ሲስተሙ (ክፍል ሁለት)

በዘመኑ አጠራር አንድ ባለሀብት ዘመድ አለችኝ፡፡ ባለሀብት ድሮ ድሮ ዲታ፣ ሞጃ፣ ሀብታም ይባል እንደነበረው፡፡ እና ይቺ ዘመዴ አንዱ የሀብቷ መጠን መለክያ በጣም አዲስ የሆነ ቴክኖሎጂ ውጤት ተጠቃሚ በመሆኗ ነው፤ በተለይ የተንቀሳቃሽ ስልክ ቀፎ የመለዋወጥ ፍጥነቷ ከማውቃቸው ሰዎች ሁሉ የላቀ ነው፡፡ ያለው ማማሩ የሌለው አለማማሩ (ይህም ሌላ አባባል ይኖረው ይሆን!)፡፡  መቼስ ቴክኖሎጂው የሚጠቅመንን ያህል ለወጪ እንደሚዳርገን ለእናንተ መንገር ለቀባሪው እንደማርዳት ነው፡፡ የሞባይል ቴክኖሎጂ በየጊዜው የሚቀያየረው ተጨማሪ አፕልኬሽኖች እና የተለያዩ ምቾቶች ስለሚጨማመሩበት ነው፡፡ ይሁንልን ደስ ያሰኛል፡፡ አቅም ካለ ከዓለም ጋር መራመድ ምን ይገዳል! ይህችን ዘመዴን ለየት የሚያደርጋት ግን የተንቀሳቃሽ ስልኳን የምትቀያይረው (ሳልጠይቃት እንደምትነግረኝ) ተጨማሪ አፕልኬሽኖችን እና የተሻለ ጥቅማጥቅም ፈልጋ ሳይሆን “አዋዋልሽን መምሰል አለብሽ” የምትለውን ምክራዊ ሀሳብ በተግባር ከማዋል አንጻር ነው፡፡ ታድያ ይህቺ ዘመዴ ስልኮቿን በመቀያየሩ ሂደት ውስጥ ለአጠቃቀም ስትቸገር አስተውያለሁ፡፡ መመርያውን አታነብም፣ የገዛች ቀን አከፋፈቱን እና አደዋወሉን ካየች ከዚያ በላይ ለማወቅ ብዙም አትጥርም፡፡ ሌላው ቢቀር ፎቶግራፎች ከጋለሪ ውስጥ ለማውጣት እና ለማሳየት እንኳን ልጆቿን ወይንም አጠገቧ ያለውን ሰው ጠይቃ ነው፡፡ ለነገሩ  በገንዘቧ የፈለጋትን ማድረግ መብቷ ነው፡፡ ግን ደግሞ ዋጋ ከከፈልንበት ላይቀር ለማወቅ እና ለመጠቀም ብንሞክር የሚል ትችታዊ ሀሳብ ጣል ለማድረግ ነው፡፡ በተለይ እንዲህ መመርያ ያላቸውን እቃዎች በማንበብ ብንሞክር! በነገራችን ላይ ስልክም ሆነ ሌላ ቴክኖሎጂ ነክ እቃዎች ማኑዋል ማንበብ ካልፈለግን በዩትዩብ ቪዲዮ ማየት እና መሞከር ወይንም አጠቃቀሙን ማወቅ እንችላለን፡፡ ያው በቴክኖሎጂ የጀመርኩት የዘንድሮ የማርች 8 መሪ ቃል ስለሆነ ነው፡፡

እንዲህ እንደ ዘመዴ አዋዋልን ለመምሰል ወይንም ደግሞ የኑሮ ደረጃን ለማሳየት ምንም የማንጠቀምበት ቴክኖሎጂ ወይም ሌላ ቁሳቁስ ላይ ከፍተኛ ዋጋ የምናወጣ ብዙ ሴቶች አለን፡፡ እኔ አቅሙ እስካለ ድረስ ዋጋ መከፈሉ ላይ የመጠየቅ ወይንም የመተቸት አቅም እና መብት የለኝም፡፡ ነገር ግን ዋጋ ያወጣንለትን ነገር በዋጋው ልክ ለምን አንጠቀምበትም በማለት እህታዊ ምክሬን ለመስጠት እንጂ፡፡ በተለይ ደግሞ እለት ከእለት የምናደርገውን ነገር  በመሞከር አልያም ደግሞ ሁልጊዜ የሚያሳዩንን ሰዎችን አንዴ ጠይቆ በደንብ በመረዳት የባለሀብት ተረጂነትን ብንላቀቅ ከማንም በላይ እርካታው ለእራሳችን ነው፡፡

