እቴጌ ጣይቱም ተገፍተዋል!

ሰሞኑን የአድዋ በዓልን በደማቅ ሁኔታ አከበርን፤ እንኳን አደረሰን! ይህን ተከትሎም የማርች ወር ስለሆነ ስለ እኛ  ስለሴቶች ብዙ ይባልልናል፤  ይህም ደስ ይላል አይደል!? የአድዋ በዓል ሲከበር በየዓመቱ የተወዳጇ ጂጂ ሽባባው “አድዋ” ዜማ በየጣብያው ይንቆረቆራል፡፡ ይሄ ደግሞ እያንዳንዳችን ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጥረው ዘመን ተሻጋሪ ስሜት በቃላት አይገለጽም፡፡ ታድያ ሁልጊዜ አድዋ ሲዘከር ቀድመው የሚጠሩት እምዬ ምኒልክ ናቸው፤ ትክክልም ነው! የሀገሪቷ መሪ እሳቸው ነበሩ፤ የእሳቸው ቁርጠኛ አመራርም ነው ለዛሬ የነጻነት አየር መተንፈስ ያበቃን፡፡ አንዳንድ ሰው ከዘመኑ ቀድሞ ይፈጠራል፤ እሳቸውም እንደዚያ ናቸው፡፡ ግን ደግሞ ብቻቸውን አልነበሩም፤ ሚስታቸው ጀግናዋ እቴጌ ጣይቱ ብጡል ከጀርባቸው ሳይሆን ከጎናቸው ነበሩ፡፡ ከጎን መሆናቸው ዋጋ ያወጣው ግን እምዬ ምኒልክ በሴት መመከር የበታች እንደማያደርጋቸው በማመናቸው ነው፡፡ ሚስት ብቻ ሳይሆኑ አማካሪም ነበሩ፤ እቴጌ ጣይቱ፡፡

እቴጌ ጣይቱን በተመለከተ ብዙዎች ስላልተሳኩት ትዳሮቻቸው ማውራት ያስደስታቸዋል፡፡ እቴጌ ከእምዬ ምኒልክ በፊት አራት ባሎችን አግብተው ፈትተዋል፡፡ እና ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ አግብተው መፍታታቸውንም ከጀግንነታቸው ጋር አቀላቅለው የሚተርኩ ሴቶች አጋጥመውኛል፡፡ ለእኔ ብዙም ውሀ ያላነሳ ነገር ነው፡፡ አበው ይሁኑ እመው ሲተርቱ “ታሪክን ከስሩ ውሀን ከጥሩ” እንዳሉት እቴጌ እያገቡ ለመፍታት ምን አነሳሳቸው የሚለውን ታሪክ እንየው፡፡ ለምሳሌ የመጀመርያ ትዳራቸውን ሲይዙ ገና የ10 ዓመት ጨቅላ ሕጻን ነበሩ፤ እንኳን ለአቅመ ሚስት ለአቅመ ሔዋን ያልበቁ፡፡ በወቅቱ ትዳር የሚመሰረተው እንደ አሁኑ ተዋውቆ ሳይሆን በቤተሰብ አማጭነት (arranged marriage) ነበር እናም የእቴጌ እጣም እንደዚያ ነበር፡፡ በዘመናቸው ያለውን የግዝዝ ትምህርት ቤተሰቦቻቸው አስተምረዋቸው ኖሮ ንቃታቸው ከሌሎች አቻዎቻቸው ከፍ ያለ ነበር፡፡ ነፍስ እያወቁ ሲሄዱ የባል ጥቅም እየገባቸው ሲመጣ ያንን የማያሟላ ወንድ አሜን ብለው መቀበል አልቻሉም፡፡ በተከታተታይ አግብተው የፈቷቸው ባሎቻቸውም በወቅቱ ከፍተኛ ማእረግ የነበbራቸው፣ የጦር አዛዦች የነበሩ (የአጼ ቴዎድሮስ ጀነራል እና የአፄ ዮሐንስ ደጃዝማች ይገኙበታል) እንደሆነ ይነገራል፡፡ ታድያ ከላይ እንደጠቀስኩት ፍቺዎቹን ፈልገውት ሳይሆን እንደማንኛውም ባለትዳር ሳይግባቡ ቀርተው ያጋጠማቸው ነው፡፡ የወንድነት ወኔ ለእሳቸው ቦታ ነበረው፡፡ በተከታታይ ካገቧቸው ባሎቻቸውም ልጅ/ልጆች አልወለዱም፡፡

