤት ንብረት ለማፍራት ቀዳሚ ነበረች፡፡ ያም ሆኖ ግን ትዳር ነውና የእኔ የሚባል ነገር ስለሌለ ሁሉም ንብረት የጋራ ነበር፡፡ ንግዷን ለማስፋፋት በጎንዮሽም እሱን የድህረ ምረቃ ትምህርት ለማስተማር የተጋች ሚስቱ ናት፡፡
ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ትዳራቸው ንፋስ እየዘለቀው አለመግባባት ሲመጣ ያፈሩትን ሀብትና ንብረት ለመጠቅለል ዱርዬ ገዝቶ ሕይወቷን ሊያቀጥፋት እንደነበረ ትደርስበታለች፡፡ ይህን ድርጊቱን ያወቀችው ደግሞ ሊገዛቸው ሲደራደር ከነበሩት ዱርዬዎች አንዱ ድሮ ተማሪ ሆና አንድ ትምህርት ቤት የነበሩ እና በተለይ ወንድሟን የሚያውቅ ሰው በመሆኑ ነው፡፡ ልጁ ድርጊቱን እንደማይፈጽም ሲነገረው ምስጢር እንዳያወጣ እራሱን ሊያስገድለው ሲል እሷንም አስጠንቅቆ ከአካባቢው ይሰወራል፡፡
ይህንን ድርጊት ያወቀ ባል የአይኗን አካባቢ በጉጠት ከወጋት በኋላ ለሕግም ሆን ለማንም አካል ትንፍሽ ብትል አይኗን እንደሚያጠፋት እና ቤተሰቧንም እንደሚያጠፋቸው አስጠንቅቆ ያስፈራራታል፡፡ ትዳሩም ማብቂያው ይሆናል፤ ካፈሩት ሀብትና ንብረት አንድም ሳትይዝ ልጇን ይዛ ከቤቷ ያስወጣታል፡፡ ይህቺ ልጅ አሁን እያንዳንዱ እንቅስቃሴዋ ከልጇም ጨምሮ በስጋት እና በጭንቀት ነው፡፡ “ልጄንም ሊወስድብኝ ይችላል” ብላ ስለምትሰጋ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ የፀባቸው መነሻ እሷ ሱቅ ስለምትውል እና ከተለያዩ ደንበኞች ጋር ስለምትትገናኝ፣ እራሷን ስለምትጠብቅ እና የእራሷ የሆነ በቂ ገቢ ማፍራት ስለቻለች ነው፡፡ ምናልባትም እቤት ቁጭ ብላ በድህነት የእሱን ደመወዝ እየጠበቀች ብትኖርስ ኖሮ? የእንደዚህ አይነት ሴቶች እሮሮ ደግሞ ገጽታው ሌላ ነው፡፡
እንደዚህ አይነት ስኬታማ ሴቶች በባሎቻቸው ከፍተኛ በደል ሲደርስባቸው ይህቺ ሴት የመጀመርያም የመጨረሻም አይደለችም፡፡ እኛ “ሴት ልጅ እራሷን ችላ ወደ ትዳር ውስጥ ብትገባ ለእራሷም ለትዳሯም ጥሩ ምሶሶ ትሆናለች” ብለን እንደምናስበው እና እንደምንመክረው በእኛ ሀገር ቀላል አይመስለኝም፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸው መልካም ወንዶች ቁጥራቸው ብዙ አይደለም፡፡ በአብዛኛው የሀገራችን ወንድ እሱ ብቻ ውጪ ወጥቶ ሰርቶ በሚያገኘው ትንሽም ይሁን ትልቅ ገንዘብ የቤቱ የኢኮኖሚ መሪ መሆን ነው የሚፈልገው፡፡ መቼስ ከቻለው እኮ ጥሩ ነበር፡፡ ሴቷም እኮ በቤት ውስጥ ከዋለች 24/7 ክፍያ የሌለው ስራ እየሰራች ነው፤ ስለዚህ ቁጭ ብላ የእሱን ገቢ እየጠበቀች ነው ማለት አይደለም፡፡ እንደዚህ በቤት ውስጥ ስራ የምታሳልፍ ሴት በአብዛኛው በሚባል ለውጪው አለም ባይተዋር ናት፡፡ እሷን የሚያሳድጋት እና የሚያጎለብታት መድረኮች ላይ አትሳተፍም፤ ይሄ ደግሞ ለእኩያን ወንዶቹ ድንቅ ምርጫቸው ነው፡፡ እኔ እንደዚህ ያሉትን ወንዶች ሌላ ስያሜ አልሰጣቸውም፤ እኩይ ናቸው በቃ!
