ፅሞና

የጥንት ፡ የግሪክ ፡ ሚቶሎጂ ፡ እንደሚለው ፡የሰው ፡ ልጅን ፡ ትክክለኛ፡ ማንነት ፣ ህያውነቱን ፡ ለመደበቅ ፡ የግሪክ ፡ አማልክቶች ፡ ተማከሩ ፤ አንዱ ፡ አምላክ ፡ “ከሰማዮች ፡ ሁሉ ፡ በላይ ፡ አርቀን ፡ እንስቀለው “ ፡ ብሎ ፡ ሀሳብ ፡ አቀረበ ፡ ሆኖም ፡ የሰው ፡ ልጅ ፡ ሰማይ ፡ ላይ ፡ የሚያወጣውን ፡ ጥበብ ፡ ይጠቀም ፡ እንደሆነ ፡ ያገኘዋልና ፡ አይሆንም ፡ ተባለ። ሁለተኛው ፡ አምላክም ፡ “ለምን ፡ ከውቅያኖስ ፡ ስር ፡ ከመሬት ፡ በታች ፡ አንቀብረውም ?” ፡ የሚል ፡ ሀሳብ ፡ አቀረበ ፡ ነገር ፡ ግን ፡ አሁንም ፡ ወደ ፡ መሬት ፡ ስር ፡ ይመለከት ፡ ዘንድ ፡ የሚያስችለውን ፡ ጥበብ ፡ ያወቀ ፡ እንደሆን ፡ ያገኘዋልና ፡ አይሆንም ፡ በሚል ፡ ውድቅ ፡ ተደረገበት ፡  ብዙ ፡ ካወጡ ፡ እና ፡ ካወረዱ ፡ በኃላ ፡ ከመካከላቸው ፡ አንዱ ፡ “ምንም ፡ ቢሆን ፡ ህያውነቱን ፡ ለመፈለግ ፡ የማያስበው ፡ ቦታ ፡ ቢኖር ፡ በራሱ ፡ ውስጥ ፡ ያስቀመጥነው ፡ እንደሆነ ፡ ነው፡፡” አለ ፡፡ በዚህም ፡ ተስማምተው ፡ በውስጡ ፡ ቀበሩት ፣ በአእድሜው ፡ ዘመንምን ፡ እንዲፈልገው ፡ ተዉት ።

እውን ፡ የሰው ፡ ልጅ ፡ ትክክለኛ ፡ ማንነቱ ፣ ህያውነቱ ፡ በውስጡ ፡ ተቀብሮ ፡ አለ?

በህይወቴ ፡ ከማልረሳቸው ፡ የህይወት ፡ አጋጣሚዎች ፡ መካከል ፡ ቪፓሳና ፡ አርምሞ ፡ ያሳለፍኩት ፡ አስር ፡ ቀናት ፡ ይገኝበታል። “ቪፓሳና”፡ ትርጉሙ ፡ ነገሮችን ፡ በትክክለኛ ፡ አተያይ ፡ መመልከት ፡ ማለት ፡ ነው ። አእምሮን ፡ ነገ ፡ እና ፡ ትላንት ፡ ከሚባሉ ፡ ነገርግን ፡ ከሌሉ ፤ ከአእሳቤ ፡ ያልዘለሉ ፡ ሁናቴዎች ፡ ቀስ ፡ ብሎ ፡ የማውጣት ፡ ሂደት ፡ ነው ።  ለ አስርት ፡ ተከታታይ ፡ ቀናት ፡ ከየትኛውም ፡ የውጪ ፡ አለም ፡ ግንኙነት ፡ ርቆ ፡ ከማንም ፡ ጋር ፡ ሳያወሩ ፣ ሳይተያዩና ፣ ሳይገናኙ ፡ እስትንፋስን ፡ ብቻ ፡ እያጤኑ ፣ “ገቢ” ፡ እና “ወጪ” ፡ እያሉ ፣ እየመረመሩ ፣ በሰውነት ፡ ላይ ፡ በሚገኙ ፡ የስሜት ፡ ህዋሳት ፡ የሚገቡ፡ መረጃዎችን ፡ በሙላ ፡ እያጤኑ ፡ ቀኑን ፡ ሙሉ ፣ አስርቱንም ፡ ቀናት ፡ መክረምን ፡ ያካትታል። ደግሞ ፡ ደጋግሞ ፡ መመርመር ፣ አሁንም ፡ አሁንም ፡ ማጥናት ፣ ማስተዋል ፣ ሳይሰለቹ ፡ መመርመር ።

የአእምሮ ፡ ስለሁሉም ፡ ነገር ፡ የማሰብ ፡ ሱስ ፡ ትንሽ ፡ ረገብ ፡ ማድረግ ። ወደራስ ፡ በደንብ ፡ ለመመልከት ፡ እድል ፡ መስጠት ። ምናልባትም ፡ የጥንቶቹ ፡ የግሪክ ፡ አማልክት ፡ ያልገመቱትን ፡ ድል ፡ ማግኘት ፣ የሰው ፡ ልጅን ፡ ትክክለኛ ፡ ማንነት ፣ ህያውነት ፡ በጥቂቱ ፣ በአኢምንቱም ፡ ቢሆን ፡ ማስተዋል ፡ ይሆን????