መጨረሻ ላይ ከሚኒልክ ጋር ሲጋቡ የሚፈልጉትን ወኔ ስላገኙ ጥምረታቸው የተሳካ ሆነ፤ በቤተክርስቲያን ስነስርዓት ጋብቻቸውን ፈፀሙ፡፡ ይሄንን የበሰለ ታሪክ ትተን መፍታታቸው ላይ ካተኮርን ትዳርን እንዳንገፋው በማለት የትዳራቸውን ሂደት ስተርክ አረዛዘምኩት መሰለኝ፡፡ አትፍረዱብኝ! እንደነገርኳችሁ ማህበራዊ ሚዲያው ላይ ለትዳር የማይገዙ ወኔአም አድርገው ስለሳሏቸው ነው፡፡ ስለትዳራቸው ይህንን ሁሉ ካወራሁ ዘንዳ ስለጀግንነታቸውመም የምታውቁትን ልድገምላችኋ! የውጫሌው ስምምነት ላይ አንቀጽ 17 መዘዝ ይዛ መምጣቷን መጀመርያ አንብበው የተረዱት እቴጌ ጣይቱ ብጡል መሆናቸውን ታውቃላችሁ አይደል!? ከዚያ ደግሞ የእምዬ ምኒልክ ዋና አማካሪ ስለነበሩ የጽሑፉን ትርጉም በማብራራት “የመጣ ይምጣ እንዳይፈርሙ!ብለው ባላቸውን የመከሯቸውም እሳቸው ናቸው፡፡ ያው የድሮ ባሎች በዚያ ላይ ንጉስ አንቱ ስለሚባል እንጂ እቴጌ በእድሜም የእምዬ ምኒልክ ታላቅ ነበሩ፡ እምዬ ምኒልክ በዚያ ዘመን በሚስታቸው ላይ ያላቸው መተማመን እኮ የሚገርም ነበር፡፡ የእኛ ባሎች እንዲህ ይተማመኑብን ይሆን!? ምኒልክ ከምር መሪ ብቻ ሳይሆኑ ባል ነበሩ፤ የሴት ብልህነት የገበባቸው ልዩ ባል!

የአድዋ ጦርነት አፍጥጦ ሲመጣ እቴጌ ጣይቱ “በድል ይመልስህ የእኔ ጀግና!” ብለው ስንቅ ቋጥረውና ስመው እያለቀሱ የሸኙ ሴት አልነበሩም፤ ይልቁንም የእራሳቸውን ጦር አሰልፈው የዘመቱ ጀግና እንጂ፡፡ የእቴጌ ጣይቱ ጦር ከተዋጊነት በተጨማሪ ምግብ በማብሰል፣ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት እና በሽለላ፣ በፉከራ እና ቀረርቶ በማበረታታት ከፍተኛ አገልግሎት የሰጠ ነበር፡፡ እንደምታውቁት ለጣልያን ሽንፈት ውሀ ጥም እንደምክንያት ተነግሮናል/ተጽፎልናል፡፡ ይሄም ታድያ የእቴጌ ጣይቱ ስትራተጂክ ስልት ነው፡፡ ጣልያን የመሸገበትን የሚያውቁት እቴጌ ወደዚያ የሚያልፈውን የውሀ መስመር እንዲቋረጥ በማዘዝ ውሀ እንዲጠሙ አደረጉ፡፡ አቅም የፈተናቸው ጣልያኖች ውሀ ፍለጋ ወጡ፤ ጨበጣ ውጊያ ተደረገ እና ኢትዮጵያ ባንዲራዋ በአለም ከፍ ብሎ ተውለበለበ፡፡ እኛም ይህንን እድሜልካችንን የምንኮራበትን ድል ተቀናጀን፡፡ እኚህ እቴጌ ጣይቱ ታድያ ድንቅም አይደሉ!? አንዲት ሴት ያለ ምክንያት ትዳሯን አትፈታም፤ ትክክለኛ አጣማጇን እስካገኘች፡፡ እሳቸውንና እምዬ ምኒልክን ያጣመደ አምላክ እኛን ነጻ ሊያወጣን አቅዶ ነው፡፡ ዛሬ የምንምነሸነሽባትን አዲስ አበባ የቆረቆሩልንም እኮ እቴጌ ጣይቱ ናቸው አይገርምም!? እቴጌ ጣይቱ ሆቴልም የመጀመርያው ዘመናዊ ሆቴላችን የእሳቸው ጥንስስ ነው፡፡

