\”የሕይወቴ ቅኝት\” በሚል ርእስ የጻፍኩትን መጽሐፍ አንዳንዴ ገለጥ ገለጥ እያደረግሁ ሳነብ ለእራሴም እንደ አዲስ የሚያስገርሙኝ ገጠመኞቼ ብዙ ናቸው፡፡ ለዛሬ ገጠመኝ አንድ ብዬ የጻፍኩትን ቅኝቴን መነሻ በማድረግ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ያታፈነ ጩኸት መኖሩን በምናቤ ቃኘሁ፡፡ እናም እነሆ አብረን ብንቃኘውስ አልኩ፡፡
መጽሐፌን ገና ላላነበባችሁ ገጠመኝ አንድ ውስጥ ከአንድ የቀድሞ የሥራ ኃላፊዬ ጋር የነበረኝን ያለመግባባት ከእነ መነሾ ምክንያቱ እና የት ድረስ እንዳዳረሰን አትቻለሁ፡፡ በሥራ ቦታ ያለ ጾታዊ ትንኮሳ (Workplace sexual harassment) በተለይ በሥራ ላይ ለተሰማሩ ሴቶች አዲስ አጀንዳ አይደለም፡፡ ለነገሩ አሁንማ ወንዶችም ላይ አልፎ አልፎ እየደረሰ መሆኑ ይሰማል፡፡ በነገራችን ላይ ጾታዊ ትንኮሳ ሲባል ዘርፈ ብዙ ነው፤ ወሲባዊ ትንኮሳ፣ አቅምን አሳንሶ መፈረጅ፣ ችሎታን አለመቀበል…ወዘተ ይካተታሉ፡፡
እና የዚያን ጊዜው አለቃዬ በመጽሐፌ የተወሱት በፈጸሙት ወሲባዊ ትንኮሳ ሲሆን ጥያቂያቸው ተቀባይነት ሲያጣ ስራዬን ለማሳጣት የሚያበቃ ውሽትን መሰረት ያደረገ ክስ መስርተውብኝ ከምችለው በላይ ተጉላልቻለሁ፡፡ በወቅቱ የተከሰስኩበት ጉዳይ ተቀባይነት ቢያገኝ ከስራ መባረር ብቻ ሳይሆን ዘብጥያ እንደሚያስወርደኝ ዝተውብኝም ነበር፡፡ ይሁንና \”ወንጀል ነው\” የተባለውን ጉዳይ ለማጣራት የሕግ ባለሙያዎችን ያካተተ ኮሚቴ መርምሮ ክሳቸው ትክክል ያለመሆኑ ከማረጋገጥም በላይ \”ውንጀላው ግለሰቧን (እኔን መሆኑ ነው) ሆነ ተብሎ ለማጥቃት የተደረገ ሴራ ነው\” ብለው ለከፍተኛው አመራሮች ሪፖርት ያደረጉበትን ደብዳቤ ጊዜና እድል ሰጥተውኝ በዓይኔ በብረቱ አይቼዋለሁ፡፡ ይሁንና ያንን ተከትሎ በወቅቱ በእሳቸው ላይ የተወሰደ ምንም አይነት (የማስጠንቀቅያ እንኳን) እርምጃ አልነበረም፡፡ ለእኔ ግን ከዚያ ክፍል ለመቀየር ጥሩ ምክንያት ሆነልኝ፤ ፍትህ የተዛባ ቢሆንም በወቅቱ ሌላ አማራጭ ያለ ስለማይመስለኝ በዚያው መ/ቤት በተቀየርኩበት ክፍል ስራዬን ቀጠልኩ፡፡ ደግነቱ የገባሁበት ክፍል አለቃዬ ደግሞ ሰውኛ ስለነበሩ መ/ቤቱን እስከለቀቅኩበት ጊዜ ድረስ ተከባብረን እንሰራ ነበር፡፡ ሁሌም አይጨልምም አይደል! በዚያ ላይ እኮ ሁሉም ወንድ አለቆች ተንኳሾች አይደሉም፡፡ አንዳንዶችማ እንኳን ሊተነኩሱ ይቅርና ድርጊቱን ከመጸየፍ አልፎም እንዳይከሰት የሚከላከሉ ብዙ ወንድ አለቆችና የስራ ባልደረቦችም ጋር ሰርቻለሁ፡፡ የእነዚህ ዓይነቶቹ ዘራቸው ይብዛላቸው አቦ!