የኢኮኖሚው አውታር ገንዘብ ስለሆነ የእሷ የቤት ውስጥ ስራም የተሟላ ይሆን ዘንድ ያለገንዘብ ስለማይከወን የበለይነቱ ጎልቶ እንዲታይ ይፈልጋል፡፡ ለሚጢጢ የበላይነት ትልቅን አቅም አስሮ ማስቀመጥ እንደምን መረጡት ይሆን!? ችግሩ ደግሞ እኮ ወንድ ብቻ ሰርቶ ቤቱን የሚያሟላበት ዘመን ያለፈበት መሆኑ ነው፡፡ የዛሬ ሙላት እና የድሮ ሙላት አንድ አይደለም፡፡ ሌላ ሌላውን ትተን ድሮ እኮ የልጆች ት/ቤት እንኳን በአብዛኛው በመንግስት ስለነበረ ወጪው ኢምንት ነበር፡፡ አመጋገብ፣ ትራንስፖርት አጠቃቀም፣ የቤቶች አገነባብ፣ አዋዋብ፣ ቴክኖሎጂ..ወዘተ ብቻ ብዙ የኑሮ ዘይቤ ለውጥ አለ፡፡ ለምሳሌ ድሮ እናቶቻችን ከቫዝሊን ያለፈ ምን ነበራቸው!? እኛ የዚያ ዘመን ሴቶች እኮ አይደለንም! ለነገሩ እነዚህ ወንዶች ያንን ዘመን ከዚህኛው እያወዳደሩ መሰለኝ ሚስቶችን የሚበድሉት፤ የድሮ ዘመን ናፋቂዎች፡፡
በነገራችን ላይ ባለታሪካችን በባሏ ለስድስት አመታት ተደብድባለች፣ ተሰቃይታለች፤ እሷ እንደምትለው ደግሞ በዋናነት ለልጃቸው ስትል የከፈለችው መስዋእትነት ነው፡፡ ልጇ አባቷን እንድታጣ ካለመፈለጓም በተጨማሪ ፈታች መባልን ስለፈራች ነበር፤ ምክንያቷ ደግሞ ከቤተሰብ ፈቃድ ውጪ በእራሷ ውሳኔ በወቅቱ በነበራቸው ፍቅር ተማምና ስላገባችው፡፡ አቤት የሴት ልጅ ፈተና እኮ አበዛዙ! በየቤቱ ለልጄ/ለልጆቼ ብለው የሚበደሉትን ሴቶች ቤት ይቁጠራቸው፤ ገና ለገና “ፈት ናት!” እባላለሁ ብለው የሚሸማቀቁትንም ጭምር፡፡ ወንዱስ አላችሁ? እሱማ ደጋግሞ አግብቶ ቢፈታም “አገባ-ፈታ” ነው በቃ፤ ስለ እሱ ብዙም አይወራም፡፡ ይህቺ ምድር ለሴቶች አንገት የምታስደፋ ኢ-ፍትሐዊ ናት የምንለው በምክንያት ነው!