በነገራችን ላይ በቴክኖሎጂው ምሳሌ አመጣሁ እንጂ በብዙ ነገር ላይ ሳይሞክሩ “አልችለውም” ማለት ለብዙዎቻች እንደ ልምድ እየሆነ ነው፡፡ አንድ ምሳሌ ልጨምርላችሁ፡፡ ከላይ የጠቀስኳት ዘመዴን ጨምሮ በሥራ እና በተለያዩ ገጠመኞች ያወቅኳቸው ሰዎች በተለይ ደግሞ ሴቶች (ሁሉም እንዳይደሉ ልብ ይሏል) እቃ ወይንም አገልግሎት ሊገዙ ገበያ ወጥተው “መከራከር አልችልበትም ወይም አይሆንልኝም” በሚል በዚህ ገዢና ሻጭ ያለከልካይ በሚገበያዩበት ገበያ የተጠየቁትን ከፍለው ይገዛሉ፡፡ ተመሳሳይ እቃ ወይንም አገልግሎት ምናልባትም 50% ወይም ከዚያ በላይ በቀነሰ ዋጋ ተገበያይታችሁ ብትመጡ እንኳን ንቃተ ሕሊናቸው አይጨምርም፤ ምክንያቱም አንዴ በተጠየቁበት ዋጋ መግዛት ብቻ እንደሚችሉ እራሳቸውን አሳምነዋል፤ አልያም ተከራክሮ መገብየት ከደረጃቸው ዝቅ የሚያደርጋቸው ይመስላቸዋል፡፡ መቼስ በሀገራችን ኢኮኖሚ ምንም ያህል ሀብታም ብንሆን ቢሊየነር እና ትሪሊየነር የመሆን እድላችን እሩቅ ነው፡፡ ታድያ አማራጮችን የማንሞክረው ለምን ይሆን? ሞኝነት? ግድ የለሽነት? ወይንስ መሞከር ያለመፈለግ?

በነገራችን ላይ ገበያውም እያበደ የሄደው እንደዚህ ያሉ የተጠየቁትን በመክፈል የሚገበያዩ ሰዎች በመኖራቸው ነው፡፡ አብዛኛው (ሁሉም አላልኩም) ነጋዴ ደግሞ ገዢ እስካገኘ 1000% (አንድ ሺህ ፐርሰንት) አትርፎ ቢሸጥም ምንም አይገደውም፡፡

በተለይ እንደዚህ ያለ ያለመሞከር ባህርይ ያላቸው ሴቶች ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም፡፡ በቤተዘመድ፣ በሥራ ቦታ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች አጋጥመውኛል፡፡ እንደዚህ ያሉ ሴቶች ሁሉም ሀብት የማሳየት ወይንም ግዴለሽነት ብቻም ሳይሆን በሌላ ባህርያቸው ፍርሀት ያላቸው ጭምር ሆኖ አይቻቸዋለሁ፡፡ ለምሳሌ የቤት ውስጥ ረዳት ከሄደችባቸው ሠራተኛ አገናኞች ጋር ሄደው “ምንም ትሁን ብቻ ሥራ የምትችል” በማለት ጠይቀው ዋጋ እንኳን ሳይደራደሩ የቤት ውስጥ ረዳቷ የጠየቀችውን ከፍለው ይቀጥራሉ፡፡ እንደዚህ ያሉ ሴቶች አንድም የቤት ውስጥ ሥራ የሚጠሉ አልያም ሥራ የማይችሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህ ግምት ከልምድ በመነሳት ስለሆነ ተሳስቼ ከሆነ ይቅር በሉኝ፡፡ በእርግጥ ሕጻናት ልጆች ወይንም አቅመ ደካማ የቤተሰብ አባል ካለ ሥራ ባይሠሩም መኖራቸው ብቻ ተፈልጎ የሚቀጠሩበት ሁኔታ እንዳለ ሆኖ፡፡  እንግዲህ በእቃ ወይንም በአገልግሎት ግዢ አልን እንጂ በሌላ በሌላም ሕይወታቸው ነገሮችን ከመሞከር ይልቅ አልችልም ብለው የሚደመድሙ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡

በአሁኑ ዘመን ኑሮን በብልሀት ካልገፋነው በስተቀር ገፍቶ ይጥለናል፡፡ ሴቶች ደግሞ ብዙ ነገር ላይ ብልሀተኞች ነን፡፡ ነገር ግን ከአዋዋል ጋር መመሳሰል፣ ከሌሎች ጋር መፎካከር፣ በእጃችን ያሉትን ነገሮች ወይንም እድሎች ያለመሞከር ብልሀታችንን እንዳይጋፉን እራሳችንን በመሆን፣ ጤናማ የሆነ ፉክክር ብቻ በማድረግ እና ሳንሞክር አንችለውም ከማለት እንጽዳ፡፡ በድጋሚ ለማስታወስ ሁላችሁም እንደምታውቁት የዚህ ዓመት የማርች 8 መሪ ቃል የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ሴቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማስተማር እና ማብቃት ነው፡፡ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነታችን ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ብሎም ለዓለም ኢኮኖሚ እድገት ተፈላጊ ነው፡፡ ግን ደግሞ ቴክኖሎጂው በእጃችን ሲኖር ሁልጊዜ የሌሎችን እርዳታ ብቻ ከመጠበቅ ይልቅ መሞከር እና መጠቀም ይኖርብናል፡፡ ከነአባባሉም እኮ “ያለመሞከር ደጅአዝማችነት ይቀራል!” ይባል የለ! አሀ ይሄ ነገር ያለመጠየቅ ነው ለካ! በቃ ያው ነው! ሞክሩ፣ እንሞክር! ጨርሻለሁ!

ፍፁም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

Share on your socials!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *