የፍክክር ቤት ያለመዘጋቱ ሳያንስ

መቼስ \”የሕይወቴ ቅኝት\” እንተ እኔ (ግለ-ታሪክ) መጽሐፌ ባለውለታዬ ነው! ወደኋላ እየሄድኩ ያለፍኩበትን እና ያሳለፍኩትን እና ያለፈኝንም ጭምር እንዳስታውስ እድል ሰጥቶኛል፡፡ ታድያ ለዛሬ የማጋራችሁ ለመጀመርያ ጊዜ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስድስት ኪሎ ላይብራሪ ሳይንስ ተመድቤ በቀኑ መርሀ ግብር ሁለት ዓመት ስማር ካሳለፍኩት የሴቶች ዶርሚታሪ ሕይወቴ አንዷን ገጠመኝ መዝዤ ነው፡፡ ጥሎብን ሕይወታችንን የምንኖረው ለእኛ በተሰጠን ወይም በሚገባን ልክ ሳይሆን ሌሎች ከሚኖሩት ጋር እያነጻጸርን እና እየተፎካከርን ነው፤ የፉክክር ኑሮ! ይሄ ደግሞ እንኳን እኛ በዚያ እድሜ የነበርነው ወጣቶች ቀርቶ አሁንም በጉልምስናችን ያልተላቀቀን እና በአብዛኛዎቻችን ላይ የምናስተውለው ነው፤ ጎጂ ባህል፡፡

ነገሩ እንዲህ ነበር የሆነው፤ ካምፓስ ስንገባ ያው ከተለያዩ የሀገራችን ክልሎች መጥተን በአንድ የሴቶች ማደርያ ሕንጻ ውስጥ እንከትማለን፤ ትምህርቱን እስክንጨርስ አልያም በተለያዩ ምክንያቶች እስክናቆም(መባረርንም ጨምሮ)፡፡ የኑሮ ደረጃችን ያው እንደመጣንበት የቤተሰብ ቁመና ይለያያል አይደል!? ታድያ የዶርሚታሪ አገልግሎት አጠቃቀማችንም እንደየኑሯችን እና እንደመጣንበት አካባቢ ይለያያል፡፡ ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ውጪ ለመጡት በግል  ይማሩ በመንግስት ት/ቤት ሁነኛ ዘመድ በአዲስ አበባ (አልፎ አልፎ የሚያድሩበት ከሌለ) ለእነሱ የዶርም ሕይወት  ብቸኛ አማራጭ ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ የተመደብነው ደግሞ ከግል ት/ቤት ከመጡት ውስጥ የዶርሚተሪ ብቻ ሳይሆን የዩኒቨርስቲውን ካፌም የማይጠቀሙ ብዙ ነበሩ፤ ወይ ብር አላቸው አልያም ቤተሰቦቻቸው ምግብ ያቀብሏቸዋል፤ ካልሆነም በመኪና ያመላልሷቸዋል፡፡ እኔና አንደኛዋ ጓደኛዬ አዲስ አበቤዎች እንሁን እንጂ የግል ት/ቤት ተማሪዎች  ዓይነት ቅምጥል ሕይወት አልነበረንም፡፡ እሷ ከአዳሪ (ሚሽነሪ) ት/ቤት የመጣች ስትሆን የሷም የእኔም ቤተሰቦች ከትራንስፖርት እና በሳምንት አንዴ ስንወጣ ተሸክመን ከምንመጣው አስቤዛ ውጪ ትርፍ ሊሰጡን አቅም አልነበራቸውም፡፡ ተሸክመን የምንመጣው የበሰለ ምግብ ደግሞ በዶርሚታሪ የጋርዪሽ ኑሮ ስሌት ከእራት እና አያልፍም፡፡  ደረቅ ምግቦቻችን ሁለት ቀናት ሊያዘልቁን ይችላሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን አርብ ወይም ቅዳሜ ደርሶ ወደየቤታችን እስክንመለስ ባሉት ቀናት ነው ጨዋታው የሚጀመረው፡፡ እኔና ጓደኛዬ እንግዲህ እራሳችንን በአዲስ አበቤነት ከግል ተማሪዎች ጋር ሀይለኛ ፉክክር ውስጥ ከተናል፡፡ እነሱ ካፌ አይሄዱማ! እኛም በመደበኛነት ላለመሄድ፡፡ እራሳችንን ከሀብታም ልጆች ተርታ በማሰለፍ!

