ደፋር ሴት ነኝ

\”የሕይወቴ ቅኝት\” በሚል ርእስ በጻፍኩት መጽሐፌ  ላይ ከልጅነት እስከ እውቀት ያለውን ታሪኬን ዝክዝክ አድርጌ ጽፌ እና አሳትሜ ለእባብያን አድርሻለሁ፡፡ መጽሐፉ ከመታተሙ በፊት  ግርድፉን በጥልቀት አንብቦ  የቃላት ግድፈቴን ያረመልኝ ባለቤቴ ከሰጠኝ  አስተያየት አንዱ \”ለካስ ከልጅነትሽ ጀምሮ እንደዚህ ደፋር ኖረሻልና!?\” የሚል ነበር፡፡ ይህንን ሲለኝ አሁን የሚያየው ደፋሩ ማንነቴ ከኋላ የመጣ እንዳልሆነ ተረድቶ ነበር፡፡  \”አዎ ደፋር ነኝ፣ ደፋር ሴት!\” አልኩት፡፡

ደፋር ሴት የሚለውን ቃል የተለያዩ መዝገበ ቃላቶች የተለያየ ትርጉም ሰጥተውታል፡፡  አዎንታዊ  ከሆኑት ትርጉሞች ውስጥ ብርቱ፣ ፍርሀት የሌለባት፣ ጠቢብ፣ መለኛ፣ ጎበዝ፣ ጀብደኛ የሚሉት ይገኙበታል፡፡  አሉታዊው ትርጓሜ ደግሞ አይን አውጣ፣ ይሉኝታ ቢስ፣ የማታፍር ይላታል፡፡

የእኛ ማህበረሰብ እና ባህሎቻችን በአብዛኛው ሴት ልጅ ደፋር ስትሆን ከአዎንታዊው ትርጉሙ ይልቅ አሉታዊውን ትርጉም ሲጠቀሙት ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ ስለደፋርነት ብሂሎችን እንኳን ብናይ አንዱ በበጎ ጎኑ  \”ደፋርና ጭስ መውጫ አያጡም\” ይልና ይህ ብሂል ለወንድ እንጂ ለሴት እንዳይደለ ለማሳየት በሚመስል ወደሴቷ ሲመጣ \”ደፋር  ሴት ጉልቻ ረግጣ ትወጣለች\” የሚል ነው፡፡  ረግጦ መውጣት በመልካም ጎኑ የሚታይ እንዳልሆነ ልብ ይሏል፡፡

ለዚህም ይመስለኛል ብዙ ደፋር ሴቶችን ማየት ያልቻልነው፡፡ ያሉን በጣም ጥቂት ደፋር ሴቶች ናቸው፡፡ እኔ እንደው ሳስበው በዓለም ላይ ደፋር ሴቶች ያሏቸው ሀገራት ተዘርዝረው ቢጻፉ  ኢትዮጵያ ከዝርዝሩ በመደበኛነት ከሥር በተደረደረችባቸው እንደ ድህነት፣ ያልተማሩ ዜጎች ብዛት፣ የሴቶች መብት ጥሰት…ወዘተ በዚህኛውም ከሥር ትደረደር ነበር፡፡ ሕቅ ነው!

እኔ ደፋርነቴን በጣም እወደዋለሁ፡፡ እንደውም በዚህ ምድር ላይ ከተሰጡኝ ገጸ በረከቶች አንዱ ደፋርነቴ ነው ብዬ ብናገር ግነት አይደለም፡፡ ከየት እንዳመጣሁት እኔም አላውቀውም፡፡ ምክንያቱም ባደግኩበት ዘመን እና ማህበረሰብ \”እከሌ\” የምላትን ደፋር ሴት አላስታውስም፡፡  በዘረ-መል ያገኘሁት ትንሽ ደፋርነት ሊኖር ይችላል፡፡ እናቴ ደፋር የምትባል አይደለችም፡፡ ጎበዝ ሴት ናት፤ ቆፍጣና የምትባል፤ ግን በማህበረሰቡ ቅቡልነት ያላቸው የሚባሉትን ብቻ ስታደርግ ነው የኖረችው፡፡ በሕጻንነቴ ያጣሁት አባቴ ግን ደፋር ነበር ይባላል፡፡ ታላላቆቼ ስለድፍረቱ ሲተርኩልኝ በዋናነት የሚነገሩኝ የዱር እንስሳት አዳኝ እንደነበር ነው፡፡ አደን ሲወጣ  ይዟቸው ይሄድ ስለነበር የትዝታቸው አካል ሆኖ ነው፡፡ ይሁንና የእኔና የአባቴ ድፍረት ግን ይለያያል፡፡ ለምሳሌ አባቴ አደን ሲወጣ በወቅቱ የደረስኩ ልጅ ብሆን እንኳን ላደንቅለት ዋነኛ ተቃዋሚው እሆን እንደነበር እገምታለሁ፡፡ ድፍረቱን ተጠቅሞ፣ በገዛ መንደራቸው ሄዶ ተኩሶ በመግደልና አንገታቸውን ቆርጦ በማምጣት የሚያስመዘግበውን ጀብድ ወይም ደፋርነት አጥብቄ መቃወም ብቻ አይደለም የምችል ከሆነ አስቆመው ነበር፡፡ ይሄ ነው የእኔ ድፍረት፤ መብት ሲጣስ የመጋፈጥ ደፋርነት!