በነገራችን ላይ ይሄ በጾታዊ ትንኮሳ የሚፈጸም በደል የብዙ ሴቶች የታፈነ ጩኸት ነው፡፡ በተለይ ከፍተኛ አመራር ላይ ያሉ ወንዶች የበታች ሰራተኞቻቸውን መተንኮስ የተለመደ ነገር ከመሆኑ የተነሳ እንደ ትልቅ ነውር ወይም ወንጀል እርምጃ እየተወሰደበት ያለ ጉዳይ አይደለም፡፡ ለነገሩ ሴቶቹም ደፍረው አይናገሩትም፡፡ እኔስ ብሆን ያን ጊዜ ያንን ሁሉ ውርጅብኝ አስተናግጄ ሳበቃ \”መነሾው ትንኮሳ ነው!\” ብዬ መች አፈረጥኩት!? ምክንያቱም ትርፉ መጠቋቆምያ መሆን ነዋ! በዚያ ላይ ቀደም ባለው ጊዜ እንዲህ እንደአሁኑ በጀት እየተመደበለት የማንቂያና የመከላከያ ስልጠና አይሰጠንም ነበር፡፡ ስለሆነም በጉዳዩ ዙርያ ማውራት እንደ ነውር አልያም እንደ ቅንጦት ይቆጠር ነበር፡፡
ዛሬም ስለ ጾታዊ ትንኮሳና ጥቃት መከላከል ይሄ ሁሉ መዋእለ ንዋይ እየፈሰሰበት እንደታፈነ እና እንደተዳፈነ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በአለቆች ወሲባዊ ትንኮሳ ምክንያት ስንቱ ትዳር ፈርሷል መሰላችሁ! የወንዶቹ አይደለም፤ የሴቶቹ ትዳር፡፡ እኔ የተወሰኑ ታሪኮችን አውቃለሁ፡፡ የሕግ ባለሙያዎች ደግሞ ብዙ ያውቃሉ ብዬ አምናለሁ፡፡
በአንድ ወቅት በመ/ቤቴ አማካይነት ለስልጠና እንግሊዝ ሀገር ሄጄ ነበር፡፡ በስልጠናው መሀከል አንድ ሰንበት አገኘሁና ለንደን ከተማ ባለች ማርያም ቤተክርስቲያን ሄድኩ፡፡ አዲስ መሆኔ ስለሚያስታውቅ በአብዛኛው ሰው \”በእንኳን ደህና መጣሽ\” አተያይ ካዩኝ በኋላ ከተወሰኑት ጋር የማውራት እድል አገኘሁ፡፡ ከቤተክርስትያን ስንወጣ በአውቶቡስ የሸኘችኝ ሴት ከአእምሮዬ አትጠፋም፡፡ ከፍተኛ የሀገርና የሰው ናፍቆት አለባት፡፡ አንድ ሰው ስታስታውስ ግን ወደ ሀገር ቤት ማሰብ አትፈልግም፤ በጸሐፊነት ሙያ ስትሰራ አለቃዋ የነበረውን ባለስልጣን ሰውዬ፡፡ ከሀገር የወጣችውም የዚሁ የአለቃዋ ወሲባዊ ጥቃት ባመጣባት መዘዝ ነው፡፡ አለቃዋ የዘመኑ ባለስልጣን ስለነበር ሲወተውታት \”ባለትዳር ነኝ ተወኝ እባክህ?