ሁሉን ቢዘረዝሩት ኪስ ይቀዳል እና የማትረሳኝን አንዷን ገጠመኝ  ላውጋችሁ፡፡  በዶርማችን የሚላስ የሚቀመስ አልነበረንም፡፡ አንዳንዴ ሻይቅጠል እና ስኳር ሲኖረን የካፌው ሰልፍ ረገብ ሲል ጠብቀን የካፌ ዳቦ ተቀብለን እንመለስና ደብቀን ባስገባነው ስቶቭ ሻይ አፍልተን እየነከርን እንበላለን፤ እንጠግባለንም፡፡ ያን ቀን ግን ጓደኛዬ ካፌ ሄዶ ዳቦ ማምጣቱንም አልፈለገችም፡፡ እጃችን ላይ ትንሽ ሳንቲም አለ፡፡ እሷ የፈለገችው በወቅቱ በብር ከሃምሳ ሳንቲም የሚገዛ ፍርፍር ሎው ላውንጅ ተብሎ  በሚጠራው ካፌ ሄደን አንድ ገዝተን ለሁለት እንድንበላ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ መጠኗ ትንሽ ስለሆነችና ለሁለት ተማሪ ስለማታጠግብ በነፍስ ወከፍ ዳቦ በወተት ብንበላ እንደሚሻል ሀሳብ አቀረብኩ፡፡ አንዳችን የሌላችንን ሀሳብ ሳንቀበል በመቅረታችን በዶርማችን በባዶ ሆዳችን ልናመሽ ተገደድን፡፡ እኔ ረሀቡ ፋታ ስላልሰጠኝ  አንድ  የመፈናከት አቅም የነበረው የደረቀ ዳቦ ጠረጴዛ ስር ሳገኝ መብላት እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ ልብ በሉ የተረሳ ያልተከደነ እና ዝም ብሎ ተቀምጦ ደርቆ የከረመ ዳቦ ነበር፡፡ የመጣልኝ መላ እላዩ ላይ ውሀ አፍስሼ ሲርስ ስኳር ነስንሼ መግመጥ ነበር፤ ጓደኛዬ እንኳን ተጥሎ የደረቀ ለትኩስ ዳቦም ፍቅር አልነበራትምና አልተጋራችኝም፡፡ በላሁት፡፡ ግን በሁኔታው ስለተበሳጨሁ አኮረፍኩ፤ ጓደኛዬም አኮረፈች፡፡ ምክንያታችን አንዳችን በሌላችን ሀሳብ ያለመስማማታችን እንጂ የያዘን የፉክክር አባዜ አናዶን አልነበረም፡፡ ልጅነት ደጉ ሁሉን እረስተን በነጋታው አብረን ወደ ክፍል ሄድን፡፡

