ውሸት አቁሙ

ልጅ እያለን የሚነገሩን አፈ ታሪኮችን ጨምሮ ብሎም ኮስተር ያሉ ማስፈራሪያዎች ትልቅ ተፅእኖ እንዳላቸው የገባኝ በቅርብ ጊዜ ፖሊስ መጣ ሲባል የደነገጥኩበት ጊዜ ላይ ነው። ፖሊስ መምጣቱ ምንም ስርቆት ካልፈፀምኩትና ህግ ካልተላለፍኩት እኔ ጋር ምን አገናኝቶት ነው ምደነግጠው? አይምሮዬ የዚህን ፍርሀት ምንጭ ለማሰብ ሞከረ። ሙከራዬም ወደ ልጅነቴ ወደኋላ ጎተተኝ። “ይሄን ምግብ በልተሽ ካልጨረሽ ፖሊሱን ነው ምጠራብሽ!” የእናቴ ድምጽ ወደጆሮዬ መጣ። ከልጅነቴ ጀምሮ ፖሊስ አልወድም። ለምን እንደሆነ ግን ማውቀው ነገር አልነበረም። “ፖሊሱ መጣልሽ” የሚሉትን ቃላት “አያ ጅቦ መጣልሽ” ከሚሉት የቃላት ስብስብ እኩሌታ ያህል ሰምቼዋለሁ። እናም ፖሊስ ለክፉ ግዜ ደራሽ ከመሆኑ ይልቅ፣ ከጅብ እኩል ቢያገኘን እንደሚበላን እንስሳ የምንፈራው አስተዳደጋችን እንደሆነ ግልጽ ነው።

ያም ብቻ አይደለም፣ ጆሮ ቆራጩ አባባ! እኛን ሽማግሌ ጎረቤታችንን ሳይ ጆሮዬን ይዤ ማልቅሰው ለቅሶ እስካሁን ከሰፈሩ ሰው ጆሮ የሚጠፋ አይመስለኝም። ለሽማግሌዎች ክብር ያጣነው ለዛስ ይሆን?

“እውነቱን ከነገርከኝ አልመታህም!” የሚለውን ቃል አምኖ እውነቱን የተናገረ ልጅ እስቲ ማነው ከመገረፍ የተረፈ? ቃልን የመሰለ ሀያል ነገር የሚክዱት ወላጆቻችን አልያም ታላላቆቻችን፣ አሁን ሀሰትን እንደመዳኛ አርገን ጋሻችን ለማረጋችን ተጠያቂ አይሆኑም?

ከሁሉም ከሁሉም ግን በአሳዳጊዎች ዘንድ የማስተውለው የልጅ አስተዳደግ ችግር የልጅን በራስ መተማመን ማጥፋት ላይ ነው። “ለህጻናት ቦታ የለንም!” ከሚሉ የሰርግ ጥሪ ወረቀቶች ይጀምራል። የኛ ማህበረሰብ ህጻን ልጅ እድሜው ከፍ እስከሚል ድረስ እንደ “ሰው” ለማየት ሲቸገር እናየዋለን። እንግዳ ሲመጣ ጓዳ እንዲገቦ ከማዘዝ ጀምሮ በልጆች ፊት ስለልጆች ክፉ ጎን ለጨዋታ ድምቀት ሲባል እያነሱ መሳለቅ ለአብዛኛው የኛ ማህበረሰብ እንደቀልድ የሚታይ ግን አሁን ላይ ላለንበት ማንነት ተጠያቂ የሚደረግም ነው።

ከዚ በፊት የጻፍኳት አንድ ጽሁፍ ትዝ አለችኝ። እነሆ
የፀጉሬ ኪንኪነት እንዴት ለእቃ ማጠቢያነት ሊያገለግል እንደሚችል ለመነጋገር ስብሰባ ተቀመጡ = የሰው ፀጉር አስተክዬ ወጣሁ
በቅንድቤ መሳሳት ሲያሽካኩ ተሰማኝ = ተኩዬም ወጣሁ
በከንፈሬ መጥቆር ሲንሾካሾኩ ተሰማኝ = ሊፒስቲክ ተቀብቼ ወጣሁ
በቁመቴ ማጠር ሲወያዩ ደረስኩ = ታኮ ጫማ ተጫምቼ ወጣሁ
ማድያታምነቴን አይተው ባሏ እያቃጠላት ነው ተባልኩ = ፊቴን በዱቄት ደብቄ ወጣሁ
በውፍረቴ ስም ሰጡኝ = ኩርሲ አርጌ ወጣሁ
በጥርሴ ወጣ ገባ መሆን ዜና መሆኔ አልቀረም = የጥርስ አጥር አሳስሬ ወጣሁ
የአይኔን ትልቀት፣ ያፍንጫዬን ጎራዳነት፣ የጆሮዬን ዲሽነት…… ማስተካከል ስላልቻልኩ እንደወጣሁ ቀረሁ
ፀቡ ከኔ ይሁን ከፈጣሪዬ እስኪለይ …………

ገና ከልጅነታችን ጀምሮ የውበት መስፈርት የተሰጠን ይመስል አንድን ሰው ውብ ካልሆነም ደግሞ አስቀያሚ ብሎ የመፈረጅ “አባዜ” አለብን። ይህስ ታዲያ ከአስተዳደግ የመጣ አይሆንምን? አብዛኞች ወላጆች ልጆቼ ከሰው ልጅ እንዳያንሱብኝ ሲሉ እንሰማለን። ሰምተን ብቻ አንቀርም፣ ለልጆች ብዙ መስዋትነት ሲከፈል አይተናል። የገንዘብ እና የንብረት መስዋትነት። የቁሳቁስ ዘመቻ ብንለውም የሚቀል ይመስለኛል። ልጆቼ ከሰው ልጅ እንዳያንሱብኝ ማለት ትርጉሙ ምን ይሆን? ማነስ ምን ማለት ይሆን? የሁልጊዜም ጥያቄ ነው።