የፍትህ እናት

ፍትህ ሲወሳ፣ የፍትህ እናት ወይም (Lady justice) ሳትነሳ መቅረት አትችልም። የፍትህ እናትን ከሩቅ ሳያት አይኗ መታሰሩን፣ የማያዳላው ሚዛን፣ አስፈሪው ሰይፍ፣ የለበሰችው ቀሚስ በፈረንጅ አፍ ቶጋ፣ በአንድ እግሯ የረገጠችው መጽሀፍ እንዲሁም እባብ ፣በዋናነት ደሞ በሴት መመሰሏ ምንን ሊያሳይ እንደሚችል ሁሌም አስብ ነበር። ደፈር አልኩ መሰለኝ ትንተና ውስጥ ገባሁ። እውነተኛውን ትርጉም ከራሴ እይታ ጋር ቀይጬ እዘለዝለው ልግባ።

የአይኗ መታሰር ማንም ሁን ማን ሳላይ፣ ሳላነፃፅር ልፈርድልህ፣ ባጮልቅ እንኳን ችግር ነውና በድፍን ጨለማ ውስጥ ሆኜ ለተበደልከው ላንተ ብርሀን ልሆን ወድጃለሁ እንደሆነ ይሰማኛል። በዚ ጩሀት ዘመን ግን እንደው ያቺ ምስኪን አይኗን ትንሽ ገለጥ አርጎ ጆሮዋን ጥጥ ሚወትፍላት ቢኖር ባይ ነኝ። የያዘችው ሚዛን ላታዳላ የማለችበት ነው። በዘመነ ፍትሀ ነገስት በአንዱ ሚዛን በኩል አይን ያጠፋ ቢቀመጥ በሌላው በኩል የአይን አጥፊውን አይን በማጥፋት ሚዛኑ ልክ እንዲመጣ ይደረግ ነበር። በአሁን ጊዜም እንደዚ ሚዛን ልክ ሚያመጣ ውሳኔ ለምን አልተሰጠንም ብለው ቢወቅሱ ቁጭ አርጎ መዝኖ ሚያሳያቸው አጥተውም ሊሆን ይችላልና መዛኝ ፍርድ ቤቱ መቅጠሩ ማይቀር ነው።

አስፈሪው ሰይፍ የፍትህን ሀያልነት ሚያሳይላት ነው። ሴት ሰይፍ ስትይዝ ማየት ብዙም ባይለመድም፣ ለፍትህ ስትል ሀይሏን የምትጠቀም የተበዳይ ፊት አውራሪ መሆኗን የሚያሳይ ነው። እንደው ይዣት ብዞርና እነዛን ለያዥ ለገራዥ ያልተመለሱትን አንድ ብትልልኝ ምንኛ ደስታዬ ነበር! የረገጠችው መጽሀፍ የፍርድ ቤት ህግና በዋናነት ህገ መንግስቱን መሆኑ ሲገባኝ እንዴት ይህ ክቡር መጽሀፍ ይረገጣል ብዬ ያዙኝ ልቀቁኝ ብዬ ነበር። ኋላ የፍትህ መሰረቷ ህጉ መሆኑን ለማሳየት ነው ሲሉኝ ነው እፎይ ያልኩት።

በመርገጥ እና መሰረት በመሆን ውስጥ ያለው ልዩነት መቼ እንደሚገባን እንጃ። በደረት ተሳቢውን እባብ ከህግ መጽሀፍ በላይ ሆኖ እሱንም እረግጣዋለች። እፎይ እባብስ የታባቱ ይረገጥ ብዬ እንደለመደብኝ ላልፍ ስል እንደው ትርጉሙ ምን ቢሆን ይሆን ብዬ ለማወቅ ጓጓሁ። ትሳሳታለች ብላችሁ ነበር እንዴ? ይቅርታ እባብ እባብ ነው። መሰረቷ ሳይሆን እውነትም ረግጣው ነው። ቢያንስ ኢቺን አለመሳሳቴ ሰላም ሰጥቶኛል። እውነቴን እኮ ነው! እባብ የፍትህ መሰረት ቢሆን ምን ሊፈጠር ይችል ነበር? መልሱን ለናንተ ትቼዋለሁ። ቀጥሎ ያስተዋልኩት ልብሷን ነበር። ቶጋ ይባላል። ለምን ቶጋ አለበሷት? ለምን ፈትሏን አላለበሷትም ብዬ ልጣላ ዳድቶኝ ነበር። ሆኖም ግሪካውያን አማልክት በነበሩ ጊዜ የሚለብሱት እንደሆነ ቆይቼ ነው የሰማሁት ። አንዳንዶች ይህ የግሪኮሮማን ልብስ ፍትሕን የሚያካትት የፍልስፍና አመለካከት ደረጃን ያመለክታል ብለው ይተነትኑታል። እኔ አሁንም ፈትሏን ብትለብስ አልጠላም። ሀገር ወዳድነትን ማንፀባረቅ ማንፈልግበት ቦታማ አይገኝም። በስተመጨረሻም በዚ የወንዶች አለም ላይ ሴት እንዴት ፍትህን ወክላ ፊት ቆመች የሚለውን ማሰብ አስገራሚ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነውና ለምን እንደዚ እንዲሆን እንደወሰኑ ለማወቅ ሳገላብጥ፣ አንድ ሰው ለዚሁ ጥያቄ የሰጠው ምላሽ አስገራሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። መልሱ እንዲ ይላል፣”የፍትህ እመቤት ሴት እንጂ ወንድ አይደለችም ብዬ እገምታለሁ ምክንያቱም ከፈለገች መውለድና ዘር እንዲቀጥል ማረግ የምትችለው
እሷ ናት። እና ፍትህ ዘርን ማስቀጠል ከፈለገች ማስቀጠል የምትችለው እሷ ናት፤ በዛም የሰው ዘር መቀጠል የሚችለው በፍትህ ነው ባይ ነኝ።” ይል ነበር። ግሪካውያንና ሮማውያን እነዛን ሴት አማልክት ቴሚስ እና ጁቲካ ፍትህን እንዲወክሉ ሲመርጧቸው የራሳቸው ብዙ ምክንያቶች እንደነበሯቸው እሙን ቢሆንም፣ የዚ ሰው እይታ ግን ሀያል እንደሆነ ተሰምቶኛል። የናንተስ ሀሳብ ምን ይሆን?