ታድያ ይህንን ሁሉ ውለታ ለሀገር የዋሉ ድንቅ ሴት የመጨረሻ ዘመን በጣም አሳዛኝ ነበር፡፡ ማህበረሰባችን ከአያት ቅድመ አያት የወረሰው ውለታ ቢስነት ይኖርበት ይሆን እንዴ!? ይገርማችኋል እቴጌ ጣይቱ በመጨረሻ ዘመናቸው በዋሉት ውለታ ልክ እንደጀግና አልተከበሩም፤ ይልቁንም ተገፍተዋል እንጂ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡ ከባላቸው ያልተናነሰ ጀግንነታቸው ታፍኖ እንዲቀር ተፈልጎ ነው፤ የሀገራችን አባዊ ስርዓት ዋዛ አይደለማ! እምዬ ምኒልክ በደካከሙ ጊዜ በባላቸው እግር እንዳይነግሱ ሹማምንቱ ከቤተ መንግስት አስወገዷቸው፡፡ መጨረሻቸውም ያ ሁሉ ጀግንነትና የዲፕሎማሲ ስራቸው ተጨፍልቆ በቤተክርስትያን አገልግሎት ተወሰነ፡፡ የእንጀራ ልጃቸው የነበሩትን እቴጌ ዘውዲቱን በደንብ ሜንቶር አድርገዋቸው እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡ ነገር ግን የሴቶች ወደመሪነት መምጣት ፈተና የነበረበት ያ ዘመን ብዙ እንዲቆዩ እድል አልሰጣቸውም፡፡ እቴጌ ዘውዲቱ በዙፋኑ ላይ ብዙ ሳይቆዩ ንግስናቸው በአጼ ኃ/ስላሴ ተቀማ፡፡ የአድዋ ድል ሲከበር ሁልጊዜ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል ብዙም ያልተነገረለት ጀግንነት ይከነክነኛል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ውለታቸውን ከጤፍ ባለመቁጠር ከቤተመንግስት አውጥቶ ጥግ ያደረጋቸውን አባዊ ስርዓታችንን የምራገም ነኝ፡፡ ይህ ስርዐዓት በሌላው ጾታ ተፈላጊነት ስላለው መቼም እንደማይነቀል ሳስበው የሴቶች እኩልነት የሚረጋገጥበት ዘመን ይመጣል ብዬ እንዳላስብ ያደርገኛል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ “ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ” እንዲሉ “የመሪነት እኩልነቱን ትተሸ ጾታዊ ጥቃት የሚደርስባትን ሴት ነጻነት አስቢ” የሚለኝ መንፈስ አለ፡፡ በየቤቱ፣ በየግጭት ቦታዎች፣ በየት/ቤቱና በየስራ ቦታው በሚደርስባቸው ጥቃት እና ትንኮሳ እንደወንድ አቻዎቻቸው በሰላም ወጥተው የማይገቡትን ሴቶች ቤት ይቁጠራቸው! በዚህ በእኛ በሰለጠነው ዘመን፡፡  ለማንኛውም “የሴቶች እኩልነት መቼም አይረጋገጥም” ብለን ተስፋ አንቆርጥም! ቢገፉንም ላለመውደቅ እንንገዳገዳለን፡፡ ደግሞስ ብዙ ጭላንጭል እያየንም አይደል! በእኛ ዘመን የሴት ፕሬዚደንት፣ የሴት ከንቲባ እና የሴት ምኒስትሮች አይተናል፤ ገና ብዙ እናያለን፤ ሴት ልጆቻችንን እስካስተማርን ድረስ!  አቦ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል የጀግንነት መንፈስ ይምጣ! ሴቶችን የሚገፋው የአባዊ ስርዓት መንፈስ ይመታ! ለዛሬ ጨርሻለሁ!

የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

Share to your circles!

1 thought on “እቴጌ ጣይቱም ተገፍተዋል!”

  1. Etagegnehu getahun

    Women’s we have a powervto change this world, but most of time they are/Men’s /take the advantage frist.

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top