የእኔና የጓደኛዬ ከአቅማችን በላይ ፊክክር ውስጥ መግባት ጦማችንን አሳድሮን ይሆናል፡፡ ከነበርንበት የእድሜ እርከን እና የእውቀት ልኬትም ቀላል ሊመስል ይችላል፡፡  ይሄ የተፎካካሪነት ባህርይ ግን አድጎ በጉልምስናችንም መገለጫችን ሲሆን ያሳፍራል፡፡ ይሄ ደግሞ የእኛ የሰዎች (የሌሎችን ሀገራት አላውቅም) በተለይ የከተሜ ሴቶች አንዱ ጎጂ ባህላችን ነው፡፡ ብዙዎቻችን እንደ እራሳችን እና እንደቤታችን ሳይሆን እንደ እነሱ ወይም እንደ እሷቤት ለመኖር እየፈለግን ተጋግጠን ማለቃችን ነው፡፡ የምንፎካከርበት ነገር ከመብዛቱ የተነሳ እና ሌሎች ሴቶች ያደረጉትን ስለምናደርግ ከምንፈልገው የማንፈልገው ነገር ቤታችንን እና ኑሯችንን እያጨናነቀብን ነው፡፡  ፉክክራችን ደግሞ በቁሳቁስ ብቻ ቢቆም ደግሞ መልካም ነበር፡፡ ãረ ስንት ጉድ አለ መሰላችሁ! በቀደም እለት አንዲት ሁለት ልጅ ከወለደች በኋላ በኑሮ ምሬት \”በቃኝ\” ያለች ወዳጄ ሦስተኛ አርግዛ አገኘኋት፡፡  እናም እኔ \”በቃኝ አላልሽም እንዴ?\” ብዬ የምጠይቃት መስሏት እራሷው ተማርራ የነገረችኝን አስታውሳ ነው መሰለኝ \”አሁን እኮ ፋሽኑ ሦስት ልጅ ሆኗል! እኔም በቃኝ ካልኩ በኋላ እንትና፣ እንትና፣ ሲወልዱ…\”!? እንግዲህ ልጅም በፉክክር ይረገዛል፣ በፉክክር ያድጋል፣ በፉክክር ት/ቤት ተመርጦ ይማራል፣ ልቀጥል!? ለነገሩ ያው የአብዛኛዎቻችን ኑሯችን አይደል እናውቀዋለንኮ!

አሁን አሁን ደግሞ የኑሮ ግለቱ ያልበገረው በደማቅ እየተከበረ ያለው የሠርግ ዝግጅት ፉክክር ለእኛ ለጎልማሶችም ተርፏል፡፡ ሠርጉ ቀረብ ያለ ዘመድ ወይም ወዳጅ ቤት ከሆነ \”አንድ አይነት ሀገር ልብስ እያሰፋን ነው፤ ተቀላቀይን፤ ደግሞ ሳትነግሩኝ ብለሽ ቅር እንዳይልሽ…\” የሚሉ ጥያቄዎች እያስተናገድኩ ነው፡፡ ይሄ ነገር በእርግጥ ቀደም ብሎ ነው የተጀመረው፡፡ ቤተሰባዊነቱ፣ ድምቀቱ፣ ሀገር ልብስ መሆኑ ሁሉ ደስ ያሰኘኛል፡፡ ግን ደግሞ አሁን አሁን ሳየው ያንን ሀገር ልብስ በሰው ምርጫ ተጭኖብን አሰፍተን ደግመን የማንለብሰው ከሆነ አልያም ደግሞ ቅርበታችን ለአቅመ ሀገር ልብስ የማያደርሰን ከሆነ እና \”ከማን አንሼ\” ብለን በፉክክር የምናደርገው ከሆነ ትልቅ ኪሳራ ነው፡፡

ፉክክር ሁልጊዜ ክፉ ጎን አለው እያልኩ አይደለም፡፡ በፉክክር መማር፣ በፉክክር ማንበብ፣ በፉክክር ቤት መስራት…ወዘተ ብቻ በፉክክር ጤናማ በሆነ መንገድ ሠርቶ በቁስም በአእምሮም ላይ ኢንቨስት ማድረግ መልካም ነው፡፡ አንዳንዴ እኮ የሚበልጡን ሰዎች ሲኖሩም ጥሩ ነው፤ ያተጉናል፡፡ አስተዳደጋችንንም በአንዴ መቀየር አይቻልም፡፡ ያው ትምህርታችንም 1ኛ፣ 2ኛ…ውራ (መጨረሻኛ) እየተባባልን እየተፎካከርን ወይም እየተወዳደርን አይደል ያደግነው!  ነገር ግን ጤናማ ያልሆነ ፉክክር አብሮን እንዳያረጅ አንድ ቦታ ልናቆመው እና የራሳችንን ኑሮ በአቅማችን እንደቤታችን እየኖርን ለሰውነታችን ሰላም እና ጤና ብንሰጠው ይሻላል፡፡ የፉክክር ቤት ያለመዘጋቱ ሳያንስ እኛንም ከኑሮ መስመር እንዳያስወጣን ለማለት ነው፡፡ ለዛሬ ጨርሻለሁ!