እንግዲህ እኔ የዚህቺን ልጅ ታሪክ በምሳሌነት ያጋራኋችሁ ብዙ የእሷን ጽዋ እያነሱ ያሉ ሴቶች እህቶቻችን ስላሉ ነው፡፡ አንድ ቦታ ላይ ነጻ የሚያወጣ ሲስተም እስካልመጣ ድረስ እኩያን ወንዶች ከጊዜ ወደጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ ነው፡፡ በትምህርት ወይንም በንግድ አቅማቸውን ያጎለበቱ ሴቶች የትዳር ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡ ትዳሩ በተናጋ ቁጥር ከፈረሰ ትዳር የሚወጡት ልጆች ትዳርን እየፈሩ እና እየጠሉ ስለሚሄዱ የትዳርን ነገአዊ እጣ ፈንታ የሚያጨልም እየሆነ ነው፡፡ ትዳር ደግሞ ለቤተሰብ ብሎም ለሀገር ዋናው መሰረት መሆኑ የማይካድ ሐቅ ነው፡፡
ጤናማ ትዳር የማይፈልግ ሰው አለ ብለን አናምንም፡፡ ለዚህ ደግሞ እነዚህ ዘ-እኩያን የድሮ ናፋቂ ወንዶች የነቃች ወይንም የመንቃት አቅም ያላትን ሴት የመቀበል ዝግጁነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ካልሆነ ሁለት ወዶ አይቻልምና ያልነቃችዋን ወይንም የማትነቃዋን ሴት ከሌላ አለም ላይ ይፈልጉ፡፡ ይሄኛው አለም አሁን ተለውጧል፤ ሴት ልጁን የማያስተምር ወላጅ የለምና ያቺን ብዙ ርቀት ካልሄዱ አያገኙም፡፡ በነገራችን ላይ በፈረሰ ትዳር ሴት ብቻ አይደለችም የምትጎዳው ወንዱም እንጂ፡፡ ለምሳሌ የባለታሪካችን ባል ከእሷ በኋላ ሁለቴ አግብቶ ከሁለቱም ወልዶ እና ተፋቶ መጨረሻ ላይ ብቻውን ነው የቀረው፡፡ በመጨረሻም ሀ ብሎ በሳር መማር ሲያቅተው ለስራ በሄደበት ሀገር እዚያው ከድቶ በመቅረት በስደት የጉልምስና ኑሮውን በአሳር እየገፋ ነው ብላኛለች( ያጋነንኩት ከነገረችኝ ተነስቼ ነው)፡፡ ሳልረሳው ልንገራችሁ፡፡ ባለታሪካችን ለወንዶች ያላትን የጅምላ ጥላቻ፣ ለትዳር ያላትን ፍራቻ በተከታታይ በነበረን የመደማመጥ እና የሜንቶርሽፕ ጊዚዎች ድል አድርገን ዛሬ ላይ ዳግም ካገኘችው ፍቅር ጋር በስርዓተ ተክሊል ተጋብተው ልጅ አፍርተው በደስታ እየኖሩ ስለሚገኙ እንኳን ደስ አለን!
በነገራችን ላይ ከአንዳንድ ወንድ ጓደኞቼ ጋር ስጨዋወት በአቅም እራሷን ያጎለበተች ሴት “እራሴን የቻልኩ፣ እራሴን ማስተዳደር አቅም ያለኝ ሴት ነኝ የማንንም ድጋፍ አልፈልግም!” በማለት ትመጻደቃለች፤ ወንድ ትንቃለች ብለው በአንድ ቋት ከተው ያጭቁናል፡፡ እዲህ አይነት ሴቶች የሉም ብዬ የምከራከር አይደለሁም፡፡ እርግጥም በኢኮኖሚ ጥገኛ ስለነበረች ያገባች እና በኋላም ከጥገኝነቷ ስትላቀቅ ትዳሯን ለመማፍረስ የምትወዛገብ ሴት ካለች እሷም እኩይ ናት፡፡ ትዳር በኢኮኖሚ አቅም ብቻ አይሰፈርምና! ብቻ ነገሩ ውስብስብ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሁሉም ሰው ልቦና ይስጥ!
ለዛሬ ጨርሻለሁ!
Share with your Circle!