\” የሚለው ተማጽኖዋ ሊዋጥለት አልቻለም፡፡ ስለዚህም እኩይ እቅዱን ነድፎ ብቻዋን ቢሮ እንድታመሽ ትእዛዝ እየሰጣት ጥቃቱን ጀመረ፤ ተመቸውም፡፡ የበለጠ በቁጥጥሩ ለማድረግ ባለቤቷን ከሚሰራበት መ/ቤት እንዲባረር አደረገ፤ በእንቢታዋ እንዳትፀና የባለቤቷ እጣ እንዳይደርሳት እያስፈራራት ስለነበረና ስራዋን ቢያሳጣት ከእነልጆቿና ባለቤቷ ሊራቡ እንደሆነ ስታውቅ ያለውዴታዋ እጁ ላይ ወደቀች፡፡ ብዙም ሳይቆይ ይህ ድርጊት ባለቤትየው ጆሮ ደረሰ፤ መጠጣት፣ መስከርና እሷን ጨምሮ ሌሎች ሰዎችን መደባደብ ጀመረ፡፡ ይህን በቅርበት የሚከታተለው ባለስልጣኑ አለቃዋ አስደበደበው፤ ብዙም ሳይቆይ ባለቤቷ በህመም ማቅቆ ሕይወቱ አለፈ፡፡ ባለስልጣኑ በይፋ ቤቷ መምጣት ሲለውም ይዟት እየወጣ ማሳደር ጀመረ፡፡ እሷም ባለስልጣኑን አለቃዋን የበለጠ ጠላችው፡፡ ብዙም ሳትቆይ ቤቷን በማስያዝ ከግለሰብ ገንዘብ ተበድራ ልጆቿን ይዛ በኬንያ አድርጋ ተሰደደች፡፡ ልጆቿን በሰው ሀገር ብቻዋን ያገኘችውን ሥራ እየሰራች አሳደገቻቸው፡፡ ሲያድጉ ግን \”አባታችንን ያስገደለው ያንቺ ሰው ነው\” በሚል ጥላቻቸውን ነገረዋት ብቻዋን ትተዋት ወጡ፡፡ በምድር ላይ ያሏት የዚያ ቤተክርስቲያን ቤተሰቦቿ ብቻ መሆናቸውን ነገረችኝ፡፡ አንድ ዶላር የሚባል ገበያ ስገባም አገዛዛችኝ፡፡ ስላዳመጥኳትም ስላላቀስኳትም ሂሳቤን ዘጋችልኝ፤ አድራሻ ተለዋውጠንም ተለያየን፡፡ ይሔ የአንዲት ሴት የታፈነ ጩኸት ነው፡፡ ቁጥሩን ለመግለጽ የተጠና ጽሑፍ ባላገኝም ብዙ ሺዎች ታፍነዋል፡፡
ገጠመኞቼ በስራ ቦታ ያተኩሩ እንጂ የባሰው ያለው ደግሞ በየጎዳናው፣ በየዱሩ ነው፡፡ በሀገራችንም በተፈጠረው ጦርነት እና ስደት የብዙ ሴቶችና ሕጻናትን የከፋ ጉዳት ሰምተናል፡፡ እና መቼ ይሆን ይህ የታፈነ ጩኸት ድምጽ ዘርቶ እውነተኛ ጩኸት ሆኖ የሚደመጠው? መቼ ይሆን ሴት ልጅ እንደ ሰው በነጻነት ሳትሳቀቅ ሰርታ የምትገባው? መቼ ይሆን መቻሏ ተቀባይነት የሚያገኘው? መቼ ይሆን ተንኳሾች፣ አጥቂዎችና ደፋሪዎች ትክክለኛ ፍርድ የሚያገኙት? መቼ ይሆን ፍትህ ፍትህ የምትሆነው? አልጨረስኩም!