በሥራ ሕይወቴ ላይ ከብዙ መልካም የስራ ባልደረቦች እና እንዲሁም ኃላፊዎች ጋር ሰርቻለሁ፤ የዚያን ያህል ደግሞ በእነሱም ሆነ በእኔ የግል ባህርይ አማካይነት ሳንግባባ የቀረን ነበርን፡፡ እናም ወደኋላ ሄጄ ሳስታውሰው ያለመግባባታችን መነሻዎች በአብዛኛው ከደፋርነቴ ጋር ይገናኛሉ፤ ያላመንኩበትን በድፍረት መቃወም፣ መብቴ የሆነውን በድፍረት መጠየቅ፣ ትክክል ያልሆነውን እና የተድበሰበሰውን በድፍረት በማውጣት እና ፊት ለፊት በመጋፈጥ…ወዘተ፡፡ ይህ ባህርዬ በወቅቱ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ጎድቶኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰዎች እውነትን መጋፈጥ ስለሚፈሩ ከእኔ ጋር ላለመታየት አግልለውኝ ያውቃሉ፤ ሥራዬን እስከማጣት ደርሼ አውቃለሁ፤ አብሮነቴን ሊተዉኝ ያልፈለጉ ደግሞ \”ቢቀርብሽ፣ ብትተይውስ!?\” ብለው መክረውኝም ያውቃሉ፤ \”እንደ አንቺ ያለችውን ማን ደፍሮ ያገባል!?\” ተብዬም አውቃለሁ፤ ኸረ ስንቱ!

በጨዋታችን ላይ ደፋር መሆን ማለትን በሁለት ገጽታው እንድናየው እፈልጋለሁ፡፡ አንደኛው ደፋርነት አሉታዊው ደፋርነት ነው፡፡ ለሌብነት፣ ለክፋት እና ለጥፋት፣ የሚደረግ ደፋርነት፤ እኔ የመረጥኩት ደፋርነት አዎንታዊውን ነው፡፡ ይህም እውነተኝነት፣ ታታሪነት፣ መብት ጠያቂነት፣ ተቆርቋሪነት እና ሰው አክባሪነትን ነው፡፡ እውነትነት ያለው ደፋርነት ደግሞ አርነት ያወጣል፡፡

ደፋርነቴ መሆን የምፈልገውን እንድሆን እና የመረጥኩትን መንገድ እንድጓዝ አግዞኛል፡፡ ምክንያቱም ማድረግ እየፈለግሁ \”ሰዎች ምን ይሉኛል? ይጠሉኝ ይሆን? ያገልሉኝ ይሆን?\” የሚሉ ሰበቦች ሸብበው አልያዙኝም፤ በሕይወቴ ወሳኝ የሆኑ ውሳኔዎችን ለማድረግ ፍርሀት የለብኝም፡፡ ሀሳቤን በነጻነት ገልጬ ለሀሳቤም ኃላፊነት ለመውሰድ ተሸማቅቄ አላውቅም፡፡

ከብዙ ገጠመኞቼ አንዱን ምሳሌ ልናገር፤ መጀመርያ ከኮሌጅ የተመረቅኩት በዲፕሎማ ነበር፡፡ ቀጣዩ ሕልሜ የነበረው ባሻሻልኩት የ12ኛ ክፍል መልቀቅያ ፈተና ውጤት አማካይነት ቀን እየሠራሁ በማታው የድግሪ መርሀግብር የዩኒቨርስቲ ትምህርቴን መቀጠል ነበር፡፡ ታድያ ልክ ሥራ እንደያዝኩ በልጅነቴ ትምህርቴን ጨርሼ ወደ ሥራ ዓለም መቀላቀሌ ያስደሰተውና ያኮራው የአጎቴ ልጅ \”አኮራሽን፣ አሁን ትዳርና ልጅ በልጅነት ነውና ወዲያ ወዲህ ሳትይ እንድታገቢ ባል አምጥቼልሻለሁ!\” አለኝ፡፡ በሁለታችን መሀከል ያለው የእድሜ ርቀት የአባትና የልጅ ያህል ስለነበር ምላሼ እሺታ እንደሚሆን ጥርጣሬ አልነበረውም፡፡ እኔ ግን በድፍረት \”ማንም የሕይወት አጋሬን አይመርጥልኝም፤ ቅድምያም ለትምህርቴ እሰጣለሁ\” ብዬ በቁርጥ በመመለሴ ምክንያት የደረሰብኝ ውግዘትና ኩርፊያው ይሉኝተኛ አላደረገኝም፡፡ ይልቁንስ ሰባት ዓመታትን ተምሬ የፈለግኳትን እኔ ሆንኩ እንጂ፡፡ ይህ አንድ ምሳሌ ሲሆን ብዙ በድፍረቴ የተሻገርኳቸው የሕይወት ድልድዮች አሉ፡፡

ለማጠቃለል እኔ ደፋር ሴት በመሆኔ ካጣሁት የተጠቀምኩት ይበልጣል፤ ትምህርቴን የምችለው ድረስ ተምሪያለሁ፤ የምፈልገውን የስራ ላይ እድገት አግኝቻለሁ፤ ለሐቅ ቆምያለሁ፤ ማየት የምፈልጋትን እኔን ሁኔታዎች በሚፈቅዱላት ልክ ደርሳ አይቻታለሁ፡፡ አሁን ደግሞ እድሜ ለኢትዮጵያ የደፋር ሴቶች ማህበር! ከሌሎች ደፋር ሴቶች እህቶቼ ጋር አገናኝታኛለች፤ አብረን እንሻገራለን!  መሻገርያው የጠፋቸውንም እህቶች እየመራን አብረን እንሻግራለን!